በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ!!!
“ከዚህ የበለጠ ምሥጢር ምን ምሥጢር አለ????”= ክፍል አንድ
“ለመኑ እመላእክቲሁ ይቤሎ እምአመ ኮነ ወልድየ አንተ ወአነ ዮም ወለድኩከ ፤ ወካዕበ
አነ እከውኖ አባሁ ወውእቱ ይከውነኒ ወልድየ (ከሆነ ጀምሮ ከመላእክት ወገን “አንተ ልጄ ነህ እኔ ዛሬ ወለድኩህ፤ ዳግመኛም እኔ
አባት እሆነዋለሁ እሱም ልጄ ይሆነኛል” ማንን አለው? ዕብ ምዕ 1 ቁ 5፡፡
==============+==================================
በክርስቶስ
ክርስቲያን በወልድ ውሉደ እግዚአብሔር የተሰኛችሁ በሜሮን ቅብዓት የታተማችሁ ኦርቶዶክሳውያን ወንድም እህቶቼ እንደምን ሰነበታችሁልኝ!
፡፡ አምላክ በቸርነቱ ጠብቆ ለዚህ ስላደረሰን ክብርና ምሥጋና በፈጠረው ፍጥረት አንደበት ሁሉ ይድረሰው ፡፡ ለዛሬ የምንነጋገርበት
ዋና ዓላማችን በዚህ በምሥራቃዊት ምድር ተወልደን አድገን ለከፍተኛ ዘመናዊ ትምህርት ወደ ዘመናዊ መካነ አእምሮ ቀያችንን ለቀን
ስንጓዝ በክርስትና ሃይማኖታችን ከተለያዩ አካላት የሚቀርቡ ጥያቄዎች ልቡናችንን እያወኩ ፤ ወደ ሁለተኛ ጥምቀት እያመሩን ስለሆነ
መጽሐፍ ቅዱስ ስለምናምናት ክርስትናችን ምን ይላል የሚለውን እውነታ ለማስረዳት ያህል ነው ፡፡
እነሆም
የማናውቅ ከሆነ ለማወቅ መዘጋጀት ፤ የምናውቅ ከሆነ ደግሞ ለሌሎች ለማሳወቅ መትጋት እዳለብን መዘንጋት የለብንም ፡፡ ስለሆነም
መጽሐፍ ቅዱስ የተናገረውን እውነት ለምን እደዚህ ይሆናል ብለን እንጠይቅ ዘንድ ተገቢ አይደለም ፡፡ ለምሳሌ፡- መጽሐፍ ቅዱስ አብ
ወልድን ቀባው አከበረው ይላል ፡፡ ታዲያ እዚህ ላይ ለምን ያከብረዋል? እዴት ሊሆን ይችላል? የሚሉ ጥያቄዎች ዋጋ የሌላቸው ጥያቄዎች
ናቸው ፡፡ ምክንያቱም እኛ ፍጡራን ለምን ሊያከብረው ይችላል? የሚል ጥያቄን የመጠየቅ አቅም የሌለን የአከበረበት ምሥጢሩ ከኅሊናችን
በላይ ስለሆነ ቅዱሱ መጽሐፍ አከበረው ካለው እኛም አከበረው የሚለውን እንቀበላለን እንጅ ፤ ካላገባን ገብተን ስለምን ሊያከብረው
ይችላል እንዴት እንዲህ ሊሆን ይችላል? ብሎ ያዙኝ ልቀቁኝ ማለት የማያዋጣ ነው ፡፡ ለምን ብንል እኛ ሰው የሚል ስም ተሰጠን?ለምን
ዛፍ የሚል ስም አልነበረንም?ለምን በሁለት እራችን ሄድን ስለምን ዓራት እር አልኖረንም?.....የመሳሰሉትን ጥያቄዎች ብንጠይቅ
ለአእምሮአችን የከበዱ ለኅሊናችንም የረቀቁ ናቸው ፡፡ ታዲያ ይህንን ያልመለሰች ኅሊናችን ደፍራ ራሱ ባለቤቱ መድኅን ክርስቶስ
“የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ላይ ነው ለድሆች ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ቀብቶኛል” ብሎ የተናገረውን እውነታ “ለምን ሊቀባው ይችላል
