Monday, September 23, 2019

ክፍል 3

ቀመር
ቀመር ማለት ማስላት ፣ መቁጠር ማውጣት ማለት ነው ፡፡ ቀመርም ጥንታትን መሠረት ያደረገ ነው ፡፡ ጥንት ማለትም ለዘመን መቆጠር መሠረት የሆነ ማለት ነው ወይም መነሻ መጀመሪያ ማለት ነው ፡፡ እነዚህም ሦስት ናቸው ፡፡ ምን ምን ቢሉ ፤ አንድ ዓለም የተፈጠረችበትን ቀን ዕለት እሑድ ሲሆን ፤ ይኸውም ጥንተ ዕለት ይባላል ፡፡ አንድም አትክልት ዕፅዋት ተፈጥረው ዕድሜ የተቆጠረላቸውን ቀን ዕለት ሠሉስ ሲሆን ፤ ይኸውም ጥንተ ቀመር ይባላል ፡፡ አንድም ፀሐይ ፣ ጨረቃ ከዋክብት የተፈጠሩበት ዕድሜም መቆጠር የተጀመረባቸውን ቀን ዕለት ረቡዕ ሲሆን ፤ ይኸውም ጥንት ዖን ይባላል ፡፡ ዖን ማለት ብርሃን ማለት ነው ፡፡ በዚህ መሠረት መታሰቢያ ቀመርን ለመስፈረያ ወይም ለመቁጠሪያ የሚያገለግሉት ሰባት(፯) ናቸው ፡፡ ከምን አገኘነው ቢሉ ፤ አቡሻሕር “ወሤሞ በመካነ ቀዳማይ ዕለታት ዓመት ወርኃዊት ፤ ወበመካነ ዕለተ ኍልቊ ኬክሮስ ፤ ወበመካነ ኬክሮስ ኍልቊ ካልዒት ፤ ወበመካነ ካልዒት ኍልቊ ሣልሲት ፤ ወበመካነ ሣልሲት ኍልቊ ራብዒት ፤ ወበመካነ ራብዒት ኍልቊ ኃምሲት ፤ ወበመካነ ኃምሲት ኍልቊ ሳድሲት ብሎዋልና ፤ ይኸን መሠረት አድርገን ቀመርን የምንሰፍርባቸው 7 ናቸው ፡፡ 

ስለሆነም የእነዚህ መሥፈሪያ ግንኙነት እንደሚከተለው ነው፡- 
፩ ቀን ………………………………………፷ ኬክሮስ……..፲፪ ሰዓት
፩ ኬክሮስ …………………………………..፷ ካልዒት
፩ ካልዒት ………………………………….፷ ሣልሲት
፩ ሣልሲት …………………………………፷ ራብዒት
፩ ራብዒት …………………………………፷ ኃምሲት
፩ኃምሲት…………………………….………፷ሳድሲት
ከላይ ባየናቸው የጊዜ መሥፈሪያዎች የፀሐይንና የጨረቃን ዓመታዊ ጉዞ ብዛት በቁጥር ስንገልጸው እንደሚከተለው ነው ፤ የፀሐይ አንድ ቀን ጉዞ ፲፪ ሰዓት ከ፶፪ ካልዒት ከ፴፩ ሣልሲት ሲሆን ፤ የጨረቃ ደግሞ 59 ኬክሮስ 3 ካልዒት 40ሣልሲት 16 ራብዒት 18 ኃምሲት 48 ሳድሲት ነው ፡፡ ዓመት የምንለውም ፀሐይና ጨረቃ ፲፪ቱን መስኮት በ፴ በ፴ ቀን ውለው ዳግመኛ የሚጀምሩበትን ጊዜ ነው ፡፡ ስሌቱም አባቶች ባቆዩልን መሠረት ትርፉን ብቻ በመያዝ የሚያሰሉበትን በጥንተ ስሌትና (በአብነት ቤተ ጉባኤ ልሳን) በዘመናዊ (አስከኳላ) የአሰላል ስሌት ስናየው የሚከተለው ነው ፡፡
