Monday, April 17, 2023

 ዜና ትንሣኤሁ ለኢየሱስ ክርስቶስ

=======+==========
ክፍል ሁለት
======
ከክፍል አንድ በቀጥታ የቀጠለ
====================
ወማርያምሰ ቆመት ኀበ መቃብር አፍአ ወትበኪ
ማርያም ግን ከመቃብር አጠገብ ሁና ታለቅስ ነበር ፡፡
ወእንዘ ትበኪ ሐወጸት ውስተ መቃብር
እያለቀሰች ወደ መቃብር በተመለከተች ጊዜ
ወርእየት ክልኤተ መላእክተ በጸዓድው አልባስ
ሁለት መላእክት ብሩህ ብሩህ (ነጭ ነጭ) ልብስ ለብሰው
ወይነብሩ አሐዱ ትርኣሰ ወአሐዱ ትርጋጸ ኀበ ነበረ ሥጋሁ ለእግዚእ ኢየሱስ
የጌታችን ሥጋ ካለበት ቦታ አንዱ በራስጌ አንዱ በግርጌ ተቀምጠው አየች ፡፡
ወይቤልዋ እሙንቱ መላእክት ምንት ያበክየኪ ኦ ብእሲቶ
እነዚያ መላእክት አንች ሆይ ምን ያስለቅስሻል
ወመነ ተኃሥሢ
ማንንስ ትሻለሽ አሏት ፡፡
ወትቤሎሙ እስመ ነሥእዎ ለእግዚእየ እምውስተ መቃብር
ጌታየን ከመቃብር ውስጥ ወስደውታልና
ወኢየአምር ኀበ ወሰድዎ
ወደየት እንደወሰዱት ግን አላውቅም አለቻቸው ፡፡
ወዘንተ ብሂላ ተመይጠት ድኅሬሃ
ይህንን ተናግራ ወደኋላ ተመለሰች ፡፡ ስለምን ወደኋላ ተመለሰች ቢሉ
የአዘንተኛ ዓይኑ ባካና ነውና ፡፡ አንድም መላእክት ከወደፊቷ ሲሰግዱ አይታቸዋለች ፡፡ ከወደኋላዋ ጥላውን ጥሎባታል ፡፡ መለስ ብትል ቁሞ አይታዋለች ፡፡
ወኢያእመረት ከመ እግዚእ ኢየሱስ ውእቱ
ጌታ ኢየሱስ እንደሆነ አላወቀችውም ፡፡
ወይቤላ እግዚእ ኢየሱስ ብእሲቶ ምንት ያበክየኪ
ጌታ ኢየሱስም አንች ሆይ ምን ያስለቅስሻል
ወመነ ተኃሥሢ
ማንንስ ትሻለሽ (ትፈልጊያለሽ) አላት ፡፡
ወመሰላ ላቲሰ ዓቃቤ ገነት ውእቱ
ለእሷም አታክልት ጠባቂ መስሏት ነበር ፡፡
ወትቤሎ እግዚእየ እመኒ አንተ ነሣእኮ ንግረኒ ኀበ ወሰድኮ
ጌታየን አንተ ወስደኸው እንደሆነ ወደየት እንደወሰድከው ንገረኝ
ከመ እሑር አነ ወአንሥኦ ኀቤየ ከመ ዕቅብዖ ዕፍረተ
እኔም ሂጄ ወደኔ አምጥቼ ሽቱ ዕቀባው ዘንድ አለችው ፡፡
ወይቤላ እግዚእ ኢየሱስ ማርያም
ጌታ ኢየሱስም ማርያም አላት ፤፡
ወተመይጠት ወትቤሎ በነገረ ዕብራይስጥ ረቡኒ
ተመልሳ በዕብራውያንን አነጋገር (ቋንቋ) ረቡኒ አለችው ፡፡
ዘበትርጓሜሁ ሊቅ ብሂል
ትርጓሜውም መምህር ማለት ነው ፡፡
ወይቤላ እግዚእ ኢየሱስ ኢትልክፍኒ እስመ ዓዲ ኢዐረጉ ኀበ አቡየ
የተግሳጽ አነጋገር ነው ፡፡ ወደ አባቴ አልወጣሁም ማለት ገና አላመንሽብኝምና ፡፡ አንድም የመሰናበቻው ጊዜ የደረሰ መስሏት ቀርባለችና የማርግበት (አላረግሁም=ረን አጥብቅ /ዕርገቱን ሲያጠይቅ ነው) ጊዜ ገና ነውና አትንኪኝ አላት ፡፡ ይህም ካህናት ልብሰ ተክህኖ ለብሰው ሳሉ ሊነኳቸው እንዳይገባ ለማጠየቅ ነው ፡፡
ወሑሪ ባሕቱ ኀበ አኃውየ ወበሊዮሙ አዓርግ ኀበ አቡየ ወአቡክሙ ኀበ አምላኪየ ወኀበ አምላክክሙ ፡፡
