Saturday, December 22, 2018

የሥሉስ ፡ ቅዱስ ፡ ህልውና

በስመ ፡ አብ ፡ ወወልድ ፡ ወመንፈስ ፡ ቅዱስ ፡ 

አሐዱ ፡ አምላክ

የሥሉስ ፡ ቅዱስ ፡ ህልውና
ዛሬ ፡ የምንመለከተው ፡ ሥላሴ ፡ በህልውና(በአነዋወር) ፡ አንዴት ፡ እንደሆኑና ፤ ቤተ ፡ አይሁድ ፡ ካሮች ፡ ሳይረዱት ፡ ሳያውቁት ፡ ብዙ ፡ ክርስቶሳውያንን ፡ ሁለተኛ ፡ እያጠመቅ ፡ አይሁድ ፡ አረሚ ፡ ለሚያደርጉበት ፡ የክሕደት ፡ ቃል ፡ ፍቱን ፡ መድኃኒት ፡ የሚሆን ፡ መልእክትን ፡ ይሆናል ፤ ይህንን ፡ ቃልም ፡ የጻፍኩላችሁ ፡ ቤተ ፡ አይሁድ ፡ ኬልቄዶናውያን ፡ እቤታቸው ፡ ታቅፈውት ፡ ከሚገኘው ፡ አክሲማሮስ ፡ ከተባለ ፡ የብራና ፡ መጽሐፋቸው ፡ ነው ፡፡ =============================================
የሥላሴ ህልውና እንዴት ነው እንደምን ይኖራሉ ቢሉ ፤ እንደ አንድ ሰው ይኖራሉ ፡፡ የ1ሰው ኑሮው እንዴት ነው ቢሉ ፤ በልቡ አስቦ በቃሉ ተናግሮ በእስትንፋሱ ተንፍሶ ደኅና ሁኖ ይኖራል ፡፡ በልቡ ሲያስብ ቃሉና እስትንፋሱ አይለዩም ፤ በቃሉም ሲናገር ልቡናው እስትንፋሱ አይለዩም ፡፡ ሥላሴም እንዲህ ናቸው ፡፡ ሰው ቃሉ እስትንፋሱ ሳይለየው በልቡ አስቦ ደኅና ሁኖ እንዲኖር ወልድና መንፈስ ቅዱስም ለባውያን በአብ ናቸው ፤ በአብ ያስባሉ ፤ ለወልድና ለመንፈስ ቅዱስ ልባቸው አብ ነው ፤
ሌላ ልብ የላቸውም ፡፡ ሥላሴ እምቅድመ ዓለም ያስቡ ነበር ማለት የማያውቁት ነገር ኑሮ አውጥተው አውርደው የሚናገሩ ሁነው አይደለም ፤ ነገር ግን ሥላሴ እምቅድመ ዓለም ሳሉ በዚህ ዓለም የሚሠራውን ሥራ የሚደረገውን ነገር ሰፍረው ቆጥረው ያውቁት ነበር ፡፡ ዛሬም ሥላሴን ያስባሉ ማለት ያንን እምቅድመ ዓለም የሚአውቁትን ነገር መዓትም ምሕረትም ቢሆን ይህን ጊዜ እንዲህ ይደረግ ብለው ጊዜ ይሰጡታልና ሥላሴ እምቅድመ ዓለም ያስቡ ነበር ማለት ስለዚህ ነው ፡፡ “ውእቱሰ ፡ እምቅድመ ይኩን አእመረ ወእምቅድመ ይግበር