በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ
አምላክ
=========================================
ሌቦች ወይንም ወንበዴዎች ስለምን ምሥራቅ
ጎጃምን ኢላማ አደረጉ?
=================================================
ዉድ
የፊት ገጽ ተከታታይ ወንድም እህቶቼ እንደምን አላችሁ?አግዚአብሔር ይመስገን እኔም ደህና ነኝ ፡፡ የዛሬዉ ጽሁፌ ከተለመደዉ የነገረ
ሥጋዌ ምሥጢር የተሰብአ እና የተቀብዐ አንቀጽ ቅርጹን ቀየር ያደረገ ፤ ነገር ግን መደረግ ያለበት ሁኖ ስላገኘሁት አንድ ነገር
ልላችሁ ወደድኩ ፡፡ የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት በጥንት አጠራሩ በአራጃ ሲታወቅ የብቸና እና የሞጣ አዎራጃዎች የነበሩት ነዉ
፡፡ ይህ ሀገረ ስብከት በብሉይ ኪዳን ከነበሩት ስድት ብሔረ ኦሪት መካከል ሁለቱን ይዞ ይገኛል ፤ እነሱም ርእሰ ርኡሳን መርጡ
ለማርያም ገዳም ና ደብረ ከርቤ ዳግማዊት ኢየሩሳሌም ደብረ ወርቅ ማርያም ገዳም ናቸዉ ፡፡ ይህ ሀገረ ስብከት ከሌሎቹ ሀገረ ስበከቶች
ለየት የሚያደርገዉ ደግሞ ሀገረ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በአዉሮፓዉያን የተሠራባትን ሴራ በመቃወም ቀዳሚዉ መሆኑ ነዉ
፡፡ አደራችሁን ለማበላለጥ እና ዘረኝነትን ለማስፋፋት የተጠቀምኩት አስመስላችሁ እንዳትወስዱት ፡፡ በመጀመሪያ ብንመለከት ቅድመ
ሱስንዮስ በዘመነ ገላዉዴዎስ ከአዉሮፓ የመጡ የካቶሊክ ሚሲዮናዉያን ኦርቶዶክስን ካቶሊክ ለማድረግ ሲጣጣሩ(ምንም እንኳ ኋላ መላዉ
ኦርቶዶክስን “ተዋሕዶ” የሚል ስም ሰጥተዉ “ምንታዌን” አሸክመዉት የሄዱ ቢሆንም) ፤ እንደነ ቅዱስ ቄርሎስ ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያንን
ወክለዉ የተገኙት የምሥራቅ ጎጃሟ የአቡነ ሲኖዳ በዓት ከነበረችዉ ደብረ ጽሙና መነኮሳት ሊቀ ካህናት አባ ዝክረ ማርያምና አባ ጴጥሮስ
የተሰኘ አባ ጳዉሊ ነበሩ ፡፡
የነዚህን ደጋግ አበዉ ሊቃነ ካህናት ሙሉ ታሪክ ለማግኘት በተለያዩ ጥታዉያን ገዳማትና አድባራት
( ጎንደር ቁስቋምን ጨምሮ) የሚገኘዉን ዝክሪ የተሰኘ የብራና መጽሐፍ መመልከት ይቻላል ፡፡ መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬም ቅርጹን
ወደ ካቶሊካዉያን ባህል(ወደ ምንታዌ) ቀይረዉታል እንጅ በመቅድመ መድሎተ አሚን የታሪኩን ጅማሬ አስቀምጠዉታል ፡፡
ይህ
የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት በመጻሕፍት ትርጓሜ ባለ ብዙ ሐተታና ምሥጢር አዘል ትንታኔ ከሌሎች ሀገረ ስብከቶች ለየት ያለ ነዉ
፡፡ በንጉሡ በፊት ከነበሩ የታሪክ ድርሳናት እንደምንረዳዉ በምሥራቅ ጎጃም የመጻሕፍት ትርጓሜ ይትበሀል አንድ መምህር ዐራት ዓይና
ለመባል በትንሹ የ37 ዓመታት ደጅ ጽናት ይጠይቀዉ እንደነበር መታዘብ ይቻላል ፡፡ በዜማዉም የኔቢጤ ሰነፍ ሊጮኸዉ የማይችል ፤
ልቡናን የሚመስጥ “ቆሜ” የተሰኘ ዜማ ትምህርትም የሚሰጥበት ሀገረ ስብከት ነበር ፡፡ በሊቃዉንት ጉባዔ የ4ቱ
ጉባዔ የምሥክር ጉባዔ ቤት ደብረ ወርቅ በነ መምህር ሰዉአገኝ (ሊቀ ሊቃዉንት) ይሰጥበት እንደነበር ታሪክ ያስታዉሰናል ፡፡ እነ
ሊቀ ሊቃዉንት መንክር መኮንን (ከእዝራ ሐዲስ በፊት የጎንደር ቤተ ጉባዔ መምህረ የነበሩ) ብሉያትንና ሊቃዉንትን ተምረዉ የተመረቁ
ከዚህ ከምሥራቅ ጎጃም ቤተ ጉባዔ ነዉ ፡፡ ከእነሱ በፊትም እነ ዐራት ዓይና ጎሹን ያህል ታላላቅ ሰዎች ያፈራ ሀገረ ስብከት ነዉ
ምሥራቅ ጎጃም ፡፡ በቅኔዉም በኩል እነ የኔታ ተስፋ ተገኝ(ቀራንዬ መድኃኒ ዓለም) ፤ እነ የንታ ፈንታ( መርጡ ለማርያም) ፤ እነ
የንታ ኄኖክ ፈንታን-------ሌሎች በእኔ አንደበት ተዘርዝረዉ የማያልቁ ሊቃዉንትን ፤ በድጓዉ ያልን እንደሆን እነ የኔታ ታየን
ያህል ዓለማዊነትን ከብሕትዉና ጋር አስተባብረዉ የተገኙ ደጋግ አበዉን ያፈራ ሀገረ ስብከት ፤ በኋላም እነ መምህር ይኸይስን ያፈራ
ሀገረ ስብከት ፤ እነ ሊቀ ሊቃዉንት የኔታ ገብረ ሥላሴን ፤ እነ ሊቀ ሊቃዉንት አያሌዉ ታምሩ ፤ እነ መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬን
የመሰሉ አበዉን ያወጣ ሀገረ ስብከት ነዉ ፡፡ ከዚህ ላይ እነ መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬን ለምን ጠራሃቸዉ ፡፡ እነሱ እኮ
“የተዋሕዶ ሊቃዉንት ናቸዉ በስማቸዉ መደበቅ አይቻልም” የምትሉ ወንድሞችና እህቶች ትኖሩ ይሆናል ፡፡ አዎ ሊቆች ናቸዉ ይሁን እንጅ
እነዚህ ሰዎች ዛሬ እናንተ እንደምታስቡት ጠባብ አእምሮ የነበራቸዉ ሳይሆኑ ፣ ጎጃምን ለመከፋፈል የማይጥሩ ልዩነታቸዉን በያሉበት
ይዘዉ ተቻችለዉ የሚኖሩ እንጅ “አንተ መናፍቅ ነህ እኛ ጻድቅ ነን” እያሉ ትዉልድን የሚበታትኑ ፣ ሀገር የሚያፈርሱ ባለመሆናቸዉ
ጠቀስኳቸዉ እንጅ በእነሱ ስም ልደበቅ ፈልጌ እንዳልሆነ ይታወቅልኝ ፡፡ ስለ አኗኗራቸዉ (በተለይ የስድስቶ(መልአከ ብርሃን አድማሱ
ጀንበሬ)ና የመሪጌታ ይኸይስን አነጋር) ተከባብረዉ ፣ ተፈራርተዉ የሚኖሩ እንደነበሩ በቅርቡ በህይወት ካሉ አንድ አባት አረጋግጫለሁ
