ዕዝራ ሐዲስ Vs ዕዝራ ሱቱኤል
==================
ክፍል --ሁለት
በክርስቶስ ክርስቲያን በወልድ ውሉደ እግዚአብሔር በመንፈስ ቅዱስ መንፈሳውያን የተሰኛችሁ ኦርቶዶክሳውያን አባቶቼ ካህናት ፤ ወንድሞቼ ዲያቆናት ፤ እህቶቼና ወንድሞቼ ሁላችሁም እንደምን ሰነበታችሁልኝ ፡፡
በክፍል አንድ መልእክቴ በ2008 ዓ.ም ድርሳነ ቄርሎስን ለሕትመት ያበቁትና በአሁኑ ሰዓት በስሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት በመንበረ መንግሥት መድኃኔ ዓለም የዐራቱ ጉባዔያት ትርጓሜ ምስክር መምህር ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ሐዲስ ቄርሎሱን ሲያሳትሙ ተቀብዓ የሚለውን ተሰብአ እያሉ እየለወጡ መጻፋቸውን ስለ አንዱ ሀሳብ መጻፌ የሚታወስ ነው ፡፡ እነሆ ዛሬም በዚህ በክፍል ሁለት ጽሁፌ ደግሞ በነቢዩ በኢሳይያስና በክቡር ዳዊት ስለ ተቀብዓ የተነገሩ ትንቢቶችን ቆርጠው ያስቀሯቸው መሆኑንና ብራው ላይ ያለውን ቃል በፎቶ አስዳስሳችኋለሁ፡፡ ጽሁፉ ልክ እንደ ክፍል አንድ ከእውነት እና ከእውነተኞች ጋር እሄዳለሁ የሚል ሰው ብቻ ይመለከተው ዘንድ የተጻፈ ሲሆን ግዴታ የለውም ፡፡ የመሰለው ብቻ ሀሳቡን ይውሰድ ፡፡ እውነትንም ይጠብቃት ፡፡ ያልመሰለው ደግሞ አለማየትም አለመስማትም ሙሉ መብቱ ነው ፡፡ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ሐዲስ ራሳቸው ቁጥር በሰጡት ድርሳነ ቄርሎስ ድርሳን 65 ቁጥር 6 ላይ “ወዓዲ ይብል በቃለ ክርስቶስ(ዳግመኛም በክርስቶስ አነጋገር ገብቶ እንዲህ አለ” ብለው ጽፈዋል ፡፡ ይህ በምዕራፍ 65 ላይ የተነገረው ሀሳብ ክርስቶስን ዕሩቅ ብእሲ ብሎም ወልደ ዮሴፍ ለሚሉት ሰዎች አማናዊ አምላክ ካልሆነማ ስምዖን “ባሪያህን አሰናብተው ማዳንህን አይተዋልና” እያለ ስለምን በተናገረ ነበር እያለ መድኅን ክርስቶስን ወልደ ዮሴፍ ለሚሉ ሰዎች የተሰጠ ማብራሪያ ያለበት ቃል ነው ፡፡ እናም ከመነሻው ቁጥር አንድ ላይ “ኢትመውት ዘእንበለ ትርአይ መሢሖ ለእግዚአብሔር (እግዚአብሔር የቀባውን ሳታይ አትሞትም)” ተብሎ ትንቢት ስለተነገረለት(ሉቃ 2) አረጋዊው ስምዖን መድኅን ክርስቶስን በክንዱ አቅፎ ይዞ “ይእዜ ትስእሮ ለገብርከ(አቤቱ ባሪያህን አሁን አሰናብተው)” ይህም የክርስቶስን