በስመ
አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ !!!
“የተቀብዐ
እንግዶች” ክፍል ዐራት
==============+==============
“ሰላም
ለክሙ ወጸጋ ለእግዚአብሔር አቡነ ወእግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ ፤ ነአኵቶ ለእዚአብሔር አቡሁ ለእዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘልፈ በእንቲአክሙ፤
ወንጼሊ እምአመ ታፈቅርዎሙ ሰማዕነ ሃይማኖተክሙ በኢየሱስ ክርስቶስ ወዘከመ ታፈቅርዎሙ ለኵሎሙ ቅዱሳን ፤ በእንተ ተስፋክሙ ዘሥዩም
ለክሙ በሰማያት ዘአቅደምክሙ ሰሚዐ በቃለጽድቅ ትምርተ ወንጌል
ሰላም
ለእናንተ ይሁን የአባችን የእግዚአብሔር የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ይደርባችሁ ፡፡ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባቱ እግዚአብሔርን
ዘወትር ስለ እናንተ እናመሰግነዋለን ፡፡ በኢየሱስ ክርስቶስ ማመናችሁንና ቅዱሳንን ሁሉ መውደዳችሁን ከሰማንበት ጀምሮ እንጸልያለን
፡፡ የእውነት ቃል በሆነው በወንጌል ትምርት አስቀድሞ ስለ ሰማችሁት በሰማያት ስለ ተዘጋጀላችሁ ስለተስፋችሁ” ቆላ ምዕ 1 ቁ
2-5 ፡፡
ወንድም እህቶቼ መሢሐውያን
እደምን ሰነበታችሁ? ከመጻሕፍት
ዓለም የራቁ ዘላን የምድረበዳ
እንግዶች አማናዊ መሢሕ
ኢየሱስ ክርስቶስ መሢሕ
ወበኩረ ምእመናን የተሰኘባትን
እውነት ሙጥጥ ጭልጥ
አድገው ክደው ፤
የራሳቸው መካድ ሳያንስ
ማንም ሳይነካቸው ማንም
ሳያስገድዳቸው ቤታችንን ለነኩን
ዉልደ መጥባሕት በሙሉ ኦርቶዶክሳዊ
መልሳችንን እንሰጣቸው ዘንድ
ተገቢ በመሆኑ በባለፈው
በክፍል አንድ ላይ
ስሙን የጠቀስኩለት እንግዳችን
“ዲ/ን ሁነኛው ተሾመ” የጻፈውን ጦማረ ክሕደት መሠረት አድርጌ ክፍል ዐራትን እደሚከተለው ጻፍኩላችሁ፡፡
1ኛ‹‹‹‹‹“ሥላሴ በከዊን ከመገናዘብ በቀር አንዱ አካል በአንዱ አካል አያድርም
፡፡ አንዱም ለሌላው ክብር አይሆንም በክብር ዕሩያን ናቸውና” ብሏል በክሕደት ጽሁፉ
ገጽ 24 ፡፡
ቅዱስ መጽሐፍ አብ ወልድን በመንፈስ ቅዱስ ቀባው ብሎ ቢናገር (ሐዋ 10 ቁ
38) ፤ ራሱ ክርስቶስ “የእግዚአብሔር መንፈስ በኔ ላይ ነው ለድሆች ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ቀብቶኛል” ኢሳይያስ 61 ቁ 1፤