ወደ ወንድሞቼ ሂጅና ወደ አባቴ ወደ አባታችሁ ወደ አምላኬ ወደ አምላካችሁ (ወደፈጣሪየ ወደፈጣሪያችሁ) ዐርጋለሁ ብለሽ ንገሪያቸው እንጅ አትንኪኝ አላት ፡፡
አቡየ ብሎ ስለልደት ተናገረ
አቡየ ያለው የእሱን የባሕርይ ልደቱን ያጠይቃል ፡፡ አቡክሙ ያለው የኛን የጸጋ ልደት ያጠይቃል ፡፡
አምላኪየ አለ በሥጋ ይፈጥረዋልና አምላክክሙ አለ በጥንተ ተፈጥሮ በሐዲስ ተፈጥሮ ፈጥሮናልና ፡፡
ቁጥር 17 ድረስ
አሜን
================
ከዚህ ላይ አንዳንድ ነጥቦችን እናንሳና ኦርቶዶክሳዊ መሠረታችንን እናጽና ፡፡
================================
መድኅን ክርስቶስ “ኀበ አምላኪያ ወአምላክክሙ--ወደ አምላኬ ወደ አምላካችሁ” ብሎ ተናግሯል ፡፡ ክቡር ዳዊት በትንቢቱ “ቀብዐከ እግዚአብሔር አምላክከ” ብሎ ተናግሯል ፡፡
ክርስቶስ አምላኪየ ብሎ የጠራው እግዚአብሔር አብን ነው ፡፡ አምላኪየ ያለበት ምክንያቱ ደግሞ በሥጋው ፍጡር መሆኑን የሚያጠይቅ ነው ፡፡ አምስት ኪሎ ላይ ያለችዋ መንበረ ፓትርያርክ ላይ ያሉት የሲኖዶስ አባላት ጳጳሳት በ2015 ዓ.ም ጥቅምት ላይ “ወልደ አብ የተባለ መጽሐፍ ወልድን ፍጡር ብሏል” ብለው አውግዘውታል ፡፡ ወልደ አብ የተናገረው መድኅን ክርስቶስ በዮሐንስ ወንጌላዊ አድሮ የተናገረውን ነባራዊ ሐቅ ነው ፡፡ አውጋዞች ዘመዶቻችን ግን ወልድን ፍጡር ይላል ብለው ሲያወግዙ ዮሐንስ ወንጌላዊን ራሱ ክርስቶስን እንዳወገዙት ተረድተውት ይሆን?
ለሁሉም ትንሣኤ ልቡና ያድልልን
እኔና እናንተ ዕዝነ ልቡናችንን በዚህ ምሥጢር ላይ አርፈን ክርስትናችንን እንጠብቅ ዘንድ እንትጋ ፡፡ እውነት ተከታዩአ እጅግ ጥቂት ነው ፡፡ ለዚህም ሰሙነ ሕማማትን ማሰብ እጅግ ከበቂ በላይ ነው ፡፡ በተለይ በተለይ ዕለተ ዓርብ ድንቅ ምሥጢር የተገለጠባት ፡፡ እነ ይሑዳንም እነ ዮሐንስንም በደንብ አድርገን የተመለከትንባት ምሳሌአችን ናት ፡፡
ክቡር ዳዊት አምላክከ ያለውና ክርስቶስ አምላኪየ ብሎ የጠራው እግዚአብሔር አብ ነው ፡፡ ይህ ሁኖ ሳለ ሊቀ ሊቃውንት ስምዐ ኮነ መልአክ “እግዚአብሔር አምላክከ የሚለውን እግዚአብሔር አምላክህ ብለን ከተረጎምነው ለክርስቶስ ሌላ አምላክ አለው ያሰኝብናልና የብሉይ ኪዳን እግዚአብሔርናከ አምላክናከ --እግዚአብሔርነትህ አምላክነትህ ብለን አቅንተን እንተረጉማለን” በማለት ጽፈውልናል (ቃለ ጽድቁ ለአብ 2007 ዓ.ም 2ኛ ዕትም ገጽ 124)፡፡
ሰውየው ተቀብዐ በመቀባቱም ክርስቶስ ተባለ መባሉን ላለማመን ሲሉ እንደዚህ ደንደሳሙን ክሕደት ተናግረውታል ፡፡ የክሕደታቸው ደንደስ ከዮሐንስ ወንጌል ጋር አጣልቶ በራሳቸው መንገድ እንዲጓዙ አደረጋቸው ፡፡ ተቀብዐን አመልጣለሁ ሲሉ የወልድን ሰውነት ፈጽመው አጠፉት ካዱት ፡፡ ከዚያም ወደ ሮማዊቷ ኩትለካ ሽምጥጥ ብለው ሮጡ ፡፡
እንዴት አትሉኝም ወንድም እህቶቼ
