Saturday, September 8, 2018

ገድለ እስትንፋሰ ክርስቶስ [ ረከብናሁ ለማስያስ - በዲ/ን ትንሣኤ ደምሴ ]


ዘበትርጓሜሁ ይብልዎ ክርስቶስ (ዮሐ. ፩ ፥፵፪)
በትርጓሜው ክርስቶስ የሚሉት ማስያስን አገኘነው!!!
ይድረስ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት በሙሉ

ምዕራፍ ፬
የጻድቁ የአቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ ሃይማኖት

※※※※※※※※※※† † † † ※※※※※※※※※※

በዚህ ምዕራፍ የምናየው ጻድቁ ከፈጣሪያቸው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ስለሃይማኖት ያደረጉትን ንግግርና የልመና ቃል የብራናውን ገድላቸውን ከሕትሙ ገድላቸው ጋር እያነፃጸርን የምናይ ይሆናል፡፡
ሰው ከሌሎቹ ፍጡራን ኹሉ ልዩ የተለየ የሚያስብለው አንዱ ነገር በጎውንም ይኹን ክፉውን ነገር በሕሊናው አሰላስሎ በአእምሮው አመዛዝኖ፣ የተረዳውን ያህል እና የወደደውን ነገር የሀሳቡ መሰብሰቢያ አዳራሽ ወደኾነው ወደቅንጭላቱ ክፍል ማስተጋባቱ ነው፡፡ በመኾኑም ወዳጆቼ ይህን የጻፍኩትን መልእክት /ጽሑፍ/ አቡነ አስትንፋሰ ክርስቶስ የሚያምኑበትን ሃይማኖት ሲኾን ጽሑፉም የተወሰደው፤
1ኛ . . ከብራናው የገድላቸው መጽሐፍ (ሰሜን ወሎ ክፍለ ሐገር ዳውንት ከተባለች ገዳም የተገኘ)
2ኛ . . ከሕትሙ የገድላቸው መጽሐፍ (በአሁኑ ሰዓት በገበያ ላይ የሚገኝ) ገጽ ፲፱-፳፩ ነውና ለማንበብ ቅን ልቦና ያላችሁ ኹሉ በተለይ ግዕዝ ልሳን የምታውቁ ምሁራን ወንድሞቼ እና አባቶቼ የብራናውን ከሕትሙ እያነጻጸራችሁ እንድታዩት በትህትና አደራ እላለሁ፡፡ ንጽጽሩንም ካያችሁ በኋላ ሰው እንደመኾናችሁ መጠን ራሳችሁን ዳኛ አድርጋችሁ የፈረዳችሁትን ውሳኔ ለሌሎች ብታካፍሉ መልካም ነገር ይኾናል ብየ አምናለሁ፡፡

እኒህ ደግ ኢትዮጵያዊ ጻድቅ የነበሩበት ዘመን በግምት ከዐፄ ፋሲል ዘመነ መንግሥት ጀምሮ እስከ ጻድቁ ዐፄ ዮሐንስ ልጅ ኢያሱ /ዓድያም ሰገድ/ እንደኾነ ከገድላቸው መጽሐፍ እና ከሌሎችም የታሪክ መጻሕፍት መረዳት ይቻላል፡፡ በዘመናቸውም ታላላቅ ሊቃውንትን እነ አቡነ አካለ ክርስቶስ፣ አቡነ ዘኢየሱስ (ዕውር የካሮች ቅጽል ስም)፣ አቡነ አብርሃም፣ ፅጌ ድንግል፣ ዘሥላሴ ተክለ ሐዋርያት እኒህን በእምነታቸው እንዲጸኑ በሰማዕትነት እንዲሞቱ በመንፈሳዊት ምክር ኦርቶዶክሳዊት ጽናት እንዲኖራቸው የቅድስና ሥራቸውን ተወጥተዋል፡፡ በረከታቸው ይደርብንና የእኒህም ሊቃውንት በሰማዕትነት ያረፉት በዐፄ ዮሐንስ (ጻድቁ) ልጅ በኢያሱ (አድያም ሰገድ) ሰይፍ ከብዙ ምእመናን እና ካህናት ጋር አንገታቸውን ተቀልተው እንደኾነ የአቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ የገድላቸው መጽሐፍ ይናገራል ፡፡ ስለዚህ ነገር በሚቀጥለው በምዕራፍ ፭ በአማን ነፀረ ከጻፉት (ዕውር ዘኢየሱስ) ከሚለው ጽሑፍ ጋር በአንፃር ስለምናየው እዚህ ጋ ይበቃናል፡፡
ለግዕዙ ቋንቋ † ለአማረኛዉ ※ ይጠቀሙ፡፡ ግዕዝ የማትሰሙ † ምልክት አልፋችሁ ※ ምልክት አማረኛውን አንብቡ፡፡
እነሆ የጽሑፍ ንጽጽር ጀምረናል፤