የባሕርይ አምላክ ቢሆን ነው እንጅ ባይሆንማ ኖሮ ስምዖን አረጋዊ “አቤቱ አሰናብተኝ” እያለ ባለመነው ነበር የሚለው ምሥጢር ከገለጸ በኋላ ደግሞ በተጨማሪ የባሕርይ አምላክ በመሆኑ ነዳያን ትሩፋንን ደስ ያሰኘ መሆኑን፣ በቊሱለ መቀራ የተያዙትን ያድን ዘንድ ፣ ለተማረኩትም ነጻነትን ይሰብክ ዘንድ ፣ ዕውራነ ልቡና እስራኤል ያዩ ዘንድ ስለዚህ በባሕርይ ሕይወቱ በመንፈስ ቅዱስ ተቀብቶ የተላከ መሆኑን ለማጠየቅ ሊቁ ቅዱስ ቄርሎስ በሉቃስ ወንጌል መነሻነት የክርስቶስን መቀባት ሲያስረዳ ወዓዲ ብሎ የኢሳይያስን ትንቢት የተናገረበ አንቀጽ ነው ፡፡ እናም “ወዓዲ” ብሎ የጀመረው ከላይ ስለ ስምዖን አረጋዊ ክርስቶስን በእቅፉ ይዞ አቤቱ ባሪያህን አሰናብተው ብሎ መለመኑ ክርስቶስ አምላክ ስለሆነ እንጅ ዕሩቅ ብእሲ ስለሆነ አይደለም የሚለውን ከአስረዳ በኋላ ደግሞ ወደ ኢሳይያስ ትንቢት መምጣቱን ሲነግረን ነው ፡፡
ሊቁ የጻፉትም “ወዓዲ ይብል በቃለ ክርስቶስ (ዳግመኛም በክርስቶስ አነጋገር ተገብቶ እንዲህ አለ)፤ ንባብ መንፈሰ እግዚአብሔር ላዕሌየ ፤ እዜነዎሙ ለነዳያን ፈነወኒ ወእስብክ ግዕዛነ ለፂውዋን ወለዕውራን ርእየተ ኢሳ 61 ፡ 2” ይላል ፡፡
ከብራናው ላይ ያለው ቃል ደግሞ
“ወዓዲ ይብል በቃለ ክርስቶስ ፤ መንፈሰ እግዚአብሔር ላዕሌየ ፤ ዘበእንቲአሁ ቀብዓኒ ፤ እዜነዎሙ ለነዳያን ፈነወኒ ወእስብክ ግዕዛነ ለፂውዋን ወለዕውራን ርእየተ”
ትርጉም፡- ዳግመኛም በክርስቶስ ተገብቶ እንዲህ አለ ፤ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ላይ ነው ፤ ለድሆች የምስራችን እነግር ዘንድ ቀብቶኛል ፡፡ ለታሰሩት መፈታትን ለእውራን ማየትን እሰብክ ዘንድ ልኮኛል/ልኮኛልና)” ሲለን ነው ፡፡
ይሁን እንጅ የተቀብዓ ስደተኛው ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ሐዲስ “በእንተ ዝንቱ ቀብዓኒ” የሚለውን ነቅለው አስቀርተውታል ፡፡ እንግዲህ ዓይንን የፈጠረ አምላክ አያይምን?ፍርዱን ለፈጣሪ ትተን ቅብዓተ መንፈስ ቅዱስን ላለመቀበል ሲሉ መጽሐፍ ቅዱስን እያደሱት እየከለሱት እንደሆነ ሁሉም ሰው ሊገነዘበው የሚሻ ጉዳይ መሆኑን አሳስባለሁ ፡፡
