Monday, September 23, 2019

ክፍል 1

ክፍል 1
ባሕረ ሐሳብ
ባሕረ ሐሳብ ማለት ቁጥር ያለው ዘመን ማለት ነው ፡፡ እንዴት ቢሉ ፤ ባሕር ዘመን ፣ የተቆጠረ ተብሎ ይተረጎማልና ፤ ይህስ ከምን እናገኘዋለን ቢሉ ፤ ዕዝራ ሱቱኤል ተናግሮታል ፡፡ ይኸውም “ይህ ዓለም በሚዛን ተመዝኗልና ፤ ባሕሩንም በመስፈሪያ ሰፍሮታልና ፤ የተሰጠውንም መስፈርት እስኪፈፀም ድረስ ዝም ይላል ፤ አይነቃምም (ምዕ 2 ቊ "7)” በማለት ባሕር የተቆጠረ ፤ ዓለምም የተመዘነች ፤ የተለካች መሆንዋን እግዚአብሔር በነቢያት አድሮ ገልፆልናል ፡፡
ባሕርን በመስፈሪያ ቆጥሮታል ካልን መስፈሪያውንስ ለማን ገለጸው ቢሉ ፤ መቁጠሪያ ዘመንንስ በሱባኤ ፣ በኢዮቤልዩ እንዲቆጥር ለአዳም (ሱባኤ አዳም) ፤ መስፈሪያንም ለሄኖክ ሰጥቶታል ፡፡ ሐሳብስ ማን ቁጥር አለው ቢሉ ፤ ቅዱስ ዳዊት ነው ፡፡ ምን አለው ቢሉ ፤ “ብፁዓን እለ ተኀድገ ሎሙ ኃጢአቶሙ ፤ ወእለ ኢሐሰበ ሎሙ ኵሎ ጌጋዮሙ ፤ ብፁዕ ብእሲ ዘኢኈለቈ ሎቱ እግዚአብሔር ኃጥአቱ (ኀጥአታቸው ይቅር የተባለላቸው ብፁዓን ናቸው ፤ በደላቸውንም ኹሉ ያልቆጠረባቸው ፤ እግዚአብሔርም ኃጢአቱን ያልቆጠረበት ሰው ብፁዕ ነው” እንዳለ (መዝ " ቊ -2) ፡፡ ስለዚህም ባሕር ሐሳብ ማለት ቀድሞ የነበረ ፣ አሁንም ያለ ፣ ለወደፊትም የሚኖር ዘለዓለማዊ እግዚአብሔር በዚች ባለንባት ዓለም ሌሊቱንና ቀኑን እያፈራረቀ የሚመግብ እግዚአብሔር መሆኑን በቁጥር ፣ በስፍር መዝኖ የሚያስረዳ ማለት ነው ፡፡
ባሕር ሐሳብ በስንት መንገድ እናየዋለን እንተ
ረጉመዋለን ቢሉ ፤ በሦስት መደብ እናየዋለን ምን ምን ብለን ቢሉ-
. መርሀ ዕውር (የዕውር መምሪያ) ማለት አላዋቂዎችን መርቶ ወደ ዕውቀት ደረጃ የሚያደርስ ፤ በውስጡም የአጽዋማትንና የበዓላትን አወጣጥ መንገድ የሚያወጣበትን ሥርዓት ፣ የሰንበታትን ፣ የሱባኤያትንም አወጣጥ አጠቃሎ የያዘ ማለት ነው ፡፡
2. ሐሳበ አቡሻህር ማለት የፀሐይን ፣ የጨረቃንና የከዋክብትን የሥነ-ፈለክም ነገር የሚናገር ቀመረ ትሩፋትን ፣ ቀመረ ዐረብን (የጨረቃ አቆጣጠርን) የያዘ ማለት ነው ፡፡ ቀመረ ዐረብ ስንል ግን ዐረቦች በጨረቃ የሚቆጥሩ ናቸው ለማለት እንጅ ፤ ዘመንስ መቆጠር የጀመረው አዳም በቃል ኪዳኑ ዘመን ጀምሮ ነው ፡፡
3. ሐሳበ ፈለክ ማለት የፀሐይ ፣ የጨረቃና የከዋክብትን መመላለስ ወይም አዘዋወርን ስለ፲፪ቱ ነፋሳት (ሄኖክ ፳፭) የሚናገር ፣ የሚያስረዳ ማለት ነው ፡፡ ነገር ግን እነዚህን አንድ በአንድ ልማር ቢሉ ፤ በቤተ ጉባኤ ከሦስትና ከዐራት ዓመት በላይ ይፈጃልና ለመግቢያ ያህል ከብዙው፣ በጥቂቱ ፣ ከረጅሙ በአጭሩ መርሀ እውርን እንደሚከተለው እንገልጻለን ፡፡
