Friday, September 21, 2018

ስለ ልደተ ክርስቶስ የተሰጠ መግለጫ - ዘመነ ዮሐንስ

ልደተ ክርስቶስ በዘመነ ዮሐንስ ታህሳስ ፳፱ ቀን ብቻ እንደሚከበር ሲናገር
በዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ 62ኛ ዓመት ቁ.69 ከኅዳር- ታህሳሥ 2008 ዓ/ም 
ልደተ ክርስቶስ ሁልጊዜ/በ4ቱም ዘመን/ ታህሳሥ 29 ቀን ብቻ እንዲከበር የተሰጠ መግለጫ

“ ልደተ ክርስቶስ በዘመነ ዮሐንስ [በሊቀ ማእምራን ብርሃነ መስቀል አጠና ]
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት “እነሆ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራችን እነግራችኋለሁና አትፍሩ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና” ሉቃ 2፥10-11 ተብሎ የተነገረለት ሰዎችና መላእክት በአድነት የዘመሩለት እጅግ ከፍ ያለ ታላቅ የበዓላት ራስ ነው፡፡ ስለሆነም በዓለም ያሉ ክርስቲያኖች ሁሉ በየዓመቱ በፍጹም ደስታ ያከብሩታል፡፡


እንዲህ በየዓመቱ የሚከበር ከሆነ በእርሱ ልደተ ክርስቶስ በዘመነ ዮሐንስ ተብሎ በልዩነት መነገሩ ስለምንድን ነው የሚል ጥያቄ ቢነሣ ይህን በአጭሩ ለመመለስ በዓሉ ከተመሠረተ ከአንድ ሺህ ሦስት መቶ ዓመታት በኋላ ዕብሪተኞች ነገሥታት በሃያ ስምንት ቀን በግድ እንዲከበር ስለአደረጉ ነው የሚል ይሆናል መልሱ ፡፡ ነገሥታቱ በዓለ ልደቱን በዘመነ ዮሐንስ በሃያ ስምንት እንዲከበር ያደረጉበት ምክ ንያት በመጠኑ ግልጽ ለማድረግ በመጀመሪያ ይህን ነገር የጀመረው ዮስጣትያኖስ የተባለ የሮሙ ቄሣር ነው፡፡ ይህ ዮስጣትያኖስ በአንባ ገናንነት ስሙን ለማስጠራት ከዘመነ ሐዋርያት አንሥቶ እርሱ እስከ ነገሠበት ዘመን ድረስ ታኅሣሥ ሃያ ዘጠኝ ቀን በየዓመቱ ይከበር የነበረውን ‹‹ጌታ ሁን እንደሻህ ሁን›› እንዲሉ በማን አለብኝነት ለእርሱ ክብርና ዝና ሲባል ሁል ጊዜ በየዓመቱ ታኅሣሥ ሃያ ስምንት ቀን እንዲከበር አዋጅ አስነገረ፡፡ ነገር ግን ተቀባይነት ስላጣ በግድ ለማሳመን ብዙ ሕይወትን አጠፋ ብዙ ደምን አፈሰሰ፡፡
ከብዙ እልቂት በኋላ ድርጊቱ ያሳሰባቸው ሰዎች የንጹሐን ደም ለምን በከንቱ ይፈሳል፡፡ ይህ ሥርዓት እንጂ ሃይማኖት አይደለም ደግሞም የአሁኑ ንጉሥ ያፋለሰውን ከእርሱ በኋላ የሚነሣ ንጉሥ ወደነበረው ሊመልሰውና ሊያስተካክለው ይችላል፡፡ ስለዚህ እልቂቱን ለማስቆም ለጊዜው በሦስቱ ወንጌላዊያን እንደነበረው ታኅሣሥ ሃያ ዘጠኝ ቀን እንዲከበር በዘመነ ዮሐንስ ብቻ በሃያ ስምንት ቀን እንዲከበር ይሁን የሚል አስታራቂ ሐሳብ አቀረቡ ንጉሡና ከተቃዋሚዎች በከፊል ተቀበሉት ቀሪዎቹንም ንጉሡ በማስገደድና በማባበል እንዲቀበሉት አደረገ ይላል፡፡/ዜና ምእምናን ወአላውያን/::

