በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ!!!
========+++======+++=====+++========
መሢሐውያን ወንድም እህቶቼ እናት አባቶቼ እንደምን አላችሁ?
በዛሬው መልዕክቴ የ2014 ዓ.ም ምህረት ዘመን በዓላትና አጽዋማት የሚውሉባቸውን የባሕረ-ሐሳብ ቀመሮችን ቀለል ባለ አቀራረብ ይዤላችሁ መጥቻለሁ ፡፡
=======+++=========+++=========
ለመግቢያ ያህል ነቢየ እግዚአብሔር ክቡር ዳዊት ስለዘመን መቀያየርና ዘመንን ሲለሚለውጠው የዘመናት ባለቤት እንዲህ ሲል የተናገረውን ላስነብባችሁ ወደድኩ፡፡
==========+++========+++========
“ሐወጽካ ለምድር ወአርወይካ ( ይህችን ዓለም በረድኤት ጎበኘሃት አንድም ኢየሩሳሌምን ከሰብዓ ዘመን በኋላ በረድኤት ጎበኘሃት ፤ ማለት የዘሩባትን እንድታበቅል የተከሉባትን እንድታጸድቅ አደረግሃት) ፤ አንድም ትሩፍን ከሰብዓ ዘመን በኋላ በረድኤት ጎበኘኻት) ፤ አንድም ምእመንን ከአምስት ሽህ አምስት መቶ ዘመን በኋላ በልጅነት ጎበኘሃት፡፡
ወአብዛኅኮ ለብዕላ (የዚህችን ዓለም አንድም የኢየሩሳሌምን ብዕለ ሥጋዋን አበዛኸው) ፤ አንድም ብዕለ ሥጋዌን አበዛኸው ፤ አንድም ብዕለ ነፍሷን አበዛኸወ ፡፡
ፈለገ እግዚአብሔር ምሉዕ ማያተ (እግዚአብሔር የፈጠራቸው ዐራቱ አፍላጋት ፤ አንድም እግዚአብሔር በረድኤት ያደረባት የኢየሩሳሌም ወንዝ ዉሀን የተመላ ነው ፤ ወአሦጡ ቀሳውስቲሆሙ ዕራቃቲሆን እንዲል ፤ ተማርከው ባቢሎን ሲወርዱ ወንዙ ሁሉ ደርቆባቸው የሚጠጡት አጥተው ባዶ ዕቃቸውን ይዘው እያለቀሱ ወርደዋል ፤ በሚጠት ጊዜ ግን ዝናም ዘንቦላቸው ወንዙ ሁሉ ዉሀ ሞልቶላቸው እነሱ እየጠጡ ወገኖቻቸውንም እያጠጡ ደስ ብሏቸዋልና እንዲህ አለ) ፡፡ አንድም ፈለገ እግዚአብሔር ነቢያት ትንቢትን ካህናት ትምህርትን የተመሉ ናቸው ፤ አንድም ሐዋርያት ሰብዓ አርድዕት ትምህርትን ገቢረ ተአምራትን ልጅነትን የተመሉ ናቸው ፡፡አስተዳሎከ ሲሳዮሙ እስመ ከማሁ ታስተዴሉ (ምግባቸውንም አዘጋጀህላቸው አስተዳሎከ ብየ እንዲህ እንደተናገርኩ ታዘጋጅላቸዋለህና አንድም ምግባቸውን አዘጋጀህላቸው እንዲህ በስነ ፍጥረት ለአዳም ማዘጋጀት ልማድህ ነውና) ፤አንድም ገቢረ ተአምራት ወመንክራት አዘጋጀህላቸው ፤ አንድም እንዲህ ለሙሴ ለአሮን ማዘጋጀት ልማድህ ነውና ፤ አንድም ሥጋህን ደምህን