በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡
ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ-ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተላለፈ ቃለ-ግዘት!!!
እኛ በኢትዮጵያ(ጎጃም) የምንኖር ኦርቶዶክሳውያን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያንን ሕግና ሥርዓት ጠብቀንና አምነን መቆየታችን አሁንም እየጠበቅን የምንገኝ መሆናችን የሚታወስ ነው ፡፡ በዚህ ቆይታ ወደኋላ መለስ ብለን ስለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን ታሪካዊ ክስተት ብንመለከት የውጭ ሀገር ሚሲዮኖች ወደ ሐገራችን በመምጣታቸው በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ልዩ ችግር ተፈጠረ ፡፡ ሆድ አደር ሊቃውንትም አንዲት የቀናች መንገድን (ኦርቶዶክስን) በውጭ ጠላት ገንዘብና ሹመት ተደልለው፤በምፀት አነጋገርና በጥላቻ መንፈስ “ቅብዐት፣ ካራ፣ ፀጋ ፤ ሚናስ ፤ ፃማ” በመበባል እርስ በእርሳቸው ይነቃቀፉ እንደነበር የታሪክ መጻሕፍትን አገላብጦ መመልከት ይቻላል ፡፡
ይህ ሁሉ ሲሆን እኛ የጎጃም ሊቃውንት በተለይ ከ1950ዎቹ ጀምሮ አባት የሌላችሁ እጓለማውታ፣ሃይማኖት የሌላችሁ መናፍቃን፤ከሐድያን፣ቤት የሌላችሁ ምንዱባን ተብለን ትርጓሜውንና ምሥጢሩን ሳይለዩ በጭፍን ጥላቻ “ቅብዓቶች” የሚል ስም ተሰጥቶን፤ብሂለ ዲዮስቆሮስን ቀይረው ብሂለ ልዮንን በተቀበሉ፣የቤተ ክርስቲያንን ስምና ምልክት በሥጋዊ ስምና ምልክት በቀየሩ፣አንድ ክርስቶስን መንፈቁን አክባሪ፣መንፈቁን ከባሪ፣መንፈቁን ክብር አድርገው ለሦስት በከፈሉ፤እንደመለካውያን በአስተምሮአቸው “ካራ” በሚባል ስም በተሰጣቸው፣ማስተዋል በጎደላቸው ደቀ ልዮናውያን ስንገለል፣ስንታሰር፣ ስንገፋ ሁሉንም ታግሰን እስከ ግንቦት 16/2012 ዓ.ም ቆይተናል ፡፡
ነገር ግን ጥንታውያን መጻሕፍትን እየቆነጻጸሉና እየቆራረጡ ዘራቸውን(ፊደላቸውን) በመፋቅ፣መፋቅ ያልቻሉትን ደግሞ ግሱን ዋና ነቁን እየለወጡ በማሳተም፤ደገኛውን ምሥጢረ ሃይማኖት የሚያጠፉበት እኩይ ተግባራቸው እየባሰ በመምጣቱ በ1993 ዓ.ም ከጥንታዊ ኦርቶዶክሳውያን የተገኘውንና ነሥአ ተወክፈን ከምሥጢረ ቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ ጋር ብጥር ጥርት አድርጎ የሚናገረውን ፣ ስለ ጽንዓ ተዋሕዶ የሚያብራራውን ፣ ስለ ምሥጢረ ሥላሴ በሰፊው የሚያስረዳውን መጽሐፍ ለመጀመሪያ ጊዜ “በአቡነ ዘካርያስ” ድጋፍ በማሳተም እውነታውን ለዓለም ሕዝብ የማድረስ እንቅስቃሴአችንን እኛ የምስካበ ቅዱሳን ቆጋ ኪዳነ ምሕረት አጸደ ኤዎስጣቴዎስ አንድነት ገዳም ማኅበረ መነኮሳትና ከገዳም ውጭ በዓለም ከሚኖሩ እውነተኛ ክርስቲያኖች ጋር በመተባበር እንደ እግዚአብሔር ቸርነት ጀመርነው ፡፡