በጥንተ ስሌት በዘመናዊ ወይም አስከኳላ ስሌት
መሰብሰብ ………………………………..ማባዛት
መግደፍ …………………………………ማካፈል”
መግጠም ………………………………..መደመር
መንሳት …………………………………መቀነስ
አሐቲ አእትት ………………………….አንድ ለዘመን ቀንስ
የአሰላል ትንታኔውን እንዲህ ከገለጽን ከላይ የጀመርነውን የፀሐይን ዓመታዊ ጉዞ እናሰላለን ፡፡ ይኸውም በወር በዓመት እየመደብን የዓመቱን የዕለት ብዛት በቀን በኬክሮስ በካልዒት በሣልሲት መድበን ማወቅ እንችላለን ፤
ሀ. የቀኑ መደብ ……………………፲፪ ሰዓት
በወር ……………………….፲፪ x ፴ = ፫፻፷ ሰዓት =፴ ቀን
በዓመት….. …………………፴ x ፲፪ = ፫፻፷ ቀን ይሆናል
ለ. የካልዒት መደብ ……………….፶፪ ካልዒት
በወር ………………………..፶፪ x ፴ = ፲፻፭፻፷ ካልዒት
በዓመት ……………………..፲፻፭፻፷x፲፪ = ፻፻፹፻፯፻፳ ካልዒት
በኬክሮስ ስንገድፈው ………..፻፻፹፻፯፻፳/፷ = ፫፻፲፪ ኬክሮስ
በሰዓት ስንገድፈው …………..፷ ሰዓት ከ፪ ኬክሮስ ይሆናል
ሐ. የሣልሲት መደብ ………………፴፩ ሣልሲት
በወር ………………………..፴፩ x ፴ =፱፻፴ ሣልሲት
በ፲፪ ወር ……………………፱፻፴ x ፲፪= ፻፻፲፻፷ ሣልሲት
በካልዒት ሲወሰድ …………..፻፹፮ ካልዒት
በኬክሮስ ሲወሰድ …………...፫ ኬክሮስ ከ፮ ካልዒት ይሆናል
በአንድ ላይ ጠቅለን ስንደምረው ወይም ስንገጥመው ፫፻፷ ቀን ሲገጠም ፷ ሰዓት ከ፪ ኬክሮስ ሲገጠም ፫ ኬክሮስ ከ፮ ካልዒት በድምሩ ፫፻፷፭ ቀን ከ፫ ሰዓት ከ፮ ካልዒት ይሆናል ፡፡ ስለዚህ ፫፻፷ውን ቀን በ፲፪ ወር መድበን ቀሪውን ፭ ጳጉሜ እንላለን ፡፡ ምክንያቱም ጳጉሜ ማለት የወሮች ጥርቅም ስብስብ ማለት ነውና ፡፡ “ወትቤሎ እግዝእትነ ለናዖድ ንጉሠ ኢትዮጵያ ዛቲ ወርኃ ጳጕሚት ዘተረክበት ትሩፈ እምአርባዕቱ አዝማናት ወእምዐሠርቱ ወክልኤቱ አውራኅ ተኃብር ፤ ወበእንተዝ ተሰምየት ጳጕሚት ወዛቲ ዘመን ዘመነ ምጽኣት ይእቲ” እንዲል ፤ በዚህም ምክንያት የጳጉሜ የቀን ብዛት ፭ ቀን ከ፫ ሰዓት ከ፮ ካልዒት ናት ፤ ፫ ሰዓቱም መጠነ ራብዒት ማለት ነው ፡፡ ፭ ቀን በየዓመቱ የጳጕሜ መጠን ነው ፡፡ ፫ ሰዓት ከ፮ ካልዒት በ፬ ዓመት ፲፪ ሰዓት ከ፳፬ ካልዒት ይሆናል ፡፡ ስለዚህም ጳጉሜ ከዐራት ዓመት አንዴ ስድስት ትሆናለች ማለት ለዚህ ነው ፡፡ በዚህም ከአንድ ዓመት ወደ አንዱ ዓመት በመሸጋገር አንዱ ወንጌላዊ ከሌላው ጋር አብሮ የሚውልበት ቀን በመሆኑ መጠነ ራብዒት ይባላል ፡፡ ትርጉምም ከዐራቱ ወንጌላውያን የተጠራቀመ ማለት ነው ፡፡የቀረችውንም የካልዒት መጠን ስንቀምራት እንደሚከተለው ነው -