አልቀባውም፣ ምንም ቅብዓት አይፈልግም” እያሉ ቢፍጨረጨሩ ድንጋይ መንከስ ነው ፡፡ ምክንያቱም መድኅን ክርስቶስ በነቢዩ አድሮ ቀብቶኛል
ብሎ ስለተናረ እኛ ቀብቶታል ብለን ማመን እንጅ አልቀባውም እንዳንልማ ራሱ እኮ ቀብቶኛል ብሎንናልና ውርደቱ ለማንም ሳይሆን ለራሳችን
ነው ፡፡ ስለሆነም በመጽሐፍ ቅዱስ የምናምን ከሆነ ትክክለኛውን ትርጓሜ (ቀደምት አበው አጥርተው የተረጎሙትን) እየተረዳን በአቅማችንና
በልካችን መኖር ይኖርብናል ፡፡
ወደቀደመው
ነገሬ ስገባ በተለምዶ አነጋገር “ቅብዓቶች” እያሉ የሚጠሩን በትክክለኛው በሰዋስው አነጋርም ሆነ በሃይማኖታዊት አጠራራችን መሢሐዉያን
ቅቡዓን እንባል ዘንድ የሚገባን እኛ በብዙ አለአዋቂዎች በየቦታው ስንሰደብ ስንደበደብ ስንታሠር ስንወገር የመገኘታችን ዋናው ምሥጢሩ
፤ እንደሌሎቹ የሐገረ ስብከት ገንዘብ መዝብረን ፣ ከመነኮስን በኋላ በካባችን ቀልደን ወንዶች ከሴት ጋር ሴቶች ከወንድ ጋር የዝሙት
ሥራ ሠርተን ፣ መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረውን እውነታ ለውጠን ተርጉመን
ወይም ቆርጠን አውጥተን ቀደን ጥለን ፣ አንዲት ጥምቀትን
ሁለት ጊዜ ተጠምቀን ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን ጥሰን ሳይሆን ፤ አምላኳን የሰቀለች ከንቱ ዓለም ከንቱን ትወዳለችና እውነትን በመከተላችን
፣ መጽሐፍ ቅዱስ አሐቲ እያላት ስለምን ሁለተኛ ጥምቀትን እንጠመቃለን ብለን በመጮሃችን፣የቤተክርስቲያናችንን ካዝና ሙጥጥ አድርገው
የዘረፉ ሊቀ ጳጳስንና ሌላውን አካል አንቱ ብላ ያነገሠች ዓለም እውነተኞቹን ጳጳሳት እያሳደደች በምትኝት ወቅት ለምን ብለን በመጠየቃችን
፣ መጽሐፍ ቅዱሱ በመንፈስ ቅዱስ ከበረ ብሎ እየተናገረ ሳለ ዘሩን ምሥጢሩን ለውጠው የሚናገሩ ሰዎችን ለምን ብለን በመጠየቃች ነው
፡፡ ይህም ሆኖ ሳለ እነሱ እንደፈለጉ መሆን ሲችሉ የራሳቸው ሲያርባቸው የሰው ለማማሰል የሚታትሩ ናቸውና ሳንደርስባቸው ስለደረሱብን
፣ ሳንነካቸው ስለነኩን ለምን ትነኩናላችሁ ለምንስ ትደርሱብናላችሁ ብለን በመናገራችን ከላይ ከ”ሲኖዶሱ” ጀምሮ እስከታች እስከ
ምእመኑ ድረስ ባላገባቸው ገብተው እየበጠበጡን መገኘታቸው ደግሞ አቤት ጉድ!!! የሚያሰኝ እውነታ ነው ፡፡ በመንግሥት ምድራዊ በኩልም
ቢሆን ዘመኑ ዘመነ አፍ እንጅ ዘመነ መጽሐፍ ስላይደለ ፤ እኛው ለተገፋን ፣ እኛው ለተሰደብን ፣ እኛው ድጋሚ ተጠመቁ ተብለን አዋጅ
ለወጣብን ፤ ዞሮ እኛኑ ትከፋፍላላችሁ ፣ ትለያያላችሁ ፣ ሰላም ታውካላችሁ……ወዘተረፈ እያለ ያውከናል ፡፡ ይህንንም ስንመለከተው
በርባን ይፈታ ኢየሱስ ይሰቀል ያለች የአይሁድ ምድር የመንጋ ጩኸትን የምታስታውሰን እንደሆነች መገንዘቡ አይከፋም ፡፡ ምድራዊ መንግሥት