አዘጋጀህላቸው እንዲህ በመልከቴዴቅ ማዘጋጀት ልማድህ ነውና ፤ አንድም ልጅነትን ትምህርትን አዘጋጀህላቸው እንዲህ በአዳም ማዘጋጀት ልማድህ ነውና ፡፡ አርውዮ ለትለሚሃ (ዚህችን ዓለም አንድም የኢየሩሳሌምን ትልሟን አርካው) አንድም ልቡናዋን ደስ አሰኛት ፤ አንድም ልቡና ነፍሷን ደስ አሰኘው ፡፡ ወአሥምሮ ለማዕረራ (መኸሯን አብጀው) ፤ አንድም ሚጠተ ሥጋዋን አብጀው ፤ አንድም ሚጠተ ነፍሷን አብጀው ፡፡ ወበነጠብጣብከ ትበቊል ተፈሢሓ (እንዲህ የሆነ እንደሆነ ጠብ ጠብ ብሎ በሚዘንበው ዝናብ የዘነበ እንደሆን ተካክላ ትበቅላለች ፤ ብርቱ ዝናም የዘነበ እንደሆነ ከነመሬቱ ድሶት ይሄዳል (ጠራርጎ ይወስደዋል) ፤ አንድም በነጠብጣበ ምሕረትህ ደስ ብሏት ከባቢሎን ወደ ኢየሩሳሌም ትወጣለች ፤ አንድም ጠብ ጠብ ብሎ በፈሰሰ ማየ ገቦህ ተጠምቃ ደስ ብሏት ከሲኦል ከገሃነም ወደገነት ወደ መንግሥተ ሰማያት ትወጣለች ፡፡
ወትባርክ አክሊለ ዓመተ ምሕረትከ (በቸርነትህ ዘመን የተገኘውን እህሉን ታበዛዋለህ ፡፡ ገበሬው እንደ ዘውድ አድርጎ ያመርተዋልና አክሊል አለው ፤ አንድም እክል(እህል) በርዕሰ እጽ ይገኛልና ፤ አንድም የስንዴ የገብስ ትቱ ዘውድ ነውና ፡፡ አንድም የዘሩባቤልን ዘውድ ታከብረዋለህ ፤ አንድም በቸርነትህ ወንጌላዊውን ታከብረዋለህ ፤ አንድም ልጅነትን ታከብረዋለህ ማለት እንዲሰጥ ታደርገዋለህ ፤ ፡፡ ወይጸግቡ ጠላተ ገዳም (ገዳማት ልምላሜውን አግኝተው ደስ ይላቸዋል) ፤ አንድም አሕዛብ ኦሪትን ይቀበላሉ ፤አንድም ሕዝበ እስራኤል ወንጌልን ይቀበላሉ ፡፡ ወይረውዩ አድባረ በድው ( በበረኃ ያሉ ተራራዎች ዝናቡን ይረካሉ) ፤ አንድም ነገሥተ አሕዛብም ኦሪትን ይቀበላሉ) ፤ አንድም ነገሥተ እስራኤልም ወንጌልን ይቀበላሉ” መዝ 65 ቁ 11-13 ድረስ
እንዲህ ሲል በትንቢት ያየውን ነግሮናል ፡፡ ዘመናትን በቸርነቱ የሚያቀዳጅ አምላክ እድሜ ለንስሐ ዘመን ለፍስሐ ያድለን ፡፡ ከዚህ በመቀጠል የ2014 ዓ.ም ከመባቻ ጀምሮ የሚውሉ በዓላትን አጽዋማንት እንዲሁም ዕለታትን እንደሚከተለው አቅርቤአለሁ ፡፡
==============+++=============+++=============
