Thursday, December 20, 2018

በተዋሕዶ ከበረ ባዮች ምንፍቅና በሊቃውንት መጽሐፍ[በዝክሪ ወጳውሊ ዘደብረ ጽሞና መጽሐፍ]




“የዘማርያን ምንፍቅናና የካሮች[በተለምዶ ተዋሕዶ ብለው ራሳቸውን የሚጠሩ] አስተምህሮ በምስራቅ ጎጃም በምትገኘው ደብረ ጽሞና ገዳም ይኖሩ በነበሩትና ካቶሊካውያንን ተከራክረው የቅዱሳን አበውን ትክክለኛዋን አስተምህሮ ያቆዩልን አባ ዝክሪና አባ ጳውሊ ከሚባሉት ሊቃውንት መጽሐፍ ላይ ተቀንጭቦ የተወሰደ”
~~~~~~~~~~~~//~~~~~~~~~~~~~//~~~~~~~~~~~~~~~
“በአለም ሰገድ በመንግስቱ ዘመን በነገሰ በአስራ አምስት ዓመቱ ክርስቶስ ቀባዒና ተቀባዒ ቅብዕ የሚል ስሙ ዘማርያን የተባለ መናፍቅ ዳግመኛ ተነሳ:: ይሄውም ዘማርያን 
ጀርማናዊው ደቀ መዝሙር ነበር ከእርሱም ትርጓሜውን ሰማ እንደ መምህሩም ሆነ ክርስቶስ ቀባዒና ተቀባዒ ቅብዕ ነው እያለ ያስተምር ጀመር፤
.......ምዕመናንም ሰሙት ምዕመማንም ይህን ትምህርትና ይህን ሃይማኖት ማን አስተማረህ አሉት:: 

.......መናፍቁ ዘማርያንም መለሰ ጌታችን በወንጌሉ እኔ በአብ አብ በእኔ እኔና አብ አንድ ነን ያለውን እርሱ ምስክሬ ነው አላቸው:: እኔም ይህን ነገር አውቄ አብ ከወልድ ጋር ካለ ስለዚህ ክርስቶስ ሌላ ቀባዒና ቅብዓትን አይፈልግም እርሱ ቀባዒ እርሱም ተቀባዒ እራሱም ቅብዕ ነው እላለሁ አለ:: 

....... ምዕመናንም ጮሁ ይህ ነገርስ በጉባኤ ይሆናል እንጅ በቀስታ አይሆንም አሉት ይህንንም ብለው መጽሐፍትን ወደሚያውቁና ወደ ምዕመናን ላኩ ከብዙ አድባራትም ተከማቹ የአቡነ ኤዎስጣቴዎስ የልጅ ልጅ አቡነ በትረ ማርያም ባነጸው በዘጌ ገዳም ጉባኤ አደረጉ በዓለም ሰገድ በመንግስቱ ላይም ክርክር ተነሳ:: 
....... በዚህም ጉባኤ ጳጳሱ ማርቆስ አለ ጳጳሱም የጉባኤውን ማህበር እስኪ ቆዩኝ ትንሽ ዝም በሉ እኔ እጠይቀዋለሁ ሃይማኖቱ እንደ እኛ ጥሩ ከሆነ የምዕመናን አለቃ እንሾመዋለን አላቸው:: ከእኛ የተለየ ከሆነ መምህሩ ከሄደበት እዚያ በስቃይ ይሄዳል:: ይህንንም መናፍቅ ክርስቶስን ቀባዒና ተቀባዒ ቅብዕ በቃልህ የምትለው እውነት ነውን? አለው:: 