ከብራናው:-

† ወይቤ አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ እስፍንቱ ልደትከ ቦ እለ ይብሉከ ፪ኤ ወቦ እለ ይብሉከ ፫ት፡፡
ወይቤ እግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ እምቅድመ ዓለም እምእግዚአብሔር አብ ዘእንበለ እም ተወለድኩ አነ፤ ወበደኃሪ መዋዕል እማርያም ዘእንበለ አብ ዘእንበለ ዘርዕ ወኢሩካቤ ተወለድኩ በግብረ መንፈስስ ቅዱስ ነሣእኩ እምሥጋሃ ወእምነፍሳ ወእምደማ ወእምፀጉራ ነሢእየ አስተዋሐድኩ ምስለ መለኮትየ ወኮንኩ ሰብአ፡፡
※ አቡነ አስትንፋሰ ክርስቶስም ልደትህ ስንት ነው?ልደትህን ኹለት ነው የሚሉህ አሉ፤ ሦስት ነው የሚሉህም አሉ?
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም እምቅድመ ዓለም ከእግዚአብሔር አብ ያለእናት ተወለድኩ፤ በኋላ ዘመን ደግሞ ከማርያም ያለአባት ያለ ሩካቤ ያለዘር በግብረ መንፈስ ቅዱስ ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ፣ ከደሟ፣ ከፀጉሯ ነስቼ ከመለኮቴ አዋሕጄ አንድ አድርጌ ኹለተኛ ተወለድኩ፡፡

ከሕትሙ፡-

† ወአውሥኦ አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ ወይቤሎ ለእግዚእነ እስፍንቱ ልደትከ ፪ቱ ልደትከኑ ወሚመ ፫ቱ ልደትኑ ቦ እለ ይብሉከ ፪ቱ ወቦ እለ ይብሉከ ፫ቱ ልደት፡፡ ወተሠጥዎ እግዚእነ ኢሱስ ክርስቶስ ለአቡነ ወይቤሎ ቀዳሚ እምቅድመ ዓለማት እምእግዚአብሔር አብ ዘእንበለ አም ተወለድኩ፡፡ ወበደኃሪ መዋዕል እማርያም እምቅድስት ድንግል ዘእንበለ አብ ተወለድኩ፤ ዘእንበለ ዘርዕ ወኢሩካቤ በግብረ መንፈስ ቅዱስ ነሣእኩ እምነ ሥጋ ወእምነ ነፍሳ ወነሢእየ አስተዋሐድኩ ምስለ መለኮትየ ኮንኩ ሰብአ፡፡
※ አባታችን እስትንፋሰ ክርስቶስ ጌተችንን “ልደትህ ስነት ነው?” ኹለት ነው የሚሉ አሉ፤ ሦስት ነው የሚሉ አሉ፤ እስኪ ንገረኝ” አለው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ዓለም ሳይፈጠር አስቀድሞ ከእግእዚአብሔር አብ ያለእናት ተወለድኩ፤ ድኅረ ዓለም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቼ ሥጋ እና መለኮትን አዋሕጄ ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ በመኾን ተወለድኩ፡፡

ከብራናው፡-

† ኦ ወልድየ ወፍቁርየ እስትንፋሰ ክርስቶስ መሲሐዊ ርቱዐ ሃይማኖት አምሳሊሆሙ ለ፲ቱ ወ፪ቱ ሐዋርያት አርዳእየ ወ፫፻ ፲ ወ፰ቱ ኤጲስ ቆጶሳት ኅሩያንየ በል “አብ ቀባዒ ወልድ ተቀባዒ መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ” ወእለሰ ይብሉኒ ወልድ በፀጋ መናፍቃን ወሐሳውያን እሙንቱ፤ ኢያፈቅሮሙ ወእሰይም ላዕሌሆሙ አሕዘበ ወአረሜ ዘይቀንይዎሙ
※ ለአሥራ ኹለቱ ተማሪዎቼና ለሦስት መቶ ኤጲስ ቆጶሳት ምርጦቼ ምሳሌያቸው የምትኾን ሃይማኖትህ የቀና ልጄ ወዳጄ መሲሐዊ እስትንፋሰ ክርስቶስ ሆይ “አብ ቀባዒ ወልድ ተቀባዒ መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ” በል፡፡ ነገር ግን “የጸጋ ልጅ ነው” የሚሉኝ ሐሰኞች መናፍቃን ናቸው እንጂ፤ በሥቃይ በግፍ የሚገዟቸውን አሕዛብንና አረሚዎችንም አስነሣባቸዋለሁ፡፡