ወንጌል ቅዱስ “ወተቀብዖሰ በመንፈስ ከመ ካህናት ሐዲስ” እያለ ቢናገር ፤ “መንፈስ ዘዚአየ በህላዌ ለሊሁ ኀደረ ላዕሌየ” ብሎ
ሳዊሮስ ቢተረጉም ፤ ኀደረን በሰው ሰወኛው ፤ ግዙፋን ነገሮች አንዱ በአንዱ ላይ እንዲነበር እንዲደረብ እንዲያድር አድርጎ የሚያስብ
ኅሊና በቁሙ የሞተ ነው ፡፡
አስተውል ወዳጄ በቅዱስ መጽሐፍ ተቀብዐ ፣ ነሥአ፣ ኀደረ፣ ከብረ እየተባለ በየአንቀጹ
በየአገባቡ የተነገረበት ቦታ ብዙ ነው ፡፡ እነዚህ ነገሮች በተለያየ አነጋገር ይነገሩ እንጅ ትርጉማቸው አንድ ነው አገባቡም እንዲሁ
አንድ ነው ፤ ይኸውም ተቀብዐ በመንፈስ ቅዱስ ፣ ነሥአ መንፈሰ ቅዱሰ ፣ መንፈስ ዘዚአዬ በህላዌ ለሊሁ ኀደረ ላዕሌየ ፣ ከብረ
በመንፈስ ቅዱስ ተብሎ ቢነገር ማሠሪያው አምላክ ወልደ አምላክ ሰው ስለመሆኑ በሰውነቱ በንሥአተ መንፈስ ቅዱስ፣ በኅድረተ መንፈስ
ቅዱስ፣ በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ ከበረ ማለት ነው ፡፡ ይህ ሲባል ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚያሻው ረቂቅ ምሥጢር ነው ፡፡ ማለትም ተቀብዐ
በመንፈስ ወይም መንፈስ ቅዱስ ኃደረ ላዕሌየ ብሎ ሲናር ስጋዊ ደማዊ አእምሮ በምታስበው ልክ በመንፈስ ቅዱስ ከበረ፣ መንፈስ ቅዱስ
በእኔ ላይ አደረ የሚሉትን አናቅጽት እንደግዙፍ ቅብዓት ወይም እኛ ፍጡራን እንደምንቀባው ቅብዓ ሜሮን መቀባት መቁጠር ጽኑዕ ክሕደት
ነው ፡፡ ወይም መንፈስ ቅዱስ ለወልድ ቅብዕ /ቅብዓት/ ሆነው ቢባል ሰው ሠራሽ የሆነ ቅብዓ ሜሮን በሰው አካል ላይ እንዲፈስ መንፈስ
ቅዱስም በወልድ አካል ፈሰሰ ማለት አይደለም ፡፡ ይልቁንም ተቀባ ከበረ እየተባለ መነገሩ ለሰው በሚገባ ቋንቋ መናገር ነው እንጂ
ምሥጢሩስ ከአእምሮ ከህሊና በላይ ነው ፡፡ ለምሳሌ ወልድ ቅደመ ዓለም ከአብ ተወለደ ሲባል መወለዱን ተወለደ ባለው ቃል ተረዳነው
እንጅ የአወላለዱን ምሥጢር ልንረዳው ልንገነዘበው አይቻለንም ብቻ ተወለደ እንላለን እንጅ ፡፡ ሁነኛው የተናገረውን “በህልውና መገናዘብ”
የሚለውን ቃል እኳን በአነዋወራቸው ይገናዘባሉ በሚለው እንግባባበታለን እንጅ እንዴት ይገናዘቡ ለአእምሮ የረቀቀ ለልቡናም የመጠቀ
ነው ፤ ብቻ በህልውና እንዲገናዘቡ እናውቃለን እንጅ የሚገናዘቡበት ምሥጢርና ሥርዓት ግን ለሰው አእምሮ ከመረዳት በላይ ነው ፡፡