.......ይህም መናፍቅ መለሰ አዎን እኔ እለዋለሁ እርሱ ራሱ ክርስቶስ በወንጌሉ እኔ በአብ አብ በእኔ አለ፤ እኔና አብ አንድ ነን ብሏል አለው አብና ወልድ ሁለታቸው አንድ ከሆኑ ወልድ ብቻውን ቀባዒና ተቀባዒ ቅብዕ ይሆናል በዚህ ጽሁፍ ክርስቶስን ቀባዒና ተቀባዒ ቅብዕ ነው አዎን እለዋለሁ ቀባዒንም ሆነ ቅብዓትን አይፈልግም አለ:: መለኮት አልተቀባም የቃል አካል ቀባዒ የሥጋ አካል ተቀባዒ ሆኖ በድንግል ማርያም ዘንድ አደረ የቃል አካል ከሥጋ አካል ጋር በተዋሀደ ጊዜ ለሥጋ አካል የቃል አካል ቀባዒና ቅብዕ ሆነው በመንፈስ ቅዱስ ቅብዕነት የባህርይ ልጅ አልሆነም ቃል በመወሀዱ ሥጋ ከበረ እንጅ:: 

....... ጳጳሱ ማርቆስም መለሰለት መናፍቅ ሆይ ይህ ነገር አንዱን ክርስቶስን ወደ ሁለት ህላዌያትና ወደ ሁለት ባህርያት ወደ ሁለት አካላትም ይከፍለዋል ይህ ቃልህስ ዜናው የከፋ እንደ ልዮን ትምህርት ይሆንብሃል:: 

.......ይህ መናፍቅም አብ በወልድ ወልድ በአብ የለም ትላላችሁ አለው::
.......ጳጳሱ ማርቆስም መለሰ አዎን አብ በአካሉ ሳለ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ልብ ሆኖ ህልው ነው ወልድም በአካሉ ሳለ በአብና በመንፈስ ቅዱስ ቃል ሆኖ ህልው ነው መንፈስ ቅዱስም በአካሉ ሳለ በአብና በወልድ እስትንፋስ ሆኖ ህልው ነው:: ባህልህና ሃይማኖትህ እንደ ከሃዲው ሰባልዮስ ሃይማኖት ነው እነሆ ሶስቱን ገጽ አንድ ገጽ ሶስቱን አካላትም አንድ አካል አደረካቸው:: አንድ ጊዜም ወልድን እርሱው አብ እርሱው ወልድ እርሱው መንፈስ ቅዱስ አደረግኸው በመቅባቱ አብ በመቀባቱ ወልድ በቅብዕነቱ መንፈስቅዱስ ዳግመኛ አደረከው::
መናፍቅ ሆይ ልብ አድርገህ ስማ እኛስ አብና ወልድ መንፈስ ቅዱስም በአካል ይለያያሉ በመለኮት አንድ ይሆናሉ እንላለን:: መናፍቅ ሆይ ስማ እኔ በአብ አብም በእኔ ባለ ጊዜ ክርስቶስ ይህንን ቃል ይዘህ እርሱው አብ እርሱው ወልድ እርሱው መንፈስ ቅዱስ እነሆ ትለዋለህ መናፍቅ ሆይ ልብ አድርገህ ስማ ክርስቶስ በወንጌሉ እኔና አብ አንድ ነን ባለ ጊዜ ሰባልዮስ ምስክሬ ነው ብሎ አብና ወልድ መንፈስ ቅዱስም አንድ ገጽ ናቸው አለ:: 

.......