ክፍል 2
መርሀ ዕውር
የዘመን መቆጠር የተጀመረው ራሱ ባለቤቱ ልዑለ እግዚአብሔር በአርያውና በአምሳሉ ያሞገሰው ሰው ፤ የተሰጠውን ሕግ ትዕዛዝ በመጣሱ ፤ የተሰጠውንም ክብር ተነፍጎ ፤ ብሎም በዲያብሎስ የደረሰበትን መከራና ሥቃይ እግዚአብሔር አይቶ ፤ ያቀረበውንም መሥዋዕቱን ተመልክቶ ፤ ቃል ኪዳን ለአዳም ከተሰጠው በኋላ ነው ፡፡ በዚህም ቃል ኪዳን መሠረት የአዳም ልጆች እኩሉ በጨረቃ ፤ እኩሉ በፀሐይ ፤ እኩሉ ደግሞ በከዋከብት መቁጠር ጀመሩ ፡፡ የሚቆጠረውም በግዕዝ ቋንቋ የፀሐይ አቆጣጠር ፣ በእብራይስጥ ቋንቋ ደግሞ የጨረቃ አቆጣጠር በሌሎችም ቋንቋዎች በተመሳሳይ መንገድ መቁጠር ጀመሩ ፡፡ ነገረ ግን በዚህ ላይ የምናየው የፀሐይን አቆጣጠርን ለይተን በጥቂት በማቅረብ ሲሆን በስፋት በመጽሐፍ አቡሻህር መመልከት ይቻላል ፡፡ ባሕረ ሐሳብ ቁጥር ያለው ዘመን ማለት ሲሆን የቁጥር ዘመኑም ቋሚና ተንቀሳቃሽ ብለን እንከፍለዋለን ፡፡ ምንን መሠረት አድረገን ከፈልነው ቢሉ ፤ መሠረት ያደረግነውስ ተውሳክን ነው ፡፡ ተውሳክ ማለትም ጭማሪ ፣ ድማሪ ማለት ነው ፡፡ አንድም ተደምሮ ከተወሰነለት ሕግ ወዲያ ወዲህ የሚያደርግ ማለት ነው ፡፡ በዚህም ምክንያት በዓላትን ስናወጣ ቋሚና (ተውሳክ የሌላቸው) ተንቀሳቃሽ (ተውሳክ ያላቸው) በማለት ከፈልነው የምንለው ለዚህ ነው ፡፡ አቆጣጠሩም እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ቃል ኪዳን የሰጠበትን ፤ ድንቅ ተአምር ያደረገበትን ፤ ሱባኤ የተቆጠረለትን ነውና ፤ ጌታችን ለአባቶቻችን በገለጸላቸው መሠረት አስረድተውናል ፡፡
ቋሚ መታሰቢያ የምንለው ሱባኤያትን (አጽዋማትን) ስንቆጥር ተውሳክ ሳይኖራቸው ተውሳኩ አልቦ(ባዶ) ሆኖ ተቆጥሮ ከቦታቸው (ከሚውሉበት ቀን) ወዲህ ወዲያ የማይሉ (የማይወጡ የማይወርዱ) ናቸው ፡፡ ስለምን ጥንተ ዕለታቸው እየተለያየ በቋሚ ቀን ይውላሉ ቢሉ ፤ ይኸስ እንኳን የቀናት ቁጥር መለዋወጥ ይቅርና ፣ የፀሐይ ርዝማኔ እንኳን ከወር ወር ይለያያል ይህም በመሆኑ የመጣው ልዩነት በሱባኤ ተቆጥሮ ፤ ከአንድ ወር ወደ አንድ ወር በሚተርፈው አጽፍህ አውራኅ ይነገራል እንጅ ፤ ወሩ በገባበት ቀን አይቀያየርም ከአጽዋማት ውስጥ እንደ ጾመ ነቢያት ፤ ጾመ ገሀድ ፤ ጾመ ፍልሰታ ፣ እንዲሁም ከጌታ ዐበይት በዓላት መካከል እንደ ፅንሰተ ክርስቶስ ፤ ልደተ ክርስቶስ ፣ ጥምቀተ ክርስቶስ ፣ በዓለ ስምዖን ያሉ በዓላት ጥንተ ቀናቸውን ሳይለቁ በዓመት በዓመት ይከበራሉ “አድኀነ ነፍሳቲነ በምጽአቱ ቅዱስ (በልዩ አመጣጡ መጥቶ አዳነን)” እንዳለ ቅዱስ ኤፍሬም (ውዳሴ ማርያም ዘረቡዕ) ፡፡ ልዑል አምላክ እግዚአብሔር በጽኑዕ ቀጠሮው ፶፻፭፻ ዘመን ሲፈጸም ከድንግል ተወለደ ፤ አንዲትንም ካልዒት እንኳ አላሳለፋትም በማለት በዓለ ልደቱ የማይወጣ የማይወርድ ቋሚ መሆኑን ገልጾልናል ፡፡