እንደዚህም ሁሉ ኀደረ የሚለውም ራሱ ወልድ “ኀደረ ላዕሌየ” ብሎ ገለጠልን እንጅ ከአእምሯችን በላይ ነው እንዴት እንደሆነ ምሥጢሩ
ረቂቅ ነው ፡፡ በሥጋዊ አረዳዳችን ፣ በዓለማዊ አነዋወራችን ፣ በግዙፋን ፍጥረታት አረዳድ ተረድተን “ኀደረ” የሚለውን ቃል እንደ
ብርድ ልብስ መንፈስ ቅዱስን በወልድ ላይ ተደረበ ብለን እንተርጉም ብንል እንደነ ሁነኛው ተያይዘን መጥፋት ብቻ ነው የሚሆነው ፡፡
ስለሆነም አምላክ ወልደ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ “መንፈስ ዘዚአዬ በህላዌ ለሊሁ ኀደረ ላዕሌየ” ብሎ የተናገረበት አንቀጽ ለእኛ
በቀረበን አነጋገር የተነገረ እንጅ እንዲሁ በልሙጥ አእምሮ እቃን በእቃ ላይ እደማሳደር አድርገን ለመረዳት ማሰብ በራሱ ጽኑዕ ክሕደት
ነው ፡፡ በኔ ላይ አደረ ብሎ መድኅን ክርስቶስ የተናገረውን የኀደረ ፣ ነሥአን እና ተወክፈን ምሥጢር ቁልጭ አድርጎ ቅዱስ ሳዊሮስ እንደሚከተለው
ተርጉሞልናልና ከእሱ መረዳት እንችላለን ፡፡
“ወበእንተዝ ኵሉ ይትበሀል
ከመ ውእቱ ነሥአ መንፈሰ
ዚኣሁ ዘተነግረ በኢሳይያስ
ነቢይ
ሰው ስለሆነ በኢሳይያስ እንዲህ
ተብሎ የተነገረ የባሕርይ
ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስን
ገንዘብ እንዳደረገ ይነገራል፡፡
እንዘ ይብል መንፈሰ
እግዚአብሔር ዘላዕሌየ በእንተ
ዝንቱ ቀብዓኒ፡፡
የእግዚአብሔር ሕይወቱ መንፈስ
ቅዱስ በእኔ ላይ
አለ፤ ሰው ስለሆንኩ
ተሰጠኝ፤ አከበረኝም፤ ብሎ
በኢሳይያስ የተነገረ ሕይወቱ
መንፈስ ቅዱስን ገንዘብ
እንዳደረገ ሊነገር ይገባል፡፡
ሰበከ በእንተ ዝንቱ
እንዘ ይብል እስመ
መንፈስ ዘዚኣየ በህላዌ
ለሊሁ ኀደረ ለዕሌየ፡፡
ሰው ስለሆንኩ በህልውናዬ ያለ
መንፈስ ቅዱስ ተሰጠኝ
ብሎ አስተማረ፡፡
ወለምንትኑ ተሰመይኩ መሲሐ
- - - እንኪያ ስለምን መሲሕን
ተባልኩ፤
ዘእንበለ ዳዕሙ ሶበ
ኮንኩ ሰብአ - -ነፍስን
ሥጋን ብዋሐድ ነው
እንጂ ብሎ አስተማረ፡፡
ወዘሰ ኀደረ ላዕሌሁ
መንፈስ ቅዱስ በእንተ
ሥርዓተ ትስብእት ውእቱ
- -
መንፈስ ቅዱስ ተሰጠው
የተባለ ለሰውነቱ በሚገባ
ነው፡፡ አንድም ሰው
ስለሆነ ስለከበረ ሥጋ
ነው፡፡
ወእመ አኮሰ እስመ
መንፈስ ቅዱስ ዘዚኣሁ
ውእቱ በህላዌ መለኮት
-- ሰው ካልሆነማ በባሕርየ መለኮቱ
መንፈስ ቅዱስ ገንዘቡ
ነውና፤ አንድም የባሕርይ
ሕይወቱ ነውና እንደምን
ተሰጠው ይባላል፡፡
ዘከመ እግዚአብሔር በእግዚአብሔር
- - አብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ
ህልው ሁኖ እንዲኖር
መንፈስ ቅዱስም በባሕርየ
መለኮቱ ገንዘቡ ነውና
ሰውማ ካልሆነ እንደምን
ተሰጠው ይባላል፡፡ በከመ
ይቤ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ
ፈጹም፡፡
ወዝ ግብር ኢኮነ ክፉለ
ዘከመ ፩ዱ እምነቢያት
-- ይህ ክብር ከነቢያት እንደ
አንዱ ሊያከብረው በተከፍሎ
የተሰጠው አይደለም፤ ወኢበእንተዝ
ኀደረ ላዕሌሁ መንፈሰ
እግዚአብሔር በእንተ ሥርዓት
-- በጸጋም ሊያከብረው በተከፍሎ
የተሰጠው አይደለም፤
አላ በከመ ይቤ ኢሳይያስ
ነቢይ ሶበ ፈቀደ
ይምሀረነ ፍጻሜ ግብሩ
ኈለቈ ዘንተ ፯ተ
ጊዚያተ ወይቤ ኀደረ
ላዕሌሁ መንፈሰ እግዚአብሔር
መንፈሰ ጥበብ፣ መንፈሰ
አእምሮ፣ መንፈሰ ምክር፣
መንፈሰ ልቡና፣ መንፈሰ
ኃይል፣ መንፈሰ ፈሪሃ
እግዚአብሔር፡፡
ለምእመናን የሚሰጠውን ፍጹም
ክብሩን ያስረዳ ዘንድ
በወደደ ጊዜ ኢሳይያስ
እንዲህ ብሎ መላልሶ
እንደተናገረ ገንዘቡ ነው
እንጂ በጸጋ ሊያከብረው
የተሰጠ አይደለም፡፡ አንድም
ለምእመናን የሚሰጠውን ፍጹም
ክብሩን ያስረዳ ዘንድ
ኈለቈ ዘንተ ፯ተ
ጊዚያተ ይህን ሰባት
ጊዜ መላልሶ ተናገረ እንጂ፡፡
እስመ ኍልቈ ፯
በኀበ ዕብራውያን ፍጹም
ውእቱ፡፡ ፯ ማለት
በእብራውያን ዘንድ ፍጹም
ነውና ለምእመናን የሚሰጠውን
ፍጹም ክብሩን ያስረዳ
ዘንድ በወደደ ጊዜ
ኢሳይያስ እንደተናገረ ገንዘቡ
ነው እንጂ በጸጋ ሊያከብረው
የተሰጠው አይደለም፡፡ (ሃ.
አ. ዘሳዊሮስ ም. 87፣
17-19 አንድምታ) ብሎ ተርጉሞልናል ፡፡
እግዲህ
እንግዳችን ሁነኛው ተሾመ በቅዱስ መጽሐፍ የተነገረውን እንዳልተነገረ አድርጎ ሲክደው ምን ይባላል? ፡፡ እኛ ግን አበው የነገሩንን
ይዘን እንጓዛለን እነሱ እደሆኑ እንደ አይሁድ ዓይነ ልቡናቸው ታውሯል ፤ እንደ ፈርዖንም ደንድኗልና ይሰማሉ ብለን አናምንም ፡፡
ዳሩ ግን በእነሱ ስሕተት ተጠልፈው መውደቅ የሌለባቸው ነፍሳት ስላሉ ለእነሱ ሲባል ይህች ተጻፈች ፡፡ በመንፈስ ቅዱስ ከበረ ፣
መንፈስ ቅዱስ በእኔ ላይ አደረ ብሎ ክርስቶስ መናገሩ ለከንቱ የሚመስላቸው እኒህ ቢጽ ሐሳውያን ከበረ የተባለበትን ተቀብዐ የተባለበትን
ምሥጢር ባለመረዳታቸው ዘወትር ያስደንቁኛል ፡፡
ለስሙ አምላክ ታመመ፣ ተራበ ፣ ደከመ፣ ተጠማ ፣ ተገረፈ፣ተሰደደ፣ ተቸነከረ
፣ ሞተ ብለን እናምናለን ይላሉ ፡፡ ይህንን ያመኑ እነሱ ከበረ ሲባሉ ግን እጅግ ይጨንቃቸዋል ይጠባቸውማል ፡፡ እንዲያውም በቅብዓተ