ከሕትሙ፡-

† ኦ ፍቁርየ እስትንፋሰ ክርስቶስ ለሊሁ ቅብዕ ወለሊሁ ቀባዒ፤ ወለሊሁ ተቀባዒ ከነ በል፡፡ ኦ ፍቁርየ እስትንፋሰ ክርስቶስ ወልደ አብ በፀጋ ይቤሉኒ መናፍቃን ሐሳውያን፡፡ ወበበይነዝ እሠይም ላዕሌሆሙ አሕዘበ ወአረማውያነ ዘይቀንይዎሙ ወዘያጠፍኦሙ እምገጸምድር፡፡
※ ወዳጄ እስትንፋሰ ክርስቶስ ሆይ እርሱ ክቡር እራሱ አክባሪ እራሱ የሚያከብር ነው በል፡፡ ሐሰተኞች መናፍቃን ‘የፀጋ ልጅ’ ይሉኛል፡፡ ስለዚህ እነሱን አልወዳቸውም፡፡ በእነርሱ ላይ የሚገዟቸውን እና የሚያጠፏቸውን ጨካኞች አህዛብን አሰለጥንባቸዋለኹ፡፡

ከብራናው፡-

† ይቤ እግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ ኮንኩ ወልደ ባሕርዩ ለአብ አነ ኢየሱስ በኩረ ምእመናን ሊቀ ካህናት ንጉሠ ነገሥት አምጻኤ ሕይወት ኮናኔ ዓለማት ኮንኩ አነ ትስብእት እመለኮት መለኮት እምትስብእት ከመ ተዋሕዶተ ነፍስ ወሥጋ፡፡
※ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአብ የባሕርዩ ልጅ ኾንኩ፤ እኔ ለምእመናን በኩር፣ ሊቀ ካህናት፣ ንጉሠ ነገሥት፣ ሕይወትን ያስገኘ፣ ዓለማትን የሚገዛ ነኝ፡፡ ነፍስ ከሥጋ ጋር ተዋሕዳ እንዳለች እኔም መለኮት ከሥጋ ሥጋ ከመለኮት አንድ ኾንኩ፡፡

ከሕትሙ፡-

† ወካዕበ ይቤ እግዚእነ ኢሱስ ክርስቶስ ለአብ በባሕርዩ ኮንኩ ወልደ፤ ወአነ በኵረ ምእመናን ሊቀ ካህናት በኵረ ምእመናን ንጉሠ ነገሥት አምጻኤ ሕይወት ኰናኔ ዓለማት፣ ወከመ ነፍስ እምሥጋ ከማሁ ነግሠ በተዋሕዶ ትስብእት እመለኮት መለኮት እምትስብእት በከመ ይቤ መጽሐፍ ቃል ሥጋ ኮነ፤ ወውእቱ ቃል እግዚአብሔር ውእቱ፡፡
※ ዳግመኛም ጌታችን ኢየሱሰስ ክርስቶስ የአብ የባሕርይ ልጁ የምዕመናን በኵር ሊቀ ካህናት የነገሥታት ንጉሥ ዓለማትን የሚገዛ፣ ሕይወትን የሚሰጥ እንደነፍስና ሥጋ ትስብእት ከመለኮት መለኮት ከትስብእት በተዋሕዶ ከበረ በል፡፡ መጽሐፍ ቃል ሥጋ ኾነ ያም ቃል እግዚአብሔር ነው እንዳለ፡፡

ከብራናው፡-

† ወእምድኅረ ዜነዎ ለአባ እስትንፋሰ ክርስቶስ በከመ ይቤ እግዚእነ ወይቤ ትርጓሜሆን ለአስማትየ አማኑኤል ብሂል እግዚአብሔር ምስሌነ ዘተሰመይኩ አምንገለ ትስብእትየ ኢየሱስ ብሂል መድኅነ ዓለም ክርስቶስ ብሂል ቅብዑ ማስያስ ብሂል መሲሕ ወልደ እግዚአብሔር መሢሕ ብሂል ቅቡዕ ዘተቀባዕኩ ለመንግሥት ወለክህነት ጊዜ ኮንኩ ሰብአ በውሳጤ ማሕፀን ማርያማዊ በዘቦቱ ተቀደስኩ አነ፡፡