ዮሐንስ ጌታችን አምላኬ ማለቱ በሥጋ ስለሚፈጥረው ነው ብሎ ተረጎመው ፡፡ ታዲያ ዮሐንስ ወንጌላዊ የተናገረውን ቃል የሚለውጡና የሚያቃኑት ታላቁ ሊቅ ስምዐኮነ መልአክና እሳቸውን የመሳሰሉቱ ሊቃውንት ከዮሐንስ ወንጌላዊ የተሻለ አረዳድና ዕውቅና ተሰጥቷቸው ይሆንን?ንኅሥሥ፡፡ ወደ አምላክነቴ በማለት ሥጋን ከቃል ለያይቶ ነጣጥሎ መኮትለክ አይደል ይኄ::
ሲቀጥል ክቡር ዳዊት እግዚአብሔር አምላክከ ያለውን እንደነ ሊቀ ሊቃውንት ስምዐኮነ አነጋገር “እግዚአብሔርናከ አምላክናከ” ብለን ከለወጥነው እንደ እሳቸው አነጋገር ደግሞ አቃንተን ከተረጎምነው ፤ በዚህ በዮሐንስ ወንጌል “ኀበ አምላኪየ ወኀበ አምላክክሙ” ያለውን “ኀበ አምላክናየ ወኀበ አምላክናክሙ” ማለት ግዴታችን ይሆናላ! ፤ እንዴት አትሉኝም ባለቤቱ አንድ ነዋ! ፡፡
እንዲህም ብለን እንደነ ሊቀ ሊቃውንት ስምዐኮነ አቃንተን ከተረጎምነው የሚያመጣብን እጅግ ደንደሳም ክሕደት ነው ፡፡
እንዴት ያመጣል ቢሉ ፤
ኀበ አምላክናየ ማለት ወደ አምላክነቴ ማለት ሲሆን ቃል ከሥጋ ጋር ሲዋሐድ አምላኩን አጥቶ ነበርና እንደገና ወደ አምላክነቴ ላርግ አለ ያሰኛልና ፡፡ ዉላጤና ሚጠት የተሰኙ ደንደሶችን ያጎናጽፋልና ፡፡
ሌላውና ዋነኛው ደግሞ በእውነቱ ክቡር ዳዊት “እግዚአብሔር አምላክከ” ብሎ ሲነግረን ምሥጢሩ ሳይገለጥለት ቀርቶ ይሆን እነ ሊቀ ሊቃውንት ስምዐኮነ እና መሰሎቻቸው የብሉይ ኪዳን መምህራን “እግዚአብሔርናከ አምላክናከ” ብለው ሊያቃኑት የቻሉት?ይኸንንም ንኀሥሥ ፡፡
የትንሣኤው ንጉሥ ትንሣኤ ልቡናን ያድለን አሜን!
ይቆየን!
ስብሐት ለእግዚአብሔር ኪያነ ዘፈጠረነ ከመ ናምልኮ
ስብሐት ለማርያም እመ አምላክ እግዝእትነ ወመድኃኒትነ
ስብሐት ለመስቀለ ክርስቶስ ዕፀ መድኃኒት ኃይልነ ወፀወንነ፡፡
ክፍል ሦስት ይቀጥላል ፡፡
All reactions:
1

ዜና ትንሣኤሁ ለኢየሱስ ክርስቶስ
=======+==========
ክፍል አንድ
====================
እነሆ የክርስቶስን ትንሣኤ የሚያወሱ ዐበይት ቃላትን ከዕለቱ ሥርዓተ ቅዳሴና የዋዜማ ሥርዓት ለአዘክሮት እንመልከት ፡፡
==========================
“የመጀመሪያው (ከቅዳሴ በፊት የሚሰበከው ምስባክ)
==============================
“ወተንሥአ እግዚአብሔር ከመ ዘንቃህ እምንዋም
ወከመ ኃያል ወኅዳገ ወይን
ወቀተለ ጸሮ በድኅሬሁ”
መዝሙር 77 ፡65
አንድምታ ትርጉም
“ወተንሥአ እግዚአብሔር ከመ ዘንቃህ እምንዋም ፤ ወከመ ኃያል ወኅዳገ ወይን ፤ ወቀተለ ጸሮ በድኅሬሁ” ”
የተኛ ሰው ፈጥኖ እንደሚነሳ እግዚአብሔርም ከሰባ ዘመን በኋላ ፈጥኖ በረድኤት ተነሣ