መንፈስ ቅዱስ ከበረ ማለት እሱን ማሳነስ ነው ይላሉ ፤ እኒህ ሞኞች ሞተ ብለው ሲያምኑት በእዉኑ ወልድ ሞተ ስለተባለ ከአብ ከመንፈስ
ቅዱስ አነሰ ማለት ነውን? ታመመ ደከመ ሲባል በእዉኑ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ አነሰ ማለት ነውን? አይደለም ይልቁንም ታማሚ ደካማ
መዋቲ የሆነ ሥጋን ተዋሕዶ በተዋሕዶም የሥጋን ገንዘብ(ሕማምን ፣ ድካምን ፣ ሞትን) ገንዘቡ ስላደረገ በሥጋው ታመመ ፣ በሥጋው
ደከመ፣ በሥጋው ሞተ ተብሎ ተነገረለት እንጅ ፡፡ ተቀብዐ መባሉም እንዲሁ ነው ክብር(ቅብዐት) የሚሻ ሥጋን ተዋሕዶ የሥጋን ገንዘብ
(ተቀባዒነትን) በተዋሕዶ ገንዘቡ ስላደረገ እነሆ ተቀብዐ በመንፈስ ተብሎ ተነገረለት ፡፡ ቅዱስ ሳዊሮስም “አብ በወልድ በመንፈስ
ቅዱስ ህልው ሁኖ እንዲኖር መንፈስ ቅዱስም በባሕርየ መለኮቱ ገንዘቡ ነውና ሰውማ ካልሆነ እንደምን ተሰጠው ይባላል” ብሎ ቁልጭ
አድርጎ ተናግሮታል ፡፡
ሌላው ሁነኛው እንዳለው ስለ ዕሪናው ቅዱስ ቄርሎስ እንዲህ ብሏል “ወለብዕለ ህላዌ መለኮት ንሕነ ንሬእዮ በልዕልና ስብሐቲሁ ዘውእቱ ላዕለ ኵሎሙ ፍጡራን ወአምጣነ ንዴተ ትስብእት ዘነሥአ ይትበሀል ከመ ውእቱ ተሰብሐ እምአብ፤ ወዝንቱ ዓዲ ይትሜሰል ዘተብህለ ከመ ውእቱ ነሥአ ስብሐተ ወመንግስተ ወሥልጠነ ላዕለ ኵሉ ነሢእሰ ይትበሀል በእንተ ዐቅመ ትስብእቱ ወንሕነ ነአምር ከመ ውእቱ እግዚአ ስብሐት በመለኮቱ ወይነብር ምስለ አብ ወአልቦቱ ሕጸጽ በምንትኒ እምልዕልና ስብሐተ ወላዲሁ ወኢእምነ ግብሩ ዘስንዕው በህላዌ መለኮቱ ዝ ውእተ አምሳል ወበተአምኖቱ ንከውን ዕሩያነ……. የባሕርየ መለኮትን ክብር ከፍጡራን ሁሉ በራቀ በልዑል ጌትነቱ እንዳለ እኛ እናውቀዋለን፤ የተዋሐደው ሥጋ ክብርን የሚሻ በመሆኑ መጠን ከአብ ክብርን ገንዘብ አደረገ ይባላል፤ ይህም ጌትነትን መንግሥትን በሁሉ ላይ ሥልጣንን እርሱ ገንዘብ እንዳደረገ የተነገረውን ይመስላል፤ ክብርን ገንዘብ አደረገ መባሉ ሰው ስለመሆኑ ይነገራል፤ በመለኮቱ የክብር ባለቤት እንደሆነ፤ ከአብ ጋርም እኩል ትክክል እንደሆነ ከአባቱ ልዑል ጌትነት፤ በባሕርየ መለኮቱም አንድ ከሚሆንበት ግብሩ በምንም በምን ሕጸጽ እንደሌለበት እናውቃለን፤ አምነን አንድ የምንሆንበት ትምህርት ይህ ነው፡፡ (ዳን. 7፣ 13-255፤ዮሐ. 12፣18፤17፣1፣-6)፡፡ (ሃአ ም. 79፣75) ፡፡ ይህንን እያየ እንደ ሁነኛው በጨለማ የሚጓዝ ካለ አምላከ