※ ክርስቶስ ይህን ለአባ እስትንፋሰ ክርስቶስ ከተናገረ በኋላ “ሰው በመኾኔ የተጠራኹባቸው የስሞቼም ትርጓሜ አማኑኤል ማለት እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነው፤ ኢየሱስ ማለት የዓለም መድኀኒት፣ ክርስቶስ ማለት የተቀባ፣ ማስያስ ማለት መሲሕ የእግዚአብሔር ልጅ፤ መሲሕ ማለት የተቀባ ማለት ነው፤ በዚህም እኔ በማሕፀነ ማርያም ሰው ስኾን ለመንግሥት እና ለክህነት በመንፈስ ቅዱስ ተቀብቼ የከበርኩበት የነገሥኩበት ነው ፡፡
† ይቤ እግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ በሰብናየ ተቀባዕኩ በትስብእትየ ተወካፌ፤ ወኮንኩ ወሀቢ በመለኮትየ በከመ ይቤ ዳዊት ፍቁርየ በእንተዝ ቀብዐከ እግዚአብሔር አምላክከ ቅብዐ ትፍሥሕት እምለ ከማከ በከመ ይቤ ሳዊሮስ እስመ መንፈስ ዘዚኣየ በህላዌ ለሊሁ ኀደረ ላዕሌየ፤ ወለምንትኑ ተሰመይኩ መሲሐ ዘእንበለ ዳዕሙ ሶበ ኮንኩ ሰብአ፤
※ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በሰውነቴ ተቀባኹ፤ ሰው ስለኾንኩ ተቀባይ ነኝ፤ በመለኮቴ ግን ሰጪ ነኝ፤ “ስለዚህ እግዚአበሔር አምላክህ እንዳንተ ያሉ ከተቀቡት ልዩ የኾነ የደሥታ ዘይት ቀባህ” ብሎ ወዳጄ ዳዊት እንደተናገረ፡፡ ሳዊሮስም እንዳለ፤ “በህላዌ መለኮት ገንዘቤ የሚኾን መንፈስ ቅዱስ እርሱ በእኔ ዘንድ አደረ፤ የተቀባን ለምን ተባልኩ? ሰውን ብኾን ነው እንጂ፡፡”
† ወቄርሎስ ይቤ እስመ ውእቱ ኢነሥአ መንፈስ ቅዱሰ በህላዌሁ አላ ነሥአ በእንቲአነ ለዕጓለ መሕያው እስመ አዲሁ ርኁር እምእለ የኃድሩ ዲበ ምድር ወከመዝ ነአምሮ ከመለሊሁ ተቀብዐ ከመ ሥርዓተ ትስብእት ዳዕሙ ለሊሁ ዘይቀብዕ ርዕሶ ባሕቲቶ ወናሁ ርኢናሁ ይውህብ መለኮቶ ኢይጽሕቅ ቅብዓተ በህላዌ መለኮቱ አላ ተቀብዐ በሰብእናሁ፡፡ ወተቀቢዐከ ምነተ ኮንከ እመ ትቤለኒ ኮንኩክሙ በኵረ ምእመናን
※ ቄርሎስም “በባሕርየ መለኮት መንፈስ ቅዱስን የተቀበለ አይደለም፤ ስለእኛ ስለሰው ልጆች በነሣው በሥጋው ተቀበለ እንጂ፤ እርሱ መንፈስ ቅዱስ በምድር ከሚያድሩት ኹሉ ገና ርቆ ነበርና፡፡ ሰው በመኾኑ እንደተቀባ እናውቀዋለን፤ እርሱ ራሱን ብቻውን የሚቀባ እርሱ ነው እንጂ፡፡ እነሆ በመለኮቱም ሲሰጥ አየን፤ በህላዌ መለኮቱ መቀባትን አይሻም፤ ሰው በኾነበት ገንዘብ ተቀባ እንጂ፡፡” ብሎ ተናገረ፡፡ “ተቀብተኽ ምን ኾንክ?” ብትለኝ፤ “ለእናንተ ለምእመናን በኵር ኾንኳችኹ፡፡”
† ወይቤ በአብረክሲስ አማን አንገለጉ አሕዛብ በዛቲ ሐገር ላዕለ ቅዱስ ወልድከ ዘቀባዕካሁ በዘተሰብአ ተቀብዓ ወበከመ ተቀብዓ ከማነ ከመ ሥርዓተ ትስብእት ከማሁ ሞተ፡፡ እመቦ ዘይቤ ከመ ቃል አምላክ ዘይገብር በኢየሱስ ከመ ሰብእ ወበስብሐትኒ እንተ ዘዋህድ ያብጽሕዎ ኀቤሁ ከመ ካልዕ ውጉዘ ለይኩን፡፡
※ “በመጽሐፈ አብረክሲስም በቀባኻው በቅዱሱ ልጅኽ ላይ በዛች ሐገር አሕዛብ አንጎራጎሩ፡፡ ሰው በኾነበት ገንዘብ ተቀባ፤ እንደ እኛ በሰውነት ሥርዓት እንደተቀባ እንዲሁ በሰውነቱ ሞተ፡፡ አምላክ ቃል በሰው አድሮ እንዲኖር በኢየሱስም አድሮ ሥራ ይሠራል፤ ምስጋናም ለእርሱ ለቃል በብቻው ከሥጋው በተለየ ያመሰግኑት ዘንድ ይገባል የሚሉ የተወገዙ ናቸው፡፡” ብሎ እንደተናገረ፡፡

