“ጽንዓ ተዋሕዶ ወይስ ጽንዓ ምንታዌ”
ክፍል አንድ
ሰሞኑን በሳምባ ምች ምክንያት ጋደም ብየ አንድ መጽሐፍ እያነበብኩ እገኛለሁ ፡፡ የመጽሐፉ ርዕስ “ጽንዓ ተዋሕዶ” ይባላል ፡፡ በአማን ነጸረ በሚባል ጸሐፊ ሰኔ 2012 ዓ.ም የታተመ መጽሐፍ እንደሆነ ከመግቢያው ይናገራል ፡፡
የመጽሐፉ ርዕስ መሢሐውያን አበው ከጻፉት ወልደ አብ ከተባለው ጉምቱ መጽሐፍ የተወሰደ ስም ነው -ጽንዓ ተዋሕዶ ፡፡ ሀሳቡ ተቀብዐ ተኮር ሐተታዎችንና ታሪኮችን ያነሳሳል ፡፡ ስሙ ደስ ብሎኝ ነበር ነገር ግን ያው እንደሌሎቹ “ተዋሕዶዎች” እነልዮንን እነ ንስጥሮስን በቃል እየነቀፈ በግብር እነሱን የደገፈ መጽሐፍ ሆኖ አግኝቸዋለሁ ፡፡
ተቀብዐን በግድ እየጎተተ ቃል ቅብዕ ለማለት ከእስአሁኑ ራሳቸውን “ተዋሕዶዎች” እያሉ ከሚጠሩ ጸሐፍያን በተሻለ መልኩ አቅርቦታል ፡፡ እነ መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሮ “በተዋሕዶ ከበረ ወልድ ቅብዕ” እያሉ በድፍኑ ሲያንከባልሉት የነበረውን ምንታዌ ግልጥልጥ አድርጎ አቅርቦታል ፡፡ ከግእዝ ወደ እንግሊዝ በመጓዝም አንዳድ ይረቡኛል ይጠቅሙኛል የሚላቸውን ሰነዶችን ለመዳሰስ ጥሯል ፡፡ ይህ ሁሉ ልፋቱ ግን ያው ቃልን ቀባዒ ትስብእትን በቃል ቅብዕነት ተቀባዒ አድርጎ ከነጠለው ከምንታዌ አልራቀም - አልሸሹም ዘወር አሉ ነው ነገሩ ፡፡
ወደ ፊት ጊዜና ጤንነት ሳገኝ እያንዳዱን ስሕተት የምነቅስና የማወጣ ይሁንና ለአሁኑ ግን ደገኛው ኦርቶዶክሳዊ አባት አፈወርቅ ዮሐንስ “ለሊሁ ቀባዒ ለሊሁ ተቀባዒ” ይላል በማለት የጠቀሰውን ማንሳት ሻትሁ ፡፡
ፀሀፊው በአማን ነጸረ የሚለው ስሙ የጽሑፍ ስሙ ነው ፡፡ እውነተኛው ስሙ ግን በአማን አይደለም ፡፡ ተቀብዐን እንደፈለገ በልኩ እየቀደደ እየሰፋ አንድ ጊዜ ለእሱ አልጠቀመውም ለእኛ እንጅ ሌላ ጊዜ ደግሞ ቅብዓትን አይሻም ሌላ ጊዜ ደግሞ ጭራሹኑ ቅብዓት ማለት ተዋሕዶ ነው እያለ ሲወላገድ ይገኛል ፡፡ ጊዜ ሲኖረን እያንዳንዱን የምናይ ይሆናል ፡፡ ለአሁኑ ግን ከላይ እንደተናገርኩት በመጽሐፉ ገጽ 27 ላይ “ዮሐንስ አፈወርቅ ለሊሁ ቀባዒ ለሊሁ” ተቀባዒ ይላል ያለበትን አንቀጽ ጠቅሰን እንመልከተው ፡፡
“ወካዕበ ይትበሀል በእንተዝ ኦ አምላክ ቀብዐከ አምላክከ ፡፡ ሐተታ ኦ አምላክ ብሎ ቀብዐከ አምላክከ ማለቱ ቀባዒነቱንና ተቀባዒነቱን ያስረዳልና……..በዚህ አንቀጽ ተጠራጣሪዎች አይሁድን (አምላክ ወሰብእ ብሎ) ፣ እለ ጳውሎስ ሳምሳጢን( ወልድ ቀዳማዊ እንደሆነ ተናግሮ) ፣ አርዮሳውያንን (መንበርከ እግዚኦ ለዓለመ ዓለም ብሎ ኢፍጡር እንደሆነ አስረድቶ) ፣ ሰባልዮሳውያንን በክልኤ ገጽ አካለ አብ አካለ ወልድ ብሎ አንድ ገጽ እንዳይደለ በማስረዳት) ፣መንክዮንን (አግሀደ ሎቱ ከመ መለኮት ኢይትቀባዕ ዘእንበለ ዳእሙ ትስብእተ ሥጋሁ-ምትሐት የሚሉ እለ መንክዮንን በሰውነቱ እንጅ በአምላክነቱ ከበረ እንዳይባል (and against the