ዘማርያንም አብና ወልድን አንድ እንዳይሆኑ ትለዩአቸው አላችሁ አለው::
....... ጳጳሱ ማርቆስም መለሰ እኔ በመለኮት አለያቸውም በአካላትም አንድ አላደርጋቸውም ስለዚህ ሐዋርያት እንዳስተማሩን ሶስት ሲሆኑ አንድ አንድ ሲሆኑ ሶስት እንላለን በቤተ ክርስቲያን ላይ ሁለተኛ ሰባልዮስ ተነሳህ::

.......ዘማርያንም አብና ወልድ መንፈስ ቅዱስም በመለኮት አንድ ከሆኑ ለምን ሌላ ቀባዒ ይፈልጋል አለው፤ አብና ወልድን መንፈስ ቅዱስንም ትለዩ አቸው አላችሁን:: ባልኩህ ጊዜ አለያቸውም ሶስት ሲሆኑ አንድ ይሆናሉ አንድ ሲሆኑ ሶስት ይሆናሉ ትለኛለህ ክርስቶስን በመለኮቱ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ያንሳል ትለዋለህ በአንድ ጎዳና እስኪ በል ሌላ ቀባዒ ከፈለገ እንዲህ ከሆነ ክርስቶስ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በምን ይተካከላል:: ነገር ግን እኔ እንደ ሃይማኖቴ እላለሁ፤ የቃል አካል እርሱ አምላክ ሲሆን አምላክነቱን ይዞ ሌላ ቀባዒና ቅብዕን አይፈልግም የሥጋን አካል የራሱ አካል ቀባው፤ መንፈስ ቅዱስ በእርሱ ህልው ሆኖ ሳለ መንፈስ ቅዱስ በወልድ የለም ትላለህ አለ::
....... ጳጳሱ ማርቆስም መለሰ የቀደሙ አባቶቻችን አብ ቀባዒ ወልድ ተቀባዒ መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ ያሉት ቅዱሳት መጽሐፍት ዋሹን? አለው::
.......ዘማርያንም እንዲህ አለ የቃል አካል ከሥጋ አካል ጋር በተዋሀደ ጊዜ አብና መንፈስ ቅዱስ በወልድ ተገኙ፤ የቃል አካል ከሥጋ አካል ጋር ሲዋሀድ መወሀዱ ለሥጋ ቀባዒና ቅብዕ ሆነው፤ በተዋህዶም እንዲህ ከሆነ::

.......ይህስ ዜናው የከፋ ወደ ሰባልዮስና ወደ ልዮን ሐይማኖት ይመራል እንደ ባህልህስ የክርስቶስ ስም ለሁለት ሆነ፣ ይኸውም የቃል አካል ቀባዒ የሥጋ አካል ተቀባዒ:: የጀርመን ልጅ መናፍቅ ሆይ ስማ መምርህስ እንደሆነ እነሆ አሁን አወቅን ተረዳን እንዲህ ባልክ ጊዜ የቃል አካል ከአብ ከሠረፀው መንፈስ ቅዱስን ሕይወትን ተቀበለ፣የሥጋ አካልም ከወልድ ከሠረፀው መንፈስ ቅዱስህይወትን ተቀበለ ይሆንብሃል አለው:: እንዲህስ ከሆነ ክርስቶስን አንድ ያይደለ ወደ ሁለት አደረከው እንደ ባህልህስ ክርስቶስ አስራፂ ሆነ መንፈስ ቅዱስም ከአብ ያይደለ ከወልድ ሠራፂ ሆነ:: ዳግመኛም ክርስቶስን እርሱው አብ እርሱው ወልድ እርሱው መንፈስ ቅዱስ አደረከው በመቅባቱ አብ አልከው በመቀባቱ ወልድን አደረከው በቅባቱም መንፈስ ቅዱስን አደረከው እነሆ ሶስቱን አካላት አንድ አካል አደረካቸው ሶስቱን ገጻትም አንድ ገጽ ሦስቱንም ስም አንድ ስም::
