Thursday, February 28, 2019

ውሉደ ይሁዳ (ክፍል አንድ)

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

ይድረስ  ለ “ሊቀ ሊቃውንት”  ሰሎሞን ዳዊት
===========================================
በ21ኛው መቶ ክፍለዘመን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን በምሥራቃዊት ጎጃም ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ሥር (መቀመጫውን ደብረ ማርቆስ ባደረገው) የዐራቱ ጉባዔ መምህር ተብለው የሚጠሩት መሪጌታ ሰሎሞን ዳዊት "ቅባትን በእሳት" የምትል ርእስ ያላት በዋጋዋ ክርስቶስን እንደሸጠ እንደይሁዳ መንፈስ ቅዱስን በ30 ብር የምትሸጥ መጽሐፍ ጽፈዋል ፡፡ እጅጉን የሚደንቀው ደግሞ ግሱንም ይሆን ከግሱ የሚወጣውን ሳቢ ዘር የማይለዩ ጨዋ ሰው ሁነው ሳገኛቸው ፤ ስማቸውና ማንነታቸው የማይገናኙ መሆናቸው የበለጠ ግልጽ ይሆናል ፡፡ “እሱም ቅባትን በእሳት” የሚል ነው ፡፡

ይህች የጨዋ ንግግራቸው የተቀብዐን ረቂቅ ምሥጢር ከማናገር ይልቅ እጥፍ ድርብ ክሕደትን አጎናጽፋቸዋለች ፡፡ እነሆም እንደ ይሁዳ 30 ብሯን እየተቀበለች መንፈስ ቅዱስን የምትሸጥ የምትለውጥ በመሆኗ ፣ በመጽሐፏ ሆድ እቃ ውስጥ ያለውን ትምህርተ ንሥጥሮስ ገላልጦ ለማውጣት እና አምላኩን የካደ ይሁዳን የመሰለ ባለቤት ስላዘጋጇት ፣ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ እንዲሉ መጽሐፏንም ጸሐፊዋንም የሚገልጽ አንድ ስም በማስፈለጉ ወልደ ይሁዳ የሚል ርዕሰ አንቀጽ ሰጥቻታለሁ ፡፡ ለሀሳብ ለትችት ፣ ለእውቀት ለውይይት ያግዘን ዘንድ ከሰውየው መጽሐፍ የተነገሩ አንጋረ ንሥጡር ወይም ይትበሃሎችን እያነሳሁ ኦርቶዶክሳዊውን ምላሽ ከእኔ አንደበት ሳይሆን ከኦርቶዶክሳውያን አበው አንደበት ከቅዱስ መጽሐፍ አስቀምጣለሁ ፡፡ በመሆኑም ልፌትና ስድብ የሚቀናችሁ ልቡናችሁ ያጠረ ምላሳሁ የረዘመ ክልኤ ጥሙቃን ሁላችሁም በሀሳብ በመጽሐፍ እንሞጋገት እንነጋገር ፤ ከዚያ ውጭ ስድብና ለፈፋ የሚጽፍ ካለ ስድቡን እና ተንኮሉን ወዲያውኑ አጠፋዋለሁ፡፡

ወደመጽሐፉ ከመግባቴ በፊት ሰውየው “ቅባት” ያሉት ቃል “ቅብዐት” ወይም “ቅብዓት” የሚል መንገድ እንጅ “ቅባት” የሚል መንገድ ስለሌለው ፤ በመጀመሪያ ራሳቸውን አስተካክለው በገቡ ይሻል ነበር ፡፡ ለነገሩ “አምልኮ ከርሥ” ይህችን ይህችን ሳይሆን ክሕደት ክሕደቱን ብቻ ነው የሚያሳያቸውና ያሻሽሉታል ብለን አናምንም ፡፡ እነሆም “ቅብዐት”  የሚለው ቃል ትርጉሙ ለእሳቸው እንግዳ እንደማይሆን አምናለሁ ፡፡ ከመጽሐፋቸው የይዘት ሀሳብ ስንረዳው ግን  ለመግለጽ የፈለጉት ቅባትን በእሳት” ማለታቸው በተለምዶ በሚናገሩት የአለአዋቂነት ንግግራቸው  “ቅብዐቶች” የምንባል እኛ ሰዎችንእሳት ይብላቸው ፣ ከእሳት እንጨምራቸውበማለት ከአባታቸው ከነ በዝብዝ ካሳ እና ከዳግማይ ግራኝ የወረሱትን የአራዊትነት ሥራቸውን ለመግለጽ ያሰቡ ይመስላል ፡፡ በጽሁፋቸው የገለጹበት መንገድ ደግሞ ከላም ወተት የሚገኘውን  ቅቤውን ፣ ከአምራች ድርጅቶች የሚገኘውን ዘይቱን በሚጠሩበት ስም ሲጠሩ ስመለከት በእውነቱ ሊቅነታቸው ከማጀት እስከ ወለል ብቻ እንደሆነ አረጋገጥኩ ፡፡ 