ወደ ኢሳይያስ ትንቢት ስንመለስ በክርስቶስ ተገብቶ የተናገረው ነቢዩ ኢሳይያስ ሲሆን ትንቢቱንም ገና ክርስቶስ ከመወለዱ በፊት የተናገረው ትንቢት ነው ፡፡ ይህ ትንቢት “ቅብዓትን አልፎንሱ ሜንዴዝ በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አመጣው” ለሚለው ነጭ ትውልድ አፍ ማዘጊያ ነው ፡፡ እንዴት ቢሉ ፤ ትንቢቱና ቃሉ የተነገረው ገና ክርስቶስ ከመወለዱ ከ600 ዓመታት በፊት ሲሆን ሜንዴዝ አልፎንሱ ኢትዮጵያ ውስጥ የመጣው ክርስቶስ ከተወለደ በኋላ በ1600 ዓመታት በኋላ ነው ፡፡ በኢሳይያስ ትንቢት መነገርና በአልፎንሱ ሜንዴዝ ኢትዮጵያ ውስጥ መምጣት መካከል ቢያንስ በትንሹ የ2000 ዓመታት ርቀት አለው ፡፡ እናማ ወገኖቼ!! እነ እንትና አልፎንሱ አመጣው እያሉ የሚናገሩት ተረት ተረት መሠረት የሌለው ልብወለድ ፈጠራ መሆኑ በዚህ ይታወቃል ፡፡
በሌላ መልኩም እነ እንትና የኢሳይያስን ትንቢት ሲተረጉሙ “ቀብዓኒ” የሚለውን “አዋሐደኝ” ብለው ለውጠው በጨዋ በአለአዋቂ ትርጉማቸው ለሚተረጉሙ ሰዎች አፋቸውን የሚዘጋ ትንቢት ነው ይህ ትንቢት ፡፡ እንደምን ቢሉ፤ ትንቢቱ የተነገረው ለኢሳይያስም ለክርስቶስም ነው ፡፡ ለኢሳይያስ ሲነገር በብሉይ ኪዳን ካህናት ለክህነት ነቢያት ለትንቢት ሲመረጡ በተቀመመ ሽቱ አማካኝነት ጸጋ መንፈስ ቅዱስን ተቀብለው ነው ነቢይ ወይም ካህን የሚሆኑት ፡፡ አማናዊ መሲሕ መድኅነ ዓለም ክርስቶስም “ኦሪትንና ነቢያትን ልፈጽም እንጅ ልሽር አልመጣሁም” ብሎ እንደነገረን በቅዱስ ወንጌል የባሕርይ ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስን በማኅፀነ እሙ ተቀብቶ ክርስቶስ መሢሑ ለእግዚአብሔር አብ ተብሎበታል ፡፡ለዚህም ይኸው ኢሳይያስ በትንቢቱ ምዕራፍ 11 ቁ 1 ላይ “ወትወጽእ በትር እሥርወ እሤይ (ከነገደ ዕሤይ በትረ ሕይወት እመቤታችን ትወለዳለች) ፤ ወየዓርግ ጽጌ እምኔሃ (ከነገደ እሤይ ከተወለደች ከእሷም ጌታ ይወለዳል)፡፡ ወየአርፍ ዲቢሁ መንፈሰ እግዚአብሔር (በእርሱ ላይ መንፈስ ቅዱስ ያድርበታል) ፤ መንፈሰ ጥበብ ወአእምሮ (ለሌላው ጥበብ ዕውቀት የሚገልጥበት) ፤ መንፈሰ ኃይል ወምክር (ለሌላው ኃይል የሚያደርግበት) ፤ ወምክር (ለሌላው ምክር የሚገልጽበት) ፤ መንፈሰ ልቡና ወጽድቅ (ለሌላው ዕውቀት የሚገልጥበት ፣ ምግባር ትሩፋት እንዲሠራ የሚያርግበት) ፤ ወይመልዕ ላዕሌሁ መንፈሰ ፍርሃተ እግዚአብሔር (እግዚአብሔርነቱን