በዚህ ጉዞ ውስጥ ብጹዕ አቡነ ዮሐንስ አፈወርቅ ከጎጃም እስከ አዲስ አበባ ድረስ ብዙ መንገላታትና ሥቃይን ስለ ሃይማኖታቸው ተቀብለዋል፡፡ ዘመንን ዘመን እየወለደው በወቅቱ ለፍትሕ ሚኒስተር(1994 ዓ.ም) “እኛ መናፍቃን፤እነሱ ጻድቃን ሁነው በአንድነት የምንተዳደርበት የሞግዚት አስተዳደር ሕግና ሥርዓት አንፈልግምና ለነጻነታችን እውቅና ስጡን” ብለን ጥያቄ ብናቀርብም ዛሬ ነገ በማለት መብታችን ታፍኖብን ቆይቷል ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ስቃዩና በደሉ የተቀዛቀዘ ቢመስልም እናቶቻችን ፣ አባቶቻችን ፣ ወንድሞቻችን ፣ እህቶቻችን ከአካባቢያችን (በተለይ ከጎጃም) ተነስተው ለተለያዩ መንፈሳዊ አገልግሎቶች ማለትም ገዳማትንና አድባራትን ለመሳለም ፣ ለጸበል፣ ለአብነት ትምህርት፣ ሊቃውንት መምሕራን ሰፋ ላለው መንፈሳዊ አገልግሎት ዓባይን በሚሻገሩበት ጊዜ፤ እንዲሁም ወጣቶች ለዘመናዊ ከፍተኛ ትምህርት ወደ ተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ብሎም እስከ ውጭ ሀገር ድረስ በሚሄዱበት ጊዜ “እነዚህ ሃይማኖት የሌላቸው ቅብዓቶች ውጉዛን ናቸው” እየተባለ የሚደርስብንን ጫናና መገፋት የሰማዩ አምላክ ይቁጠረው ፡፡ ይህ ሁሉ አልበቃ ቢላቸው ከ1995 ዓ.ም ጀምረው ደግሞ የግፋቸው ግፍ በዝቶ አንድ ጊዜ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አምኖ ተጠምቆ ክርስቲያን የተባለውን ኦርቶዶክሳዊ ምእመን “ጥምቀት የለህም፤ክርስቲያን አይደለህም” በማለት ድጋሚ ጥምቀትን አመጡብን ፡፡ በዚህ እኩይ ተግባር ለከፍተኛ ዘመናዊ ትምህርት ወደተለያዩ ተቋማት የሄዱ ኦርቶዶክሳውያን ወጣቶችን በዚያው አካባቢ ባለ ቤተ-ክርስቲያን “ግቢ ጉባዔ” በሚባል አዳራሽ እየሰበሰቡ “ከጎጃም የመጣችሁ ተማሪዎች ክርስቲያን ስላይደላችሁ ድጋሚ መጠመቅ አለባችሁ” እየተባሉ ብዙዎች ድጋሚ እንዲጠመቁ ተደርገዋል ፡፡ ለጸበል ወደ ታላላቅ ገዳማትና አድባራት የሄዱ ምእመናን “ኢአማኒ ስለሆናችሁ ከመጠመቃችሁ በፊት የልጅነት ጥምቀት መጠመቅ አለባችሁ” እየተባሉ ብዙዎቹ ድጋሚ ተጠምቀዋል ፡፡ ካህናት