፳፬ ካልዒት በ፬ ዓመት
፷ ካልዒት = ፩ ኬክሮስ በ፲ ዓመት
፮፻ ካልዒት = ፲ ኬክሮስ በ፻ ዓመት
፫፻፷ ካልዒት = ፷ ኬክሮስ = ፲፪ ሰዓት = 1 ቀን በ፮፻ ዓመት
ስለዚህ ፮ ካልዒት በ፮፻ ዓመት ስንሰበስበው ዓመቱ የመጠነ ራብዒት መደብ ስለሆነ ጳጕሜ ፯ ትሆናለች ፡፡ ጳጕሜ 7 በምትሆንበት ጊዜ ሰሌዳው በፀሐይ ሰሌዳ እኩልና ባሕርዩም ጽሉም የሆነ አቅድ የሚባል ኮከብ በየ 600 ዓመት መጥቶ ፀሐይን ሙሉ ብርሃኗን እንዳትሰጥ ይጋርዳታል ፡፡
መዓልቱም ሌሊቱም ጨለማ በመሆኑም የመከራ ፊታውራሪ ፣ አጫፋሪ ይባላል ፡፡ ስለዚህ የጳጉሜ የቀን መጠን ፭ ፣ ፮ና ፯ መሆን ትችላለች ፡፡
በዚህም የተነሳ ወንጌላውያን የሚቀጥለውን ተውሳክ እንዳይነኩ ጳጉሜ ፮ና ፯ ስትሆን በመጠነ ራብዒት ተካፍለው የሚውሉ ናቸው እንጅ ፤ አጽዋማትን ወይም በዓላትን አያፋልሱም ፡፡ ይኸውም ይታወቅ ዘንድ ልደተ አበቅቴ ከነሐሴ 8 በታች አይወርድም ፤ ከጨረቃ መመላለሻ አልፎ በሕፀፅ ልክ ይሆናልና ፤ አንድም ከጳጕሜ 5 በላይ አይወጣም ፤ ለምን ቢሉ ኃምስቱ ቀኖች የአንድ ወንጌላዊ የትርፍ ጥርቅሞች ናቸውና ፤ አንድም ፮ኛና ፯ኛ የጳጉሜ ቀኖች የ4ቱ ወንጌላውያን ስብስብ ናቸውና ፡፡
የፀሐይ ወርኃዊ ጉዞ በአንዱ መስኮት ፴ ቀን ሲውል ፤ ጨረቃ ግን በአንድ መስኮት አንዴ ፴ አንዴ ፳፱ ስለሚውል ከ፲፪ቱ ወር ፮ ቀን የጨረቃ ትርፍ ቀኖች እናገኛለን ፡፡ ይህም የጨረቃ ሕፀፅ ወይም ጉድለት ይባላል ፡፡ የጳጕሜም የቀን ብዛት ከሕፀፅ ጋር ተደምሮ የሚሰጠው የቀን ብዛት ፲፩ ቀን ሲሆን የጨረቃ የሁለት ወር ሕፀፅም አንድ ነው ፡፡ ያነሰውን ትቶ የበዛውን ይዞ መናገር የመጽሐፍ ልማዱ ነውና የፀሐይ ዓመታዊ ዕድሜ ከጨረቃ ዓመታዊ ዕድሜ የሚበልጥበት የቀን መጠን ፲፩ ነው ፡፡ ለምን ቢሉ ፤ ጨረቃ ከፀሐይ አንፃር የምታጎድለው የቀን ብዛት በዓመት ፲ ቀን ከ፶፫ ኬክሮስ ከ፬ ካልዒት ከ፳፪ ሣልሲት ከ፯ ራብዒት ከ፲፪ ኀምሲት በመሆኑ ነው ፡፡ መጽሐፍም የአነሰውን ትቶ የበለጠውን ይዞ መናገር ባሕሉ ነውና ፤ ፶፫ ኬክሮስ ወደ አንድ ዕለት አስተጠግተን የቀን