“ኤዎስጣቴዎስ ከፋሌ ባሕር”
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ!
አንተ ት(ኮ)ንን ኃይለ ባሕር---ውቅያኖስን የምትገዛ አንተ ነህ ፤ ወአንተ ታረምሞ ለድምፀ ማዕበላ---እስከ ዝየ ብጽሒ ብለህ
የውቅያኖስን ማዕበል ሞገዷን ፀጥ የምታደርገው አንተ ነህ ፡፡ አንተ አኅሠርኮ ለዕቡይ ከመ ቅቱል--- ሌዋታንን እንደሞተ ያዋረድከው አንተ ነህ ማለት በባሕር ተወስኖ እንዲኖር ያደረግኸው አንተ ነህ” መዝ 88፥ 9-10
====================================
አመ አሥሩ ወሰሙኑ ለመስከረም በዛቲ ዕለት አዕረፈ ኤዎስጣቴዎስ መምህረ ሃይማኖት ወሰባኬ ወንጌል (አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም መስከረም ዐሥራ ስምንት በዚህች ቀን ወንጌልን የሚሰብክ የሃይማኖት መምህር አባታችን ኤዎስጣቴዎስ አረፈ) ፡፡
የዚህም ቅዱስ የአባቱ ስም ክርስቶስ ሞዓ ፤ የእናቱ ስም ስነ ሕይወት ይባላል ፡፡ ሁለቱም ደጋጐች እግዚአብሔርን የሚፈሩና በሕጉ ጸንተው የሚኖሩ ነበሩ ፡፡
ከዚህም በኋላ በከበረ መልአክ በቅዱስ ገብርኤል አብሣሪነት ይህን ቅዱስ ወለዱት ስሙን የጌታ ጥብቅ ብለው ሰየሙት ፡፡ በአደገም ጊዜ የዳዊትን መዝሙርና ፣ የቤተክርስቲያንን መጻሕፍት አስተማሩት ፡፡ ከዚህም በኋላ የእናቱ ወንድም አባ ዘካርያስ ወደአለበት የመነኰሳት ገዳም ወሰዱት ፡፡ አባ ዘካርያስም የእግዚአብሔርን ጸጋ እንዳደረበችት አውቆ የምንኵስናን ሥርዓት አስተምሮ የመላእክትን አስኬማ አለበሰው ፡፡ ከገድሉ ጽናት የተነሣ በገዳም ያሉ አረጋውያን እስኪያደንቁ ድረስ በጾም ፣ በጸሎት የተጠመደ ሆነ ፡፡ እርሱ በጥበብና በዕውቀት የጸና ነውና ፡፡
ከጥቂት ጊዜ በኋላም ዲቁና ተሾመ ፡፡ የዲያቆናት አለቃ እንደሆነ እንደ እስጢፋኖስም ለቤተክርስቲያን አገለገለ ፡፡ ከዚህም በኋላ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሚካኤልና ከገብርኤል ጋር ተገለጠለትና ሰላምታ ሰጠው ፡፡ በንፍሐትም መንፈስ ቅዱስን አሳደረበት :: እንዲህም አለው “ወዳጄ ኤዎስጣቴዎስ ሆይ እኔ ከእናትህ ማሕፀን መረጥኩህ ያለ ፍርሀትና ድንጋፄ ወንጌልን ለብዙዎች ሕዝቦች ትሰብክ ዘንድ ከኢትዮጵያ እስከ አርማንያ ድረስ መምህር አደረግሁህ ፡፡ አንተን የሰማ እኔን ሰማ ፤ አንተን ያልሰማ እኔን አልሰማም” ፤ ጌታችን ይህንን ተናግሮ ወደ ሰማይ በክብር ዐረገ ፡፡
ቅዱስ ኦዎስጣቴዎስ ወደ ጳጳስ ሒዶ ቅስና ተሾመ፡፡
የወንጌልንም ሃይማኖት ይሰብክ ዘንድ ጀመረ ፤ ብዙ ሰዎች ወደ እርሱ እስቲሰበሰቡ ድረስ በእርሱም እጅ መንኵሰው ደቀመዛሙርትን ሆኑት ከእርሳቸውም ታላቁ አብሳዲ ነው ፡፡
ብዙዎችንም የከፋች ሥራቸውን አስትቶ ከክህደታቸው መለሳቸው ፡፡ ትምህርቱም በሀገሩ ሁሉ ደረሰ ፡፡ በመላ ዘመኑም የሰንበታትና የበዓላት አከባበር የጸና ሁኖ ተሠራ ከሐዋርያትም ሕግና ሥርዓት ወደ ቀኝም ሆነ ወደ ግራ ሁሉም ፈቀቅ አላሉም ፡፡
ወደ ኢየሩሳሌምም ሁለት ጊዜ ሔደ ፡፡ እግዚአብሔርም በእጆቹ የዕውራንን ዐይን በማብራት አንካሶችንና ጎባጦችን በማቅናት ፣ አጋንንትን በማስወጣት ቁጥር የሌላቸውን ተአምራት አደረገ ፡፡