ከመ ዘኃደጎ ሥካረ ወይን ይላል አብነት የወይን ሥካር እንዳለፈለት ሰው አንድም ከመ ኅዱግ ወይን ይላል አበርትቶ እንደተጣላ ወይን ፡፡ በሀገራቸው ፅኑ መጠጥ አለ ሰው የጠጣው እንደሆነ ሦስት ቀን ወድቆ ይሰነብታል ፡፡ በሦስተኛው ቀን ጥዒና (ጤና) አግኝቶ ኃይል ተሰምቶት ይነሣል ፡፡ አንድም ወይ በተተከለ በሦስት ዓመት ዳስ ጥለውት ያፈራል ፡፡ አንድም ወይን በክረምት ወድቆ ይከርማል በበጋ ዳስ ጥለው በዚያ ላይ ያደርጉታል ይለመልማል ያብባል ያፈራልም ፡፡ ጌታም ቱሩፋንን ይዞ ከባቢሎን ወጥቷልና ፡፡
በእስራኤል ከፈረደ በኋላ በአሕዛብ ፈረደባቸው ፡፡ አንድም እስራኤልን ተከትለው የመጡ ግብጻውያንን አሰጠመ ፡፡
አንድም በዘድኅሬሁ ይላል አብነት ወደኋላው በተመለሰ ውኃ ግብጻውያንን አጠፋቸው ፡፡
አንድም ወተንሥአ ይላል
ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት በከርሠ መቃብር አድሮ ተነሣ
ወከመ ይላል
የወይን ሥካር ያለፈለት ሰው ፈጥኖ እንዲነሣ ጌታም ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት በከርሠ መቃብር አድሮ ተነሣ ፡፡
አንድም ከመ ኅዱግ ይላል
አበርትቶ እንደተጣለ ወይን ፤ ያንን ጠጥቶ ወድቆ ይሠነብታል በሢስኛው ቀን ፈጥኖ ይነሣል ፤ ጌታም በሦስተኛው ቀን ፈጥኖ ተነሥቷልና ፡፡
ወቀተለ ይላል
በአዳምና በሔዋን ከፈረደባቸው በኋላ በአጋንንት ፈረደባቸው ፡፡
አንድም በዘድኅሬሁ ይላል
በኋላው በተተከለ መስቀል ዲያብሎስን ድል ነሣው ፡፡ አንድም ተከታይ ጠላት ዲያብሎስን አንድም ታናሽ ጠላት ዲያብሎስን ድል ነሣው ፡፡
በቅዳሴ ሰዓት የሚሰበከው ምስባክ
ዛቲ ዕለት እንተ ገብራ እግዚአብሔር
ንትፈሣሕ ወንትሐሰይ ባቲ
ኦእግዚኦ አድኅንሶ
ይህች ዕለተ ሚጠት እግዚአብሔር አሕዛብን አጥፍቶ ትሩፋንን አውጥቶ ሥራውን የሠራባት ናት ፡፡ አንድም ይች ዕለተ ዐርብ እግዚአብሔር አጋንትን አጥፍቶ ነፍሳትን አውጥቶ ሥራውን የሠራባት ዕለት ናት ፡፡
በሷ ፈጽሞ ደስ ይበለን ፡፡
አቤቱ አድነና ፡፡ አንድም አቤቱ አድነን ፡፡
በቅዳሴ ጊዜ የሚነበበው ወንጌል
የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 20 ፡ 1-19
“ወበእሑድ ሰንበት መጽአት ማርያም መግደላዊት ኀበ መቃብር
በአንድ ሰንበት አንድም በመጀመሪያው ሰንበት እሑድ ሰንበት በተባለበት ቀን ማርያም መግደላዊት ማለዳ ገሥግሣ ወደ መቃብር መጣች ፡፡
እንዘ ዓዲሁ ጽልመት
ገና ጨለማው ሳይለቅ ገና ጨለማ ሳለ ፡፡
ወረከበት ዕብነ እቱተ እምአፈ መቃብር
ደንጊያውን ከመቃብሩ ላይ ተነሥቶ አገኘችው፡፡
ወሮጸት ወበጽሐት ኀበ ስምዖን ጴጥሮስ ወኀበ ዝኩ ካልዕ ረድእ
ከሌለኛው ባለሟሉና ከስምዖን ጵጥሮስ ዘንድ ፈጥና ሄደች ፡፡ባለሟሉ ያለው ራሱ ዮሐንስን ነው ፡፡
ወትሎሙ ነሥእዎ ለእግዚእየ እምውስተ መቃብር
ጌታየን ከመቃብር አውጥተው ወስደውታል ፡፡
ወኢየአምር ኀበ ወሰድዎ
ወደየት እንደወሰዱት ግን አላውቅም ፡፡
መጽኡ ኅቡረ ስምዖን ጴጥሮስ ወዝኩ ካልዕ ረድእ ወሖሩ ኀበ መቃብር
ጴጥሮስና ሌላኛው አገልጋዩ መጥተው ወደ መቃብር ሄዱ ፡፡