ከሕትሙ፡-

† ወእምድኅረ ዜነዎ እግዚእነ ዘንተ ነገረ ለአቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ ይቤሎ ካዕበ ስማዕ እነግረከ ትርጓሜኾን ለአስማትየ አማኑኤል ብሂል እግዚአብሔር ምስሌነ ኢየሱስ ብሂል መድኀኔ ዓለም ክርስቶስ ብሂል ቅቡዕ ማስያስ ብሂል መሲሕ ወልደ እግዚአብሔር መሲሕ ብሂል ቅቡእ ዘተቀባዕኩ ለምንግሥት ወለክህነት ጊዜ ኮንኩ ሰብአ በውስተ ማሕፀነ ድንግል ማርያም በዘቦቱ ተቀደስኩ አነ ይቤ እግዚእነ ኢሱስ ክርስቶስ በሰብእናየ ተቀባዕኩ እንዘ በመለኮትዬ ወሀቤ ኵሉ፡፡
※ ለአባታችን ለአቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን ከነገረው በኋላ የስሜ ትርጓሜ
አማኑኤል ማለት እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነው ማለት ነው፡፡ ኢየሱስ ማለት የዓለም መድኀኒት ማለት ነው፡፡ ክርስቶስ ማለት የከበረ፤ ክቡር፣ የሚያከብር ማለት ነው፡፡ ማስያስ ማለት መሲሕ የእግዚአብሔር አብ የባሕርይ ልጅ መሲሕ ማለትም ለመንግሥት እና ለክህነት በድንግል ማርያም ማሕፀን “በተዋሕዶ የከበርኩ” በመለኮቴ ኹሉን ሰጪ ስኾን በሰውነቴ በተዋሕዶ ከበርኩ፡፡

ከብራናው፡-

† ወበእንተ ዝንቱ ወረደ ላዕሌሁ ኃይለ ዝንቱ ግዘት እመቦ ዘይብል ፫ቱ ልደት ውጉዘ ለይኩን በሥልጣነ ዚኣየ ወበሥልጣነ ዚኣከ እመቦ ዘይብል ወልደ አብ ወልደ ማርያም ፍቱሕ ወንጹሕ ይኩን በቅድሜየ ወበቅድመ አቡየ ዘበሰማያት ወኢይለክፎ ባሕረ እሳት ይህልፍ ምስሌከ በግህደት ፍቁርየ እስትንፋሰ ክርስቶስ
※ ስለዚህም ነገር ሦስት ልደት ብሎ የሚናገርና የሚያሰትምር በዚህ ግዝት በእኔ ሥልጣን እንዲሁም ባንተ ሥልጣን የተወገዘ ይኹን፡፡ ነገር ግን የአብ ልጅ የማርያም ልጅ ኹለት ልደት ብሎ የሚያምን በሰማዊ አባቴ እና በእኔ ፊት የተፈታ ንፁህ ይኹን፤ ከአንተ ከወዳጄ ከእስትንፋሰ ክርስቶስ ጋርም ባሕረ እሳትን በግልጥ ፈጽሞ ሳይነካው ይለፍ፡፡
† ወይቤ እግዚእነ አልብየ አብ በዲበ ምድር ወአልብየ እም በሰማያት እምአብ ዘእንበለ እም ተወለድኩ ፩ዱ በድኃሪ ዘመን እማርያም ዘእንበለ አብ ተወለድኩ፤ ፪ ልድትየ፤ አነ ይቤ እግዚእነ እለ ይብሉኒ ወልደ መንፈስ ቅዱስ በአፍአ ይትኴነኑ ምስለ አክላብ ጽዩዓን በእለተ ደይን ዘያወጽእ ብየ አበ በውስተ ድንግል ፪ አብ ዘይብል ውጉዝ ውእቱ፡፡
※ ጌታችንም “በምድር ላይ አባት በሰማያትም እናት የለኝም፡፡ ከአብ ያለእናት የተወለድኩት፤ በኋላ ዘመን ያለአባት ብቻ ከእናት የተወለድኩት ልደቴ ኹለት ነው፡፡” አለ፡፡ ነገር ግን ደፍረው በአፍአ የመንፈስ ቅዱስ ልጅ ነው የሚሉኝ ሐሳውያን በደይን ቀን ከ፭ቱ ውሾች ጋር በአንድነት ይጋዛሉ፡፡ ከድንግል በተወለድኩት ልደት አባት የሚያበጅ፣ ኹለት አባት የሚል የተወገዘ ነው፡፡