ፈጸመ(እርሱ ፡ ሳይደረግ ፡ አወቀ ፤ ሳይሰራ ፡ ፈጸመ)” ፡ እንዳሉ ፡ ቅዳሴ ፡ 300(t 38) ፤ አንድም ፡ “እምቅድመ ፡ ይፍጥሮ ለአዳም የአምር ግብሮ (አዳምን ፡ ሳይፈጥረው ፡ ሥራውን ፡ ያውቃል)” ፡ እንዳሉ ፡ ቅዳሴ ፡ 300(t 39) ፤ አንድም ፡ “ወለነዋህኒ እምርሑቅ የአምሮ() ፡ እንዳለ ፤ እግዚአብሔር መስተበቅል ገሀደ(እግዚአብሔር ፡ በግልጽ ፡ ተበቃይ ፡ ነው)” እንዳለ(መዝ 93 t 1) ፡፡
ሰው ፡ ልቡ ፡ እስንፋሱ ፡ ሳይለየው ፡ በቃሉ ፡ ተናግሮ ፡ ደኅና ፡ ሁኖ ፡ እንዲኖር ፡ አብና ፡ መንፈስ ፡ ቅዱስ ፡ ነባብያን ፡ በወልድ ፡ ናቸው ፡፡ በወልድ ፡ ይናገራሉ ፡ ለአብና ፡ ለመንፈስ ፡ ቅዱስ ፡ ቃላቸው ፡ ወልድ ፡ ነው ፤ ሌላ ፡ ቃል ፡ የላቸውም ፡፡ ሰው ፡ ልቡ ፡ ቃሉ ፡ ሳይለየው ፡ በእስትንፋሱ ፡ ተንፍሶ ፡ ደኅና ፡ ሁኖ ፡ እንዲኖር ፡ አብና ፡ ወልድም ፡ በመንፈስ ፡ ቅዱስ ፡ ሕያዋን ፡ ሁነው ፡ ይኖራሉ ፡፡ ለአብና ፡ ለወልድ ፡ ሕይወታቸው ፡ መንፈስ ፡ ቅዱስ ፡ ነው ፤ ሌላ ፡ ሕይወት ፡ የላቸውም ፡፡ “አብኒ ፡ ልቦሙ ፡ ለወልድ ፡ ወለመንፈስ ፡ ቅዱስ ፤ ወልድኒ ፡ ቃሎሙ ፡ ለአብ ፡ ወለመንፈስ ፡ ቅዱስ ፤ መንፈስ ፡ ቅዱስኒ ፡ ሕይወቶሙ ፡ ለአብ ፡ ወለወልድ(አብ ፡ ለወልድና ፡ ለመንፈስ ፡ ቅዱስ ፡ ልባቸው ፡ ነው ፤ ወልድም ፡ ለአብና ፡ ለመንፈስ ፡ ቅዱስ ፡ ቃላቸው ፡ ነው ፤ መንፈስ ፡ ቅዱስም ፡ ለአብና ፡ ለወልድ ፡ ሕይወታቸው ፡ ነው)” ፡ እንዳለ ፡ አቡሊዲስ ፡ ዘሮሜ(ሃይ.አበው ፡ ምዕ ፡  ፡ ክ ፡ 2 t 8) ፡፡
 በተዋሕዶ ፡ ከበረ የሚሉ ፡ ሰዎች ፡ ግን ፡ የእስትንፋስ ፡ ትርጓሜው ፡ ሕይወት ፡ እንደሆነ ፡ ባያውቁ ፡ መንፈስ ፡ ቅዱስ ፡ ለአብና ፡ ለወልድ ፡ እስትንፋሳቸው ፡ ነው ፡ እንጅ ፡ ሕይወታቸው ፡ አይደለም ፡ ብለው ፡ ተነሥተዋል ፡፡ እንዲህም ፡ ማለታቸው ፡ ሦስቱን ፡ ሕይወት ፡ ያልን ፡ እንደሆነ ፡ ነሥአ ፡ ተወክፈ ፡ ከማለት ፡ እንድናለን ፤ በተዋሕዶ ፡ ከበረ ፡ ለማለት ፡ ይመቸናል ፡ ብለው ፡ ነው ፡፡ ለነዚህ ፡ ምን ፡ ይመልሷል ፡ ቢሉ ፤ መላእክት ፡ በጥንተ ፡ ፍጥረቱ ፡ “መኑ ፡ አንተ” ፡ ብለው ፡ በጠየቁት ፡ ጊዜ ፡ እራሱ ፡ መንፈስ ፡ ቅዱስ ፡ “አነ ፡ ውእቱ ፡ ሕይወቱ ፡ ለዘገብረ ፡ ሰማየ ፡ ወምድረ(እኔ ፡ ሰማይን ፡ እናንተንም ፡ ምድርንም ፡ ለፈጠረ ፡ ሕይወቱ ፡ ነኝ)” እንዳለ ፡ አክሲማሮስ ፡ ዘእሑድ(ክ ፡ 2 ፡ ቊ ፡ 5) ፡፡ ለራሱማ ፡ ቢሆን ፡ “ሕይወት ፡ ለርእስየ” ፡ ባለ ፡ ነበር ፡ እንጅ ፡ “ሕይወቱ ፡ ለዘገብረ ፡ ሰማየ ፡ ወምድረ” ፡ ባላለ ፡ ነበር ፤ ሰማይን ፡ ምድርን ፡ ለፈጠረ ፡ ለአብ ፡ ሕይወቱ ፡ ነኝ ፡ ሲል ፡ ነው ፡ እንጅ ፤ ሕይወትነቱን ፡ ሲያመለክት ፡ “ወበከመ ፡ ነፍስከ ፡ ለሥጋከ ፡ ሕይወት ፡ ከማሁ ፡ መንፈስ ፡ ቅዱስኒ ፡ ሕይወቶሙ ፡ ለአብ ፡ ወለወልድ(ነፍስ ፡ ለሥጋ ፡ ሕይወት ፡ እንደሆነችው ፡ እንዲሁ ፡ መንፈስ ፡ ቅዱስም ፡ ለአብና ፡ ለወልድ ፡ ሕይወታቸው ፡ ነው )” ፡ እንዳለ ፡ አረጋዊ ፡ መንፈሳዊ(ድር ፡ 22) ፡፡ እንዲህም ፡ ማለቱ ፡ ነፍስህ ፡ ለሥጋህ ፡ ሕይወት ፡ ሁናው ፡ እንዲኖር ፤ ለአብና ፡ ለወልድም ፡ ሕይወታቸው ፡ መንፈስ ፡ ቅዱስ ፡ ነው ፡ ሌላ ፡ ሕይወት ፡ የላቸውም ፡ ሲል ፡ ነው ፡፡ “ነአምን ፡ ከመ ፡ አብ ፡ ልብ ፡ ወወልድ ፡ ንባብ ፡ ወመንፈስ ፡ ቅዱስ ፡ ሕይወት(አብ ፡ ልብ ፡ እንደሆነ ፤ ወልድም ፡ ንግግር ፡ እንደሆነ ፤ መንፈስ ፡ ቅዱስም ፡ ሕይወት ፡ እንደሆነ ፡ እንመን)” ፡ እንዳለ ፡ ያዕቆብ ፡ ዘእልበራዳኢ(ምዕ ፡ 3 ፡ ቊ ፡ 13) ፤ አንድም ፡ “ንሕነሰ ፡ ክርስቶሳውያን ፡ ኢንብል ፡ በእንተ ፡ መለኮተ ፡ ቅድስት ፡ ሥላሴ ፡ አሐደ ፡ አካለ ፡ ወዘንተ ፡ ሶበ ፡ ንቤ ፡ ንትሜሰል ፡ ከመ ፡ አይሁድ ፡ እለ ፡ ይሰልብዎ ፡ ንባቦ ፡ ሕይወቶ(እኛ ፡ ክርስቶሳውያን ፡ ግን ፡ የቅድስት ፡ ሥላሴ ፡ ባሕርይ ፡ አንድ ፡ ነው ፡ ስለአልን ፡ አንድ ፡ አካል ፡ ነው ፡ አንልም ፤ ይህንን ፡ ብንናገርስ ፡ አምላክ ፡ ያላደረባቸውን ፡ ቃሉን ፡ ሕይወቱን ፡ ያሳጡተርን ፡ አይሁድን ፡ መምሰላችን ፡ ነው)” ፡ እንዳለ ፡ አባ ፡ ስኑትዩም ፡ ዘእለእስክንድርያ(ሃይ.