Saturday, October 27, 2018

መሰረታችን ጽኑ ነው!

እውነትን አንለቅም፤ በክህደት አንጠመድም ብላችሁ አንጀታችሁ እያረረ፤ ዐይናችሁ የእንባ ውሃ እየቋጠረ፣ በምድር ላይ ሀሰት ነግሦ ውሸት ከምድር ልትጠፋ ብትቃረብም መጥፋት ግን ከቶ አትችልምና  እራሳቸውን “ተዋህዶ” ብለው በመለኮታዊ ምስጢር ስያሜ  የሚጠሩ ግብራቸውም:-
¨  ሰውን ማሳደድ አልፎም እስከ ማስገደል፣
¨  ሃይማኖትን በግድ እንዲቀበል ማስገደድ፣
¨  መጽሐፍትን መቆነጻጸል[ቃላትን እየቆረጡ ማውጣትና አጣሞ መተርጎም]፣
¨ለምን” እንዲህ ሆነ ብሎ የሚጠይቀውን ምዕመን መናፍቅ፣ ተሃድሶ በማለት እንዲሸማቀቅ ማድረግ ቤተ ክህነቱንና ቤተ መንግስቱን፤ ፖለቲካዉንና መንፈሳዊ ሕይወቱን መለየት እስኪያቅተን ድረስ ብልሹ አሰራርን በመስራታቸው ተቸግረናል::  

በተለይም ደግሞ ከሁለት አስርት አመታት በፊት የተመሰረተው እራሱን ማህበረ ቅዱሳን [ማህበረ ደናቁርት] ብሎ  የሚጠራው ቡድን ምንም እንኳን ቤተ ክርስቲያንን  እንደ ልጅ ሆኜ እታዘዛለሁ፣ አገለግላለሁ፣ ችግሯን ሁሉ ለመቅረፍ ሌት ከቀን ደፋ ቀና ብየ ቤተ ክርስቲያንን አስከብራለሁ በማለት መጀመሪያ መመሪያ ቢቀበልም እየዋለ እያደረ ግን እንደ ልጅ ሳይሆን እንደ ወንበዴ፣ እንደ መንፈሳዊ ሳይሆን እንደ ዓለማዊ  ገንዘቧን በተለያየ የመሰብሰቢያ ዜዴ በመጠቀም በራሱ ካዘና ሲያጠራቅም ይውላል ለተመልካችም ይመች ዘንድ በአካፋ ወስዶ በማንኪያ ይሰጣል::

ከዚህም አልፎ ተርፎ ደግሞ ሊቃነ ጳጳሳትን በሙሉ የእሱ ደጋፊ ለማድረግ የማይወጣው ዳገት የማይወርደው ቁልቁለት የለም:: ነገር ግን የእሱን እኩይ ተግባር የሚመለከቱ  ደግሞ ይህንን ክፉ ተግባሩን እንዲያቆም ቢናገሩም  እየሰሙ እንዳልሰሙ ያልፉታል ምክንያቱም ማህበሩን የሚነካ ሰው ከፊት ከኋላ፣ ከቀኝ  ከግራ  ሰው ይላክበታል [መጀመሪያ በፀባይ፤ ካልሆነም በኃይል] ከዚያ በፊት ግን ሁሉም ለጥቅም፣ ለዝና፣ ለክብር አጎብዳጅ ስለሆኑ ብዙዎች ሳይወዱ በግድ ዝምታን ይመርጣሉ::

ሰሞኑንም የሊቃውንት መፍለቂያ የሆነችውን የምስራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ማርቆስን ለስድስት ዓመታት ያህል የእነሱን ክህደት ስላልተቀበሉ፣ ያመነ የተጠመቀ ምዕመንን ዳግመኛ ስላላጠመቁ፣ ክፉ ጥፉ ሥራውን  በማየት ማህበረ ደናቁርትን ስላልደገፉ፣ ሌሎች ውጫዊ ጉትጎታዎችን [እንደ አቡነ ዘካርያስ ዘፍኖተ ሰላም] በመጠቀም የሸዋ ማህበር የሆነው ማህበረ እኩያን አቡኑን በተለያዩ  ምክንያቶች በመክሰስ፣ በድንጋይ በማባረር፣ ምዕመኑን በውሸት በማሳመፅ ሴራ ሲሰራ እንደኖረ የማይካድ ሀቅ ነው::

ለእኛ አቡነ ማርቆስ ቢኖሩ መልካም ነው እንደ አባት ይባርኩናል፣ ያስተምሩናልም:: ነገር ግን ከሀገረ ስብከቱ ቢነሱም “እኛ ያው እኛ ነን” ምክንያቱም መሰረታችን  ወልድ ዋህድ፣ ክርስቶስ፣ መሲህ፣ ማስያስ፣ ቅቡዕ፣ የተቀባ ተብሎ የተነገረለት ከኃጢያት ባርነት ነፃ ያወጣን የአብ አንድያ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለሆነ ነው:: ለወደፊቱ ከዚህ በፊት ከነበረው “ሰምቶ ማለፍ” ቀርቶ ሌላ መፍትሔ ስለሚኖር ቅያሬውን ብዙም አልጠላውም::   የሚመጡት ሊቀ ጳጳስስ እንዴት አድርገው እንደሚያስተዳድሩንም በዚያው ማየቱ መልካም ነው:: ቅዱስ ሲኖዶስም እንዲህ ጀምሮ እንደማይተወው ተስፋ አደርጋለሁ::

ነገር ግን በተዋህዶ ከበረ ብለው የሚያምኑ ወገኖች መጽሐፍቱን ታቅፈው ለምን ያስቀምጡታል? ዝም ብለው ቢያስቀምጡትም መልካም ነበር ቆማመጡት እንጅ! ወገኖቼ ለጊዜው ከሰው ላለመለየት፣ እንዳንገለል፣ ዝናችን፣ ክብራችን፣ ጥቅማችን እንዳይነካ ከእውነት ብንሸሽ የሆነ ጊዜ ግን እውነት እራሷ ትከሰናለች፣ ትታዘበናለች፣ የህሊና እረፍትን ትነሳናለችና ሁላችንም እውነት እንፈልጋት፣ ዝም ብለንም ከማመንና በደመ ነፍስ ከመነዳት እራሳችንን የት ላይ እንደሆን መፈተሽ ግድ ይለናል::
“እውነትን ግዛት አትሽጣትም” ምሳ 23፥23


No comments:

Post a Comment