ከሕትሙ፡-

† በከመ ይቤ ዳዊት ፍቁርየ በእንተዝ ቀብዐከ እግዚአብሔር አምላክከ ቅብዓ ትፈሥሕት እምለ ከማከ፤ እመቦ ዘይብል ወየአምን ክልኤተ ልደታትየ ወልደ አብ ወልደ ማርያም ብሂሎ ዘየአምን ፍቱሐ ወንጹሐ ይኩን በቅድሜየ ወበቅድመ አቡየ ዘበሰማያት ወኢይለክፎ ባሕረ እሳት ወይኅልፍ ምስሌከ በግህደት፡፡ እምቅድመ ዓለማት እምአብ ዘእንበለ እም ተወለድኩ፤ ወበደኀሪ መዋዕል እማርያም እምቅድስት ድንግል ዘእንበል አብ ተወለድኩ፡፡ አልብየ አብ በዲበ ምድር ወአልብየ እም በመልዕልተ ሰማያት ዛቲ ይእቲ
※ ስለዚህ ነቢዩ “ዳዊት በተዋሕዶ ከበረ” እንዳለ ኹለት ልደት ነው፡፡ ወልደ አብ ወልደ ማርያም የሚል በእኔ ፊት እና በአባቴ ፊት የተፈታ ንፁሕ ይኹን፡፡ የእሳት ባሕር አይነካውም፤ በግልጥ ከአንተ ጋር ያልፋል፡፡
ዓለም ሳይፈጠር አስቀድሞ ያለእናት ከአብ ተወለድኩ፤ ዓለም ከተፈጠረ በኋላ ያለአባት ከድንግል ማርያም ተወለድኩ፡፡ በምድር አባት የለኝም፤ በሰማይም እናት የለኝም፤ ወዳጄ እስትንፋሰ ክርስቶስ ሆይ ትክክለኛ ሃይማኖት ተዋሕዶ ናት፡፡
† እመሰ ቦ ዘይብል ፫ቱ ልደት ውጉዘ ለይኩን በሥልጣነ መለኮትየ ወእለ ይብሉኒ ወልደ መንፈስ ቅዱስ በአፍአ ይትኴነኑ ምስለ ፭ከለባት በእለተ ደይን ውፁዓን እመንግስተ ሰማያት አሌሎሙ ለእለ ይክህዱ ፪ተ ልደዳትየ አሜሃ በደኃሪ ዕለት አመ ምፅአትየ እኴንኖሙ በእኩ ኩነኔ፡፡ ወእመቦ ዘይብል ፪ቱ አብ ወ፪ቱ እም ውጉዘ ሌኩን፡፡ ወለእመቦ ሞተ በኢፈቃዱ ውጉዘ ለይኩን
※ ዳግመኛም ሦስት ልደት የሚል በእኔ ሥልጣን እና በአንተ ሥልጣን የተወገዘ የተለየ ይኹን፡፡ በአፍአ የመንፈስ ቅዱስ ልጅ ነው የሚለኝ ከአምስት ውሾች ጋር በዕለተ ምጽአት ከመንግሥተ ሰማያት ይወጣሉ፡፡ ኹለቱ ልደቴን የሚክዱ ወዮላቸው፤ ወዮታ አለባቸው፡፡ ያን ጊዜ በመጨረሻ ዕለት በምጽአት ቀን የከፋ ፍርድን እፈርድባቸዋለኹ፡፡ ኹለት አባት ኹለት እናት አለው የሚል የተወገዘ የተለየ ይኹን፡፡ ያለፈቃዱ ሞተ የሚል የተለየ የተወገዘ ይኹን፡፡

ከብራናው:-

† እመቦ ዘይሜህር ፫ ልደታተ እምዘ መሀሩ ሐዋርያት ወ፫፻ ፲ወ፰ቱ ዘይዌስክ ውጉዘ ለይኩን፡፡ አነ ይቤ እንዘ እሜህሮሙ በምኩራባተ አቡየ ፈነወኒ ኀበ ድንግል አበውየ ፈነዉኒ ኢይቤ አልብየ አብ በውስተ ምድር ዘእንበለ አቡየ ዘበሰማያት ወዘእንበለ እምየ በምድር፡፡ ቦቱ በምድር ብሂል ጽርፈት ውእቱ ወይሬስዩኒ ወልደ በፀጋ ከማሆሙ ሣልሰ ነሢኦሙ መለኮትየ አልቦቱ ብሂሎሙ መንፈስ ለሊሁ ውጉዝ በቃልየ ሕሡር ወነዳይ እለ ይብሉ ውጉዘ ለይኩኑ፡፡
※ አሥራ ኹለቱ ሐዋርያት ፫፻ ፲፰ቱ ሊቃውንት ከወሰኗት ሃይማኖት የሚጨምር የሚቀንስ የተወገዘ ይኹን፡፡ እኔ በአዳራሽ ሳስተምራቸው “ወደድንግል አባቴ ላከኝ አልኩኝ እንጂ አባቶቼ ላኩኝ አላልኩም፤ ከሰማዊ አባቴ በቀር ምድራዊ አባት የለኝም፤ ከምድራዊቷ እናቴም በቀር ሰማያዊት እናት የለችኝም፡፡ አባት በምድር አለው ማለት ጽርፈት ስድብ ነው፤ ጎስቋላ ነዳይ፣ የፀጋ ልጅ እንጂ መንፈስ ቅዱስ የባሕርዩ ነው የማይሉ በቃሌ የተወገዙ ይኹኑ፡፡” አለ፡፡

ከሕትሙ፡-

※ከ12ቱ ሐዋርያት እና ሃይማኖትን ከአቀኑ ከ118ቱ ሊቃውንት ሃይማኖት ያጎደለ ሦስት ልደት ነው ብሎ የጨመረ በእነርሱ ቃል የተወገዘ የተለየ ይኹን፡፡ የፀጋ ልጅ ነው የሚል ቢኖር የተወገዘ ነው፡፡ አስቀድሞ ኢያኔስ እና ኢንበሬስ በሙሴ ላይ፣ ቢጽ ሐሳውያን በሐዋርያት ላይ በጠላትነት እንደተነሱ መናፍቃን አርዮስ እና መቅዶንዮስ ንስጥሮስም እንደተነሱ እንደዚሁ በመጨረሻ ዘመን መናፍቃን በኢትዮጵያ ሐገር ይነሣሉ፡፡ ብዙ ፀብ እና ክርክር ያነሣሉ፡፡ እሾህን አሜከላን ይተክላሉ፤ በስንዴም መካከል እንክርዳድን