፡፡
ወደ
ቀደመ ነገሬ ልመለስና ይህንን ሙሉ የሆነ ሀገረ ስብከት ካለፉት 40 ዓመታት ወዲህ ግን ምንም የሌለዉ ለማድረግ አቅዶ የሚሰራ የሰይጣን
ቡድን ያለ ይመሥለኛል ፡፡ ለዚህም ብናነሣ ምሥራቅ ጎጃም ከብሔረ ኦሪት ጀምሮ አምልኮተ እግዚአብሔርን ሲተገብር የነበር ሕዝብ መሆኑ
እየታወቀ ፤ “ካቶሊኮች ቅብዓት የሚባል እሾህ ተከሉብህ” ተብሎ ካለ ስሙ ስም ፣ ካለ ግብሩ ግብረ ተሰጥቶስ ይገኛል ፡፡ ከታሪክ
ድርሳናት እንደምንረዳዉ ካቶሊካዉያን ከሀገራቸዉ እንደመጡ ለመጀመሪያ ጊዜ የተቀመጡት ጎንደርና ትግራይ ክፍለ ሀገር ነዉ ፡፡ እሾህ
ተከሉ ተብሎ የተተረተለት ግን ለምሥራቅ ጎጃም ነዉ ፡፡ እጅጉን ሲደንቀኝ የሚኖረዉ ጉዳይ ደግሞ ካቶሊካዉያንን ተከራክረዉ አሸንፈዉ
ትክክለኛዉን የኢትዮጵያን ሃይማኖት እንዲጸና የተናገሩት ሁለቱ የምሥራቅ ጎጃም ካህናት ሁነዉ ሳለ የእነዚህን አባቶች ስም ለማጥፋት
በሚመስል አሠራር “ቅብዓቶች በብዛት ጎጃም ደብረ ወርቅ ይገኛሉ” እየተባለ
ታሪከ ነገሥትን ጨምሮ በተለያዩ የተረት ተረት መጻሕፍት ላይ ተጽፎ መገኘቱ ነዉ ፡፡ እነዚያ ካቶሊካዉያ አንድ ወልድን
ሁለት ግብር ፣ ሁለት ጠባይዕ አለዉ ብለዉ የሚያምኑ መሆኑን እሾህ ተከለ ከሚባለዉ ከሜንዴዝ አልፎንሱ አንደበት መመልከት ይቻላል
፡፡ እዉነታዉ ሜንዴዝ አልፎንሱ ምንታዌን(ሁለትነትን) የሚያምን ካቶሊካዊ ሲሆን “ቅብዓትን አስተማረ” በማለት የነቢያትን ፣ የሐዋርያትን
፣ የሊቃዉንትን አስተምህሮ ለአልፎንሱ በማሸከም ይህንን ደገኛ ሀገረ ስብከት ከሐዲ አስመስለዉ አቅርበዉ ትዉልድን ለማጥፈት የተሰለፉት
ዘራፊዎች ዛሬ ሳይሆን ጥንትም እንደነበሩ ማስተዋል ይቻላል ፡፡ ከዚህ ላይ እንደጥያቄ
በእዉነቱ ለመመጻደቅ
ሳይሆን እዉነትን ለመናር የምሥራቅ ጎጃም ሃይማኖቱ የአልፎንሱ ሜንዴስ ቢሆን ኖሮ፡-
v ሁለት አካል ፣ ሁለት ባሕርይ ፣ ሁለተ ጠባይዕ የሚል አይሆንም ነበርን?
v የጽድቅ መጀመሪያና መጨረሻ ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያምን ወለተ ዳዊት ወላዲተ አምላክ እያለ
የሚያምን በሆነ ነበርን?
v ሱስንዮስ ንጉሥ ዓርብና ረቡዕ ጾምን ሻሩ ፤ ሰንበትን አታክብሩ ብሎ የክሕደት አዋጁን በማወጅ
ብዙዎችን ሲገድላቸዉ ፤ ያኔ የምሥራቅ ጎጃም ምእመን በሰይፍ እየተቀላ ባለቀ ነበርን?ዛሬ ላይ ያለዉ አርሶ አደሩ ሳይቀር የሰንበት
አከባበር ሥርዓቱ ካቶሊካዊ የሚያስብለዉ ነበርን?
ከዚያ
ጊዜ ጀምሮ ምሥራቅ ጎጃም አርፎ እንዳይቀመጥ ከራሱ እጣ የሚሆን ደብረ ድማኅን አስነስቶ “በተዋሕዶ ከበረ ወልድ ቅብዕ ፤ አካለ