በእርግጥ ሰውየው የመሸምደድ አቅማቸው እሳት ናቸው ከምሥጢር ላይ ግን ያን ያህል ሊቅ ናቸው የሚያሰኝ አቅም አላገኘሁባቸውም ፤ አበበን ሲያገኙ አበበን ፣ ከበደን ሲያገኙ ከበደን የመምሰል እስትንፋሳቸው አየል የሚልባቸው ፣ ራሳቸው በመጽሐፋቸው እንደገለጹት በቁመታቸው ስንዝሮ ከሚባሉት የሚመደቡ ሰው ናቸው ፡፡ ከመጽሐፋቸው እንደተረዳሁትም ቁመታቸው ብቻ ሳይሆን ልቡናቸውና እውቀታቸውም እንደ ቁመታቸው እንደዚያ ሳይሆን አልቀረም ፡፡ ዞሮ ዞሮ በጨዋ ንግግራቸው “ቅብዐትን በእሳት” ብለው በተናገሯት ልሳናቸው ሳያውቁት መንፈስ ቅዱስ ፊታቸውን ጸፍቶ አፋቸውን ከፍቶ እንዳናገራቸው ልብ ይሏል ፡፡ እንደምን ቢሉ በመጽሐፋቸው ከገጽ 28 ላይ “ እግዚአብሔር እሳት ይባላል ፣ የእግዚአብሔር ቃል እሳት ፡ ይባላል ፤ ገጽ 29 ላይ “ተዋሕዶ ሃይማኖታችን” እሳት ትባላለች በእሳት ትመሰላለች” ብለው ጽፈዋል ፤ “ተዋሕዶ ሃይማኖታችን” ያሏት ቃል መጽሐፍ ቅዱሳዊ ስላይደለች በሚቀጥለው ክፍል በሰፊው እመለስበታለሁ ፡፡ ምክንያቱም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ተዋሕዶ ሃይማኖታችን”  ብሎ ያስተማረ አንድም ሊቅ የለንምና ፡፡

ወደቀደመ ነገራችን እንመለስና በእሳት በተመሰለው በእግዚአብሔርና ፣ በቃለ እግዚአብሔር ዓይነ ልቡናን ከፍተው ቢመለከቱት ይህ ቅብዐት ጣዕመ ምሥጢሩ መንፈስ ቅዱስ እንደሆነ ያሥረዳል ያሳውቃልም (መጽሐፈ አክሲማሮስ ዘእሑድ 4፡ እና ዘሠሉስ 2፡18ን ተመልከት ) ፤ አንድም  በጨዋነታቸው ያልተረዱት ቁም ነገር ቢኖር ፤ ቅብዐት ሥጋዊውን ባለሙያዋ ሴት በእሳት አቅልጣ አንጥራ ለምግብነት እንድታውል ሁሉ ፤ እሳት በተሰኘ ቃለ እግዚአብሔር ቅብዐቱን ቢመረምሩት ጣዕመ ምሥጢሩን የሚያናግር ነውና ሳያውቁት አናገራቸው ማለታችን ለዚህ ነው ፡፡

በሌላ መልኩ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ መንፈስ ቅዱስን በእሳት ይመስለዋል “ንበሩ ኀበ ኢየሩሳሌም እስከ ትብሱ ኃይለ እምአርያም” እንዲል ፤ እንዲሁም መንፈስ ቅዱስን መጻሕፍት በክብርነቱ ቅብዕ ይለዋል (ሐዋ 10፡38) ፤ ታዲያ ሊቀ ሊቃውንት የሚሏቸው “ሰሎሞን ዳዊት” ሳያውቁት “ቅብዐትን በእሳት” ብለው ቢጽፉ ፣ ቢላፈፉ ፣ ልፌታቸው ይህ በቅብዐት የተመሰለው እሳት መንፈስ ቅዱስ ነውና “መንፈስ ቅዱስን በመንፈስ ቅዱስ” ወይም “እሳትን በእሳት” የሚያሰኝ ጸያፍ ቃል መናገራቸውን እንኳን አላስተዋሉትም ፡፡

እንዚሁም ሁሉ በአባቶቻችን ብሂል “ከእሳት ያልወጣ ታቦት ጣዖት” እንደተባለው ፤ እነሱ የሚያሳድዱት “ቅብዐት” ትርጓሜው መንፈስ ቅዱስ እንደሆነ ከቅዱስ ኢጲፋንዮስ መጽሐፈ አክሲማሮስ ላይ ይገኛልና ይህንን ቅብዐት በእሳት አቃጥላለሁ በማለት በ30 ብር ቢቸበችቡት ፤ በግብረ ሐዋርያት የተጠቀሰውን ሲሞን የተሰኘ ከሐዲን የሚያስመስላቸውና ፤ እንደ አባታቸው እንደ ንስጥሮስ መንፈስ ቅዱስ ሕጹፅ የሚሉ እንደሆኑ በደንብ ይነግራቸዋል ፡፡ በዚያውም ላይ በተለምዶ “ቅብዐቶች” እየተባሉ የሚጠሩ ሰዎች ከጥንት ጀምረው በቢለዋ በቆንጨራ ፣ በሰይፍ በገጀራ ፣ በእሳት እንደተቃጠሉ የታሪክ ድርሳናት የሚያስረዱ ናቸው ፡፡ እነሆም ሊቃውንቱ በነ በዝብዝ ካሳ(ዮሐንስ 4ኛ) እና በነዳግማይ ግራኝ(አጼ ቴዎድሮስ) ብሎም ስማቸው ብቻ ጳጳስ በሆነው በአባ ሠላማ ሦስተኛ ቅቡዐን ሊቃውንትን በእሳት አቃጥለዋቸዋል ፡፡ 