የሚያስተዳራትን እና የሚገዛትን (በእግጥ ገዥውም አስተዳዳሪውም ፈጣሪ ነው) ምድር የያዘቻቸውን ሕዝቦች በእኩልነት የማገልገል ግዴታውን
በአግባቡ ሲወጣ ፤ የሚገዛቸው ሕዝቦቹም በቅንነት እንዲገዙት የታወቀ ነው ፡፡ አሁን በምድራችን ላይ እያየነው ያለነው ግን ብዙዎቹ
በውሸት ከጮሁ የጥቂቶቹ እውነት የሚሰማት እንደሌለ እያስተዋልን እንገኛለን ፡፡ ይህም ማለት በምሥራቃዊት ጎጃም “በአለአዋቂው”
ተናጋሪ “ቅብዓቶች” የምንባል እኛ ሁለተኛ ተጠመቁ የምንባል ከሆነ ከድጋሚ አጥማቂቆች ጋር ኅብረት የለንምና በራሳችን እንመራ ዘንድ
ምድራዊ ፈቃድ ስጡን ብለን ብንጠይቅም እስከ አሁን መልስ አልተገኘም ፡፡ እንዲያውም በአሁኑ በሐገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ዮሴፍ
አማካኝነት ጉዳዩ እንዲከሽፍ እየተሤረ መሆኑን መረጃዎቻችን እያመላከቱን ይገኛሉ ፡፡ ለዚህም ቢሆን ጊዜ ስለአለው ፈጣሪን በተስፋ
እየጠበቅን እነዚህ የማያውቁ እና የማይነቁ ሰዎች በማያዉቁት ገብተው
የሚበጠብጡበት እውነታው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የለምን? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ የሚያስችለንን ኃይለ ቃል አንስተን እንወያያለን
፡፡ አፍ ብቻ የሆነውን ትውልድ የምናሸንፈው በገንዘብ አልያም በጉልበት ሳይሆን በመጽሐፍ ነው ሁላችን ነቅተን የምናምነውን ሃይማኖት
ከመጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃው ጋር አቅማችን በፈቀደውና ፈጣሪ በገለጠንል መጠን ጠንቅቀን ልናውቅ ይገባናል ፡፡
በዚህ
ክፍል የምናነሳው አንደኛው ማስረጃችን ቅብዓት ሲባል ምን ማለት ነው? በእውኑ እነዚያ ክፉ ጥፉ የሆነ አእምሮን የተሸከሙ ሰዎች
እደሚሉት “እመቤታችንን ተቀባት” ማለት ነውን? ወይስ ምንድር ነው? የሚለውን ጥያቄ የሚመልስልን ኃይለ ቃል መመልከት ይሆናል ፡፡ ይህንንም ጥርት አድርገን
አንድ በአንድ በል ወለድ ሳይሆን በመጽሐፍ ቅዱስ እንነጋገራለን ፡፡ አምላክ ምሥጢሩን ጥበቡን ይግለጽልን ፡፡
“አፍቀርከ
ጽድቀ ወአመጻ ጸላእከ ወበእንተዝ ቀብዐከ እግዚአብሔር አምላክከ ቅብዓ
ትፍስሕት ዘይኄይስ እምእለ ከማከ (ጽድቅን ወደድክ አመጻን ጠላህ ስለዚህም እንዳንተ ካሉት የሚበልጥ የደስታን ዘይት ቀባህ” ዕብ
1 ቁ 9 ፡፡ ይህንን ቃል የተናገረው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ሲሆን ፤ እርሱ በሐዲስ ኪዳን ከመናገሩ በፊት በብሉይ ኪዳን መድኅን
ክርስቶስ ከመወለዱ በፊት ክቡር ዳዊት በመዝሙር 44 ቁ 7 ላይ ቁልጭ አድርጎ ተናግሮታል ፡፡ ይህ እውነታ የሚነግረን እነዚያ አእምሮ የሌላቸው ነጭ ሰዎች እንደሚናገሩት
“ መድኅን ክርስቶስ እመቤታችንን ተቀባት” የማለት እንዳልሆነ ነው ፡፡ ይኸውም “እግዚአብሔር አምላክህ እንደአንተ ካሉት የሚበልጥ