አንደኛ፡-በባሕረ-ሐሳብ የመጀመሪያው ስሌታችን ዓመቱ የተሰየመበትን ወንጌላዊ መለየት ነው ፡፡ ወንጌላዊውን ለማግኘት ዓመተ ዓለምን(ዓለም ከተፈጠረች እስከ አሁን ድረስ ያለው ዘመን) ለዐራት አካፍለን የሚቀረው ቀሪ ቁጥር ወንጌላዊውን እንድናውቅ ያግዘናል ፡፡ ዓመተ ዓለም ደግሞ ዓመተ ምህረትን እና ዓመተ ፍዳን በመደመር የምናገኘው ነው ፡፡ በመሆኑም በ 2014 ዓመተ ዓለም = ዓመተ ምህረት + ዓመተ ኩነኔ ፤ 2014+ 5500 =7514 ነው ፡፡ በዚህም መሠረት በዓመቱ የሚሰየመው(የሚሾመው ወንጌላዊ) ዓመተ ዓለምን ለዐራት አካፍለን በምናገኘው ቀሪ የሚወሰን ነው ፡፡
ትኩረት፡- ስናካፍል
ቀሪው ዜሮ “0” ከሆነ ዘመኑ ዘመነ ዮሐንስ ይሆናል፤
ቀሪው አንድ “1” ከሆነ ዘመኑ ዘመነ ማቴዎስ ይሆናል ፤
ቀሪው ሁለት “2” ከሆነ ዘመኑ ዘመነ ማርቆስ ይሆናል፤
ቀሪው ሦስት “3” ከሆነ ዘመኑ ዘመነ ሉቃስ ይሆናል ፤
ለዐራት የሚደርሰው ድርሻው መጠና ራብዒት ይባላል ፡፡
በመሆኑም በ2014 ዓ.ም ዓመተ ዓለም 7514 ሲሆን ፣ 7514 ÷ 4 = 1878 ደርሶ 2 ይቀራል ፡፡ ይህ ተካፍሎ ሙሉ የደረሰው ቁጥር የ2014 ዓ.ም መጠነ ራብዒት ነው ፡፡
ስለዚህ ቀሪው '2' ስለሆነ የዘንድሮው(የ2014 ዓ.ም) ወንጌላዊ ማርቆስ ሲሆን ዘመኑ ዘመነ ማርቆስ ይባላል።
ሁለተኛ፡- ሁለተኛው ሥሌታችን ዕለተ ቀመር ይባላል ፡፡ ይህም መባቻ (መስከረም አንድ የሚውልበት ቀን) ማለት ነው፡፡
ይህ ዕለተ ቀመር ዓመተ ዓለምን እና መጠነ ራብዒትን ደምረን ለሰባት በማካፈል ድርሻውን ትተን ቀሪውን በመያዝ የምናገኘው ስሌት ነው ፡፡ ማለትም ዕለተ ቀመር= ዓመተ ዓለም + መጠነ ራብዒት÷7
ትኩረት፡- ደምረን እና አካፍለን ከጨረስን በኋላ
ቀሪው ዜሮ “0” ከሆነ መባቻ ሰኞ ይሆናል ፤
ቀሪው አንድ “1” ከሆነ መባቻ ማክሰኞ ይሆናል፤
ቀሪው ሁለት “2” ከሆነ መባቻ ረቡዕ ይሆናል፤
ቀሪው ሦስት “3” ከሆነ መባቻ ሐሙስ ይሆናል፤
ቀሪው ዐራት “4” ከሆነ መባቻ ዓርብ ይሆናል፤
ቀሪው አምሥት “5” ከሆነ መባቻ ቅዳሜ ይሆናል፤
ቀሪው ስድስት “6” ከሆነ መባቻ እሁድ ይሆናል፤
በዚህም መሠረት የ2014 ዓም መባቻ (መስከረም አንድ የሚውልበት ቀን)
= 7514 + 1878 =9392 = 9392 ÷ 7 = 1341 ቀሪ 5 ስለሆነ ቅዳሜ ይሆናል ፡፡
ሦስተኛ፡- ሦስተኛው ስሌታችን መደብ ይባላል ፡፡ መደብ ዓመተ ዓለምን ለ19 በመግደፍ(በማካፈል) ድርሻውን በመተው ቀሪውን በመውሰድ እናገኘዋለን ፡፡ ስለሆነም የ2014 ዓ.ም መደብ = 7514፥19=395 ቀሪው 9 ስለሆነ መደቡ 9 ይሆናል፡፡