marcionites, that the Godhead is not anointed, but the manhood.) አስረዳቸው ፡፡ “ በማለት ግእዙንም እግሊዙንም እየቀጣጠለ ጠቅሶ ማስረጃውን ደግሞ በግርጌ ማስታወሻው (Footnote) ላይ ድርሳነ ቄርሎስ ገጽ 74 ምዕ 3 ፡ 72-74 ይላል ፡፡
ይህ የጸሐፊው በአማን ንግግር ብዙ ስሕተቶች አሉበት ፡፡
የመጀመሪያው ስሕተቱ፡- ባለቤቱን መቀየሩ ነው ፡፡ ማለትም እሱ አልፎ አልፎ የጠቀሰልን ቃል ባለቤቱ ዮሐንስ አፈወርቅ እንጅ ቄርሎስ አይደለም ፡፡ መገኛውም ድርሳነ ዮሐንስ አፈወርቅ ድርሳን 3 ነው ፡፡ እሱ ግን የእርማት ስሕተት ይሁን የእውቀት ክፍተት አናውቅም ድርሳነ ቄርሎስ ብሎ መጥቀሱ ስሕተት ነው ፡፡
ሁለተኛው ስሕተቱ፡- “ሐተታ ኦ አምላክ ብሎ ቀብዐከ አምላክከ ማለቱ ቀባዒነቱንና ተቀባዒነቱን ያስረዳልና” ብሎ የጠቀሰው ቃል የዮሐንስ አፈወርቅ ቃል ሳይሆን ድርሳነ ዮሐንስ አፈወርቅን የተረጎመው ቃል ቅብዕ ሥጋ በቃል ተቀባዒ ብሎ የሚያምን ስሑት ሰው የጨመረው ቃል ነው-በአንድምታ ስም የገባ ሥርዋጽ ማለት ነው ፡፡ አንባቢው ከዚህ ላይ በደንብ አስተውልልኝ! አንድምታ አንጻሩን መሠረቱን አውዱን ጠብቆ የሚነገር እንጅ የማይገናኘውን አስመስሎ እንደሚገናኝ አድርጎ መናገር አይደለም ፡፡ የዚህ የዮሐንስ አፈወርቅ ትርጓሜ መነሻው የክቡር ዳዊት 44ኛው መዝሙር ላይ የተነገረው ቃለ ትንቢት ሲሆን አፈወርቅ የወሰደው ደግሞ ጳውሎስ ዕብራውያን 1 ቁ 9 ላይ ከዳዊት ወስዶ የተናገረውን ራሱኑ ቃል ነው-ልዩነቱ ቅዱስ ጳውሎስ ዘይኄይስ ማለቱ ብቻ ነው ፡፡
በክቡር ዳዊት የተነገረው ትንቢት
“መንበረከ እግዚኦ ለዓለመ ዓለም
በትረ ጽድቅ ወበትረ መንግሥትከ
አፍቀርከ ጽድቀ ወዐመፃ ጸላእከ
በእንተዝ ቀብዐከ እግዚአብሔር አምላክከ
ቅብዐ ትፍስሕት እምእለ ከማከ” መዝ 44 ቁ 7
የሚል ሲሆን
በቅዱስ ጳውሎስ የተነገረው ፍጻሜ ትንቢት ደግሞ
“መንበረከ እግዚኦ ለዓለመ ዓለም በትረ ጽድቅ ወበትረ መንግሥትከ
አፍቀርከ ጽድቀ ወዓመፃ ጸላእከ
በእንተዝ እግዚአብሔር አምላክከ ቅብአ ትፍሥሕት ዘይኄይስ እምእለ ከማከ” ዕብ 1፡8-9
ይላል ፡፡ አሁን ቅዱስ ጳውሎስ ዘይኄይስ ከማለቱ በስተቀር አንድ ዓይነት ነው ፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ይህን ቃል ሲተረጉምልን
“ወበእንተ ወልድሰ ይቤ መንበረከ እግዚኦ ለዓለመ ዓለም
ስለ ወለድ ግን መንበረከ እግዚኦ ለዓለመ ዓለም አለ፡፡
ወዝንቱ ያሌቡ እንበይነ መንግሥት
መንበርከ ያለው መንግሥቱን ያስረዳል ፡፡
በትረ መንግሥትከ በትረ ጽድቅ
መንግሥትህ የቅንነት በትር ነው ፡፡
ወዝኒ ካልእ ትእምርት በእንተ መንግሥት
መንበርከ ላለው ሁለተኛ የሚሆን መንግሥትከ በትረ ጽድቅ ያለው መንግሥቱን ያስረዳል ፡፡
ወእምዝ አትለወ ወይቤ በእንተ ሥጋዌሁ አፍቀርከ ርትዐ ወዓመፃ ጸላእከ በእንተዝ ቀብዐከ እግዚአብሔር አምላክከ ቅብዐ ትፍሥሕት እምእለ ከማከ ፡፡
በትረ መንግሥትከ ካለ በኋላ ስለ ሰውነቱ በእንተዝ ቀብዐከ እግዚአብሔር አምላክከ አለ ፡፡
ዘንተኒ ይቤ በፍኖተ ክላሕ
ይህንን አሁን የተናገረውን ነገር በትንቢት በምሳሌ ባገባብ ተናገረ ፡፡
አንድም በጩኸት በድፍረት ተናገረ ፡፡