የደስታ ዘይትን ቀባህ” አለው እንጅ “አንተ ድንግልን ተቀባሃት” እንዳላለን በደንብ እንረዳለን ማለት ነው ፡፡ እህ! ታዲያ ቀባህ
ያለውን ለውጠው ነው እንዴ “ተቀባት” የሚሉ? ቢሉ ይህስ እነሱ ልቡናቸው
እንደወደደ አእምሮአቸው እንደወደደ ይናገሩታል እንጅ ተቀባት የሚል ትምህርትስ የለንም ፡፡
ቅዱስ
ጳውሎስ “እንዳንተ ካሉት የሚበልጥ የደስታ ዘይትን ቀባህ “ያለውን ቅዱስ ዮሐንስ በደንብ ተርጉሞታል ፡፡ ወንድም እህቶቼ እያስተዋልን
፤ እነዚያ አሳዳጆቻችን መጠሪያቸውን እንኳን አስተካክለው ሳይለዩ እኛን ሲበጠብጡን አፋቸውን ማስያዝ ይጠበቅብናልና እንንቃ እንማርም
፡፡ በቤታው ለክሕደታቸው መደበቂያ ይህንን የቅዱስ ጳውሎስን ቃል ማስረጃ ብታቀርቡላቸው “ ትርጓሜ ያሻዋል” እንደሚሏችሁ ምንም
ጥርጥር የለውም ፡፡ እናም “ቀባህ” የሚለውን “አዋሐደህ” ፤ እግዚአብሔር አምላክህ የሚለውን ደግሞ “እግዚአብሔርነትህ አምላክነትህ”
ብለው ለውጠው ገልብጠው እንደሚተረጉሙላችሁ ይታወቃል፡፡ እንግዲህ
በእነሱ ቤት ትርጓሜ አበበን ከበደ እያሉ መተርጎም ልምዳቸው ነውና እንዲህ እያገለባበጡ እየቆማመጡ የሚተረጉሙት ትርጓሜ የመንፈስ
ቅዱስ ሳይሆን የሰይጣን እንደሆነ ልናውቅ ይገባል ፡፡ ይህንን የምለው ዝም ብየ በስማ በለው ወይንም እንደነሱ በክፉ ጥላቻ ተነስቼ
ሳይሆን እውነተኞቹ አበው እነ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የተረጎሙት ትርጓሜ ይዤ ነው ፡፡ መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ተቀባ ከበረ
የተባለው ክብር የሚሻ ሥጋን ተዋሕዶ የሥጋን ገንዘብ (ክብር መሻትን) ገንዘቡ በማድረጉ ነው ፡፡ ከዚህም ላይ በደስታ ዘይት ቀባህ
ያለውን ነጠላ ቃል ይዘው “ዘይት ፣ ቫዝሊን…”ሌላም ሌላም እያሉ የኮከና ፊታቸውን በሚያወዙበት በዚያ በልቅምቃሚ ነገራቸው እየመሰሉ
ያጣጥሉታል ያዋርዱትማል፡፡ በዚህ ግብራቸው ደግሞ ቅድመ አያቶቻቸውን
አይሁድን ይመስሉበታል ፡፡ እንዴት ቢሉ መድኅን ክርስቶስ አጋንንትን በሚያወጣበት ተአምራትን በሚያደርግበት ጊዜ “አጋንንትን በአጋንንት
አለቃ በብዔልዜቡል ስም ያወጣል“ ያወጣል እያሉ ይዘባበቱበት ነበር፤ ብሎም መንፈስ ቅዱስን ብዔልዜቡል እያሉ ይሳደቡ ነበር ቅ ድመ
አያቶቻቸው፡፡ ቅድመ ዓያቻቸው በግብር ስለሚመስሏቸው ነው ፡፡ እነሱም ሳያውቁትና ሳይለዩት ቅዱሱን ቅብዓት መንፈስ ቅዱስን “ቫዝሊን”
ሌላም ሌላ እያሉ ይሰድቡታል ፡፡ አባታቸው መቅዶንዮስም እንዲሁ መንፈስ ቅዱስን ሲሳደብ ነበር ፡፡ መንፈስ ቅዱስን የተሳደበ ደግሞ
ሥርየተ ኃጢአት የለውም ማቴ 12 ቁ 32፡፡
እነሱ እያገለባበጡ ለክሕደታቸው መደበቂያ ዋሻ እያዘጋጁ የሚከትሙበትን ቅዱስ
ዮሐንስ አፈወርቅ ምን ብሎ ተርጉሞታል ቢሉ!