 በሮም የተቀሰቀሰ በሽታ ወደ አገራችን እንዴት ተጋባ?
ከጉባኤ ኬልቄዶን በኋላ የሮማ ቤተ ክርስቲያን ከኦርቶድክስ አብያተ ክርስቲያናት ይልቁንም አንድ አካል አንድ ባሕርይ ከሚሉ ከአምስቱ አኃት አብያተ ክርስቲያናት ማለት ከኢትዮጵያ፣ ከግብጽ/ከእስክንድርያ/፣ ከሶርያ፣ ከሕንድ ፣ ከአርማንያ በሃይማኖትም በሥርዓትም ተለይታለች ይህ በሮም የተፈጠረው በሽታ ወደ እኛ አገር /ወደ ቤተ ክርስቲያናችን/ እንዴት ሠርጎ ሊገባ ቻለ ወደ አገራችን የገባው በፖለቲካ ምክንያት ነው፡፡ ይኸው በአሥራ አራተኛው ምእት አጋማሽ ማለት ከአሥራ ሁለት ዘጠና ሰባት/1297/ እስከ አሥራ ሦስት ሃያ ሰባት/1327/ በኢትዮጵያ ነግሦ የነበረው ዓምደጽዮን በምሥራቅ በኩል ጠላት በበረታበት ጊዜ ከሮም መንግሥት ወታደራዊ ርዳታ ጠየቀ፡፡
በወቅቱ የነበረው የሮም ንጉሥ ርዳታውን ለማግኘት እንዲችል በዘመነ ዮሐንስ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን በዓለ ልደት ታኅሣሥ ሃያ ስምንት ቀን ብሔራዊ በዓል አድርጎ እንዲ ያከብር ስለአስገደደውና እርሱም ግዴታውን በክብር ተቀብሎ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ላይ ተግባራዊ ለማድረግ ታጥቆ ተነሣ፡፡ ነገር ግን ከጥቂቶች አድርባዮችና የንጉሡ ግብረ በላዎች ከሆኑ በስተቀር ብዙዎች የቤተ ክርስቲያን አባቶችና ሕዝበ ክርስቲያኑ በጽናት ተቃወሙት ከተቃዋሚዎቹ መካከል የደብረ ሊባኖሱ ሦስተኛ ዕጨጌ አቡነ ፊልጶስ ኢትዮጵያን ከአሥራ ሁለት ተካፍለው ለማስተማር የተመደቡ አሥራ ሁለቱ ንቡራነ እድ ፣ ግብጻዊው ጳጳስ አቡነ ያዕቆብ ይገኙበታል፡፡ ይሁን እንጂ ከዚያ በኋላ በአሥራ ስድስተኛው ምእት በጎንደር ነግሦ የነበረው የአፄ ፋሲል አባት አፄ ሱስንዮስ በዚህ አንጻር ከሮም መንግሥት ወታደራዊ ርዲታ በጠየቀ ጊዜ የካቶሊክን ሃይማኖት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሃይማኖት ለማድረግ ካልተስማማ በስተቀር ርዳታውን እንደማያገኝ ሲነገረው ስምምነቱን አሜን ብሎ በመቀበል የካቶሊክ ሃይማኖት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሃይማኖት እንዲሆን በማወጁ በከተማና በገጠር የነበረው ወንዱም ሴቱም በሙሉ ሲቃወመው ብዙኃኑን ያለርኅራኄ በጭካኔ እንዲስፈጀ ሁሉ ዓምደጽዮንም የጌታችን በዓለ ልደቱን ከማፋለሱም ባሻገር የአባቱን ዕቅብት ከሕግ ሚስቱ ደርቦ አግብቶ ስለነበረ እነዚህን ስሕተቶች እንዲያርም ዕጨጌው ከሌሎቹ መምህራን ጋር በተደጋጋሚ ቢመክሩት ቢዘክሩት አልሰማም ስላለ በኅብረት አወገዙት፡፡ እርሱም በግርፋት፣ በእሥራት፣ በስደትና
በሞት ይቀጣቸው ያንገላታቸው ጀመር ግብጻዊው ጳጳስ አቡነ ያዕቆብም በአባቶች መሰቃየትና መንገላታት ይልቁንም ከተሰደዱት መካከል ዕጨጌው አቡነ ፊልጶስ ነበሩና በዕጨጌው መሰደድ ተበሳጭተው ወደአገራቸው ለመሄድ ተነሡ፡፡
 ንጉሡ ይህን ሲሰማ በመደናገጥ ዕጨጌውን እፈታለሁ የምትሰጡኝም መመሪያ ሁለ እቀበላለሁ በማለት ጳጳሱን ተለማምጦ አስቀራቸው ዕጨጌውንም ለጊዜው ፈታቸው፡፡ ነገር ግን ንጉሡ ስሕተቱን ባለማስተካከሉ ዕጨጌው መልሰው አወገዙት እርሱም ዕጨጌውንና ሴቶችንም ወንዶችንም ተከታዮቻቸውን ልብሳቸውን ገፍፎ ካስገረፋቸው በኋላ እራቁታቸውን በከተማ እየጎተቱ እንዲዘበትባቸው አደረገ ይልቁንም የንጉሡና የመኳንንቱ ዕቁባቶች ሲሳለቁባቸው በዚህ ጊዜ መነኮሳይያቱ/ሴቶቹ መነኮሳት/ ምን ያስቃችኋል በአባቶቻችን ያለው በባልቻችሁ ያለነው በእኛ ያለው በእናንተ ያለው ነው በራሳችሁነው የምትስቁት ከእናንተ የተለየ ተፈጥሮ የለንም በማለት ያለፍርሀትና ያለእፍረት በድፍረት እየተናገሩ መከራውን በደስታ እንደተቀበሉት ገድለ ፊልጶስ ይናገራል ገድሉ ጨምሮ እንደሚያስረዳው ያን ጊዜ ሲገረፉ በመሬት ላይ ከተንጠባጠበ ደማቸው እሳት ተነሥቶ ከተማውን አቃጠለው ይላል፡፡ ከይኩኖ አምላክ እስከ ልብነ ድንግል በሚል ርእስ የተጻፈ የኢትዮጵያ ታሪክ ግን የፊልጶስ ደጋፊዎች በአባታችን በአቡነ ፊልጶስ ገቢረ ተአምራት ተቃጠለ ይላሉ፡፡ የዓምደ ጽዮን ደጋፊዎች ደግሞ የፊልጶስ ተከታዮች አቃጠሉት ይላሉ በማለት ጸሐፊው ተአምራቱን ለማደብዘዝ ቢጥርም የጌታችን በዓለ ልደት መዛባት የለበትም እያሉ የሚጋደሉ መነኮሳት ሲገረፉ ከተማው እንደተቃጠለ ግን እውነተኛ ምስክርነቱን ሰጥቷል፡፡