የሚያስፈራ መንፈስ በእርሱ ላይ ይመላል) በሕልውናው ይኖራል ብትልም ይሆናል) በኢሳይያስ የሚቈጥራቸው ሰባቱ ሐብታት እሊህ ናቸው ፤ እሊህ ብቻ ሁነው አይደለም በፍጹም ቈጥሮ እንዲህ አለ እንጅ” ይለናል ፡፡ እነ እንትና ይህችንም ሲተረጉሙ “መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ወርዶ በራሱ ላይ ይቀመጣል” ይህም ወፍራም ክሕደትን ያመጣባቸዋል ፡፡ ምክንያቱም ኢሳይያስ ነቢይ “መንፈሰ እግዚአብሔር ይነብር ዲቤሁ” ብሎ ከተናገረ በኋላ 7 ሐብታተ መንፈስ ቅዱስ ገንዘቡ እንደሆኑለት ተናግሯል ፤ ታዲያ ይህንን ጊዜ መድኅን ክርስቶስ እነዚህን ሰባቱን ሐብታተ መንፈስ ቅዱስ ስለሰውነቱ በማኅፀን የተቀበላቸው ሲሆን በዮርዳኖስ ነው ቢሉ ፤ መድኅን ክርስቶስን የፀጋ የማደጆ ልጅ የጸጋ አምላክ ማድረጋቸው እንደሆነ ያሰቡበት አይመስልም ፡፡ ምክንያቱም በዮርዳኖስ መንፈስ ቅዱስ በእርሱ ላይ ማደሩ የአንድነት የሦስትነቱን ምሥጢር ለመግጽ ብሎም አምላክ ወልደ አምላክ መሆኑን ለማጠየቅ እንጅ በዮርዳኖስ ባረፈበት ጊዜ 7ባቱን ሐብታ ገንዘብ አደረገ ማለት ልክ እንደ እኛ እሱን የጸጋ አምላክ የጸጋ ልጅ ማድረግ ነው ፡፡ በአምሳለ ዮርዳኖስ በ40 በ80 ቀናችን በውኃ ከተጠመቅን በኋላ በቅብዓሜሮን ተቀብተን ስመ ክርስትና ተሰጥቶን ውሉደ እግዚአብሔር የምንሰኘው እኛ ነን ፡ እርሱ ግን በማኅጸነ እሙ ነው ገንዘብ ያደረገው ፡፡ ለዚህም “አንሰ ተሰየምኩ ንጉሠ በላዕሌሆሙ በጽዮን በደብረ መቅደሱ(እነሱ ባያውቁ ዕሩቅ ብእሲ ወልደ ዮሴፍ ይሉኛል ፤ እኔ ግን በማኅፀነ ማርያም ነግሻለሁ)” መዝ 2 ብሎ በክቡር ዳዊት አድሮ ራሱ ክርስቶስ ነግሮናል ፤ ንግሥና በምንድን ነው ያሉ እንደሆነ በቅብዓት ነው እንላለን ፡፡
እነ እንትና ግን የኢሳይያስን “ቀባኝ” ብለው የክርስቶስን “አዋሐደኝ” ብለውታል ፡፡ አየህ ከእሾህ ቢሸሱ ጋሬጣ ይሉሀል ይሄ ነው ፡፡ በአንድ ነቢይ የተነገረውን ቃል ለአንዱ አከበረኝ ለሌላኛው አዋሐደኝ እያሉ እነሱ ጠፍተው እውነትን ያጠፉ ዘንድ ተነስተዋልና መንፈሳዊት ሕሊና ትኖረን ዘንድ ዘወትር እንጸልይ ጎበዝ!!! የእኛ አቅማችን ጸሎትና ጸሎት ብቻ ነው ፡፡ ብሩንም ፣ ጉልበቱንም ፣ ብዛቱንም ፣ ሌላውንም ሁሉንም ጠቅልለው የወሰዱት እነሱው ናቸው ፡፡ እናማ ወገኖቼ ቅዱስ መጽሐፍ እንዲህ እየተለወጠ እየተቀየረ እየተበረዘ ይገኛልና ልቡናችንን አንቅተን ክርስትናችንን እንጠብቃት ፡፡ ኃይለ-ቃሉን እየቆረጡ ከማውጣት የበለጠ ክሕደት ምን ክሕደት አለ?፡፡