ከብራናው፡-

† ወእምዝ ይቤ አቡነ ቅዱስ እስትንፈሰ ክርስቶስ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ሥሉስ ዕሩይ መቅድመ ኵሉ አአምን በ፩ አምላክ ዘቦቱ ሠለስቱ አካላት አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ እንዘ ሠለስቱ አሐዱ ወእንዘ አሐዱ ሠለስቱ ኢኮነ ፩ አካለ ዘከመ ይሄልዩ ሰብአ ሰባልዮስ ዓላውያን አላ ውእቱ መለኮት በዘቦቱ ፫ቱ አካላት እስመ አብ አብ ውእቱ ወወልድሂ ወልድ ውእቱ ወመንፈስ ቅዱስሂ መንፈስ ቅዱስ ወእቱ ወኢሀሎ አብ አሐተ ሠዓተ ወኢቅጽበተ ዓይን እንበለ ወልዱ ወመንፈሱ ቅዱስ አላ ህልው ውእቱ ምስሌሆሙ በኵሉ ጊዜ አልቦሙ ጥንት ወኢተፍጻሜት አላ እሙንቱ ጥንት ወተፍጻሜት ለኵሎሙ ፍጡራን፡፡
※ ከዚህ በኋላ አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ከኹሉ በፊት የተካከለ ሦስትነት በአንድ አምላክ አምናለሁ፤ በአካል ሦስት እኒህም አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ናቸው፡፡ አንድ ሲኾኑ ሦስት ሦስት ሲኾኑ አንድ ይኾናሉ፡፡ ሰባልዮስ እንደሚናገረው በአካል አንድ አይደሉም፤ አንድነታቸው በመለኮት ነው እንጂ፡፡ በአካልስ ሦስት ናቸው፤ እኒህም አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ናቸው፡፡ አብ አብ ነው፤ ወልድም ወልድ ነው፤ መንፈስ ቅዱስም መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ በጊዜው ኹሉ አብ ከልጁ ከወልድ ከመንፈስ ቅዱስ ተለይቶ ለዐይን ጥቅሻ ያህል እንኳ የኖረበት ጊዜ የለም፡፡ ነገር ግን በዘመኑ ኹሉ በእነርሱ ህልው ኹኖ ይኖራል እንጂ፡፡ ለአኗኗራቸውም ጥንት መነሻ ፍጻሜ መድረሻ የላቸውም፤ እነርሱ ጥንት መነሻ ፍፃሜ መጨረሻ ናቸው እንጂ፡፡
† በዝ ሃይማኖትየ ነበርኩ ውስተ ዝንቱ ዓለም በአምጣነ ሕይወትየ እንዘ አወግዞሙ ለዕልዋን፡፡ እስመ አልቦሙ ጽንዕ ለደቂቀ እግዚአብሔር ምስለ ደቂቀ ጋኔን እለሰ ተጠምቁ በሃይማኖተ ክርስቲያን ወለእመ ገብኡ ኀበ ሃይማኖተ መናፍቃን ነአምር ከመ ቂዓቶሙ ከርሠ ጥምቀት በከመ ቂዓቶሙ ማያተ ግብጽ ለቆርነናት እስከ ፄዓት ምድር እምአብድንት ከማሁ ትቀይዖሙ ከርሠ ጥምቀት ለመናፍቃን እለ ሀለዉ በኢትዮጵያ ወግብፅ ወኖብ፡፡
※ በዚህ ዓለም ውስጥ ዐላውያንን ሳወግዝ በዚህ ሃይማኖት ኖርኩ፤ የእግዚአብሔር ልጆች ከጋኔን ልጆች ጋር ኅብረት አንድነት የላቸውምና፡፡ በክርስቲያን ሃይማኖት ተጠምቀው ወደመናፍቃን ሃይማኖት የሚገቡ የተቀደሰችው ጥምቀትንም መትፋታቸውን እንዲህ እናውቃለን፤ የግብጽ ውሃ ቆርናናትን እስከ ጌዓት ምድር ድረስ በድናቸውን እየተፋች እንደጣለቻቸው ማሕፀን ጥምቀትም እንዲኹ በኢትዮጵያ፣ በግብጽ እና በኖብ ያሉ መናፍቃንን ትተፋቸዋለች