ዐራተኛ፡- ዐራተኛው ስሌታችን ወንበር ይባላል ፡፡ ወንበርን ከመደብ አንድን ለዘመን በመተው(መደብ-1) እናገኛለን። በዚህም መሠረት ከላይ እንዳየነው የ2014 መደብ 9 ሲሆን ወንበሩ ደግሞ 9 - 1= 8 ይሆናል።
አምስተኛ፡- አምስተኛው ስሌታችን አበቅቴ ይባላል ፡፡ አበቅቴን ለማግኘት ወንበርን በጥንተ አበቅቴ(11) አባዝተን በ30 እንገድፋለን(ለ30 አእናካፍላለን) ። ከላይ እንዳየነው የ2014 ዓ.ም ወንበር 8 ሲሆን አበቅቴ =11*8፥30= 88፥30= 2 ቀሪ 28 በመሆኑ አበቅቴው 28 ነው ።
በተጨማሪም አበቅቴን ለማግኘት የባለፈው ዓመት አበቅቴን እና ጥንተ አበቅቴን (11ን) በመደመር ማግኘት ይቻላል ፡፡ ይህም ማለት ለምሳሌ የ2013 ዓ.ም አበቅቴ 17 ነበር ፡፡ በዚህም መሠረት የ2014 ዓ.ም አበቅቴ 17+11=28 ይሆናል ማለት ነው።
ስድስተኛ፡- ስድስተኛው ስሌታችን መጥቅዕ ይባላል ፡፡ መጥቅዕን ጥንተ መጥቅዕን (19) በወንበር አባዝተን ለ30 ገድፈን (ለ30 አካፍለን) ድርሻውን በመተው ቀሪውን በመውሰድ የምናገኝ ይሆናል ።
በዚህም መሠረት በ2014 ዓ.ም መጥቅዕ = 19×8 = 152 ÷ 30= 5 ቀሪ 2፣ ስለሆነ 2 ይሆናል።
በተጨማሪም ጥንተ መጥቅዕን (19) እና የባለፈውን ዓመት መጥቅዕ ከደመርን በኋላ ለሰላሳ በማካፈል ድርሻውን በመተው ቀሪውን በመውሰድ ማግኘት እንችላለን ፡፡ ይህም ማለት ለምሳሌ የ2013 ዓ.ም መጥቅዕ 13 ነበር፤ በዚህም መሠረት የ2014 ዓ.ም መጥቅዕ 13+19=32 ይህን በ30 ስንገድፈው(ለ30 ስናካፍለው) ቀሪው 2 ስለሆነ የ2014 መጥቅዕ 2 ይሆናል ማለት ነው ።
ትኩረት፡- መጥቅዕና አበቅቴ ድምራቸው ሁልጊዜ 30 ነው ፡፡ ከ30 አያንስም ከ30 አይበልጥም፡፡
እንዲሁም መጥቅዕ ከ14 በላይ ከሆነ በመስከረም ይውላል፤ መጥቅዕ ከ14 በታች ከሆነ በጥቅምት ይውላል፡፡ መጥቅዕ በመስከረም የሚውል ከሆነ ጾመ ነነዌ በጥር ይሆናል በሌላ መልኩ መጥቅዕ በጥቅምት የሚውል ከሆነ ጾመ ነነዌ በየካቲት ይሆናል ።
በዚህም መሠረት የ2014 ዓ.ም መጥቅዕ 2 በመሆኑ ከ14 የሚያንስ ስለሆነ መጥቅዕ የሚውለው በጥቅምት 2 ይሆናል ማለት ነው ፡፡
ሰባተኛ ፡- ሰባተኛው ስሌታችን መባጃ ሐመር ነው ፡፡ መባጃ ሐመር መጥቅዕን እና መጥቅዕ የዋለበትን ዕለት ተውሳክ በመደመር በ30 በመግደፍ (ለ30 በማካፈል) ይገኛል ፡፡