በመቀጠልም ቅዱስ ቄርሎስ ክቡር ዳዊት በመዝሙር 44 ቁ 7 ላይ የተናገረውንና ቅዱስ ጳውሎስ በዕብራውያን መልእክቱ ምዕ 1 ቁ 9 ላይ የደገመውን ቃል አብራርቶ የተናገረበትን የዳዊቱን ቆርጠው አስቀርተው የቄርሎስን ደግሞ ተቀብዐ የሚለዉን ተሰብአ እያሉ የለወጡትን ለማሳየት እወዳለሁ ፡፡ በቅን ልቡና ተከታተሉኝ ፡፡
በድርሳን 56 ቁ 3 ላይ “(ንባብ) ወበእንተሰ መላእክቲሁ ይቤ ዘይሬስዮሙ ለመላእክቲሁ መንፈሰ ወለእለ ይለዐክዎ ነደ እሳት ወበእንተሰ ወልዱ ይቤ መንበርከ እግዚኦ ለዓለመ ዓለም በትረ ጽድቅ ወበትረ መንግሥትከ ፤አፍቀርከ ጽድቀ ወዓመፃ ጸላዕከ ፡ ከማከ ዕብ 1 ቁ ፡ 9፡፡” ብለው አስቀምጠውታል ፡፡
ብራናው ድርሳነ ቄርሎስ ላይና ዕብራውያን 1 ቁ 9 ያለው ደግሞ “ወበእንተሰ መላእክቲሁ ይቤ ዘይሬስዮሙ ለመላእክቲሁ መንፈሰ ወለእለ ይለዐክዎ ነደ እሳት ወበእንተሰ ወልዱ ይቤ መንበርከ እግዚኦ ለዓለመ ዓለም በትረ ጽድቅ ወበትረ መንግሥትከ ፤ አፍቀርከ ጽድቀ ወጸላዕከ ዓመፃ ፤ በእንተዝ ቀብዓከ እግዚአብሔር አምላክከ ቅብዓ ትፍስሕት እምእለ ከማከ” ሲል ተጽፎ ይገኛል፡፡
ትርጉም፡- “ስለ መላእክቱስ/ስለመላእክቱም መላእክቱን ነፋሳት የሚላኩትንም የእሳት ነበልባል የሚያደርጋቸው እሱ ነው ፡፡ ስለልጁ ግን ጌታ ሆይ ዙፋንህ ለዘለዓለም ነው ፤ የመንግሥትህም በትር የዘለዓለም በትር ነው ፤ ጽድቅን ወደድክ ዓመጻንም ጠላህ ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር አምላክህ እንዳንተ ካሉት ይልቅ የሚበልጥ የደስታ ዘይትን ቀባህ” ማለት ነው ፡፡
የተቀብዓ ስደተኛው ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ሐዲስ “በእንተዝ ቀብዓከ እግዚአብሔር አምላክከ ቅብዓ ትፍስሕት እምእለ ከማከ” የሚለውን ቁም!!!ጥ አድርገው አስቀርተውታል ፡፡ አስተውሉልኝ ወገኖቼ እርሳቸው ቆርጠው ቢያስቀሩትም መዝሙሩም አለ ዕብራውያን ላይም አለ (በዚህ ክፍል የዚህን መዝሙር ትርጓሜ በሰፊው እናይ ነበር ግን ጊዜ አይበቃንምና በሌላ ክፍል የምመለስበት ይሆናል ፡፡ በሌላ ክፍል ስመጣ መዝሙር 44 ቁ 7ንና ዕብራውያን 1 ቁ 9ን ሲተረጉሙ የተለያዩ ትርጉሞችን ተርጉመዋቸው እንደሚገኙም ያኔ እናያለን)