ተንቀሳቃሽ በዓላት ማለት ደግሞ በዐውድ አማካኝነት የሚገኙ ሲሆኑ የሚውሉበትን ቀን የሚለዋውጡ ከላይም ከታችም የሚዞሩበትን የቀን ርዝማኔ ኹሉ የተወሰነላቸው ማለት ነው ፡፡ ዐውድ ማለት ዙሪያ ፣ ክበብ ፣ ዙሮ የሚመጣ ማለት ነው ፡፡ ዐዋድዓት ማለትም እየተዘዋወሩ የዓለምን ዕድሜ የሚሰፍሩ ማለት ሲሆን ፤ እነዚህም-
፩. ዐውደ ዕለት ማለት በሱባኤ ቀናት ከእሑድ እስከ ቅዳሜ የሚመላለስ በሰባቱ ቀናት የሚዘዋወር ማለት ነው ፡፡ ዕለት የምንለውም ሌሊቱንና መዓልቱን የያዘ ማለት ነው (ዘፍ ምዕ ፩ ቊ ፭) ፡፡ መዓልት ማለትም ፀሐይ እንድትሰለጥንበት የተሰጠችበት የብርሃን ጊዜ ነው ፡፡ ሌሊት ማለትም ጨረቃና ከዋከብት እንዲሰለጥኑበት የተሰጡበት የጨለማ ጊዜ ነው (ሄኖክ ፳፩) ፡፡
፪. ዐውደ ወርኅ ማለት ዐውደ ዕለት ተመላልሰው ፬ ሱባኤ መልተው ሥላሴ ዓለምን የፈጠሩበትን ቀን ዕለተ ጠቢባንን ጨምሮ የሚገኘው ቀን ማለት ነው ፡፡ ዕለተ ጠቢባን የሚባሉትም እሑድና ሰኞ ሲሆኑ በየወሩም ሁለት ሁለት ቀኖች አሉ ፡፡ ከእነዚህም የአንዱ ወራት ለሚቀጥለው ወር ተጨምሮ ስለሚቆጠር አጽፈኅ ወርኅ በመባል የሚታወቅ ነው ፡፡
፫. ዐውደ ዓመት ማለት አውራኅ በ፲፪ቱ መስኮቶች አምሳል ፴ ፣ ፴ ቀን ዙረው ዳግመኛ ሲጀምሩ ዐውደ ዓመት ይባላል (ሄኖክ ፳፩) ፡፡
፬. ዓውደ አበቅቴ ማለት በ፲፱ ዓመት የሚመላለስ የሚዘዋወር ማለት ነው ፡፡ አበቅቴ ማለት ቃሉ የግሪክ ቃል ሲሆን ትርጉሙም የጨረቃ ዓመታዊ ዕድሜ ከፀሐይ ዓመታዊ ዕድሜ የሚያንስበት ማለት ነው ፡፡ አንድም የዘመን ቁጥር ትርፍ ማለት ነው ፡፡ ልደተ አበቅቴ ማለት ደግሞ ፀሐይና ጨረቃ ዓመታዊ ዙረትን እኩል የሚጀምሩበት ቀን ማለት ነው ፡፡ አልቦ አበቅቴ ማለትም አበቅቴ የሌለበት ዘመን ማለት ነው ፡፡ ንዑስ ቀመርም ይባላል ፡፡
፭. ዐውደ ማኅተም ማለት አበቅቴን በ፬ ስንሰበስበው የምናገኘው ቁጥር ማለት ነው ፡፡ ይኸውም ፸፮ ዓመት ማለት ነው ፡፡ ማዕከላዊ ቀመርም ይባላል ፡፡
፮. ዓውደ ቀመር ማለት ማዕከላዊ ቀመርን በሱባኤ ስንሰበስበው ማለት ነው ይኸውም ፭፻፴፪ ዓመት ማለት ነው ፡፡ ዓቢይ ቀመርም ይባላል ፡፡
፯. ዓውደ ፀሐይ ማለት ሱባኤን በ፬ት ስንሰበስበው ማለት ነው ፡፡ ይኸውም ፳፰ ዓመት ማለት ነው ፡፡

No comments:

Post a Comment