ድጋሚ ክህነት ተቀብለዋል ፡፡ በተክሊል አግብተው የነበሩ ምእመናን ድጋሚ ተክሊል ተፈጽሞባቸዋል ፡፡ መንኩሰው የነበሩ መነኮሳት ድጋሚ እንዲመነኩሱ ሆነዋል፡፡ሕገ እግዚአብሔርንም እንዲጥሱ ተገደዋል፡፡(ኤፌ ምዕ 4 ቁ 5). ፡፡ ጥምቀት፣ ምንኩስናና ሥርዓተ ተክሊል የማይደገም ምሥጢር በመሆኑ ይህ እኩይ ተግባራቸው እየተበባሰ በመምጣቱ በወቅቱ የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ለነበሩት ለ “ብጹዕ አቡነ ማርቆስ” 9 ገጽ ያለው ደብዳቤ በ11/09/2008 ዓ.ም የድምጽና የምስል መረጃ አያይዘን ብናቀርብላቸውም ሊመለከቱት አልቻሉም ፡፡ ደጋግ ሊቃውንት “ጥምቀት አንዲት ናትና ሁለተኛ እናጠምቃለን የምትሉ ሰዎች ከድርጊታችሁ ተቆጠቡ” በማለታቸው እስከ መወገር ደርሰውበታል ፡፡ ጥምቀት በቤተክርስቲያናችን ከማይደገሙና ከማይደጋገሙ ዶግማዎቻችን አንዱ ነው ፡፡
ይህንን ዶግማ የጣሰውን ትውልድና አያሌ ሊቃውንትን በድንጋይ የወገረውን ወጣት ክርስቲያን ነኝ ባይ የበላይ ጠባቂው ሲኖዶስ እሽሩሩ እያለ ይዞ ፤ የእኛን ግፍ ግን የበለጠ እያከፋው መጣ ፡፡ አበው ሐዋርያት የክርስቶስ ልደት ሁልጊዜ በየዓመቱ ታኅሣሥ 29 ቀን እንዲከበር የወሰኑትን ድንጋጌ ጥሶ ከዐራት ዓመት አንድ ጊዜ በ28 መከበር አለበት ብሎ ከቀደሙት አበው ከሐዋርያት ያላገኘውን ከሠለስቱ ምዕት ያልተረከበውን ሐዲስ ሥርዓት አምጥቶ በቤተክርስቲያን ስም መተግበሩና ጾመ ገሀድን በአዋጅ መሻሩ ሳያንሰው “ልደትን በ28 ያላከበረ መናፍቅ ነው” እያለ ብዙውን ምእመን ማሸበሩን ቀጥሎበታል ፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በ1993 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ የታተመውን ወልደ አብ የተባለውን መጽሐፍ ከነበረው ፊደሉን በማሳነስና ያልተጨመሩ ምዕራፍና ቁጥሮችን በማካተት እንደገና ለሁለተኛ ጊዜ በ2006 ዓ.ም እንዲታተም አድርገን ወጣቱና አንባቢው ምእመን በብራና ብቻ የነበረውን ታላቅ መጽሐፍ በወረቀት ታትሞ በማግኘቱ በታላቅ ደስታ ተመልክቶ እውነቱን ፍንትው አድርጎ መረዳት እንዲችል ሆነ፡፡ በዚህ መጽሐፍ “ታላላቅ የመጽሐፍ መምሕራን” የሚባሉ ሰዎችን ወጣቱ መጽሐፍ እንዲህ ይላል እኮን እያለ በየቦታው መከራከር ጀመረ ፡፡ ይህንን ክርክር ያልቻሉት አሳዳጆቻችንና ድጋሚ አጥማቂዎቻችን በመጽሐፍ የመጣውን በመጽሐፍ መመለስ ሲያቅታቸው ጉዳዩን ወደ ፖለቲካ እያዞሩ ብዙ አባቶችንና ወጣቶችን እስከማሳሰር ድረስ ደርሰዋል ፡፡ ይሁን እንጅ እኛ የታሠርነው ለሃይማኖት እንጅ ሀገር ዘርፈን ፣ ሰርቀን ፣ ቀጥፈን ስላይደለ በጸጋ እንቀበለዋለን በማለት ስንታሠር ስንፈታ ቆይተናል፡፡