ቃል አካለ ሥጋን አከበረ ለካለ ሥጋ ክብር ሆነ” የሚለዉን የሮማዉያንን የምንታዌ ባህል እንዲያስተምር በማደራጀት እርስ በእርሱ
እየተናቆረ አንድ ቀን እንኳን በሠላም እንዳያድር የሚያደርጉት ሌቦች ዘራፊዎች ስመለከታቸዉ እጅጉን ይገርሙኛል ፡፡
እስከ
2004 ዓ.ም ድረስ ሀገረ ስብከቱ ምንም የልማት እንቅስቃሴ (ከጎንቻና ከሁለት እጁ እነሴ ገዳማት በስተቀር) ሳይኖርበት የቆየ
መሆኑንም ልብ ስንል እጅጉን አንገት የሚያስደፋ ሁኖ እንመለከተዋለን ፡፡ በአቡነ ዘካርያስ ጊዜ የተጀመረዉ የእርስ በእርስ ብጥብጥ
በዚያን ጊዜ ቅዱስ ጳዉሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ብሉያትን የሚያስተምሩ በነበሩት ዐራት ዓይናዉ ሊቅ በየኔታ ገብረ ሥላሴ በተጻፈ የተሰብአንና
የተቀብዓን አንቀጽ የሚገልጽ ደብዳቤ አማካኝነት አቡነ ዘካርያስ ከጀመሩት የመለያየትና የመበታተን ሤራ ረገብ ብሎ ትንሽ ከቆየ በኋላ
በአሁኑ ወቅት ቢገኝ time value of money ታክሎበት በቢሊዮን ሊቆጠር የሚችል ፤ ከ 2.5 ሚሊዮን በላይ የሀገረ ስብከቱን
ብር ሙልጭ አድርገዉ በሚሊንየሙ መባቻ ወደ ምዕራቡ የዓለማችን ግዛት ወደ ሀገረ አሜሪካ ይዘዉ ኮበለሉ ፡፡ ሀገረ ስብከቱም “ኢትሥረቅን”
የተላለፉ አባት በማግኘቱ እጅጉን አዝኖ ተክዞ በተቀመጠ ከ 4 ዓመት በኋላ አቡነ ማርቆስ ተመደቡለት ፡፡ እናስተዉል ይህ ሀገረ
ስብከት የነበሩት ቤተ ጉባኤዎቹ ተዳክመዉ አንዳንዶቹ ጭራሹንም ተዘግተዉ በአብነት ትምህርት ቤት የነበረዉ አስተዋጽኦ እንዲህ ነበር የሚባል ብቻ ሁኖ ዛሬ እገሌ የሚባል ሥመጥር ሊቅ ሳይኖረዉ
ራቁቱን እንዲቀር ተደረገ ፡፡ ይባስ ብሎም ሌላ ሊቅ እንኳን እንዳይቀጠር ገንዘቡን ሙጥጥ አድርገዉ ይዘዉበት ኮበለሉ አባቱ አባ
ዘካርያስ ፡፡ ይህ አደባባይ የሚያዉቀዉ ነባራዊ ሀቅ ነዉ ፡፡ ከ2004 ዓም ወዲህ ግን አዳዲስ አብያተ ክርስቲያናት እየታነጹ ፤
የካህናት ማሰልጠኛዎች ሊገነቡ ታቅዶ(ለምሳሌ የደብረ ወርቁ) ፤ አባ ዘካርያስ በነበሩበት ጊዜ የነበረዉ አንተ ቅብዓት ነህ ፣ አንተ
ተዋሕዶ ነህ የሚለዉ የአለአዋቂ ንግግር ቀርቶ ሁለቱም ወገን በአለበት መንቀሳቀስና ቤተክርስቲያንን ማልማት ሲጀምር ፤ ደብረ ማርቆስ
ላይ ማዕከሉን በከፈተ “ማኅበረ ቅዱሳን” በሚባል ድርጅት አሳሳቢነትና ነገር ቆስቋሽነት ያን ባለዉለታ ሕዝብ ድጋሚ በማጥመቅ የሀገረ
ስብከቱን ማንነት ከነጭራሹ ወደ ማጥፋት እኩይ ተግባር ገቡ ሌቦቹ ፡፡ ከዚህ ላይ “እንዲያዉ ማኅበረ ቅዱሳንን ካልጠራህ አይሳካልህምን?”