በተለይ ደብረ ታቦር ላይ ከ700 በላይ የሆኑ ሊቃውንት በቴዎድሮስ ትእዛዝ በእሳት እንደተቃጠሉ ታሪክ አስረጅ ነው ፡፡ ይህ በእሳት መቃጠል ደግሞ ድሮ በነ ዲዮቅልጥያኖስ ዘመንም ሲደረግ የኖረ ነውና የአባቶቻቸውን ግብር በመጸሐፋቸው ጽፈው በማስቀመጣቸው ፤ በተለምዶ “ተዋሕዶዎች” የሚባሉ ሰዎች ሃይማኖታቸው ክርስትና ሳይሆን እርምና መሆኑን እንገነዘባለን ፡፡ ሰማዕታትም በእሳት እየተቃጠሉ ነው ሰማዕትነትን የተቀበሉት ፡፡ እኛም ሰማዕትነትን ለመቀበል ሰይፉ ቢለዋው ፣ እሳት ረመጡም ቢመጣ ወደኋላ ላንል ቆርጠን ተነስተናል፡፡

እነሆም ሰውየው “ቅብዐትን በእሳት” ብለው ሲናገሩ ፤ በብሉይ ኪዳን ነቢያት ሲቀቡ(ለምሳሌ ኢሳይያስን ቅቡዕ እም ቅብዐ ትንቢት እንዲለው) ወይም ሲከብሩ የሚቀቡበት ፣ ነገሥታት ሲነግሡ የሚነግሡበት ፣ ካህናት ክህነትን ሲሾሙ የሚሾሙበት ፣ ኤጲስ ቆጶሳት ጵጵስና ሲሾሙ የሚሾሙበት ፣ ንዋያተ  ቅዱሳት ቅዱሳት የሚሰኙበት የሚከብሩበት ፣ እኛ ምእመናን በክርስቶስ ክርስቲያን የምንባልበትና 40 80 ቀናችን ከአብረከ መንፈስ ቅዱስ በማህፀነ ዮርዳኖስ ስንወለድ የእግዚአብሔር ልጆች ስለመባላችን ማረጋገጫ ልዩ የቅድስና ማሕተምሆነን ቅዱሱ ቅብዐት(1ኛ ዮሐ 2፡20) ወይም ቅብዐ ሜሮን መገኛው ቅብዐት ከእሳት ነው(ዘጸ 30 ቁ 22 ፤ ዘጸ 30 ቁ 30 ፤1ኛ ነገ 19 ቁ 16 ፤ 1ኛ ሳሙ 9 ቁ 16) ፡፡ 

እንደምን ይገኛል ቢሉ በሐገረ እስክንድርያ  ወይራ ከተባለ ዛፍ ቅጠሉን ቆርጠው ፤ ቅርፍቱን ቀርፍተው ይህን በአንድነት ቀጥቅጠው በማድጋ በጋን አድርገው ከእሳት ላይ ይጠዱታል፡፡ ይኼ 7 ቀን ይፈላል ፡፡ በዚህም ሂደት ይህ የወይራ እንጨት በእሳት ቅብዐት ይሆናል ፡፡ እነሆም ቅብዐቱ በእሳት አማካኝነት ይገኛልና “ቅብዐትን በእሳት” ብለው የተናገሩት አባ ሰሎሞን ሳያውቁት ረቂቅ ነገርን ተናግረውበታል ፡፡ ክቡር ዳዊት በመዝ 44፡7 ላይ ቅብዐ ትፍሥሕት( የደስታ ዘይት)” ብሎ የተናረው ቃል በሰም አነጋገር ቅብዐት ቢባል ወርቁ(ምሥጢሩ) ግን መንፈስ ቅዱስ ነው(የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላትን ተመልከት) ፡፡

ዛቲ ሃይማኖት መሢሐዊት ዘትትአመን ባቲ ቤተክርስቲያን ቅድስት

ስብሐት ለሥሉስ ቅዱስ
ክብር ለቅድስት ድንግል ወለክቡር መስቀል
ይቆየን

ክፍል ሁለት “ተዋሕዶ ሃይማኖት ወይስ ምሥጢር” በሚል ሐተታ እመለሳለሁ ፡፡




No comments:

Post a Comment