ወእንዘ ይረውጹ ክልኤሆሙ ኅቡረ ፡፡
ሁለቱ ፈጥነው እየሮጡ አንድ ሁነው ሲሄዱ
በደሮ ለጴጥሮስ ዝኩ ካልእ ረድእ በጺሐ ኀበ መቃብር ፡፡
ሌላኛው አገልጋይ ጴጥሮስን ቀድሞት ወደ መቃብር ሄደ ፡፡ ስለምን ቀደመው ቢሉ ሕጻን ነው በፍቅሩ ይናደዳልና ፡፡
ወሶበ ሐወጸ ርእየ መዋጥሐ ንቡረ
ዘልቆ በተመለከተ ጊዜ መጎናጸፊያውን አገኘ ፡፡
ወኢቦአ ባሕቱ
ነገር ግን አልገባም ፡፡ ለምን አልገባም ቢሉ ሕጻን ነውና ቢፈራ ፤ አንድም ለክብረ ጴጥሮስ ፤ ከኤጲስ ቆጶስ አስቀድሞ ከመቅደስ እንዳይገባ ፡፡
ወተለዎ ስምዖን ጴጥሮስ ወበጽሐ
ስምዖን ጴጥሮስ ተከትሎት ደረሰ ፡፡ ስለምን ተከትሎት ዘግይቶ ደረሰ ቢሉ አረጋዊ ነውና በኀዘንም ተቀጥቅጧልና ፡፡
ወቦአ ውስተ መቃብር
ወደመቃብሩ ገባ ፡፡
ኤጲስቆጶስ ከቄስ አስቀድሞ መቅደስ እንዲገባ
ወረከበ መዋጥሐ ንቡረ ውስተ አሐዱ ገጽ
መጎናጸፊያውን በአንድ ወገን አገኘ ፡፡
ወሰበነኒ ዘዲበ ርእሱ እንተ ባሕቲቱ ጥብሉለ
ሻሹን እንደተጠመጠመ ለብቻው
ወአኮ ምስለ መዋጥሕ
ከመጎናጸፊያው ጋር ሳይቃወስ
ወእምዝ ቦአ ዝኩኒ ካልእ ረድእ ዘበደሮ በጺሐ ኀበ መቃብር
ከዚህ በኋላ ቀድሞ ከመቃብሩ የደረሰው ሌላኛው አገልጋይ ገባ ፤ ቄስ ኤጲስ ቆጶስን ተከትሎ መቅደስ እንዲገባ ፡፡
ወርእዩ ወአምኑ
ትሣኤውን አይተው አመኑ ፡፡
እስመ ዓዲሁ ኢያእመሩ ዘውስተ መጻሕፍት ዘከመ ሀለዎ ይትነሣእ እምነ ምውታን
ከሙታን ተለይቶ ይነሣ ዘንድ እንዳለው መጻሕፍት የተናገሩትን ገና አላወቁም ነበርና ፡፡
ወእምዝ ሖሩ ክልኤሆሙ አርዳኢሁ
ከዚህ በኋላ ሁለቱ ደቀ መዛሙርቱ ሄዱ ፡፡
ወአተው ቤቶሙ
ከቤታቸው ገቡ ፡፡
ቁጥር 10
አሜን
ውድ ኦርቶዶክሳውያን እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው አደረሳችሁ ፡፡

Monday, October 24, 2022

 

የተቀብዐ ጾመኞችና ሩጫቸው
======+====+=====
ካነበብኩት-------3
=======+======+=========
“ዘተወልደ በዳኃሪ መዋዕል በሥጋ ፤ ወተቀብዓ ውስተ ዝንቱ ዓለም በዘይትፌኖ እምኀበ እግዚአብሔር አብ ወተሰምየ ክርስቶስ ፡፡ አኮ በእንተ ካልዕ አላ በእንተ ዘተቀብዓ ፤ እስመ ክርስቶስ ብሂል ቅቡዕ ብሂል ፡፡”
==========================================
አማርኛ ትርጉም
“በኋላ ዘመን በሥጋ የተወለደ ፤ ከእግዚአብሔር አብ በሚገኝ ክብር በዚህ ዓለም የከበረው ፤ ክርስቶስ የተባለው እርሱ ነው ፡፡ በሌላም አይደለም ስለተቀባ ነው እንጅ ፤ ክርስቶስ ማለት የተቀባ ማለት ነውና”
===========================================
የሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ሐዲስ ትርጉም