ምሕረት በቸርነትህ ጎብኘው ከማለት ውጭ ምንም አንልም ፡፡ ሞቱን የተረዳች እዝነ ልቡናቸው መቀባቱን መክበሩን መረዳት እንዴት ተሳናት
ወገኖቼ? እኔ እንጃ ልቡናቸው በክሕደት ልጓም የታሠረች ሁና ነው እንጅ በሰው ሰወኛው ስንረዳውስ በእውነት ከበረ ከመባሉስ የሁሉ
ባለቤት አምላክ ሞተ መባሉ የከፋ ነበር ፡፡ ዳሩ ግን መዋቲ ሥጋን በመዋሐዱ ሞተ ተብሎ ቢነገር ከክብሩ እንዳላነሰ ሁሉ ተቀብዐ
በመንፈስ ከመ ካናት ሐዲስ ተብሎ ቢነገር ስለሰውነቱ ተቀባዒ ሥጋን ተዋሕዶ በግብር አንድ ስለሆነ በግብር የተዋሐደ በመሆኑ እነሆ
“ተቀብዐ በሥጋሁ” ተብሎ ተነገረለት ፡፡ እነ ሁነኛው ተሾመ ግን ተዋሕዶውን ግማሹን እያመኑ ግማሹን ስለሚክዱት መቼም የተቀብዐን
እና የተሰብአን ምሥጢር የሚረዱት አይመስሉም ፡፡
አካላዊ ቃል እግዚአብሔር ወልድ ከድንግል የተከፈለን ሥጋ በብቻ አካሉ የባሕርይ ተዋሕዶ
ሲዋሐደው አብንና መንፈስ ቅዱስን በጥንት ስማቸው ለማስጠራት፤ በጥንት ግብራቸው ለማጽናት አብ ሕይወቱ በሆነ በመንፈስ ቅዱስ(በመንፈስ
ቅዱስ ቅብዓትነት) በድንግል ማሕፀን አካል ዘእምአካል ባሕርይ ዘእምባሕርይ ወለደው ፤ ከድንግል የተከፈለን ሥጋ ቃል በብቻ አካሉ
የባሕርይ ተዋሕዶ ሲዋሐደው አብ በራሱ በብቻ አካሉ የባሕርይ ልደት ወለደው፤ መንፈስ ቅዱስም በራሱ በብቻ አካሉ የባሕርይ ሕይወት
ሆነው ፡፡ በመሆኑም አምላክ ወልደ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ከዊነ ትስብእት ሞተ በሥጋ እንደተባለለት ሁሉ ጥንተ ሕይወቱ መንፈስ
ቅዱስን ስለከዊነ ትስብእት በአካሉ ተቀብሎ የባሕርይ ክብር ከብሮበታል፡፡ ክርስቶስም ተብሎበታል ፤ እሱ ክርስቶስ ተብሎም አልቀረም
እኛም በጸጋ በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ ከብረን ክርስቲያን ፣ ክርስቶሳውያን ፣ ቅቡዓን ፣ መሢሐዉያን ተብለንበታል (መ.ምሥጢር
20 ቁ 49ን ተመልከት)፡፡
ዛቲ ሃይማኖት መሢሐዊት ዘትትአመን
ባቲ ቤተክርስቲያን ቅድስት
ስብሐት ለአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ
ስብሐት ለእግዝእትነ ማርያም ድንግል
ወላዲተ አምላክ
ስብሐት ለመስቀለ ክርስቶስ እጸ-መድኃኒት
ኃይልነ ወጸወንነ
ይቆየን
ይቀጥላል
No comments:
Post a Comment