ትኩረት፡- ከዕለተ መጥቅዕ ጀምረን እስከ ነነዌ ጾም መግቢያ ስንቆጥር 128 ቀናት ይኖሩናል ፡፡ ይህንን ቀን ለ30 በማካፈል ድርሻውን በመተው የምንወስደው ቀሪ ተውሳክ ይሆናል ፡፡
የዕለታት ተውሳክም ከቅዳሜ ይጀምራል ፡፡ ይህንንም እንደሚከተለው ማግኘት እንችላለን ፡፡
ቅዳሜ፡- 128፥30= 4 ቀሪ 8
እሁድ፡-127፥30= 4 ቀሪ 7
ሰኞ፡- 126፥30=4 ቀሪ 6
ማግሰኞ፡- 125 ፥30= 4 ቀሪ 5
ረቡዕ፡-124 ፥30= 4 ቀሪ 4
ሐሙስ፡- 123፥ 30= 4 ቀሪ 3
ዓርብ፡-122፥ 30= 4 ቀሪ 2
በዚህም መሠረት መባጃ ሐመርን መጥቅዕንና በዓለ መጥቅዕ የዋለበትን ዕለት ተውሳክ በመደመር የምናገኝ ይሆናል ። በ2014 ዓ.ም ዕለተ መጥቅዕ የሚውልበት ቀን ጥቅምት 2 ማክሰኞ ስለሆነ የማክሰኞ ተውሳክ ደግሞ 5 ስለሆነ 2 እና 5 ሲደመሩ ሰባት ስለሚሆኑ የ2014 ዓ.ም መባጃ ሐመር ከ30 ስለሚያንስ ራሱን 7ን ይዘን መጥቅዕ በጥቅምት በመዋሉ ጾመ ነነዌ በየካቲት 7 በዕለተ ሰኞ የሚውል ይሆናል ። በዕለተ ሰኞ መዋሉን ያወቅነው ሁልጊዜም ጾመ ነነዌ ከሰኞ የማይለቅ በመሆኑ ነው ፡፡
ትኩረት ፡- ጾመ ነነዌ ተውሳክ የሌለው ጾም ሲሆን መባጃ ሐመርን መሠረት አድርገን የምናወጣው ሲሆን ፤ ሌሎችን አጽዋማትንና በዓለትን (ተውሳከ ዕለት የሚያገኛቸውን በዓላትንና አጽዋማትን) ግን ተውሳካቸውን ከነነዌ እየደመርን ከ30 ከበለጠ ለ30 እያካፈልን ካልበለጠ ራሱን እየወሰድን ማግኘት እንችላለን ።
ይኸም ሲባል ከነነዌ ጾም እስከ ዐቢይ ጾም 14 ቀናት አሉ ። ስለዚህ የዐቢይ ጾም ተውሳክ 14 ይሆናል፡፡
ከነነዌ እስከ ደብረዘይት 41 ቀኖች አሉ ፡፡ ስለዚህ 41 ÷ 30 = 1 ቀሪ 11 ስለሚሆን የደብረዘይት ተውሳክ 11 ይሆናል ፡፡
ከነነዌ እስከ ሆሣዕና 62 ቀኖች አሉ፡፡ ስለዚህ 62 ÷ 30 = 2 ቀሪ 2 ስለሚሆን የሆሣዕና ተውሳክ 2 ይሆናል፡፡
ከነነዌ እስከ እስከ ስቅለት 67 ቀኖች አሉ፡፡ ስለዚህ 67 ÷ 30 = 2 ቀሪ 7 ስለሚሆን የስቅለት ተውሳክ 7 ይሆናል ፡፡
ከነነዌ እስከ ትንሣኤ 69 ቀኖች አሉ፡፡ ስለዚህ 69 ÷ 30 = 2 ቀሪ 9 ስለሚሆን የትንሣኤ ተውሳክ 9 ይሆናል፡፡
ከነነዌ እስከ ርክበ ካህናት 93 ቀኖች አሉ ፡፡ ስለዚህ 93 ÷ 30=3 ቀሪ 3 ስለሚሆን የርክበ ካህናት ተውሳክ 3 ይሆናል፡፡
ከነነዌ እስከ ዕርገት 108 ቀኖች አሉ፡፡ ስለዚህ 108 ÷ 30 = 3 ቀሪ 18 ስለሚሆን የዕርገት ተውሳክ 18 ይሆናል፡፡