“ዘተወልደ በደኃሪ መዋዕል በሥጋ ፤ ወከብረ በዝንቱ ዓለም በዘይትፌኔ እምኀበ እግዚአብሔር አብ፤ ወተሰምየ ክርስቶስ ፤ አኮ በእን ካልዕ ፤ አላ በእንተ በዘተሰብአ ፤ እስመ ክርስቶስ ብሂል አሐዱ እምክልኤቱ ብሂል፤
የአማርኛ ትርጉማቸው፡
“በኋላ ዘመን በሥጋ የተወለደ ፤ ከአብ በሚገኝ ክብር በዚህ ዓለም የከበረው እሱ ነው ፡፡ ከአብ የተገኘም ክብር አካለ ቃል ነው ፡፡ ክርስቶስ ተባለ ፤ በኅድረት አይደለም ፤ ቢዋሐድ ነው እንጅ ፤ ክርስቶስ ማለት በተዋሕዶ ከበረ ማለት ነውና” ብለውታል ፡፡
==========================================
የመጀመሪያው ትክክለኛው ቃል ከታች በብራናው ላይ በፎቶ የምታዩት ነው ፡፡
===========================================
ከሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ሐዲስ ሥራ ላይ እንደምትመለከቱት “ወተቀብዐ” የሚለውን ዘር “ወከብረ” ብለው ለውጠውታል ፡፡ ያው ተቀብዐን በደንብ አድርገው ይጾሟታልና ዘርን በዘር ይለውጣሉ ፡፡
===========================================
ቀጥለውም “ከአብ የተገኘ ክብርም አካለ ቃል ነው” ብለው ምንታዌን ሰተት አድርገው አምጥተዋታል ፡፡ አንባቢው ወዳጄ ሆይ! በትኩረት ተመልከትልኝ ቄርሎስ ከአብ በሚገኝ ክብር ከበረ ያለው ሥግው ቃልን ነው በመክበሩም ክርስቶስ ተባለ ያለው ሥግው ቃልን ነው ፡፡ እንደ ሊቁ አነጋገር ግን ክርስቶስ የተባለው ትስብእት ነው ፡፡ ምክንያቱም ቄርሎስ ከአብ በሚገኝ ክብር በመክበሩ ክርስቶስ መባሉን ተናግሯል ፤ እሳቸው ደግሞ ከአብ የተገኘው ክብር ቃል ነው ብለዋልና ፤ ከአብ በሚገኝ ክብር(በቃል) የከበረው ትስብእት ነውና ፤ ክርስቶስም የተባለው የተቀባው ነውና በእነሱ ቤት ክርስቶስ ማለት ትስብእት ነው ማለት ለዚህ ነው ፡፡ ተቀብዐን ማምለጥ የለም ያው መንፈራገጥ እንጅ ፡፡
===========================================
በጣም የሚደንቀው ደግሞ “ወተቀብዐ” የሚለውን “ወከብረ” ብለው ነበር ያለዘቡት ፡፡
ዝቅ ካሉ በኋላ ግን “አኮ በካልዕ” የሚለውን “በተዋሕዶ ከበረ” ወደሚለው የምንታዌ ትምህርታቸው ለመጎተት እንዲቀናቸው “ካልዕ” የሚለውን ቃል “ኅድረት” ብለው ለወጡት ፡፡ አንባቢው አሁንም መጽሐፍ ቅዱስ እየተለወጠ እንደሆነ በደንብ ተረዳ ፡፡ “ካልእ” ትርጉሙ ልዩ ሌላ እንጅ “ኅድረት” አይደለም መገናኛም የለውም ፡፡
==========================================
ካልዕ የሚለውን ኅድረት ብለው ከተረጎሙ በኋላ “አላ በዘተቀብዐ” የሚለውን “አላ በዘተሰብአ” በማለት ከላይ “ወከብረ” ብለው ከለወጡት ጋር የማይገጥም ቃልን አስቀምጠውታል ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን የመከለሱ ሥራና ሤራ ተጧጡፎ ቀጥሏል!!