ከሕትሙ፡-

† ወእምድኅረ ፈጸመ እግዚእነ ተናግሮቶ ይቤ አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ አነ ወሰብእየ ነአምን በአብ ወወልድ እንዘ ፩ ፫ቱ ወእንዘ ፫ቱ ፩፡፡ ወካዕበ ይቤ አቡነ ርስቶሙ ወክፍሎሙ ለክርስቲያን አሐቲ ወይእቲ ተዋሕዶ ወአሐቲ ጥምቀት ወዛቲ ይእቲ ፍሬ ሃይመናትየ ወቀፀላ ርእስየ ይእቲ ተዋሕዶ ሃይማኖት፡፡
※ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከአባታችን ከአቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ ጋር መናገርን በፈጸመ ጊዜ አባታችን አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስም “እኔና ቤተ ሰቦቼ ሥላሴ ፩ ሲኾኑ ፫፤ ፫ ሲኾኑ ፩ ናቸው በማለት አንድም ሦስትም ብለን እናምናለን፡፡” አለ፡፡ ዳግመኛም የክርስቲያን ዕድል ፈንታቸው ጽዋ ተርታቸው አንዲት ሃይማኖት እርሷም ተዋሕዶ ናት አንዲት ጥምቀት የሃይማኖት ፍሬ የራሴ ዘውድ ይች ሃይማኖት ተዋሕዶ ናት፡፡ መጽሐፍ አንዲት ጥምቀት አንዲት ሃይማኖት እንዳለ፡፡

ከብራናው፡-

† ይቤ አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ አንሰ በኵሉ ሰብእናየ ወኵሉ ማኅበረ ቤትየ አብ ወወልደ ወመንፈስ ቅዱሰ ናመልክ ሠለስተ አካላተ ወ፩ መለኮተ እንበለ ፍልጠት ወዕሩየ እንበለ ሐፀት ወ፪ኤ ልደታተ ፩ዱ እምአብ ወካልኡ እማርያም ዝወእቱ ዓጽፈ ሃይማኖትየ ዘበሠለስቱ ተአንመ ዝ ውእቱ አስካለ ሃይማኖትየ ዘ፫ቱ ሕንባባቲሁ ዘፈረይኩ በዓፀደ ቤተ እግዚአብሔር አሐቲ ጉባኤ ምስለ ዝ ሃይማኖትየ እቀውም ቅድሜከ እግዚአብሔር አምላኪየ ወእትመረጐረዝ በዕፀ መስቀልከ ኢየሱስ ክርስቶስ ለዓለም ዓለም ዓሜን፡፡
አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ “በፍጹም ሰውነቴ ኹሉም ቤተ ሰቦቼ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስን ሦስት አካል፣ ባለማበላለጥ እና ባለማለያየት ያለማጓደል አንድ መለኮት፣ ኹለት ልደት፣ አንዱ ከእግዚአብሔር አብ፣ኹለተኛው ከድንግል ማርያም ተወለደ ብለን እናምለን፡፡ በሦስቱ አካላት የተሠራ የሃይማኖቴ ልብስ ይህ ነው፤ በሦስቱ አካላት አብቦ በአንዲት ጉባኤ በዐፀደ ቤተ እግዚአብሔር ያፈራኹት የሃይማኖቴ ፍሬ ይህ ነው፡፡እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ በ ዚህ ሃይማኖቴ በፊትህ እቆማለሁ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይቅዱስ መስቀልህንም እመረጐዛለኹ፡፡ ለዓለም ዓለም ዓሜን
ክርስቲያኖች ሆይ ለሰው ልጅ ሕይወት ክፉ ጠላት የኾነ ዲያብሎስ ሃይማኖትን ለማጥፋት የተጠቀመውን ዘዴ አያችሁት?
1 . . የጻድቁን ዜና ገድላቸውን በከፊል ቆርጦ መጣል፤
2 . . በራስ ፍላጎት፣ ሆድ በወደደ ልብ በፈቀደ መተርጎም
3 . . ደገኛውን አነጋገር ቆርጦ በማውጣት እንደገዛ ፈቃድ አድርጎ መተርጎም
እኒህ ወረዳ ካሮች የሠሩት ሥራ ቄርሎስ ስለ ተቀብዐ የተናገረውን ሙሉ በሙሉ ቆርጠው ጥለውታል፡፡
እጂጉን የሚያስደንቀኝ፤
`ክርስቶስ ማለት የከበረ፤ ክቡር፣ የሚያከብር ማለት ነው፡፡
† በከመ ይቤ ዳዊት ፍቁርየ በእንተዝ ቀብዐከ እግዚአብሔር አምላክከ ቅብዓ ትፈሥሕት እምለ ከማከ” የሚለውን
※ ስለዚህ ነቢዩ “ዳዊት በተዋሕዶ ከበረ” እንዳለ ኹለት ልደት ነው`፡፡ ብሎ መተርጎም ይህ በራሱ ታላቅ ሞት እና ውርደት አይደለምን?
እስኪ ወልድ ቅብዕ የምትሉ ሰዎች ይህን ጥያቄ መልሱልኝ፡፡
“በመለኮቴ ኹሉን ሰጪ ስኾን በሰውነቴ በተዋሕዶ ከበርኩ፡፡” ያለውን በመለኮቱ ሰጪ ነው፡፡
“በሰውነቴ በተዋሕዶ ከበርኩ” ያለው ሰው ራሱን በተዋሕዶ ያከብረል?

ይቀጥላል....

No comments:

Post a Comment