አበው ፡ ምዕ ፡ 110 ፡ ክ ፡ 2t11) ፡ ብሏል ፡ ሲሏቸው ፡ በዚህ ፡ ይረታሉ ፡፡ ስለዚህም ፡ ነገር ፡ መንፈስ ፡ ቅዱስ ፡ ለአብና ፡ ለወልድ ፡ እስትንፋሳቸው ፡ ነው ፡ እንጅ ፡ ሕይወታቸው ፡ አይደለም ፡ ማለት ፡ ክሕደት ፡ ነው ፡፡ ለአብና ፡ ለወልድ ፡ መንፈስ ፡ ቅዱስ ፡ ሕይወታቸው ፡ ነው ፡ ካሉ ፡ መንፈስ ፡ ቅዱስ ፡ ቢለያቸው ፡ መዋትያን ፡ መሆናቸው ፡ ነዋ ፡ ቢሉ ፤ መንፈስ ፡ ቅዱስ ፡ ለአብና ፡ ለወልድ ፡ የማይለይ ፡ የባሕርይ ፡ ሕይወታቸው ፡ ነውና ፡ መዋትያን ፡ አይደሉም ፡ “ወአልቦ ፡ ፍልጠት ፡ ማዕከለ ፡ ልቡናሁ ፡ ወንባቡ ፡ ወሕይወቱ(በሕይወቱ ፡ በንግግሩና ፡ በልቦናው ፡ መካከል ፡ ልዩነት ፡ የለም)” ፡ እንዳለ ፡ ያዕቆብ ፡ ዘእልበረዳኢ(ምዕ ፡ 3 ፡ ቊ ፡ 13)  ፡፡
መንፈስ ፡ ቅዱስ ፡ ለአብና ፡ ለወልድ ፡ ሕይወታቸው ፡ ነው ፡ ካሉ ፤ “ወሕይወተ ፡ አብ ፡ ዘኢያስተርኢ(የማይገለጽ ፡ የአብ ፡ ሕይወት)” ፡ እንዳለ ፡ መጽሐፈ ፡ ኪዳን ፡ ወልድን ፡ ሕይወተ ፡ አብ ፡ ይለዋልሳ ፡ ይህ ፡ እንዴት ፡ ነው? ፡ ቢሉ ፤ ይህስ ፡ መዓዛ ፡ ዕጣን ፡ እንደማለት ፡ ነው፡፡ መዓዛ ፡ ዕጣን ፡ ማለት ፡ ከዕጣን ፡ የሚገኝ ፡ ሽታ ፡ ነው ፡ እንጅ ፡ ለእጣን ፡ የሚሸተው ፡ ሽታ ፡ ማለት ፡ አይደለም ፤ እንደዚህም ፡ ሁሉ ፡ ወልድ ፡ ለአብ ፡ ሕይወት ፡ ሆኖት ፡ አይደለም ፡፡ ነገር ፡ ግን ፡ አብ ፡ ወልድን ፡ ወርደህ ፡ ተወልደህ ፡ ተሰቅለህ ፡ ዓለምን ፡ አድን ፡ ብሎ ፡ አዝዞ ፡ ሰጥቷልና ፡ አብ ፡ የሰጠን ፡ ሕይወት ፡ ማለት ፡ ነው ፡ እንጅ ፡ ወልድ ፡ ለአብ ፡ ሕይወቱ ፡ ነው ፡ ማለት ፡ አይደለም ፡፡ መንፈስ ፡ ቅዱስ ፡ ለአብ ፡ ሕይወቱ ፡ ነው ፡ ካሉ ፡ ሕያው ፡ ያሠርፃል ፡ እንጅ ፡ ሙት ፡ ያሠርፃልን ፡ አብ ፡ በማን ፡ ሕያው ፡ ሁኖ ፡ መንፈስ ፡ ቅዱስን ፡ አሠረፀዋ!? ፡ ቢሉ ፤ በሥላሴ ፡ ሦስትነት ፡ መቀዳደም ፡ መከታተል ፡ ቢኖርባቸው ፡ ኖሮ ፡ አብ ፡ በማን ፡ ሕያው ፡ ሁኖ ፡ መንፈስ ፡ ቅዱስን ፡ አሠረፀ ፡ በተባለ ፡ ነበር ፤ ነገር ፡ ግን ፡ በZeሦስትነት ፡ መቀዳደም ፡ መከታተል ፡ የለባቸውምና ፡ አብ ፡ በመንፈስ ፡ ቅዱስ ፡ ሕያው ፡ ሁኖ ፡ መንፈስ ፡ ቅዱስን ፡ አሠረፀው፡፡
መንፈስ ፡ ቅዱስ ፡ ለአብና ፡ ለወልድ ፡ ሕይወታቸው ፡ ብቻ ፡ አይደለም ፡ ክብራቸውም ፡ መንግሥታቸውም ፡ ነው፡፡ የዚህ ፡ ዓለም ፡ ንጉሥ ፡ በዘውድ ፡ እንዲነግሥ ፤ በወርቅ ፡ በብር ፡ እንዲከብር ፤ አብና ፡ ወልድም ፡ በመንፈስ ፡ ቅዱስ ፡ ይነግሡበታል ፡ ይከብሩበታል ፡ ማለት ፡ አይደለም ፡፡ ነገር ፡ ግን ፡ የንጉሥ ፡ መንግሥቱ ፡ በሕይወቱ ፡ ሳለ ፡ እንጅ ፡ ከሞተ ፡ በኋላ ፡ ክብረት ፡ የለውም ፡ ከሞተስ ፡ በኋላ ፡ ስንኳን ፡ ክብረት ፡ ይኖረው ፡ ቀድሞ ፡ ሳለ ፡ በሕይወቱ ፡ በአዳራሽ ፡ በዙፋን ፡ በድንኳን ፡ ጃንሆይ ፡ ንጉሥ ፡ ሆይ ፡ እየተባለ ፡ ሲጋረድ ፡ ሲጓደድ ፡ ይኖር ፡ የነበረው ፡ ሰው ፤ ነፍሱ ፡ ከሥጋው ፡ ስትለይ ፡ ስመ ፡ መንግሥቱ ፡ አብሮ ፡ ተለይቶት ፡ አስከሬን ፡ እጠቡ ፡ አስከሬን ፡ አውጡ ፡ ይባላል ፡እንጅ ፡ ከሞተ ፡ በኋላ ፡ ስመ ፡ መንግሥቱን ፡ የሚአነሳው ፡ የለም ፡፡ እንደዚህም ፡ ሁሉ ፡ የአብና ፡ የወልድ ፡ መንግሥታቸው ፡ በመንፈስ ፡ ቅዱስ ፡ ሕያው ፡ ሁነው ፡ ነውና ፡ መንፈስ ፡ ቅዱስ ፡ ለአብና ፡ ለወልድ ፡ መንግሥታቸው ፡ ነው ፡ ማለት ፡ ለዚህ ፡ ነው፡፡ “ወዓዲ ፡ ይስእልዎ ፡ ከመ ፡ ያምፅእ ፡ ሎሙ ፡ መንግሥቶ ፡ ዝ ፡ ውእቱ ፡ መንፈስ ፡ ቅዱስ()” ፡ እንዲል ፤ አንድም ፡ “ፍካሬ ፡ መንግሥቱሰ ፡ ሱታፌ ፡ መንፈስ ፡ ቅዱስ ፡ ውእቱ()” ፡ እንዳለ ፡ ትርጓሜ ፡ ወንጌል() ፡፡