ህልከኛ መሆን የከፋ ጥፋት ነው
አንድ ጊዜ ልባቸው በክፋት የተደፈነ ሰዎች ምንም ታላቅ ተአምር ቢደረግ በህልከኝነት በበደል ላይ በደል ይጨምራሉ እንጂ በጥፋታቸው ተጸጽተው ንስሐ አይገቡም ለምሳሌ ክብርና ምስጋና ለእርሱ ይሁንና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ስብከቱ ብዙ አስደናቂና አስገራሚ የሆኑ ተአምራቶችን ሲያደርግ እያዩ ተቃዋሚዎወቹ ፈሪሳውያን እነርሱ የሰይጣን ማደሪያ ሁነው እያለ የባሕርይ አምላክ የሆነ እርሱን “በአጋንንት አለቃ በብዔል ዜቡል ነው እንጂ ይህስ አጋንንትን አያወጣም አሉት” ማቴ 12.24
ንጉሥ ዓምደ ጽዮንም በተደረገው ተአምራት እግዚአብሔር በቅደሳኑ አድሮ የሚሠራውን ድንቅ ተአምራቱን አይቶ ከስሕተቱ በመመለስ ፋንታ በኀጢአት ላይ ኀጢአት ለመጨመር ዕጨጌውን መልሶ አሳደዳቸው ጳጳሱ አቡነ ያዕቆብም ይህንን ሁሉ በደል በማየት ተቁጥተው ወደአገራቸው እንዲሄዱ አደረገ፡፡ በዚህ ጊዜ ሕዝበ ክርስቲያኑ ሁለቱንም አባቶች በአንድ ጊዜ በማጣቱ ንጉሡን ተባብሮ ተቃወመው ጳጳሱን መልሶ እንዲያመጣቸው ዕጨጌውንም እንዲፈታ አስገደደው የተባበረ ሕዝብ ያሸንፋልና እርሱም ተሸንፎ ሳለ እንዳ ተሸነፈ ለመምሰል ጳጳሱን ቀድሞውንም በገንዘቤ ገዝቼ ነው ያመጣሁት አሁንም በገንዘቤ ገዜቼ አመጣዋለሁ ዕጨጌውንም እፈታላችኋለሁ ብሎ ጳጳስን አመጣ ዕጨጌውንም ፈታ፡፡
ይሁን እንጂ ዓምደጽዮን አባቶችን ወደ የቦታቸው ከመለሰ በኋላ ወዲያው ስለአረፈ በእግሩ ልጁ ሰይፈ አርዕድ ነገሠ ሰይፈአርዕድም ‹‹ጅብ እስኪነክስ ያነክስ›› እንዲሉ አባቶች ቀብተው እስኪያነግሡትና ሥልጣን እስኪይዝ ድረስ ራሱን ዝቅ አድርጎ ቃላችሁን አክብሬ በመራችሁኝ መንገድ እጓዛለሁ በማለት ምሎና ተገዝቶ መንግሥት ከጨበጠ ‹‹በኋላ የክፉ ልጅ ክፉ›› እንዲሉ ሲያየው ያደገ የአባቱን ክፋት ሁሉ አንድ በአንድ አጠናክሮ ቀጠለበት ፡፡ይኸውም ምንም ፣
ሀ/ እንደ አባቱ ወይም ከአባቱ በወረሰው አንባ ገናነንነት እርሱም የጌታችንን በዓለ ልደት በዘመነ ዮሐንስ ታኅሣሥ ሃያ ስምንት ቀን እንዲከበር አደረገ፡፡
ለ/ የአባቱን ሚስት ባያገባም እንደ አባቱ ሁለት ሚስቶችን ደርቦ አገባ ፣
ሐ/ አባቱ በአባቶች ላይ ያደረሰው፤ የነበረውን ግፍ እርሱም አጠንክሮ ቀጠለበት ስለሆነም ጳጳሱን ለሁለተኛ ጊዜ ወደ አገራቸው እንዲሄዱ አደረገ ዕጨጌውንም ደቡብ ጎንደር ውስጥ ስማዳ በሚባል ቦታ አጋዛቸው፡፡
በፍጻሜ ዘመናቸው በዙያው በደቡብ ጎንደር ስማዳ ውስጥ በምትገኝ ደብረ ዕንቁ ገዳም አርፈው ብዘ ዘመናት ከኖሩ በኋላ አጽማቸውን ወደ ደብረ ሊባኖስ አፍልሰው እንዳመጡት ገድላቸው ይናገራል፡፡