“ወእምዝ አትለወ ወይቤ
በእንተ ሥጋዌሁ አፍቀርከ ርትዐ ወዓመፃ ጸላዕከ ፤ በእንተዝ ቀብዓከ እግዚአብሔር አምላክከ ቅብዓ ትፍሥሕት እምእለ ከማከ (መንበርከ እግዚኦ ፤ አንድም በትረ መንግሥትከ ካለ በኋላ ስለ ሰውነቱ ጽድቅን ወደድክ
፤ ዓመፃንም ጠላህ ፤ ስለዚህም እግዚአብሔር
አምላክህ የደስታ ዘይትን ቀባህ አለ) ፤ ዘንተኒ ይቤ በፍኖተ ክላሕ (ይህንን አሁን የተናገረውን በትንቢት ፣ በምሳሌ ፣ በአገባብ ተናገረ ፤ አንድም በጩኸት በድፍረት ተናገረ ፤ አንድም በፍኖት ከሊሖ ይላል ፤
ጮሆ ደፍሮ ተናገረ ፡፡ ትንቢት የሚመጣውን አውቆ
መናገር ነው ፡፡ ምሳሌ ቀብዓከ ብሎ በትረ መንግሥትከ
በትረ ጽድቅ ማለት ነው ፡፡ አገባብ በሰውነቱ ተቀባ ማለት
ነው ፡፡ ድፍረት አምላክ በባሕርዩ ከበረ ማለት ነው ፡፡ አንድም ድፍረት አምላክከ ማለት ነው ፡፡ ጩኸት ማለት
ኦ አምላክ ማለት ነው” ድርሳን 3ቁ
67-68 ፤ ይህንን ካለ በኋላ
“ናሁኬ ዘለፎሙ በዝየ ለንፉቃን አይሁድ ፣ ወለሕዝበ ጳውሎስ ሳምሳጢ ፣
ለአርዮሳውያን ፣ ወለመርክላን ፣ ለሰባልዮስ ፣ ወለመክንዮን (እነሆ በዚህ አንቀጽ ተጠራጣሪዎች አይሁድን ፣ የጳውሎስ ሳምሳጢን ወገኖች ፣
አርዮሳውያንን ፣ መርክላንን ፣ ሰባልዮስን ፣ እለመክንዮንን ረታቸው” ይለናል (ድርሳን 3 ቁ
73)፡፡ አስከትሎም “ለአይሁድኒ ዘለፎሙ በብሂሎቱ አምላክ ወሰብእ (አይሁድን
አምላክ ወሰብእ( አምላክና ሰው ብሎ ተናግሮ ረታቸው)) ፡፡ ሐተታ ኦ አምላክ ብሎ ቀብዓከ አምላክከ ማለቱ ቀባዒነቱንና ተቀባዒነቱን ያስረዳልና ፤ ወለሕዝበ ጳውሎስ ይትዋስኦሙ
በእንተ ሀልዎተ ወልድ ቀዳማዊ (እለ ጳውሎስ ሳምሳጢንም ወልድ ቀዳማዊ እንደሆነ አንድም ቅድመ ዓለም
እንደነበረ ተናግሮ አስረዳ (መንበርከ እግዚኦ ለዓለመ ዓለም በማለቱ) ፤ ወክመ ባሕርዩ ኢኮነ ፍጡረ (በባሕርዩ ፍጡር እንዳይደለ) ፤ በብሂሎቱ መንበርከ እግዚኦ
ለዓለመ ዓለም (መንርከ ለዓለመ ዓለም ብሎ ረታቸው) ፤ ዘንተ ይቤ ከመ ይፍልጦ እምፍጡራን (ከፍጡራን ይለየው ዘንድ ፡፡ አንድም ሊለየው መንበርከ ብሎ ተናገረ)” ድርሳን 3 ቁ 78 ፡፡ ይቀጥልና አፈወርቅ “ወለአርዮሳውያንሂ አርአዮሙ ኢፍጡር
ውእቱ (ለአርዮሳውያንም ፍጡር እንዳይደለ
አስረዳቸው) ፤ ሶበሰ ፍጡር ውእቱ እምኆለቆ ምስለ
አግብርት (ፍጡርስ ቢሆን ኖሮ ዘይሬስዮሙ ካላቸው ከመላእክት ጋር እሱንም ዘረሰዮ ብሎ በቆጠረው ነበር ብሎ ፍጡር እንዳይደለ አስረዳ) ፤ ወለመርክኖንሂ