ሊቁ ዕዝራ ሐዲስ ይህንን እንደሚመቻቸው ከከረካከሙ በኋላ የሚከተለውን ጽፈውልናል
“እመ ፈጣሬ መላእክት ፤ ዘቦቱ መንበር ዘለዓለም ፤ አፍቀረ ጽድቀ ፤ ወጸልዐ ዓመጻ ፤ በእንተዝ ይብልዎ ከብረ ክብረ ትፍሥሕት እምኀበ እግዚአብሔር አብ (መላእክትን የፈጠረ ከሆነ ፤ የዘለዓለም መንግሥት ገንዘቡ ከሆነ ፤ ሰው መሆንን ከወደደ ፤ ሰው አለመሆንን ከጠላ ፤ ሰው መሆንን ስለወደደ ከአብ በሚገኝ ክብር ከበረ ተባለ ፤ ከአብ የተገኘ ክብርም አካለ ቃል ነው ፤ ክብርነቱም ለተዋሐደው ሥጋ ነው)” ሲሉ ተርጉመውልናል ፡፡
የብራናው ደግሞ ከታች በፎቶ እንደምታዩት
“እመ ፈጣሬ መላእክት ውእቱ ፤ ዘቦቱ መንበር ለዓለመ ዓለም ፤ አፍቀረ ጽድቀ ወጸልአ ዓመፃ ፡ ወበእንተዝ ይብልዎ ተቀብዓ ቅብዓ ትፍሥሕት እምኀበ እግዚአብሔር አብ” ይላል
ትርጉም፡- “መላእክትን የፈጠረ ከሆነ ፤ የዘለዓለም ሥልጣን ገንዘቡ ከሆነ ፤ ሰው መሆንን ከወደደ አለመሆንን ከጠላ ስለዚህ ከአብ በሚገኝ ክብር(የደስታ ዘይት) ተቀባ ከበረ ይበሉት)” ማለት ነው ፡፡
አንባቢው አስተውል!! ስደተኛው ሊቀ ሊቃውንት ከባድ ከባድ ስሕተቶችን ተሸክመው እንደሚገኙ እየነቀስን እንመልከት ፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ እሳቸው “ተቀብዓ ቅብዓ ትፍስሕት እምኀበ እግዚአብሔር አብ” የሚለውን ወደ “ከብረ ክብረ ትፍስሕት” ብለው ዘሩን ነቁን ለውጠውታል ፡፡ ይክንን ከለወጡ በኋላ “ከአብ የተገኘ ክብርም አካለ ቃል ነው ፤ ክብርነቱም ለተዋሐደው ሥጋ ነው” በማለት የማይሰዳቸው ወጥመድ ውስጥ ሲገቡ ይስተዋላሉ ፡፡ ይኸውም “ይብልዎ ተቀብዓ ቅብዓ ትፍስሕት” ተብሎ የተነገረለት ከላይ መንግሥቱ ዘለዓለማዊ የሆነው ፣ መላእክትን የፈጠረው ብሎም ደግሞ ሰው መሆንን የወደደው አለመሆንን የጠላው ነው ፡፡ በደንብ አስተውል አንባቢው! ሰው መሆንን ከወደደ ሰው አለመሆንን ከጠላ “ይብልዎ ተቀብዓ ቅብዓ ሀሴት” ፤ ሰው መሆንን ወዷልና አለመሆንን ጠልቷልና(ይህንን መዝ 44ን ስናይ በሰፊው እንመጣበታለን) ስለዚህ ከአብ በተገኘ የደስታ ዘይት ተቀብቷል ይበሉት /ይሉታል ብሎናል ፡፡ እንደ ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ሐዲስ ትርጓሜ ከሆነ ደግሞ ከአብ የተገኘው ክብር አካለ ቃል ነው እያሉን ሲሆን ክብርነቱ ደግሞ ለተዋሐደው ሥጋ ነው እያሉን ነው ፤ በእሳቸው አነጋገር የተቀባው ሥጋ የቀባው ቃል ነው ፡፡ በቄርሎስ አነጋገር ደግሞ የተቀባው ሰው መሆንን የወደደው አለመሆንን የጠላው ነው ፤ በመሆኑም አባ ዕዝራ የተናገሩት ፈጠራቸው እዚህ ላይ ዋጋ ያጣል ማለት ነው ፡፡ ምክንያቱም ሥጋማ እኮ ጥንቱንም ሰው ነውና ሰው መሆንን ወደደ አለመሆንን ጠላ አይባልለትምና ፡፡ አካለ ቃልን ከአካለ ሥጋ ነጣጥለው ለያይተው ከተቀብዓ እሸሻለሁ ሲሉ በምንታዌ ጋሬጣ ተይዘው ይገኛሉ ፡፡ በደንብ ለማብራራት ተቀባ የተባለው ሰው መሆንን የወደደው አለመሆንን የጠላው በመሆኑ እሳቸው አካለ ቃልን ነጥለው ቢያስቀሩት ሥጋ በፊትም ሰው ነውና ሰው መሆንን ስለወደደ ተቀባ ለመባል ትርጉም የሌለው ከንቱ ነገር ነው ፡፡ ቀጥለውም አካለ ቃልን አክባሪ አካለ ሥጋን ከባሪ አድርገው በግብር አንድ የሆነ ወልድን ለሁለት ከፍለው ምንታዌን ታቅፈዋት ይገኛሉ ፡፡
በዚህ ብቻ አያቆሙም ሊቁ
“ምንት ንብል በዘኢይበጽሕ ሕሊናነ በእንቲአሁ ፡፡ አመ ይሬስዮሙ ለመላእክቱ መንፈሰ ፡፡ ወመንበር ቦቱ ዘመለኮት ፡፡ በእንተ ምንት ከብረ ክብረ ትፍሥሕት ፡፡ ወይፈጥር መላእክተ ከመ አምላክ ውእቱ ፡፡ ወከብረ ከመ ሰብእ ፡፡ አኮ በሕላዌ መለኮቱ አላ ተሠጊዎ በሥምረቱ ነሥአ ክብረ(ልቡናችን መርምሮ የማይደርስበትን የሱን ነገር ምን እንላለን? የአምላክነት ሥልጣን ገንዘቡ ከሆነ ፤ መላእክትን የፈጠረ ከሆነ ስለምን ከበረ ተባለ ብትል? የባሕርይ አምላክ እንደመሆኑ መላእክትን ፈጠረ ፤ ሰው እንደመሆኑ ከበረ ብየ እመልስልሀለሁ፡፡ በባሕርየ መለኮቱ አይደለም በፈቃዱ ሰው በሆነ ጊዜ ከበረ ተባለ እንጅ” እያሉ ሲውረገረጉ ይገኛሉ ፡፡
ይህ ትርጉማቸው ዘሩን ከመቀየራቸው በስተቀር ምንም ችግር የለበትም እኛም የምናምነው ይህንኑ ነው ፡፡ ይሁን እንጅ ከላይኛው ትርጉማቸው ጋር አይገጥምላቸውም ፡፡ ከላይ አካለ ቃልን አክባሪ አካለ ሥጋን በአካለ ቃል አክባሪ አድርገው ሲናገሩ ቆይተው እዚህ ሲደርሱ ደግሞ ልክ እንደተቀበበች ቀበሮ መሯጫ መውጫ አጥተው ጭንቅ ጥብብ አላቸው መሰለኝ “ሰው በመሆኑ ከበረ” ብለው ተናግረዋል ፡፡
እንዳንረሳው የብራናውን እንመልከት