ታላቅ ሰው የሚባለው በዓለም በጎ መታሰቢያ ትቶ ያለፈ ነው
“የጻድቅ መታሰቢያ ለዘለዓለም ይኖራል” መዝ.111፥6 እንዳለው ሁሉ ደግ ሰው በሕይወተ ሥጋ ሳለ በሠራው በጎ ሥራ ይመሰገናል፡፡
ከሞት በኋላም በበጎ ሥራው ለዘለዓለሙ ሲታወስና ሲታሰብ ይኖራል፡፡ በዚህ መሠረት አቡነ ፊልጶስና መሰሎቻቸው በሕይወት ሳለ ባደረጉት ተጋድልና በጎ ሥራ  እግዚአብሔር በቅደሳኑ ድንቅ ነው የእሰራኤል አምላክ እርሱ ኃይልን ብርታትንም ለሕዝቡ ይሰጣል እግዚአብሔር ይመስገን›› መዝ67፥35 እንዳለ በበጎ ሥራቸው ሲታወሱ ከመኖራቸውም በላይ እግዚአብሔር አጽማቸው በአረፈበት በመቃብራቸው ቤተ ክርስቲያናቸው በታነጸበት በጸለዩበትና በተጋደለበት ቦታ ሁለ ጠበል እንዲፈልቅ ልዩ ልዩ ተአምራት እንዲደረግ ሰዎች ከደዌ ሥጋ ከደዌ ነፍስ እንዲፈወሱ እያደረገ ቅዱሳኑ እንዲከበሩ ከማድረጉም በላይ እግዚአብሔር በቅዱስ እገሌ አድሮ ከደዌየ ከጭንቀቴ ገላገለኝ እንዲህ ያለ ድንቅ ሥራ ሠራልኝ የቅዱስ እገሌ አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን እየተባለ ይመሰገንባቸዋል፡፡ ክፉዎች ሰዎች ግን በሕይወታቸውም በሞታቸውም ሰውን ሲጎዱ ነው የሚኖሩ ለምሳሌ በአፄ ሱስንዮስ ጊዜ የነበረው አልፎንሱ የተባለው ካቶሊካዊ ጳጳስ በሕየወቱ ከሱስንዮስ ጋር የብዙዎች ደም ለማፍሰስ ተባባሪ ከመሆኑም ባሻገር በአፄ ፋሲል ጊዜ በጉባኤ ተረትቶ ወደአገሩ እንዲሄድ ሲፈረድበት ለአንዱ ኢትዮጵያዊ ደቀ መዝሙር የጸጋን ሃይማኖት ለሌላው ደቀ መዝሙር የቅብአትን ሃይማኖት አስተምሮ በኢትዮጵያ እሾክ ተክየባት ሄድሁ እንዳለ ታሪክ ይናገራል፡፡ 
ቅብዓቶች ጌታችን ኢየ ሱስ ክርስቶስን እንደፍጡራን በቅብዓተ መንፈስ ቅደስ ከበረ የሚል ነው ጸጋ በኤፌ ሶን ጉባኤ እንደተወገዘው እንደንስጥሮስ ፡-
ሀ/ ቅድመ ዓለም ከአብ የተወለደው አንድ ልደት
ለ/ በዚህ ዓለም ከማርያም ሰው ሁኖ ተወለደ ሁለት ልደት
ሐ/ በዮርዳኖስ በተጠመቀ ጊዜ እንደሰዎች የጸጋ ልጅ ሆነ/ሦስት ልደት/ ብሎ የሚያምን ነው፡፡
ስለሆነም ያ እርሱ የተከለው እሾኸ እስከ ዛሬ ሲያበጣብጥ ይኖራል፡፡
እንደዚሁም ዮስጣትያኖስና እነ ዓምደጽዮን ሳሉ ዕብሪት በተሞላበት ሥልጣናቸው የብዙ ሰው ሕይወት ከማጠፋታቸውም በላይ እነርሱ ተክለውት ያለፉ እሾኸ እስከ ዛሬ ሰዎች ሰዎችን ሲያድሙበት ይኖራሉ፡፡
ይኸውም የጾመ ልደት መግቢያ ኅዳር አሥራ አምስት ቀን ሲሆን በዘመነ ዮሐንስ አንዳንዶቹ ከኅዳር አሥራ አራት ቀን ጀምረን ነው መጾም ያለብን ይላሉ እንደዚሁም በአሥራ አራት ቀን አብዛኛዎቹ አብያተ ክርስቲያናት ጥዋት ሲቀድሱ አንዳንዶቹ ውለው ይቀድሳሉ በአንድ ቤተ ክርስቲያንም ግማሾቹ ጥዋት እንቀድስ ሲሉ ከፊሎቹ ውለን ነዉ የምንቀድሰው ይላሉ በዚህ ምክንያት በየአራት ዓመቱ በየቦታው ከፍተኛ ብጥብጥ ይነሣል፡፡ ይህ ሁሉ ችግር ደግሞ የተፈጠረው ነገሥታቱ በጀብደኝነት በዓለ ልደቱን በዘመነ ዮሐንስ በሃያ ስምንት እንዲውል በማድረጋቸው ነው፡፡
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት ታኅሣሥ ሃያ ዘጠኝ ቀን ነው ምን ጊዜም አይዛባም አይፋለስም የክርስቶስ በዓለ ልደት በዘመነ ዮሐንስ በሃያ ስምንት ይሆናል የሚለው ነገሥታቱ በዕብሪት የፈጠሩት ችግር እንጂ የጌታችን በዓለ ልደት ከታኅሣሥ ሃያ ዘጠኝ ቀን ፈጽሞ
አይፋለስም፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍትም የሚያረጋግጡት ይህነን እውነታ ነው፡፡ ከቅደሳት መጻሕፍት የተወሰኑትን ከዚህ ቀጥለን እንመልከት፡፡

1. ሲኖዶስ ዘሐዋርያት “ዘጸሐፈ ቀሌምንጦስ ትእዛዝ ሰመንቱ ወይግበሩ በዓለ ልደቱ ለእግዚእነ አመ ዕሥራ ወተስዑ ለታኅሣሥ እስመ ውእቱ ርእሰ በዓላት
አማርኛ የሐዋርያት ሲኖዶስ ቀሌምንጦስ በጻፈው በስምንተኛው ትእዛዝ የጌታችንን በዓለ ልደት ታኅሣሥ ሃያ ዘጠኝ ቀን ያክብሩ እርሱ የበዓላት ራስ ነውና ብለዋል፡፡
2. ዲድስቅልያ አንቀጽ ዕሥራ ወተስዓቱ ‹‹አፍቁረኒሁ ለእግዚአብሔር ዕቀቡ እንከ ዕለተ በዓላት ቀዳሚ በዓል ዘውእቱ ዕለተ ልደቱ ለክርስቶስ አመ ዕሥራ ወኀሙሱ ለታስዕ ወርኅ በኈልቁ ዕብራውያን ወበሐሳበ ግብጻውያን አመ ዕሥራ ወተስዐ ለረብዕ ወርኅ አማርኛ በዱድስቅልያ በሃያ ዘጠነኛው አንቀጽ የእግዚአብሔር ወዳጆች ሆይ እንግዲህ የበዓላትን ቀን ጠብቁ ይኸውም በዕብራውያን አቆጣጠር በዘጠነኛው ወር በሃያ አምስተኛው ቀን በግብጻውያን አቆጣጠር በአራተኛው ወር በሃያ ዘጠነኛ ቀን የሚውል የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ዕለተ ልደት የመጀመሪያው በዓል ነው›› በማለት በዓለ ልደት ታኅሣሥ ሃያ ዘጠኝ ቀን እንደሚከበር በማያሻማ ሁኔታ አረጋግጠዋል፡፡ እነዚህ መጻሕፍት ደግሞ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን የሐዋርያት መጻሕፍት መሆናቸውን አምና ተቀብላ ከሰማንያ አንድ መጻሕፍት መድባ የምትጠቀምባቸው ታላላቅ መጻሕፍት ናቸው በተለይ ዲድስቅሊያን የሊቃውንት ጉባኤ ግእዙን ካስተካከለ በኋላ ወደ አማርኛ በመተርጎም ቤተ ክርስቲያናችን ልትጠቀምበት የሚገባ ትክክለኛ መጽሐፍ ነው ሊታተም ይገባል የሚል ትክክለኛ ምስክርነቱን በቃለ ጉባኤ አጽድቆ ለኅትመት ስላሳለፈው እነሆ ታታሞ በቤተ ክርስቲያኗ መደብሮች እየተሸጠ ይገኛል ግእዝ የማያውቅ ሁሉ በአማርኛ አንብቦ መረዳት ይችላል፡፡