መጠኑ ፲፩ ነው እንላለን ፡፡ ይህም ትርፍ ቀን ዐበቅቴ (ከዘመን የተረፈ) ያባላል ፡፡ “ተጸውረ በከርሣ ተሰዓተ አውርኅ (ለ፱ ወር በድንግል ማኅፀን ኀደረ”) እንዳለ ቅዱስ ኤፍሬም (ውዳሴ ማር ዘረቡዕ ) የሚለውን ብንመለከት ጌታ በማኅፀነ ማርያም የቆየው 9 ወር ከ5 ቀን ሲሆን 9 ብሎ የበዛውን ይዞ መጽሐፍ እንደተናገረ ፡፡
የመጀመሪያው የፀሐይ ዓመታዊ ጉዞ አልቆ ሁለተኛውን ዐውደ አበቅቴ ለመሙላት የሚያስፈልግ የቀን መጠን መጥቅዕ ይባላል ፡፡ መጥቅዕም ማለት ሰብሳቢ ነጋሪት ማለት ነው ፡፡ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትርጉሙም መጥቅዕ ማለት
1. ደወል መቀስቀሻ ይባላል ፤ የተጀመረውም በኖህ ዘመን ነው (ዘፍ ምዕ ፮ ቊ ፳-፳፩) ፤
2. የእስራኤላውያን የበዓል ስም ነው (ዘሌ ምዕ ፳፫ ቊ ፳፫-፳፭ ፤ ዘኁል ምዕ ፳፱ ቊ ፩-፮) ፤
3. መለከት ማለት ነው (ዘኁል ምዕ ፲ ቊ ፩-፲) ፤
ሌላው መሠረታዊ የባሕረ ሐሳብ ዓዋጅ የመጥቅዕና የአበቅቴ ድምር ፴ ወይም የአንድ ወር መጠን መሆኑ ነው ፡፡ ይህ ድምር አጽዋማት የሚውልበትን ወርኅ የሚገልጽ ሲሆን ፤ የሚውለውም በመስከረም ወይም በጥቅምት ነው ፡፡ ይኸውም ከ፪ እስከ ፲፫ ቀን ሲሆን የሚውለው በጥቅምት ነው ፡፡ ከ፲፭ እስከ ፴ ቀን ሲሆን ደግሞ የሚውለው በመስከረም ነው ነገር ግን ፩ም ሆነ ፲፬ መሆን አይችልም ፡፡ ለምን ብንል አንድም ልደተ አበቅቴ ከነሐሴ ፰ የማይወርድ ከጳጕሜ ፭ የማይወጣ በመሆኑ ነው ፤ አንድም በ፳፰ ቀን ከላይ ከታች የሚመላለስ በመሆኑ ነው ፡፡ አንድም አበቅቴ ፳፱ መሆን ስለማይችል ነው ፡፡ ለምን ቢሉ ፤ ይኸስ ፈራሽ ነው እንላለን ፡፡ ለምን ፈራሽ እንላለን ቢሉ ፤ ከመመላለሻው ተላልፎ በሕፀፅ መጠን ሞልቶ በመገኘቱ ለሚወጣው ልደተ አበቅቴ መሠረት ሳይሆን አልቦ አበቅቴ ስለሚሆን ነው መጥቅዕ የዘመነ ብሉይ በዓላት ነውና የምንማረው ሐዋርያት ከአይሁድ ጋር በደም በሥርዓት በበዓል አትገናኙ ብለዋልና ለምንድር ነው ቢሉ ፤ እኛስ የምንማረው አንድም እኛ የአባቶቻችን ልጆች ነንና ከእነርሱ ላለመለየት ፤ አንድም ኦሪት ለወንጌል አምሳል መርገፍ እንደመሆንዋ መጠን ፤ የዘመነ ብሉይ አጽዋማት ለዘመነ ሐዲስ አጽዋማት መሠረት ናቸውና እንመራባቸዋለን ብለን ነው ፡፡

No comments:

Post a Comment