ከነነዌ እስከ ጰራቅሊጦስ 118 ቀኖች አሉ፡፡ ስለዚህ 118 ÷ 30 = 3 ቀሪ 28 ስለሚሆን የጰራቅሊጦስ 28 ተውሳክ ይሆናል ፡፡
ከነነዌ እስከ ጾመ ድኅነት 121 ቀኖች አሉ ፡፡ 121 ÷ 30 = 4 ደርሶ ቀሪው 1 ሲሆን የጾመ ድኅነት ተውሳክ 1 ይሆናል፡፡
ከነነዌ እስከ ጾመ ሐዋርያት 126 ቀኖች አሉ፡፡ 126 ÷ 30 = 4 ቀሪ 6 ስለሚሆን የጾመ ሐዋርያት ተውሳክ 6 ይሆናል ፡፡
በዚህም መሠረት የ2014 ዓም አጽዋማትንና በዓላትን ተውሳኮቻቸውን ከነነዌ ጋር እየደመርን ማግኘት እንችላለን ፡፡ ከላይ እንዳየነው የ2014 የነነዌ ጾም መግቢያ የካቲት 7 ይሆናል ፡፡
F የዓቢይ ጾም ተውሳክ 14 ነው = በመሆኑም 14+7= 21 ስለሚሆን የ2014 ዓ.ም ዐቢይ ጾም መጀመሪያ የካቲት 21 ነው ፡፡ ወይም የካቲት ሰባት ላይ 14 ቀን ስንጨምርበት 21 ቀን ስለሚሆን የካቲት 21 የዓቢይ ጾም መጀመሪያ መሆኑን በዚህ ማወቅም እንችላለን ፡፡
F የደብረ ዘይት ተውሳክ 11 ነው፡፡ ስለዚህ 11+7 =18 ይሆናል ፡፡ ይህ 18 ከ 30 ስለሚያንስና ከላይ የዐቢይ ጾም መጀመሪያው የካቲት መሆኑን ስላወቅን ። ስለዚህ በመጋቢት 18 እሁድ ደብረዘይት ይሆናል ። ወይም ከነነዌ እስከ ደብረ ዘይት ድረስ 41 ቀናት ያሉን ሲሆን 23ቱን ለየካቲት በመስጠት ቀሪ 18 ቀናትን ለመጋቢት በመስጠት መጋቢት 18 ደብረ-ዘይት መሆኑን ማወቅ እንችላለን ፡፡
F የሆሣዕና ተውሳክ 2 ነው ፡፡ በመሆኑም 2+7=9 ይሆናል ፡፡ ይህ 9 ከ30 ስለሚያንስና በመጋቢት ስላለፍን ቀጣዩን ሚያዚያን እናገኛለን ፡፡ ስለዚህ ሚያዚያ 9 እሁድ ይሆናል፡፡ ወይም ከነነዌ እስከ ሆሳዕና ድረስ 62 ቀናት ያሉን ሲሆን 23ቱን ለየካቲት ፣ 30ውን ለመጋቢት በመስጠት ቀሪ 9 ቀናትን ለሚያዚያ ሰጥተን ሚያዚያ ዘጠኝ ሆሳዕና መሆኑን መረዳትም እንችላለን፡፡
F የስቅለት ተውሳክ 7 ነው ፡፡ ስለዚህ 7+7=14 ይሆናል ፡፡ በዚህም መሠረት በሚያዝያ 14 ስቅለት ይሆናል ፡፡ በሌላ መልኩም ከነነዌ እስከ ስቅለት ያሉት ቀናት 67 ቀናት ናቸው ፡፡ በዚህም መሠረት 23ቱን ለየካቲት ፣ 30ውን ለመጋቢት፣ ቀሪ 14ቱን ቀናት ደግሞ ለሚያዚያ በመስጠት ስቅለት ሚያዚያ 14 መሆኑን ማወቅ እንችላለን ፡፡