3. ሠለስቱ ምእትም በፍትሐ ነገሥት አንቀጽ አሠርቱ ወተስዓቱ ‹‹አኀዊነ ተአቀቡ በመዋዕለ በዓላት ዘውእቱ በዓለ ልደቱ ለእግዚነ ወግበሩ አመ ዕሥራ ወኀሙሱ ለታስዕ ወርኅ በዕብራውያን ወበግብጻውያን አመ ዕሥራ ወተስ ለራብዕ ወርኅ›› አማርኛ ሦስት መቶ ሊቃውንት በፍትሐ ነገሥት በአሥራ ዘጠነኛው አንቀጽ ወንድሞች ሆይ በበዓላት ቀን ተጠበቁ ይኸውም በዕብራውያን አቆጣጠር በዘጠነኛው ወር በሃያ አምስተኛው ቀን በግብጻውያን አቈጣጠር በአራተኛው ወር በሃያ ዘጠነኛው ቀን የሚሆን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደትን ጠብቁ ብለዋል፡፡ ከዚህ ልናስተውለው የሚገባ አንድ ነገር አለ እርሱም በዲድስቅልያም በፍትሐ ነገሥትም ያለው ቃል ሲሆን በዕብራውያን አቆጣጠር በዘጠነኛው ወር በሃያ አምስተኛው ቀን የሚለው ነው፡፡ ዕብራውያን /እስራኤል/ ዘመን የሚለ ውጡ ወይም አዲስ ዘመን የሚቀበሉ በሚያዚያ ነውና ከሚያዚያ አንሥቶ እስከ ታኅሣሥ ዘጠነኛ ወር ስለሆነ ነው በቀን ቁጥርም እኛ ሃያ ዘጠኝ ስንል እነርሱ ሃያ አምስት ስለሚሉ ነው፡፡ እንጂ ሌዩነት የለውም፡፡

4. ዳግመኛ ሠለስቱ ምእት በዐሥራ ስምንተኛው አንቀጽ ታኅሣሥ 28 ቀን ድሩረ ጾም/ገሀድ/ አድርገው እስከ ሠርክ ጹሙ ብለዋል፡፡ ስለዚህ ጾሙን ሽሮ በተቃራኒው በዓል አድርጎ ሲበሉ ሲጠጡ መዋል ታላቅ ስሕተት ከመሆኑም በላይ ሦስት መቶ ሊቃውንትን ያናገራቸው መንፈስ ቅዱስን ማቃለል ይሆናል፡፡
5. ከላይ በሰፊው የተገለጸው ገድለ ፊሊጶስ በዓለ ልደቱ መፋለስ የለበትም በሚል አላማ ብዙ አባቶች የሕይወት መሥዋዕትነት እንደከፈሉ ይናገራል፡፡
6. የቅዱስ ሲኖዶስ አባል የሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የዝዋይ ካህናት ማሰልጠኛ ኃላፊ የነበሩት ስመ ጥር ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስም ልደት የሚከበረው ታኅሣሥ ሃያ ዘጠኝ ቀን ነው በዘመነ ዮሐንስ ጳጉሜን ስድስት ስትሆን ግን ታኅሣሥ ሃያ ስምንት ቀን ይሆናል፡፡ ይህም የተጀመረው በዓምደ ጽዮን ዘመነ መንግሥት ነው፡፡ ሁለት ቀን ልደት ማለት ግን ጥሩ አይደለም ከዚያስ ሃያ ዘጠኝን መያዝ ይሻላል፡፡ በዚህ ቀን ስሌትም ብዙ የቤተ ክርስቲያን ሰዎች ሲጣሉበት ኑረዋል ለወደፊቱም ይህን ለማስተካከል የኢትዮጵያ ኦርቶድክስ ቅዱስ ሲኖዶስ ሙሉ መብት አለው ብለዋል፡፡ /የኢትዮጵያ ኦርቶ ድክስ ተዋሕድ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ሰኔ 1991 /
ተቀባይነት ያለው ማስረጃ ማነኛውም ማስረጃ ዋጋ የሚኖረው ከሁለት በላይ ሲሆን ነው፡፡
1. “በሁለት ወይም በሦስት ምስክሮች ሞት የሚገባቸው ይገደሉ በአንድ ምስክር ግን አይገደሉም”ዘጸ.17፥6
2. ስለበደል ሁሉ ክፉ በማድረግም ስለሚሠራት ኀጢአት ሁሉ በማንም ላይ አንድ ምስክር አይሁን በሁለት ምስክሮች ወይም በሦስት ምስክሮች ቃል ነገር ሁሉ ይጸናል” ዘዳ.19፥15
3. “ባይሰማህ ግን በሁለተኛ ጊዜ ከአንተ ጋር አንድ ወይም ሁለት ምስክር ያዘ ነገር ሁሉ በሁለት ወይም በሦስት ቃል ይጸናል ማቴ 18፥16
4. እኔ ብፈርድ እውነት እፍርዳለሁ እኔና የላከኝ አብ ነን እንጂ አንድ ብቻዬ አይደለሁምና የሁለት ሰዎች ምስክርነት የታመነ እንደሆነ በሕጋችሁ ተጽፎአልና እኔ ሰለራሴ ምስክር ነኝ የላከኝ አብም ይመሰክርልኛል” ዮሐ.8፥16-18
5. “ሁለት ወይም ሦስት ምስክሮች ሳይመሰክሩበት በሽማግሌው ላይ ነገር አትስማ” 1ጢሞ5፥19 እነዚህ ሁሉ ጥቅሶች አንድ ምስክር ዋጋ እንደሌለው የሚያስረዱ ናቸው፡፡