እንደ ባህልህስ የሥጋ አካል ቅቡዕ የቃል አካል ቀባዒ እንዲህ ከሆነ በየት አንድ መሲህ ይባላል የባህርይ ልጅስ በየት ይሆናል አለው:: አንተስ አብ ቃልን ወለደው ቃልም በመቅባቱ ሥጋን ወለደው ትላለህ እንደ ባህልህስ መንፈስ ቅዱስ ሁለት ሆነ ከአብ የሰረፀው አንዱ መንፈስ ቅዱስ ለቃል አካል ህይወት ሆነው:: ከወልድ የሰረፀው አንዱ መንፈስ ቅዱስ ለሥጋ አካል ህይወት የሆነው ነው:: አብም ሁለት ሆነ አንዱ አብ ከመለኮቱ ባህርይ ወልድን የወለደው ሁለተኛው አብም ይኸው የቃል አካል የሥጋን አካል በቅባቱ የወለደው ነው:: ወልድም ሁለት ሆነ አንዱ ወልድ ከአብ ከመለኮቱ ባህርይ የተወለደው ሁለተኛው ወልድ እርሱው የሥጋ አካል በቅባት ከቃል አካል የተወለደው ነው:: መናፍቅ ሆይ! እንሆ እንደ ሃይማኖትህስ ሰውነቱን ለመቅባት መንፈስ ቅዱስን ስለአሰረጸው የአብ ስም ወደ ወልድ ስም ተፋለሰ:: የወልድ ስምም ቀባዒ ስለሆነ ወደ አብ ስም ተፋለሰ::
የጀርመን ልጅ መናፍቅ ሆይ! አብ ቀባዒ ወልድ ተቀባዒ መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ የሚሉትን ሰማንያ አንዱን መጽሐፍት ልትፍቃቸው ነውን:: እኛስ ክርስቶስ በአባቱ እጅ በመንፈስ ቅዱስ ተቀባ ብለው የቀድሞ አባቶቻችን እንደ አስተማሩን የመጽሐፍት ቃልን ምስክር አድርገን እናምናለን:: ቄር ምቅዋ ፲፪ ከመንፈስ ቅዱስ የራቀ ሆኖ አይደለም የቀድሞ ህይወቱ ነውና በህላዌው መቀባትን ሳይወድ ስለ ሰውነቱ ተቀባ እንጅ ሰውነቱን ከመለኮቱ ጋር ፈጽሞ ያለ መለየት አንድ ያደርገው ዘንድ:: አንተ የአመጽ ልጅ ሰነፍ ሆይ! ፈጽመህ ስማ የሥጋ አካል በቃል አካል የተቀባ አይምሰልህ የቃል አካል በሰውነቱ ተቀባ እንጅ ቀቢውም የቀድሞ ባህርዩ ነውና አብ ነው:: መናፍቅ ሆይ! ስማ ከመለኮቱ ባህርይ ወልድን የወለደው መንፈስ ቅዱስን ያሰረፀው ከቀድሞ ጀምሮ ባለ በአንዱ አምላክ እኛ እንዲህ ብለን እናምናለን:: ያለ እርሱ ሌላ ወላጅና አስራፂም የለም የወልድ ባህርይና የመንፈስ ቅዱስ ባህርይ ነውና:: ዳግመኛም ከቃል አካል ጋር በተዋሀደ ጊዜ በመንፈስ ቅዱስ ቅብዕነት ከመለኮቱ ባህርይ የወልድን ሰውነት እንደ ወለደው በአብ እናምናለን::
ከቀድሞ በነበረ በአንዱ ወልድም እናምናለን ከአብ ከመለኮቱ ባህርይ እንደ ተወለደ ያለ እርሱ ከአብ የሚወለድ ሌላ ወልድ የለም እርሱም የአብና የመንፈስ ቅዱስ ቃል ነው:: ዳግመኛም በወልድ ሰውነት እናምናለን ከቃል አካል ጋር በተዋሀደ ጊዜ በመንፈስ ቅዱስ ቅብዕነት ከአብ ከመለኮቱ ባህርይ እንደ ተወለደ:: ከቀድሞ በነበረ በአንዱ መንፈስ ቅዱስም እናምናለን ከአብ ከመለኮቱ ባህርይ እንደ ሠረፀ ከወልድ የሚሰርፅ ሌላ መንፈስ ቅዱስ የለም የአብና የወልድ ህይወት እርሱ ነው:: ዳግመኛም ከመለኮቱ ጋር በተዋሀደ ጊዜ ለወልድ ሰውነት ህይወት እንደሆነው በመንፈስ ቅዱስ እናምናለን እንዲህ ብለን ሌላውን እናሳምናለን እኛም እንዲሁ እናምናለን እንዲሁም ለሰው እናስተምራለን:: 

.......
ይህም መናፍቅ መለሰ ለምን ነገርህ ይበዛል አለው እኔ አስቀድሞ በዚህ ሃይማኖት እሞትበታለሁ ብየ ነገርኩህ ይህ ነገርህ ሁሉ በልቤ ውስጥ አልገባም አለ::
.......ያን ጊዜም ጳጳሱ ማርቆስ ተቆጣ በአብና በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስልጣን አወገዘው በዚያም ያሉት የቤተ ክርስቲያን ማህበሮች ሁሉ ይህን ሃይማኖቱ የጎደለ እንደ መናፍቁ አርዮስ ከእርሱ ጋር አወገዙት:: ያን ጊዜም የቤተ ክርስቲያን ማህበሮች ሁሉ ይወግሩት ዘንድ ድንጋይ አነሱ:: 

.......