F የትንሣኤ ተውሳክ 9 ነው ፡፡ ስለዚህ 9 +7 = 16 ይሆናል ሚያዝያ 16 በዓለ ትንሣኤ ይውላል። አልያም ከነነዌ እስከ ትንሣኤ 69 ቀናት መኖራቸውን ስለምናውቅ 23ቱን ለየካቲት፣ 30ውን ለመጋቢት ፣ ቀሪ 16 ቀናትን ለሚያዚያ በመስጠት ትንሣኤ ሚያዚያ 16 የሚውል መሆኑን መረዳት እንችላለን ፡፡
F የርክበ ካህናት ተውሳክ 3 ነው ፡፡ ስለዚህ 3 +7 = 10 ይሆናል ፡፡ በመሆኑም በግንቦት 10 ርክበ ካህናት ይሆናል ማለት ነው ። ከዚህ ቀለል ባለ መልኩም ከነነዌ እስከ ርክበ ካህናት ድረስ 93 ቀናት መኖራቸው የሚታወቅ በመሆኑ 23ቱን ለየካቲት ፣ 30ውን ለመጋቢት፣ 30ውን ለሚያዚያ ፣ እንዲሁም ቀሪ 10 ቀናትን ደግሞ ለግንቦት በመስጠት ርክበ ካህናት ግንቦት 10 መሆኑን መረዳት እንችላለን ፡፡
F የዕርገት ተውሳክ 18 ነው፡፡ 18 +7 = 25 ነው ፡፡ ስለዚህ ግንቦት 25 በዓለ ዕርገት ይሆናል ማለት ነው ፡፡ በሌላ መልኩም ከነነዌ እስከ ዕርገት ድረስ 108 ቀናት አሉ ፡፡ በዚህም መሠረት 23ቱን ለየካቲት፣ 30ውን ለመጋቢት፣ 30ውን ለሚያዚያ ፤ እንዲሁም ቀሪ 25 ቀናትን ለግንቦት በመስጠት ግንቦት 25 በዓለ ዕርገት መሆኑን መረዳት እንችላለን ፤፡
F የጰራቅሊጦስ ተውሳክ 28 ነው፡፡ ስለዚህ 28 +7= 35 ይሆናል ፡፡ ይህንን ለ30 ብናካፍለው 1 ቀሪ 5 ስለሚሆን ሰኔ 5 በዓለ ጰራቅሊጦስ ይውላል። በሌላ መልኩም ከነነዌ እስከ ጰራቅሊጦስ 118 ቀናት መኖራቸው ይታወቃል ፡፡ በመሆኑም 23ቱን ለየካቲት፣ 30ውን ለመጋቢት ፣ 30ውን ለሚያዚያ ፣ 30ውን ለግንቦት ፣ ቀሪ 5 ቀናትን ለሰኔ በመስጠት ሰኔ 5 በዓለ ጰራቅሊጦስ የሚውል መሆኑን መረዳት እንችላለን ፡፡
F የፆመ ድኅነት ተውሳክ 1 ነው፡፡ ስለዚህ 1 + 7 =8 ይሆናል ፡፡ ጾመ ድህነት(የረቡዕና ዓርብ ጾም) ሰኔ 8 ይገባል። በሌላ በኩልም ከነነዌ እስከ ፆመ ድኅነት መግቢያ ድረስ 121 ቀናት አሉ ፡፡ በዚህም መሠረት 23ቱን ለየካቲት፣ 30ውን ለመጋቢት ፣ 30ውን ለሚያዚያ ፣ 30ውን ለግንቦት ፣ ቀሪ 8 ቀናትን ለሰኔ በመስጠት ሰኔ 8 ጾመ ድኅነት የሚውል መሆኑን መረዳት እንችላለን ፡፡
F የጾመ ሐዋርያት ተውሳክ 6 ነው ፡፡ 6 +7= 13 በዚህም የሐዋርያት ጾም ሰኔ 13 የሚጀምር መሆኑን እንረዳለን ። በሌላም መልኩ ከነነዌ እስከ ጾመ ሐዋርያት መጀመሪያ ድረስ 126 ቀናት ይገኛሉ ፡፡ በዚህም መሠረት 23ቱን ለየካቲት፣ 30ውን ለመጋቢት ፣ 30ውን ለሚያዚያ ፣ 30ውን ለግንቦት ፣ ቀሪ 13 ቀናትን ለሰኔ በመስጠት ሰኔ 13 ጾመ ሐዋርያት የሚውል መሆኑን መረዳት እንችላለን ፡፡