ግእዙ ክርስቶስ የተባለው በሌላ ነገር አይደለም ስለተቀባ ነው እንጅ ነው ትርጉሙ ፡፡ ከላይ ከመጀመሪያው ቃል ጀምሮ ስትመለከቱት ከአብ በሚገኝ ክብር ከበረ ፤ በመክበሩም ክርስቶስ ተባለ ፤ ክርስቶስ የተባለውም በሌላ አይደለም በመቀባቱ(በመክበሩ) ነው እንጅ አለ ፡፡ እሳቸው ግን ግማሹን ተቀብዐ ግማሹን ተሰብአ እያሉ አወላግደውታል ፤፤
===========================================
ይኸም ብቻ አይደለም አንባቢው ወገኔ!!!
ከላይ ተቀብዐ ማለትን ወደ ከብረ ለውጠውት የነበረውን ሙሉ በሙሉ አፍርሰው
“እስመ ክርስቶስ ብሂል ቅቡዕ ብሂል” የሚለውን ዋና ዘር “እስመ ክርስቶስ ብሂል አሐዱ እምክልኤቱ” ብለው ሙሉ በሙሉ ደመሰሱት ፡፡
በደንብ ተረዱት የሀሳቡ ሙሉ ትርጓሜ
“ከአብ በተገኘ ክብር ከብሯልና ክርስቶስ ተባለ ፤ ክርስቶስ የተባለውም በሌላ አይደለም ስለተቀባ ነው እንጅ ፡፡ ክርስቶስ ማለት የተቀባ ነውና” ማለት ነው ፤፡
አባ ዕዝራ ግን “ከአብ በተገኘ ክብር ከብሯልና ክርስቶስ ተባለ” የሚለውን ከተቀበሉ በኋላ ፤ “ክርስቶስ የተባለው ስለተቀባ ነው” የሚለውን ለውጠው “ክርስቶስ የተባለው ቢዋሐድ ነው” ብለው ተረጎሙት ፡፡ መነሻው ግን ስለከበረ ክርስቶስ ተባለ ነበር ፤ መድረሻው ላይ ሳይደርሱ “ስለተቀባ ነው” የሚለውን “ስለተዋሐደ ነው” ብለው ከመንገድ መለሱት ፤ ያመኑትንም ሙሉጭ አድርገው ካዱት ፡፡
ከዚያም “ክርስቶስ ማለት ቅቡዕ(የተቀባ) ማለት ነው” ብሎ ወገብ ዛላቸውን እንዳይላቸው ስለሰጉ “ቅቡዕ” የሚለውን ቀይረው “አሐዱ እምክልኤቱ” በማለት ያልተጻፈውን አምጥተው አስገቡበት ፡፡ እንግዲህ ዓይናችን ያያልና መጽሐፍ ቅዱስን እየቀየሩ እውነትን ማጥፋት እስከመቼ ይሆንላቸው ይሆን???
===========================================
በዚህ ነው የሚገርማችሁ
“አሐዱ እምክልኤቱ” የሚለውን “በተዋሕዶ ከበረ” ብለው አልተረጎሙትም መሰላችሁ!!!
አየህ ግእዝን የማይሰማ ትውልድ ተፈጠረላቸውን እንዲህ እያወላገዱ ይጭኑታል ፡፡
“አሐዱ እምክልኤቱ” ትርጉሙ “ከሁለቱ አንድ ሆነ” ማለት ነው ፡፡ ሁለቱም “ቃልና ሥጋ” ናቸው ፡፡
===========================================
የቄርሎስ ማጠንጠኛ ግን ከአብ በሚገኝ ቅብዓት ተቀብቷልና ክርስቶስ ተባለ ነው ፡፡
ተቀብዐን አመልጥ አመልጥ ቢሮጡ መዳረሻው ምንታዌ ነው ፤ ማምለጥ የለም ፡፡ ተቀብዐን መጽሐፍ ቅዱስን ማደስ ግስ መቀየር ፤ መጽሐፍ ቅዱስን መሰረዝ መደለዝ የአረሚነት የከሐዲነት ግብር ነው እንጅ የኦርቶዶክሰዊነት ግብር አይደለም ፡፡ መጻሕፍትን ለሚቆነጻጽሉት አምላክ ልቡና ይስጣቸው ፡፡ ለተሳዳቢዎችም ዓይናቸውን ያብራላቸው ፡፡ ለእኛም በሃይማኖት መጽናትን ፤ እድሜ ለንሥሃ ዘመን ለፍሥሐ ያድለን አሜን!
ጆሮ ያለው መስማትን ይስማ!!
የብራናው ቃል በፎቶ ይኸው
ይኸንንም እያየ ዓይኔን ግንባር የሚል ዘላን እንደማይታጣም አብራችሁ ታዘቡልኝ!!!


Uploading: 1024761 of 1024761 bytes uploaded.