ወእሊአሁ አስተኃፈሮሙ በብሂሎቱ በክልኤ ገጽ በበአካሎሙ (አንድ ገጽ የሚሉ
እለ መርክኖንን ወገኖቹንም ፤ በአካላቸው ሁለት ገጽ ብሎ ተናግሮ ረታቸው) ፤ ዘውእቱ አካለ አብ ወአካለ ወልድ (ይኸውም አካለ አብ ፣
አካለ ወልድ ነው)” (ድርሳን 3 ቁ 79-81) ፡፡ አሁንም አስከትሎ “ወለመንክዮንሂ አግሀደ ሎቱ ከመ መለኮት ኢይትቀባዕ ዘእንበለ ዳዕሙ ትስብእተ
ሥጋሁ (ምትሐት የሚሉ እለ መንክዮንን በሰውነቱ እንጅ ፤ በአምላክነቱ
ከበረ እንዳይባል
አስረዳቸው ፡፡ ምትሐት ይላሉ እንጅ ፤ በመለኮቱ
በባሕርዩ ከበረ ይላሉን? ቢሉ ፤
መጽሐፍ ቃልን
በሥጋ ተቀባ ይለዋል በሥጋ ተቀባ እንዳይሉ
ምትሐት ይላሉ ፤ ምትሐት
ካሉ በአምላክነቱ
ከበረ ያሰኛልና ፡፡ አንድም ተቀብቶ ተዋሐደ
ይላሉና በመለኮቱ ከበረ እንዳይባል በእንተዝ በማለቱ አስረዳ” ድርሳን 3 ቁ 83 ፡፡ አክሎም “ይቤ ቅብዓ ትፍሥሕት
እምእለ ከማከ (ከባለንጀሮችህ
ይልቅ የደስታ ዘይትን ቀባህ)
አለ) ፤ መኑ እሙንቱ እለከማሁ (እምእለ ከማከ
የተባሉ እነማን ናቸው) ፤
አኮኑ ውሉደ ሰብእ (ምዕመናን
አይደሉምን) ፤ እስመ ለእግዚእ
ክርስቶስ አኮ በመስፈርት ዘተውህቦ
መንፈስ (መንፈስ ቅዱስ
ለክርስቶስ በልክ በመጠን
የተሰጠው አይደለምና ፤ ቅብዓ ትፍሥሕት
እምእለ ከማከ አለ ዘይኄይስ ያለበት
ነው)” ድርሳ 3 ቁ 84-87 በማለት ብጥር ጥርት ባለች አማርኛ የምትረዳ ትርጓሜን ተርጉሞልናል ፡፡
በአፋቸው ዮሐንስ አፈወርቅን ያስማረውን ትምህርት እኛ እናምናለን ይላሉ በግብራው ግን ዮሐንስ አፈወርቅ ያላስተማረውን
ትምህርትና ትርጓሜ ሲተረጉሙ ይስተዋላሉ ፡፡ እንግዲህ ክቡር ዳዊትና ቅዱስ ጳውሎስ “የደስታ ዘይት” ብለው በተረዳ አእምሯቸው
ያስቀመጡንት ዮሐንስ አፈወርቅ ደግሞ መንፈስ ቅዱስ እንደሆነ ቅልጭ አድርጎ ነግሮናል ፡፡ ከዚህ የወጣ ትርጓሜ ደግሞ የሰይጣን
እንጅ የሰው አይደለም ፡፡ እነሱ እንዳሉትማ ቢሆን ኖሮ እኮ ከእነሱ በእውቀትም በእምነትም የሚሻለው አፈወርቅ ዮሐንስ እንደነሱ
ገልብጦ በተረጎመልን ነበር ፡፡ ዳሩ ግን የእነሱ ትርጓሜ የጦለ የዞረ በመሆኑ ከዚህ ትርጓሜ ውጭ የሚያመጡ መናፍቃንን ነገር
ተቀብላችሁ አትካዱ ስል በፈጣሪ ስም እለምናችኋለሁ፡፡
ዛቲ
ሃይማኖት መሢሐዊት ዘትትአመን ባቲ ቤተክርስቲያን ቅድስት
ስብሐት
ለእግዚአብሔር
ክብር
ለቅድስት ድንግል ወለመስቀሉ ቅዱስ!!!
ይቆየን
ይቀጥላል
No comments:
Post a Comment