ከዚህ በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም በእግዚአብሔር ፈቃድ ለመሔድ በአሰበ ጊዜ ልጆቹን ሰብስቦ የመነኰሳትን ሥርዓት ይጠብቁ ዘንድ ፣ከመናፍቃንም ጋር እንዳይቀላቀሉ አማፀናቸዉ ፡፡ ልጁ አብሳዲንም በእነርሱ ላይ ሾመውና ወደ ኢየሩሳሌም ሰንበትን እያከበረና የክርስቶስን ሃይማኖት እያስተማረ ሔደ ፡፡ ወደ ሊቀ ጳጳሳት አባ ብንያሚን ደርሶ ከእርሱ ቡራኬ ተቀበለ ፡፡ የሃይማኖትንም ነገር ተነጋገሩ ፡፡ ዳግመኛም ከከበሩ ቦታዎች በመሳለም በረከትን ተቀበለ ፡፡ በዮርዳኖስም ተጠመቀ ፡፡
ከዚያም ወደ አርመንያ አገር ሔደ ፡፡ ወደ ኢያሪኮ ባሕርም ሲደርስ በመርከባቸው ያሳፍሩት (መሳፈር ሲል ነው) ዘንድ መርከበኞችን ለመናቸው ፡፡ በከለከሉትም ጊዜ ዓጽፉን በባሕሩ ላይ ዘረጋ በቅድስት ሥላሴ ስም በላዩ ባረከ ፡፡ራሱንም በመስቀል ምልክት ምልክት አማተበ ፡፡ እንደ መርከብም ሁኖለት በላዩ ተጫነ ፡፡ ሁለት መላእክትም ቀዛፊዎች ጌታችንም እንደ ሊቀ ሐመር ሆኑለት ፡፡ ከባሕሩም ግርማ የተነሣ እንዳይፈሩ ልጆቹን አጸናቸው ፡፡ እንዲህም አላቸው “ልጆቼ በልባችሁ ቂምንና ሽንገላን እንዳታኖሩ ተጠበቁ ፡፡ ለኔ ግን ከእናንተ አንዱ እንደሚጠፋ ይመስለኛል” ፡፡ ይህን ሲናገር ልቡ የቂም የበቀል ማከማቻ ስለሆነ ወዲያውኑ አንዱ ከእነሱ መካከል ሠጠመ ፡፡
በእግዚአብሔርም ፈቃድ ባሕሩን ተሻግሮ ወደ አርመንያ ከተማ ደርሶ ከሊቀ ጳጳሳቱ ጋር ተገናኘ :: ሰገደለትም ፡፡ ከእርሱ ቡራኬን ተቀበለ ፡፡ ሊቀ-ጳጳሱም በአየው ጊዜ ታላቅ ደስታን ደስ አለው ፡፡ በፍቅርም ተቀበለው ፡፡
አባታችን ኤዎስጣቴዎስም ሁሉም በትምህርቱ አንድ እስከሆኑ ድረስ የአርማንያን ሰዎች ሐዋርያት በሲኖዶሳቸው የሠሩትን ሥርዓት እያስተማራቸው ኖረ ፡፡
ከዚህም በኋላ ዕረፍቱ ሲደርስ ክብር ይግባውና ጌታችን ተገለጠለትና ስሙን ለሚጠራ ፣ መታሰቢያውን ለሚያደርግ ፣ ገድሉን ለሚጽፍ ቃል ኪዳንን ሰጠው፡፡ በአረፈም ጊዜ ጳጳሳትና ካህናት በታላቅ ክብር ገንዘው በሰማዕቱ በቅዱስ መርምህናም ቤተክርስቲያን ውስጥ ቀበሩት ፡፡ ከሥጋውም ብዙ ተአምራት ተገለጡ ፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ኪያነኒ ይምሐረነ ፤
ጸሎቱ ወበረከቱ ተሀሉ ምስሌነ ፤
ለዓለመ ዓለም አሜን
ለእግዚአብሔር ምሥጋና ይሁን
እኛንም በጸሎቱ ይማረን
በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር
ለዘለዓለሙ አሜን
አርኬ፡- ሰላም ዕብል ለዘረከብከ ሞገሰ ምስለ ፈጣሪ ትትናገር ሱባዔያተ ሠላሰ፤
ኤዎስጣቴዎስ ዘሦጥከ ዲበ በድነ ሕፃን ነፍሰ ፤
ጊዜ ዐደውከ ማዕበላጠ ዘአልቦ አርማሰ ፤
በዘባነ ባሕር እንዘ ትሰፍሕ ልብሰ ፡፡
ከጻድቁ በረከት ለመሳተፍ የምትፈልጉ ኦርቶዶክሳውያን ነገ መስከረም 18/ 2014 ዓ.ም በምሥራቃዊት ጎጃም ብሔረ ኦሪት ርዕስ አድባራት ወገዳማት ዳግማዊት ኢየሩሳሌም ደብረወርቅ ማርያም ገዳም ንግስ ስላለ መሄድ ትችላላችሁ ፡፡ ሐይማኖት መሢሐዊትንም ስትሰበክ ሰምታችሁ ትመጣላችሁ ፡፡ የደብር ፍሬዎች እና መላው ኦርቶዶክሳዉያን እንኳን አደረሳችሁ ፡፡
በከሐዲዎችና በሴረኞች የተዳፈነ መስቀሉን ከክፉዎች እይታ እሱ በወደደና በፈቀደ ጊዜ ያወጣ ቅዱስ አምላካችን በሴረኞችና በከሐዲዎች የተዳፈነች እውነትን በፈቃዱ ይግለጥልን ፡፡ እንዲሁም በአሁኑ ወቅት በሰሜኑ የሐገራችን ክፍል በከሐዲዎችና ሆዳው አምላካቸው በሆኑ ስግብግብ ሰዎች በወገናችን ላይ እየደረሰ ያለውን ግፍና መከራ ማብቂያ ይስጥልን ፡፡ የጻድቁ ከፋሌ ባሕር ኤዎስጣቴዎስ ጸሎቱና በረከቱ ጠረኞቹን ተንኮለኞችን ከወገናችን ላይ አንስቶ አመድ ያድርግልን አሜን ፡፡
No comments:
Post a Comment