ይህ ሁሉ ግፍ እንዳለ ሁኖ ቅዱስ ነኝ ባዩ ሲኖዶስ እውነተኛውን የሃይማኖት ምሥጢር ከመጻሕፍትም ከሊቃውንትም ማጥፋቱን ቀጥሎበት በ2010 ዓ.ም በወርኃ ጥቅምት ያ ለሁለተኛ ጊዜ የታተመውንና ከጠቅላይ ቤተ-ክህነቱ ጀሞሮ በታላላቅ ገዳማትና አድባራት የሚገኘውን ጥንታዊ መጽሐፍ “በአንድ ግለሰብ የተደረሰ ነው፣ የቅብዓትንና የፀጋን ሃይማኖት ያስፋፋል፣ካህናትን በካህናት ላይ የሚያስነሳ፣ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጭ መጽሐፍ ነው” በሚል ሀሰተኛ አነጋገር መጽሐፉን አውግዞ ከማንኛውም መንፈሳዊ አገልግሎት እንዲለይና እንዲቃጠል ሲወስን፤እኛም መጽሐፉ እኛን የሚገልጠን፣ሃይማኖታችንን የሚናገር፣ትክክኛውን የኦርቶዶክስ አስተምህሮ የያዘ በመሆኑ ፤ መጽሐፉን አውግዞ እንዲቃጠል ካደረገ እኛ ከእርሱ ጋር ሕብረት የለንም ፡፡
“ወንሕነሰ አመነ በርትዕት ሃይማኖት ከመ ናለብዎሙ ለሐዲሳን እለ ነሥኡ ጥምቀተ ወናጽንዕ አልባቢሆሙ ለንዑሰ ክርስቲያን ፡፡ ወእመሰ ዐቀብነ በአልባቢነ ሃይማኖተ ወኢያግሀደነ ለሰብእ በፍርሃተ ኵነኔ ወምንዳቤ ንከውን ውፁኣነ እምሕይወት ወዓዲ ዕቅፍተ ለካልኣን ወመሥገርተ ለብዙኃን (እኛ ግን ጥምቀቱን የተቀበሉትን አዲስ አማኞች እናሳውቃቸውና (እናለብማቸውና) የንዑሰ ክርስቲያንንም ልቡናቸውን እናጸና ዘንድ በቀናች ሃይማኖት አምነናል ፡፡ በልቡናችን ሃይማኖትን ብንጠብቅም ፍርድንና መከራን በመፍራት ለሰው ባንገልጥ ግን ከሕይወት የወጣን እንሆናለን ፤ ዳግመኛም ለሌሎች እንቅፋት ለብዙዎች እንቅፋት ለብዙዎችም ወጥመድ እንሆናለን)” (ዲድስቅልያ 24 ቁ 27-28) እንዳሉ አበው ሐዋርያት ለእውነት ብለን ብንታገሥና እውነተኛዋን ነገር ገልጠን ባንናገር ከእውነት የወጣን እንሆናለንና ከእውነት የወጣን መሆን ስለሌለብን፤ይህ መጽሐፍ(ወልደ-አብ) ቀደምት መምህራን ያዘጋጁት ምሥጢረ ሥላሴንና ምሥጢረ ሥጋዌን አብራርቶ የሚናገር ፣ ዛሬ በአንድ ግለሰብ የተዘጋጀ ሳይሆን ቀደም በነበሩ ሊቃውንት እስትግቡዕ የሆነ፤ የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ሀብትና እውነተኛ መጽሐፍ መሆኑን በመግለጽ ውግዘቱ እንዲነሳ ለቅዱስ ነኝ ባዩ ሲኖዶስና ለተለያዩ የመንግሥት አካላት በየደረጃው በ16/02/2011 ዓ.ም ባለ 12 ገጽና ዳግም ጥምቀትን በተመለከተ ደግሞ ባለ 3 ገጽ ደብዳቤ ብናደርስም ጆሮ ዳባ ልበስ ተብለን መፍትሔ ሳይሰጠን ቀረ ፡፡