ሐተታ-ትንቢት የሚመጣውን አውቆ መናገር ነው ፡፡ ምሳሌ ቀብዐከ ብሎ በትረ መንግሥትከ በትረ ጽድቅ ማለት ነው ፡፡ ድፍረት አምላክ ከበረ ማለት ነው ፡፡ አገባብ በሰውነቱ ተቀባ ማለት ነው ፡፡ ጩኸት አምላክ ከበረ ማለት ነው ፡፡ አንድም ድፍረት አምላክከ ማለት ነው ፡፡” ድር 3 ቁ 63 -68
ብሏል ፡፡ ከዚህ ውስጥ አንድም “ድፍረት አምላክከ ማለት ነው” የሚለው ተርጓሚው አብ ለወልድ በሰውነቱ አምላኩ ነው ማለትን ስለማያምን የጨመረው ሥርዋፅ ቃል ነው ፡፡ ድፍረት የተባለው ተርጓሚው በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ ቀብዐከ ሲለው አምላክን ከበረ ብሎ ደፍሮ ተናገረ ማለትን የሚያጠይቅ ነው ፡፡ እንጅ አምላክከ ማለት ድፍረት አይደለም እምነት ነው ፡፡
ቁጥር 72 ላይ ዮሐንስ አፈወርቅ “ወካዕበ ይትበሀል በእንተዝ ኦ አምላክ ቀብዐከ አምላክከ” የሚለውን ቃል ይጠቅስና በጎደሎና በሙሉ ዳዊት የሚገኘውን ቃል አነጻጽሮ ከጠቀሰ በኋላ ቁጥር 73 ላይ “ናሁኬ ዘለፎሙ በዝየ ለንፉቃን አይሁድ ወለሕዝበ ጳውሎስ ሳምሳጢ ለአርዮሳውያን ወለመርክላን ለሰባልዮስ ወለመንክዮን
እነሆ በዚህ አንቀጽ ተጠራጣሪዎች አይሁድን የጳውሎስ ሳምሳጢን ወገኖች አርዮሳውያንን መርክላንን ሰባልዮስን እለ መንክዮንን ረታቸው ፡፡
በዚህ አንቀጽ የተባለው አንቀጸ ተቀብዐ ነው ፡፡ ይህ መሆኑን ከዚህ ቀጥለን እናየዋለን ፡፡
ቁጥር 73 “ለአይሁድኒ ዘለፎሙ በብሂሎቱ አምላክ ወሰብእ
አይሁድን አምላክ ወሰብእ ብሎ ተናግሮ ረታቸው ፡፡ ሐተታ ኦ አምላክ ቀብዐከ አምላክከ ማለቱ ቀባዒነቱን ተቀባዒነቱን ያስረዳልና” ይላል ፡፡
ከላይ እንደ አያችሁት በአማን ነጸረ የመጽሐፉን ቃል ሙሉ በሙሉ ሳይጠቀም ከዚህም ከዚያም እቆነጻጸለ አፈወርቅን “ለሊሁ ቀባዒ ለሊሁ ተቀባዒ” ይላል ለማለት ተጠቅሞበታል ፡፡ በዚህ በቁጥር 73 ላይ “ሐተታ ኦ አምላክ ቀብዐከ አምላክከ ማለቱ ቀባዒነቱን ተቀባዒነቱን ያስረዳል” የሚለው ቃል ከዋናው ሀሳብ ጋር አይገናኝም ፡፡ ምክንያቱም አይሁድ እግዚአብሔር ወልድን በሥጋ ዓይተው “ዕሩቅ ብእሲ/ተራ ሰው/” አድርገው ቆጥረውታልና ኦ አምላክ ማለቱ አምላክነቱን ያስረዳል ፤ ቀብዐከ አምላክከ ማለቱ ደግሞ ሰውነቱን ያስረዳል ሲላቸው ነው ፡፡ ከዚህ ላይ ጥንቃቄ አምላክ ወሰብእ(አምላክም ሰውም መሆኑን ያረጋግጥልናል እንጅ ቀባዒነቱን ተቀባዒነቱን የሚል ሐተታ ለመጨመር መንገድም አገባብም የለውም ፡፡ በግድ ወልድ ቅብዕ ለማለት መጎተት ነው ፡፡ ስለሆነም ኦ አምላክ ብሎ ቀብዐከ አምላክከ ማለቱ አምላክ ወሰብእ መሆኑን የሚስረዳ እንጅ ቃል ቀባዒ ትስብእት ተቀባዒ ለማለት የተጠቀሰ አይደለም ፡፡
በአማን ነጸረ ግን ይኸንን ሲያብራራው “ኦ አምላክ ቀብዐከ አምላክከ---አምላክ ሆይ አምላክህ ቀባህ” ሲል ቀቢ የተባለ መለኮት ተቀቢ የተባለ ትስብእት እንደሆነ ገልጦ ክርስቶስ ማለት በተዋሕዶ የእግዚአብሔር አብ የባሕርይ ልጅ ሰው የሆነ አምላክ እንደሆነ ይገልጥላቸዋል” ብሏል ገጽ 28 ላይ ፡፡
አንባቢው በደንብ አስተውለው!!!