“ምንት ንብል በዘኢይበጽሕ ሕሊናነ በእንቲአሁ ፤ እመ ይሬስዮሙ ለመላእክቱሁ መንፈሰ ወመንበር ቦቱ ዘመለኮት ፤ በእንተ ምንት ተቀብዓ ቅብዓ ትፍሥሕት ፤ ወይፈጥር መላእክተ በከመ አምላክ ውእቱ ፤ ወተቀብዓ ከመ ሰብእ ፡፡ አኮ በህላዌ መለኮት አላ ተሠጊዎ በሥምረቱ ነሥአ ቅብዓተ” ይላል
ትርጉም፡- ሕሊናችን(ልቡናችን) መርምሮ በማይደርዝበት በእሱ ነገር ምን እንላለን! ፤ መላእክትን የፈጠረ ሲሆን ፤ የአምላክነት ሥልጣን ገንዘቡ ሲሆን በምን ምክንያት የደስታ ቅብዓትን ተቀባ? ፡፡ አምላክ ነውና መላእክትን ፈጠረ ፤ ሰው እንደመሆኑ ተቀባ ፡፡ በባሕርየ መለኮቱ አይደለም ሰው በመሆኑ በፈቃዱ ተቀባ እንጅ” ነው ፡፡
የተቀብዓ ስደተኛው ሐዲሱ ዕዝራ (ሊቀ ሊቃውንት) “በእንተ ምንት ተቀብዓ ቅብዓ ትፍሥሕት” የሚለውን ነቅለው “በእንተ ምንት ከብረ ክብረ ትፍሥሕት” ብለው ዘሩን ለውጠውታል ፡፡ ዘሩን ቢለውጡትም ትርጉሙ ግን የማያራምዳቸው በመሆኑ ትተውታል ፡፡ ከዚህ ላይ ማስታወስ የምፈልገው ነገር ቢኖር እንዲያው ምን ሲባል ዘሩ ተነቀለ ለምንስ ምክንያት ዘሩን መቀየር አስፈለጋቸው? የሚለውን ሀሳብ በደንብ እንድታጤኑልኝ ነው ፡፡ ለአሁኑ ክፍል ያለኝን ሀሳብ በዚህ ጨረስኩ በሚቀጥለው ክፍል ደግሞ ጰላድዮስና ቅዱስ ቄርሎስ እርስ በእርሳቸው እየተነጋገሩ የተጻፈውን ተሰእሎተ ጰላድዮስ በሚባለው ክፍል ላይም የዳዊትን መዝሙር ቆርጠው ያስቀሩበትንና ተቀብዓን ተሰብአ እያሉ የለወጡበትን የመጽሐፍ ቅዱስ ሕዳሴ ሥራቸውን ይዤ እመጣለሁ ፡፡ እስከዚያው ከሁለት ወይም 3 ሳምንታት በኋላ አዲስ ዓመት እንቀበላለንና ያንን አዲስ ዓመት ለመቀበል ልቡናችንን አዘጋጅተን ከሁለተኛ አጥማቂ የሱስንዮስ ደቀ-መዛሙርት ተንኮልና ሴራ ራሳችንን ነጻ አድርገን ማንነታችንን እንድናጸና የአምላካችን መልካም ፈቃድ ይሁንልን ፡፡ኮሮና የሚባል ቫይረስንም ፈጣሪ አጥቶልን ለማየት ያብቃን ፡፡ በተለየ ግን ከበሽታው በከፋ ሁኔታ ኮሮና የሆኑብንን ክልዔ አጥማቂዎችን አምላክ ወልደ አምላክ በቸርነቱ ልቡናውን አእምሮውን ያድልልን ፡፡
ስብሐት ለአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ኪያነ ዘፈጠረ ከመ ናምልኮ፤
ስብሐት ለማርያም እመ አምላክ እግዝእትና ወመዳኒትንነ፤
ስብሐት ለመስቀነ ክርስስ እጸ መድኃኒት ኃይልነ ወጸወንነ
ይቆየን
ይቀጥላል
No comments:
Post a Comment