መፍትሔ ሊሰጡን ባለመቻላቸው በቀን 13/03/2011 ዓ.ም ድርሳነ ቄርሎስ ፣ ገድለ እስትንፋሰ ክርስቶስ፣ገድለ ፊልጶስ፣ሥንክሳርና ፍትሐ ነገሥት የቀድሞ ዘራቸው እየተቀየሩ በተለይ ደግሞ “ምሥጢረ ቅብዓተ መንፈስ ቅዱስን” የሚተነትኑ መጻሕፍት ቀለማቸው እየተፋቀ፤ የቀድሞ ይዘታቸው እየተቀየረ ፤ልብሳቸው አምላካቸው በሆኑ በቀን በብዙ ሽሕ ብር እየተከፈላቸው በሚለፈልፉ ሊቃውንት ነኝ ባይ ሐሳውያን እየተቆነጻጸሉ ሲታተሙ ፤ አዘጋጆችንም ሆነ አሳታሚዎችን ከመገሰጽና መጽሐፉን ከመመርመር ይልቅ ለእነሱ ድጋፍ እየሰጠ ፤ እኛ በብራና ላይ ያለውን እውነታ መሠረት አድርገን ስንናገር ሓሳውያን እያስባለ ከቤተ ክርስቲያን ቅጽረ ግቢ እያባረረ ፤ በደላችንን በማብዛቱና ከላይ በጠቀስናቸው ምክንያቶች ከግፍ ከማያድነንና ከሚያሳድደን ሲኖዶስ ራሳችንን ለይተን የራሳችንን አባቶች በእግዚአብሔር ፈቃድ ሹመን ራሳችንን የምንችል መሆናችንን በማሳወቅ የመጨረሻ አቤቱታችንን አሁንም “ለመንበረ በትረያሬክ ጽ/ቤት” ና ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት አሳውቀናል ፡፡
በድጋሚ በ81ዱ መጽሐፍ የማይመራ፤ዶግማና ቀኖናውን ያልጠበቀ ፤ ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን የጣሰ፤ለሥጋው እንጂ ለሃይማኖቱ ያልተገዛ፤ የምዕመኑን ጥያቄ በአግባቡ ያልመለሰ ቅዱስ ነኝ ባይ ሲኖዶስ በተደጋጋሚ መልስ ሊሰጠን ባለመቻሉ አባቶቻችንን ሹመን እራስችንን የምንችል መሆኑን የሚገልጽ ደብዳቤ መጋቢት 18/07/2011 ዓ.ም ባለ 5 ገጽ ለሰላም ምኒስትር ከ1000 የምዕመን ፊርማ ጋር አባሪ አድርገን አቀረብን ፡፡ አሁንም ይህን ሁሉ ውጣ ውረድ እያየን ፍትሕ በመነፈጋችን ምክንያት በ2012 ዓ.ም ግንቦት 16 ቀን የእኛ የምንላቸውን አባቶቻችንን ከ40 ቀን ሱባኤ በኋላ ፈጣሪ በቸርነቱ ሰጠን ፡፡ የአባቶችን መሾም ለሚመስለንና ለምንመስለው ምእመን በሙሉ አደረስን ፡፡
ምዕመናንም ሁሉ ተደሰቱ ፡፡ ይህ በሆነ ጊዜ ግን ያን ጊዜ መጻሕፍት ተቆነጻጸሉ፣ዶግማና ሥርዓት ተሸረሸረ ብለን ስንጮህ የነበረውን ጩኸት ያልሰማ ቅዱስ ነኝ ባይ ሲኖዶስ ከዚህ በፊት “አባት የሌላችሁ እጓለማውታ፣ሃይማኖት የሌላችሁ መናፍቃን ፣ ቤት የሌላችሁ ምንዱባን” ሲለን ከነበረው ሰው ጋር ወደ እኛ ይጮህ ጀመር ፡፡ ያኔ ጥምቀት ተሻረች፣ ዶግማችን ፈረሰ ፣ መጻሕፍት ተቆነጻጸሉ ስንለው ያልሰማው ቅዱስ ነኝ ባይ ሲኖዶስ “ሕገወጥ ሹመት ተሾማችሁ” ብሎ በሰኔ 3/2012 ዓ.