Sunday, October 16, 2022

 የተቀብዐ ጾመኞችና ሩጫቸው

=======+=====+=====
ካነበብኩት
  • ====+====
ቄርሎስ ስለ ክርስቶስ ተቀባዒነት ከተናገረው
=====+====+===
“እመ ይሬስዮሙ ለመላእክቲሁ መንፈሰ (መላእክትን በዓይን የማይታዩ በእጅ የማይዳሰሱ ረቂቃን አድርጎ የፈጠራቸው ከሆነ ፤ አንድም የፈጠራቸው ሲሆን) ፤ ወመንበር ቦቱ ዘመለኮት (የአምላክነት ሥልጣን ገንዘቡ ከሆነ ፤ አንድም ገንዘቡ ሲሆን) ፤ በእንተ ምንት ተቀብዐ ቅብዓ ትፍሥሕት (እንደምን የደሥታ ዘይትን ተቀባ/ከበረ ብትል) ፤ ወይፈጥር መላእክተ ከመ አምላክ ውእቱ (የባሕርይ አምላክ ነውና መላእክትን ፈጠረ) ፤ ወተቀብዓ ከመ ሰብእ (ሰው በመሆኑ ተቀባ ከበረ) ፤ አኮ በህላዌ መለኮት (በባሕርየ መለኮቱ አይደለም) ፤ አላ ተሰጊዎ ነሥአ ቅብዓተ በሥምረቱ አምላክ ወሰብእ ክርስቶስ (በፈቃዱ ሰው በሆነ ጊዜ ተቀባ ከበረ ተባለ እንጅ ፤ ክርስቶስ አምላክ ነው ሰውም ነው እልሃለው)”
ብራና ምቅዋም 20 ላይ ይገኛል ፡፡ ምቅዋም ማለት ምዕራፍ እንደማለት ነው ፡፡
ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ሐዲስ ባሳተሙት ላይደግሞ ምዕራፍ 56 ላይ የሚገኝ ሲሆን
ቅብዓትን ስለሚጾሙ
“በእንተ ምንት ከብረ ክብረ ትፍስሕት” ብለው ዘሩን ቀይረውታል ፡፡ ዘሩን ከለወጡ በኋላ ከአብ የተገኘ ክብርም አካለ ቃል ነው ፤ ክብርነቱም ለተዋሐደው ሥጋ ነው በማለት የቃልንና የሥጋን ተዋሕዶ የሚያፈርስ ምንታዌን አሰልጥነዋል፡፡
እሳቸው ተቀብዐን ለማምለጥ እንዲህ ቢንፈራገጡም “ወተቀብዐ ከመ ሰብእ” በማለት ወገብ ዛላቸውን ብሎ ያሳርፋቸዋል ፡፡ እንዴት አትልም ወዳጄ!!! በእሳቸው ቤት ተቀብዐ የተባለ ሥጋ ነው ፤ ቄርሎስ ደግሞ “ወተቀብዐ ከመ ሰብእ” ያለው ሥግው ቃልን ነው ፡፡ በዚህም መሠረት ቃል ክብር ከሆነ; ለሥጋ “ከመ ሰብእ” የሚለው አንቀጽ አይስማማውም ፤ ምክንያቱም ሥጋ ጥንቱንም ሰው ነውና ለሥጋ እንደ ሰው (ሰው በመሆኑ) አይባልለትምና በዚህ ሽንጣቸውን ቆርጦ ይጥላቸዋልና ያሳርፋቸዋል ማለት ለዚህ ነው ፡፡ በቀጣይ እድሜና ጤና ይስጠን እንጅ ብዙ እጽፋለሁ ፡፡ እንነጋገራለን ፡፡ በመጽሐፍም ከች ማለታችን አይቀርም ፡፡
====+====+====+====
ዘር ቢቀይሩ ግስ ቢለዋውጡ እየነቃቀሉ ቢጥሉት ያው ክርስቶስ ማለት የተቀባ ቅቡዕ ማለት መሆኑን ስለማይለቅላቸው ማምለጫ የላቸውም
እየተከተሉ በተቀብዐ ጅራፍ ሰኮና ሰኮናቸውን መጥበስ ነው የት አባታቸውና ፡፡
ወይ ተቀብዐ ይኸን አውደልዳይ ሁሉ እንዲህ ያሯሩጠው ፡፡
እኔ የፈለሰፍኩት እንዳይመስላችሁ ከታች ያለውን የብራና ድርሳን በፎቶ ተመልከቱና አመሳክሩት (በተለይ በተለይ እነ ምላስ ብቻ)
ከፎቶው ላይ አውራ ጣት ካለበት ላይ በቀይ “እመጽሐፈ ዕብራዊያን” ተብሎ ከተጻፈው ጀምራችሁ እዩት ፡፡