ይህም መናፍቅ በውግረቱ እንደ ጨከኑና እንደ ፀኑ ባየ ጊዜ ጌቶቼ! እስኪ ታገሱኝ በድንጋይ አትውገሩኝ አላቸው እኔ ፈጽሜ በድያለሁ ቀለም በመዘንጋትም ፈጽሜ ስቻለሁ:: ዛሬም ተውኝ በሃይማኖታችሁ አምኛለሁና ከስህተቴም ተመለስኩ ቀድሞ በመዘንጋት ሳትኩ ዛሬ ግን አስተዋልኩ እግዚአብሔር እንዳሳያችሁና እናንተ እንዳወቃችሁ ቀኖና ስጡኝ አለ መመለሱ ግን ከልቡ አይደለም በድንጋይ ተወግሮ በመሞቱ ፍርሃት ነው እንጅ:: ይህስ መናፍቅ እንደ ከሃዲው አርዮስ ክህደትን ከልቡ አላጠፋም በእዳሪ ግን አመነ ተመለሰ:: በውስጡ ግን በአመጽና በሽንገላ የተዘጋ ነው::

....... ምዕመናን ግን በድንጋይ ይወግሩት ዘንድ ፈጽመው ጨከኑ እጃቸውም ከመግደል አልተመለሰም:: ጳጳሱ ማርቆስም በመናፍቁ በዘማርያን ሞት እንደጨከኑና እንደ ጸኑ ያን ጊዜ አየ ወንድሞቼ ይህ ሰው አይሙት ከስህተቴ ተመለስኩ ቀኖና ስጡኝ እያለ ብንገለው እግዚአብሔር ይጣላናል:: የኃጥዕን መሞቱን አልወድም ወደ ንስሐ መመለሱን እንጅ ብሎ መጽሐፍ እንዳለ:: ይህን ብሎ ጳጳሱ ማርቆስ በላው ላይ ወደቀ እነሆ ዛሬ ከእርሱ ጋር ጨምራችሁ ግደሉኝ አለ ከዚህ በኋላ ድንጋዩን ከእጃቸው ጣሉት:: ዳግመኛም ጳጳሱ ማርቆስ እንዲህ አላቸው ከዘሬ ጀምረን ለሚመጣው ስራ እንስራ በቤተ ክርስቲያንና በእኛ ላይ ክህደትና ኑፋቄ እንዳይነሳ አላቸው:: ከዚህ በኋላ ጳጳሱ ማርቆስ ጠየቃቸው ምዕመናንንም እንዲህ አላቸው ይህ ሃይማኖት በሃገራችሁ ምን ጊዜ ነው የገባ ይህ ትምህርትስ ምን ጊዜ መጣ ከዚህስ አስቀድሞ በኢትዮጵያ ምድር ማን ነው ያስተማረ? አለ:: ምዕመናንም መለሱ ይህ ትምህርትና ሃይማኖት የተነሳ ከጀርመናዊው ጴጥሮስ ነው ጳጳሱ ማርቆስም በእርሱ ዘንድ የተማሩት ሁሉ እንዲህ ይላሉ አላቸው:: አዎ ትርጓሜውን ከእርሱ የሰሙት ሁሉ እንዲህ ይላሉ አሉት::
ያን ጊዜም ጳጳሱ ማርቆስ አዋጅ ይነገር ዘንድ አዘዘ ከጀርመናዊው ሰው የተማሩትን ይሰዱአቸው ዘንድ አዘዘ፤ በኢትዮጵያ ምድር እንዳያስተምሩ ምድረ ዋግ በሚባል ወደ ሰሜን ተሰደው ሄዱ:: በዚያም የስህተት መጽሐፍም በየደብሩና በየሀገሩ አስተማሩ እኒህ በጀርመናዊው ሰው በዋግ ምድር በገቡ ጊዜ የላስታ ሰዎች ከተከዜ ወንዝ ጀምሮ እስከ ዘመዶ ድንበር ድረስ ያለው ሁሉ ካደ:: ክርስቶስ ቀባዒና ተቀባዒ ቅብዕ ነው አሉ፤ የመንፈስ ቅዱስ ቅባትም ለወልድ አረባውም አሉ ክርስቶስንም እርሱ ቀባዒ እርሱም ተቀባዒ እርሱው ቅብዕ ነው አሉት:: ትርጓሜውም እርሱው አብ እርሱው ወልድ እርሱው መንፈስ ቅዱስ ማለት ነው