ልዩ ትኩረት፡- ተውሳከ ዕለት የሚያገኛቸው አጽዋማትና በዓላት ገደብ አላቸው ፡፡ ያ መመላለሻ ገደባቸውም 35 ቀን ነው ፡፡ የህም ሲተነተን እንደሚከተለው ይሆናል ፡፡
F ጾመ ነነዌ ከጥር 17 በታች አይወርድም ፤ ከየካቲት 21 በላይ አይወጣም።
F ዐቢይ ጾም ከየካቲት 1 በታች አይወርድም ፤ ከመጋቢት 5 በላይ አይወጣም።
F ደብረዘይት ከየካቲት 28 በታች አይወርድም ፤ ከሚያዝያ 2 በላይ አይወጣም።
F ሆሣዕና ከመጋቢት 19 በታች አይወርድም ፤ ከሚያዝያ 23 በላይ አይወጣም።
F ስቅለት ከመጋቢት 24 በታች አይወርድም ፤ ከሚያዝያ 28 በላይ አይወጣም።
F ትንሣኤ ከመጋቢት 26 በታች አይወርድም ፤ ከሚያዝያ 30 በላይ አይወጣም።
F ርክበ ካህናት ከሚያዝያ 20 በታች አይወርድም ፤ ከግንቦት 24 በላይ አይወጣም።
F ዕርገት ከግንቦት 5 በታች አይወርድም ፤ ከሰኔ 9 በላይ አይወጣም።
F በዓለ ጰራቅሊጦስ ከግንቦት 15 በታች አይወርድም ፤ ከ ሰኔ 19 በላይ አይወጣም፡፡
F ጾመ ድኅነት ከግንቦት 18 በታች አይወርድም ፤ ከሰኔ 22 በላይ አይወጣም።
F ጾመ ሐዋርያት ከግንቦት 25 በታች አይወርድም ፤ ከሰኔ 27 በላይ አይወጣም።
v ጾመ ነነዌ፣ ዐቢይ ጾም፣ ጾመ ሐዋርያት ከሰኞ አይለቁም ።
v በዓለ ደብረዘይት፣ ሆሣዕና፣ ትንሣኤና ጰራቅሊጦስ ከእሁድ አይለቁም ፡፡
v ዕርገት ከሐሙስ አይለቅም ፡፡
v ስቅለት ከዓርብ አይለቅም ።
v ርክበ ካህናትም ከረቡዕ አይወጣም።
ማጠቃለያ፡ ከላይ የተመለከትቸው በዓላትና አጽዋማት ተውሳክ የጥንቱ ወይም የመጀመሪያው የአጽዋማቱንና የበዓላቱን ጥንት መሠረት ያደረገ መሆኑን ልብ ይሏል ፡፡ ይህም ጥንተ ስቅለቱ ጥንተ ፣ ትንሳኤው ጥንተ እርገቱን….ወዘተ የመሳሰሉትን መሠረት ያደረገ ነው ማለት ነው ፡፡ ይህንን እውነት ይዘን የካሮችን በሬወለደ ፈጠራ በጥቃቄ ልንሞግተውና የማይጠቅመንንና የሚያጠፋንን ክሕደታቸውን ከእኛ እናርቅ ዘንድ ምኞቴ ነው ፡፡ የዘመን ባለቤት ልዑል እግዚአብሔር ዘመናችንን ይባርክልን ፡፡ አዲሱን ዘመን ዘመነ ማርቆስን ባርኮ ቀድሶ ይስጠን የሠላም የጤና ያድርግልን ፡፡
===========++++=========
ስብሐት ለአምላክ ዘለዓለም ሥላሴ
ውዳሴ ወግናይ ለእመ አዶናይ
ክብር ለቅዱስ እጸመስቀል
No comments:
Post a Comment