ከቀድሞ ጀምሮ 2 የተከፋፊሉ ቡድኖች አሉ:-
1. የጌታችን በዓለ ልደት ምን ጊዜም በ29 ይከበር የሚሉ
2. በዘመነ ዮሐንስ በ28 ይከበር የሚሉ ናቸው፡፡
በዚህ ሁኔታ የጌታችን በዓለ ልደት ምን ጊዜም የማይናወፅ ታኅሣሥ ሃያ ዘጠኝ ቀን ነው የሚለው ክፍሎች ብዙ ማስረጃንና ምክንያቶችን ያቀርባሉ፡፡ በዘመነ ዮሐንስ ታኅሣሥ ሃያ ስምንት ይከበር የሚሉ ግን ማስረጃቸው አንድ መጽሐፈ ስንክሣር ብቻ ነው ይኸውም አባ ዘገየ የተባለ አባት ከግራኝ ወዲህ የተጻፈ ስንክሳር ነው እንጂ ከዚያ በፊት የነበረ ስንክሣር በሃያ ስምንት አከብሩ አይልም ሲሉ በመድበለ መጽሐፋቸው ጽፈዋል፡፡ ለማስረጃም የሦስት አብያተ ክርስቲያናት የጎንደር ደብረ ብርሃን ሥላሴን ፣ የመሐልጌ ጊዮርጊስን የታይ ጋይንት ስንክሣሮችን ጠቅሰዋል፡፡ ስለዚህ እንደ አባ ዘገየ አባባል በሃያ ስምንት ይከበር የሚሉ ማስረጃቸው አንድ ወይም ከአንድ በታች ስለሆነ ዋጋ አይኖረውም፡፡ ከዙህም ሌላ በሃያ ስምንት የሚከበረው በዘመነ ዮሐንስ ጳጉሜን ስድስት ስለምትሆን ነው ይላሉ ይህም ትክክል አይደለም ጳጉሜን ስድስት የምትሆነው በሉቃስ መጨረሻ ነው በዮሐንስ አይደለምና::

1. ጌታችን የተወለደውም አንድ ጊዜ ነው እሱም በዘመነ ዮሐንስ ተፀንሶ በዘመነ ማቴዎስ ነው የተወለደው ጳጉሜን ስድስት ከምትሆንበት ከዘመነ ሉቃስ ጋር ምንም ግንኙት የለውም፡፡
2. ጳጉሜን ስድስት ስትሆን በዓለ ልደቱ ቦታውን ይለቃል ከተባለ ግዝረቱም ጥምቀቱም ቃና ዘገሊላም ልደተ ስምዖንም ሌሎችም በዓላት ሁሉ ቦታቸውን ይለቁ ነበረ እውነትን የተከተለ ቀጥተኛ በቤተ ክርስቲያን ስሌት ቢሆን ኑሮ፡፡
3. ቅዱስ ዴሜጥሮስ ለበዓላትና ለአጽዋማት ሁሉ ኢየዐርግንና ኢይወርድን ሲሠሩ ለዚህም ይሠራለት ነበር፡፡
4. ቅዱስ ያሬድም ለበዓላት ሁሉ ለአመ ኮነን ሲሠራ ለዚህም ይሠራለት ነበር፡፡ በጥቅሉ በዓለ ልደቱ በሃያ ስምንት እንዲ ከበር የሆነው ነገሥታቱ በጀብደኝነት ጀምረው በግድ አጸኑት እንጂ የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት እንዳልሆነ ሁሉ ሊያውቀው ይገባል፡፡ ስለሆነም የአንዲት ኦርቶድክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ልጆች በሙሉ ያለ ሁከትና ያለጭቅጭቅ ጾሙን ኅዳር 15 ቀን እየጀመሩ በዓለ ልደቱን ታኅሣሥ ሃያ ዘጠኝ ቀን በማክበር በሰላምና በስምምነት እንዲኖሩ የሚመለከተው ሁሉ በዓለ ልደቱ በየዓመቱ ከሃያ ዘጠኝ ቀን እንዲይወጣ ጥረት ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ የሰላም አምላክ ይርዳን” ይላል::
እስካሁን ድረስ አንቀበልም፣ ካፈርን አንሸሽም በማለት ብዙ ምዕመናንን ግራ ስታጋቡ ቆይታችሁ አሁን ግን ከራሳችሁ አንደበት ይህን ታላቅ የምስራች እንድንሰማ ያደረገን የቅዱሳን አምላክ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን:: ስለ ልደቱም በ28 ለማክበራችሁ የራሳችሁ ማስረጃ “በሃያ ስምንት ይከበር የሚሉ ማስረጃቸው አንድ ወይም ከአንድ በታች ስለሆነ ዋጋ አይኖረውም” እንደሆነ ስትናገሩ በ29 ለመከበሩ ደግሞ “የጌታችን በዓለ ልደት ምን ጊዜም የማይናወፅ ታኅሣሥ ሃያ ዘጠኝ ቀን ነው የሚለው ክፍሎች ብዙ ማስረጃንና ምክንያቶችን ያቀርባሉ” በማለት በራሳችሁ አንደበት መሰከራችሁ::

