ልብ ያለህ አስተውል፣ ጆሮ ያለህ ስማ፣
እግርህ እንዳይገባ ከክህደት ከተማ::
የያዝከውን አጽና ልብህ አይጨነቅ፣
ለጥያቄህ መልስም ሊቃውንትን ጠይቅ::
ለእውነት የቆመ ሃይማኖቱን የሚያውቅ፣
ንባብ ትርጓሜን ጠንቅቆ የሚዘልቅ፣
ተናገር ዮሐንስ አንተ ልሳነ ወርቅ::
ቄርሎስን ጠይቀው የተቀብዐን ምስጢር፣
የክርስቶስ ነገር እንዴት እንደነበር፣
ከብሉይ ከሐዲስ በማቀነባበር፣
እንዳመሰጠረው በብዙ ምስክር::
ነቢዩ ኢሳይያስ ብርሃነ ዓለም ጳውሎስ፣
መዝሙረኛው ዳዊት ሐዋርያው ሉቃስ፣
አባ ዝክረ ማርያም ወአባ ጴጥሮስ፣
የስነ ፍጥረት ሊቅ ኤጲፋኒዮስ፣
ዝም አትበል ተናገር ቅዱስ ሳዊሮስ፣
በሥጋው መክበሩን አምላክ ክርስቶስ::
ጊዮርጊስ ተናገር አንተ የጥዋት ጮራ፣
ክርስቶስ መሲሕም ተብሎ እንደሚጠራ::
ወልድ ቅብዕ በማለት ክህደት አስተማሩ፣
የሥግው ቃል ነገር መች ገባቸው ዳሩ፣
የተዋሕዶ ምስጢር ሳይገባቸው ቅሉ፣
ሃይማኖት ከምስጢር ይደባልቃሉ::
ክርስቶስ በሥጋ እንደሞተ ሲያውቁ፣
በሥጋስ መክበሩን እንዴት አላወቁ፣
ሊቃውንት እያሉ ለምን አይጠይቁ፣
“በተዋህዶ ከበረ” ብለው ሲናገሩ፣
ለዚህ ብሂላቸው የታል ምስክሩ::
ግብርን በማፋለስ አንድ ገጽ ካለው ከሰባልዮስ፣
አንድነትን ትቶ ሁለት አካል ካለው ከርጉም ንስጥሮስ፣
መንፈስ ቅዱስ ሕጹፅ ካለው ከመቅዶንዮስ፣
ወልድ ፍጡር ካለው ከርጉም ከአርዮስ፣
የዚህም ክህደቱ በምንም አያንስ::
ፈላጊዋ ጠፍቶ “እውነት አለቀሰች”፣
ግብራቸው ተቃርኖ ሀሰት ጥላት ሄደች::
ዳሩ ግን ወገኔ ይህ ክህደት ነውና፣
ቀኑ ሳይመሽብህ መንገድህን አቅና፣
እውነትን ከፈለግክ ታገኛለህና፣
እረፍት ስላላት የህይወት ጎዳና፣
የያዝከውን ይዘህ በሃይማኖት ጽና::
No comments:
Post a Comment