“ኦ አምላክ ቀብዐከ አምላክከ - ሲል ቀቢ የተባለ መለኮት ፤ ተቀቢ የተባለ ትስብእት” ብሎ ወዳጃችን በአማን ነጸረ የተናገረው ትምህርተ ምንታዌ እንደሆነ በዚህ መረዳት እንችላለን ፡፡ መለኮትን ከትስብእት ለይቶ ቀባዒ ትስብእትን ከመለኮት ለይቶ በመለኮት(በቃል) ተቀባዒ አድርጎ አንዱን ወልድ በአካልም በግብርም ነጥሎ እየተናገረ መሆኑን ያሳያል ፡፡ የቅዱስ ጳውሎስ መልእክት “በእንተ ወልዱሰ” ብሎ ሲጀምር ስለልጁ የተናገረው እግዚአብሔር አብ እንደሆነ ስንረዳው ልጁ ሥግው ቃል መሆኑን ነው ፡፡ ርጉማን አይሁድ ዳዊት እንደተናገረው አምላክህ ቀባህ ከተባለማ ለወልድ ሌላ አምላክ አለው ብለው ነበርና ለነዚያ መልስ ሲሰጥ “ለአይሁድኒ ዘለፎሙ በብሂሎቱ አምላክ ወሰብእ--አይሁድን አምላክም ሰውም ብሎ ረታቸው” በማለት እውነተኛውን ቃል ተረጎመልን አፈወርቅ ዮሐንስ ፡፡ እነሆም የዛሬዎቹ እነ ሊቀ ሊቃውንት ስምዐኮነ መልአክ ጭምር “አምላክከ ካልነው ለወልድ ሌላ አምላክ አለው ያሰኝብናል” በማለት አምላክከ የሚለውን አምላክናከ እያሉ እየለወጡ ከነቢያትም ከሐዋርያትም ከሊቃውንትም የተሻሉ ሁነው ተገኝተው እየጠመዘዙ እውነትን ያጠፋሉ ፡፡ የሚደንቀው ግን ተዋሕዶን ሳይሆን ምንታዌን ነው የሚሰብኩት ፡፡
ለአይሁድ የነገራቸው እሱ ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰውና ኦ አምላ ማለቱ አምላክ መሆኑን ፤ ቀብዐከ አምላክከ---አምላክህ ቀባህ ማለቱ ሰው ስለሆነ ነው በማለት ---አምላክ ወሰብእ መባሉን ነው ፡፡ እነ በሬ ወለደ ግን ይህንን ለወጥ አድርገው “ቀባዒነቱን ተቀባዒነቱን ያስረዳል” ብለው ወልድ ቅብዕ ለማለት በግዴታ ጠምዝዘው አስቀምጠውታል ፡፡ በአመአን ነጸረም ይህችን ቃል ይዞ “ቀባዒ መለኮት” ተቀባዒ ትስብእት” በማለት መለኮት የመለኮትን ትስብእት የትስብእትን ሥራ ሠራ እንዳለ ርጉም ልዮን አንድ ወልድን ለሁለት ከፍሎ ያምናል ፡፡ ታዲያ ይኸ ጽንዓ ምንታዌ እንጅ ጽንዓ ተዋሕዶ እንዴት ይሆናላ!!!
በቀጣይ ክፍል እንቀጥላለን ፡፡
ይቆየን!!
ምሥጋና ለሥላሴ
ክብር ለድንግል
ክብር ለመስቀል
ይሁን!
አሜን!!!
No comments:
Post a Comment