የምትሉኝ ትኖሩ ይሆናል ፡፡ “ማቅ” በአገልግሎቱ በአንድ በኩል ጥሩ እየሠራ እንደሆነ እኔም አምናለሁ ፣ አብሬም ሠርቻለሁ ፤ ነገር ግን በሌላኘዉ በኩል አባቱን የማያከብር ትዉልድ እየፈጠረ ያለ ድርጅት
መሆኑንም መዘንጋት የለብንም ፤ እገሌ ጳጳስ የእኛ ፣ እገሌ የሚባለዉ አባት የእኛ ፤ እገሌ ተሐድሶ ፣ እገሌ ጳጳስ መናፍቅ ፣
እገሌ ካህን መናፍቅ…….ምናምን ፣ ምናምን እያልን በባዶዉ አእምሯችን
እንድንስል ያደረገን እሱ ነዉ ፤ እሱ ሳንሱር ያላደረገዉን መዝሙር እንዳንዘምር ያደረገን እሱ ነዉ ፤ የእሱ ስም ከሌለበት መጻሕፍትን
እንዳንገዛ እንዳናነብ በማድረግ ሁለተኛ ሲኖዶስ የሆነብን ይህ ማኅበር ነዉ ፡፡ እገሌ ካህን “መናፍቅ” ስለሆነ ከእሱ መስቀል እንዳትሳለሙ
እያለ አባቱን የማያከብር ትዉልድ የፈጠረ እሱ ነዉ ፡፡ ምሥራቅ ጎጃም ዉስጥ ከዲማ ዉጭ ሌላ ቦታ ሂዳችሁ ተክሊል እንዳትፈጽሙ ፣
እንዳትቆርቡ…………እያለ ለቤተክርስቲያን ያለንን ፍቅር አነሥተኛ እንዲሆን ያደረገን ስለሆነ ስሙን አንስቸዋለሁ ፡፡
ወደ
ቀደመ ነገሬ ልመለስና አባ ዘካርያስ ዘርፈዉት ሲሄዱ ዝም ያለ ምእመን አባ ማርቆስ ልማት አስለምተዉ በአቡነ ቴዎፍሎስ ስም ሰይመዉ
ሲያስመርቁለት እሳቸዉን በድንጋይ ለማስወገር ቆርጦ ተነሣ ፡፡ ታዲያ ይህ የሌቦቹ ትኩረት አይደለምን? ፤ አቡነ ዘካርያስ ከነ ጫማቸዉ
ቤተ መቅደስ ድረስ ሲገቡ ዝም ብሎ የነበረ ምዕመን ፤ አቡነ ማርቆስ በቅዳሴ ጊዜ “ዳዊት መድገም ፣ አንቀጸ ብርሃን መድገም ፣
ሰኔ ጎልጎታ መድገም አያስፈልግም” ብለዉ ሲናገሩ መናፍቅ ተብለዉ መፈረጃቸዉ ምክንያቱ ምን ይሆን? ፤ አዲስ አበባ ላይ በዘመነ
ጽጌ ፍሪዳ ተጥሎ ፣ ከፍሪዳም በላይ ቅዳሴ ጥዋት እየተቀደሰ አማናዊ ፍሪዳ መድኃኔ ዓለም ኢየሱስ ክርስተቶስ ሥጋዉ እየተቆረሰ ደሙ
እየተፈተተ ሳለ ፤ አቡነ ማርቆስ “ጽጌ ጾም” የአዋጅ አይደለም ብለዉ በመናገራቸዉ “ጽጌ ጾም አያስፈልግም አሉ” እየተባለ የሚወራዉ
ድስኩርስ ምንጩ ምን ይሆን?
እኔ
ግን ስገምተዉ ሀገረ ስብከቱ ከስሙ ባለፈ በሁሉም ነገር አሸብርቆ እንዳይቀጥል ምንም የማያዉቀዉን ምእመን እያነሳሱና እያስጮሁ ካህናትን
የማያከብር ትዉልድ በመፍጠር ሀገረ ስብከቱን ለመጣልና ፤ ከሌቦቹ ጋር የተስማማ ሊቀ ጳጳስ አስመድቦ ሀገረ ስብከቱነ ድጋሚ ለመበዝበዝ
የታሰበ ሴራ ነዉ ብየ አምናለሁ ፡፡
ምክንያቱም
የቅብዓትና
የተዋሕዶ ክርክር አሁን በአባ ማርቆስ ጵጵስና ዘመን የመጣ ሳይሆን ያኔ እነ ሱስንዮስ ሁለተኛ ጥምቀትን ፣ ሰንበትን ማበር መሻርን
፣ የዓርብና የረቡዕ ጾም መሻርን ባመጡ ጊዜ ቅብዓቶች የሚባሉት ወገኖች የቀደመዉን ክርስትና አጽንተዉ በመያዛቸዉ ገለል ተደርገዉ
ዝም ብሎ ተዋሕዶ ፣ ተዋሕዶ እያለ ምሥጢሩንና እዉነታዉን ሳይረዳዉ ወደነፈሰበት እየነፈሰ የሚገኝ ትዉልድ መፈጠሩ የሴራዉ አንድ
አካል ነዉ ፡፡
ሲጠቃለል
በአቡነ ማርቆስ ላይ የተቃጣዉ የግድያ እና የዉግረት ሴራ የምሥራቅ ጎጃምን ሀገረ ስብከት እንደ ቀድሞዉ አባት አባ ዘካርያስ በገንዘብም
፣ በአእምሮም ፣ በልማትም በሁሉም ነገር ዘርፎ ሽባ አድርጎ ለማስቀረት እንደሆነ አስበን ሁላችንም ከአፍራሽ ተግባ ተቆጥበን ታሪክ
የማይሽረዉ ሥራ ብንሠራ መልካም ነዉ እላለሁ ፡፡ አመሠግናለሁ ፡፡
No comments:
Post a Comment