በጋዜጣው ውስጥ “በአፄ ሱስንዮስ ጊዜ የነበረው አልፎንሱ የተባለው ካቶሊካዊ ጳጳስ በሕየወቱ ከሱስንዮስ ጋር የብዙዎች ደም ለማፍሰስ ተባባሪ ከመሆኑም ባሻገር በአፄ ፋሲል ጊዜ በጉባኤ ተረትቶ ወደአገሩ እንዲሄድ ሲፈረድበት ለአንዱ ኢትዮጵያዊ ደቀ መዝሙር የጸጋን ሃይማኖት ለሌላው ደቀ መዝሙር የቅብአትን ሃይማኖት አስተምሮ በኢትዮጵያ እሾክ ተክየባት ሄድሁ እንዳለ ታሪክ ይናገራል፡፡ ቅብዓቶች ጌታችን ኢየ ሱስ ክርስቶስን እንደፍጡራን በቅብዓተ መንፈስ ቅደስ ከበረ የሚል ነው” የሚለውን እውነተኛ ማስረጃ የሌለው ሀሳብ እንደ ልደቱ ማስረጃውን ስታዩ እንደምታምኑ ተስፋ እናገርጋለን:: ቅብዓት ደግሞ ምስጢር እንጅ ሃይማኖት እንዳልሆነ መጽሐፍት ይናገራሉ::
 “ቅብዓቶች ጌታችን ኢየ ሱስ ክርስቶስን እንደፍጡራን በቅብዓተ መንፈስ ቅደስ ከበረ የሚል ነው” የሚለው በሥጋ ርስት ተራበ፣ተጠማ፣ ደከመ፣ታመመ፣ሞተ ፣ተነሳ፣ ዐረገ እንደሚባለው ሁሉ ተቀብቶ ከበረ የሚባለውም ሥለ ሥጋ እንግድነት ነው:: ይህንንም ከመሬት ተነስተን፣ከአእምሯችን አንቅተን የምንናገረው ሳይሆን ቅዱሳት መጽሐፍትን መሰረት ያደረገ ነው:: እንደ ፍጡራን የሚለው የፍጡራንና የሥግው ቃል ቅብዓት የተለየ ነው:: ይኼውም የፍጡራኑ በልክ፣ በመጠን፣የጸጋ ኃጢአት ስንሰራ የሚወሰድብን ጽድቅ ስንሰራ ደግሞ የሚጨመርልን፣ ቅብዓቱም በቅብዓ ሜሮን አማካኝነት የሚገኝ ሲሆን የሥግው ቃል ግን ያለልክ፣ያለመጠን፣ የባህርይ የማይወሰድበት፣ የማይጨመርለት እንዲሁም እንደ ሜሮን ሁሉ በዐይን የሚታይ ቅብዓት የለውምና በእርሱ ፈንታ መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ ይባልለታል:: ማስረጃውን ለምትፈልጉ በመልዕክት መነጋገር እንችላለን:: ለሁላችንም ምስጢርን የሚገልጽ የቅዱሳን አምላክ እግዚአብሔር ምስጢሩን ይግለጽልን::

ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር አሜን ! ይቆየን::

1 comment:

  1. ቃለ ህይወት ያሰማልን። ለነፍስ ልምላሜ ይሰጣሉ ሙሉ ጹህፎቹ።

    ReplyDelete