በመቅባቱ አብ አሉት በመቀባቱ ወልድ አሉት በቅባቱ መንፈስ ቅዱስ አሉት በዋግ ምድርና በላስታ፤ አውራጃ እንዲህ ያምናሉ ለሰውም እንዲህ ያስተምራሉ:: እኒህንም ቤተ ክርስቲያን በውግዘት ጦር ትወጋቸዋለች ቀድሞ የተቀደሰች ሥላሴ የቀደደ አርዮስን እንደወጋችው:: እግዚአብሔርም ቀድሞ የአጋንንት ሰራዊትን እንደ ተበቀለ በፍርድና በፍዳ ቀን ይበቀላቸዋል እንደ ረሲዕ ይሁዳም ከክርስቲያን ማህበር ይለያቸዋል::
ወደ ጥንተ ነገራችን እንመለስና በዘጌ ምድር የተሰበሰቡት የምዕመናን ጉባኤዎች ነገራቸውን ጨረሱ በየሀገራቸውና በየደብራቸው በየገዳማቸውም ሄዱ:: ከዚህ በኋላም ቤተ ክርስቲያን በአምዱ በቄርሎስ ሃይማኖት በእዳሪ ትንሽ አረፈች ውስጥ ውስጧን ግን የሮም ጅቦችና የአረብ ተኩላዎች በጎቿን ውስጥ ለውስጥ እየነጠቁ አላረፈችም የተሸሸገውን የሚያውቅ እግዚአብሔር የክህደታቸውን ኃጢያት እስኪገልጥባቸው ድረስ ፤ ለእርሱ ክብርና ምስጋና እስከ ዘላለሙ ይግባው አሜን! ”
ከዝክሪ ወጳውሊ መጽሐፍ በቀጥታ የተወሰደ (በወረቀት ከታተመው ላይ ከገጽ ፵፬ - ፶፫) ይቀጥላል ...
.......“በእውነት ይህን ዘማርያን የተባለው መናፍቅ ያስተምረው የነበረውን የክህደት ትምህርት የሐዋርያት፣ የነቢያት፣ የሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ትምህርት ነው ብሎ ለትውልድ ማስተማር ተገቢ ነውን? 
እኛስ እንላለን <<የሚያናውጡአችሁ የክርስቶስንም ወንጌል ሊያጣምሙ የሚወዱ አንዳንዶች አሉ እንጂ። ነገር ግን እኛ ብንሆን ወይም ከሰማይ መልአክ፥ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የሚለይ ወንጌልን ቢሰብክላችሁ፥ የተረገመ ይሁን። አስቀድመን እንዳልን እንዲሁ አሁን ሁለተኛ እላለሁ፥ ከተቀበላችሁት የተለየውን ማንም ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን>> ገላ ፩፥፯-፱ ብሎ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንደነገረን ነቢያት በተናገሩት፣ ሐዋርያት በሰበኩት ሊቃውንቱም በተረጎሙት ቃል ጸንተን እንኖራለን እንጅ አንናወጽም::” 

“እውነትን ግዛ አትሽጣትም፥ ጥበብን ተግሣጽን ማስተዋልንም” ምሳ ፳፫፥፳፫

[ከመጽሐፈ ዝክሪ ወጳውሊ የብራና በእትሙ ደግሞ ከምስጢረ ሃይማኖት ትንቢተ ዘዝክሪ ወጳውሊ ምዕ 8 ከገጽ 45 -53 ላይ የተወሰደ]

1 comment:

  1. በእውነት እናመሰግናለን። በርቱ!

    ReplyDelete