ም አስቸኳይ ስብሰባ ጠርቶ “የተሾሙ አባቶችን ክህነታቸውን ይዣለሁ” ብሎ ጩኸቱን አሰማ ፡፡ ከዚያም የችግሩን አጣሪ ልዑካን ብሎ 10 ያህል ሰዎችን ላከ ፡፡ ለእነዚያ ሰዎችም በሰኔ 14 ቀን/2012 ዓ.ም ስላለው ችግር በሙሉ የሚገልጽ አቤቱታና፤መመለስ ስላለባቸው 9 ጥያቄዎች(ስለምሥጢረ ሥላሴ፤ ስለምሥጢረ ሥጋዌ፤ ስለምሥጢረ ጥምቀትና ስለሥርዓተ ቤተክርስቲያን ጥሰት) የሚገልጽ ባለ 22 ገጽ ደብዳቤ ከነሙሉ ማብራሪያ ጋር አድርገን ከፍተኛ የክልል፣ የዞንና የወረዳ አመራሮች በተገኙበት በጉንደወይን የአስተዳደር ጽ/ቤት መሰብሰቢያ አዳራሽ ላይ በዝርዝር አስረድተን፤እኛ ከእነሱ የተለየን መሆናችንንና የተጠየቁት 9ኙ ጥያቄዎች ሳይመለሱ ስምምነት የለም በማለት ሰነዱን ሰጥተን መለስናቸው ፡፡
ይሁን እንጅ ያ የተጠየቀ ጥያቄ ለቅዱስ ነኝ ባዩ ሲኖዶስ እንዲቀርብ ለአጣሪ ጉባኤው(ቡድኑ) ብንሰጥም የወቅቱ የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ የነበሩት አቡነ ዮሴፍ “ደብዳቤው ጠፋኝ” በማለታቸው እነሆ መልሱ የውኃ ሽታ ከሆነ አንድ ዓመት ሊሞላው ቀናት ብቻ ቀርተውታል ፡፡ ጥያቄው መልስ ሳያገኝ የውኃ ሽታ እንደሆነ፤ችግርን ተመልክቶ ከመፍታት ይልቅ በ2013 ዓ.ም በግንቦት 19 ቀን ከቀድሞው በደሉ ሳይመለስ እነሆ “የተሾሙ አባቶችንንና ከእነሱ ጋር ይወጡ ይወርዱ የነበሩ ካህናትንና ዲያቆናትን ፣ምእመናንን አውግዘን ለይተናል” በማለት ድጋሚ በደሉን ከዓባይ ማዶ ሁኖ አሰምቶናል ፡፡ ሲበዛስ ጨውም ይመራል ነውና ነገሩ ፤
እስከአሁን ድረስ ሲያደርስ የነበረውን የዶግማና የቀኖና ጥሰት ዝም ብንለው ሲኖዶሱ በየዘመኑ ከስሕተት ወደ ስሕተት እየሄደ፤ሕገ እግዚአብሔርን እየጣሰ ፤ የእምነት ምሰሶዎችን እያፈረሰ፤ብሂለ ንስጥሮስና ልዮን እየተከተለ፤ከክህደቱ የማይታረም በመሆኑ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ 636 ጳጳሳትን ከእግዚአብሔር በተሠጠው ሥልጣን እንዳወገዘ ፤ እኛም ከእግዚአብሔር በተሰጠን ሥልጣንና ኃይል ውጉዝ ከመ አርዮስ ወንስጥሮስ ወልዮን ብለን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ቅዱስ ነኝ ባዩን ሲኖዶስ አውግዘናል ፡፡ ከዛሬ ጀምሮ እኛ እነርሱን፤እነርሱም እኛን በእምነትና በሥርዓት አያውቁንም ፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ሰኔ 11/2013 ዓ.ም
ጎጃም፤ ኢትዮጵያ!!!
No comments:
Post a Comment