መንፈስ ፡ ቅዱስ ፡ ለአብና ፡ ለወልድ ፡ ክብራቸው ፡ ነው ፡ ማለት ፤ የዚህ ፡ ዓለም ፡ ሰው ፡ በወርቅ ፡ እንዲከብር ፡ አብና ፡ ወልድ ፡ በመንፈስ ፡ ቅዱስ ፡ ይከብሩበታል ፡ ማለት ፡ አይደለም ፤ የንጉሥ ፡ ክብረቱ ፡ መንግሥቱ ፡ ሳለ ፡ በሕይወቱ ፡ ነው ፡ እንጅ ፡ ከሞተ ፡ በኋላ ፡ ክብረት ፡ የለውም ፡፡ ከሞተስ ፡ በኋላ ፡ ስንኳን ፡ ክብረት ፡ ይኖረው ፡ ዘንድ ፡ ቀድሞ ፡ በሕይወቱ ፡ ሳለ ፡ በንብረት ፡ ከብሮ ፡ ገኖ ፡ ይኖር ፡ የነበረው ፡ ሰው ፤ ነፍሱ ፡ ከሥጋው ፡ ስትለየው ፡ ድሪውን ፡ ካንገቱ ፡ ልብሱን ፡ ከአካላቱ ፡ ገፈው ፡ በግማሽ ፡ ሰሌን ፡ በአሞሌ ፡ ነጠላ ፡ ገንዘው ፡ መቃብር ፡ ያወርዱታል ፡ እንጅ ፡ ያ ፡ ሁሉ ፡ ንብረቱ ፡ አብሮት ፡ አይቀበርም ፡፡ “ዕራቅየ ፡ ወጻዕኩ ፡ እምከርሠ ፡ እምየ ፡ ወዕራቅየ ፡ እገብዕ ፡ ውስተ ፡ መሬት(ከእናቴ ፡ ማኅፀን ፡ እራቁቴን ፡ ወጥቻለሁ ፤ እራቁቴንም ፡ ወደ ፡ ምድር ፡ እመለሳለሁ)” ፡ እንዳለ ፡ ኢዮብ(ምዕ ፡ 1t11) ፤  እንደዚህም ፡ አብና ፡ መንፈስ ፡ ቅዱስ ፡ ክብረታቸው ፡ መንግሥታቸው ፡ በመንፈስ ፡ ቅዱስ ፡ ሕያው ፡ ሁነው ፡ ነውና ፡ መንፈስ ፡ ቅዱስ ፡ ለአብና ፡ ለወልድ ፡ ክብራቸው ፡ ነው ፡ ማለት ፡ ስለዚህ ፡ ነው ፡፡ “ዘሰ ፡ ኢያጠሪ ፡ እምብዕለ ፡ ክርስቶስ ፡ ዝ ፡ ውእቱ ፡ መንፈስ ፡ ቅዱስ ፡ ነዳይ ፡ ውእቱ()” ፡ እንዳለ ፡ ስምዖን ፡ ዘአምድ() ፡፡
ምስጋና ፡ ለአንዱ ፡ አምላክ ፡ ለቅድስት ፡ ሥላሴ
ክብር ፡ ለአምላክ ፡ እናት ፡ ለድንግል ፡ ማርያም
ክብር ፡ ለመስቀለ ፡ ክርስቶስ ፡ እጸመድኃኒት ፡ ኃይልነ ፡ ወጸወንነ
ይህ ፡ ጽሁፍ ፡ ወልደ ፡ አብ ፡ ላይም ፡ ቁልጭ ፡ ብሎ ፡ አለ ፡ ቤተ ፡ አይሁድ ፡ አይናችሁን ፡ ከፍታችሁ ፡ ተመልከቱት ፡ ተሰናክላሁ ፡ አታሰናክሉ ፡ እባካችሁ

No comments:

Post a Comment