Thursday, September 27, 2018

“ኤዎስጣቴዎስ ከፋሌ ባሕር”

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ!

አንተ ት(ኮ)ንን ኃይለ ባሕር---ውቅያኖስን የምትገዛ አንተ ነህ ፤ ወአንተ ታረምሞ ለድምፀ ማዕበላ---እስከ ዝየ ብጽሒ ብለህ የውቅያኖስን ማዕበል ሞገዷን ፀጥ የምታደርገው አንተ ነህ ፡፡  አንተ አኅሠርኮ ለዕቡይ ከመ ቅቱል--- ሌዋታንን እንደሞተ ያዋረድከው አንተ ነህ ማለት በባሕር ተወስኖ እንዲኖር  ያደረግኸው  አንተ ነህ”   መዝ   88፥ 9-10
============================================

አመ አሥሩ ወሰሙኑ ለመስከረም በዛቲ ዕለት ኤዎስጣቴዎስ መምህረ ሃይማኖት ወሰባኬ ወንጌል--አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም መስከረም ዐሥራ ስምንት በዚህች ቀን ወንጌልን የሚሰብክ  የሃይማኖት መምህር አባታችን ኤዎስጣቴዎስ አረፈ ፡፡ የዚህም ቅዱስ የአባቱ ሥም  ክርስቶስ ሞዓና የእና ስም ስነ ሕይወት ይባላል ፡፡ ሁለቱም ደጋጐች እግዚአብሔርን የሚፈሩና በሕጉ የሚኖሩ ነበሩ ፡፡ 

ከዚህም በኋላ በከበረ መልአክ በቅዱስ ገብርኤል  አብሣረነት  ይህን ቅዱስ ወለዱት ስሙን የጌታ ጥብቅ  ብለው ሰየሙት ፡፡ በአደገም ጊዜ የዳዊትን መዝሙርና ፣ የቤተክርስቲያንን መጻሕፍት  አስተማሩት ፡፡ ከዚህም በኋላ የእናቱ አባ ዘካርያስ ወደአለበት  የመነኰሳት ገዳም ወሰዱት ፡፡ አባ ዘካርያስም የእግዚአብሔርን ጸጋ እንዳደረበት አውቆ የምንኵስናን ሥርዓት አስተምሮ የመላእክትን አስኬማ አለበሰው ፡፡ ከገድሉ ጽናት የተነሣ በገዳም ያሉ አረጋውያን እስኪያደንቁ ድረስ በጾም ፣ በጸሎት  የተጠመደ ሆነ እርሱ በጥበብና በዕውቀት የጸና ነውና ፡፡

ከጥቂት ጊዜ በኋላም ዲቁና ተሾመ ፡፡ የዲያቆናት አለቃ እንደሆነ እንደ እስጢፋኖስም ለቤተክርስቲያን አገለገለ ፡፡ ከዚህ በኋላ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሚካኤልና  ከገብርኤል ጋር ተገለጠለትና ሰላምታ ሰጠዉ በንፍሐትም መንፈስ ቅዱስን አሳደረበት  እንዲህም አለዉ ወዳጄ ኤዎስጣቴዎስ  ሆይ  እኔ ከእናትህ ማሕፀን መረጥኩህ  ያለ ፍርሀትና ድንጋፄ ወንጌልን ለብዙዎች ሕዝቦች ትሰብክ ዘንድ  ከኢተየጵያ እስከ አርመንያ ድረስ መምህር አደረግሁህ አንተን  የሰማ እኔን ሰማ ፤ አንተን ያልሰማ እኔን አልሰማም ፤ ጌታችን ይህንን ተናግሮ ወደ ሰማይ በክብር ዐረገ ፡፡ ቅዱስ ኦዎስጣቴዎስ ወደጳጳስ ቅስና ተሸመ ፡፡

 የወንጌልንም ሃይማኖት  ይሰብክ ዘንድ ጀመረ ፤ ብዙ ሰዎች ወደእርሱ  እስኪሰበሰቡ ድረስ  በእርሱም እጅ መንኵሰው ደቀመዛሙርትን  ሆኑ ፤ ከእርሳቸውም ታላቁ አብሳዲ ነው ፡፡ ብዙዎችንም የከፋች ሥራቸዉን አስትቶ ከክህደታቸው መለሳቸው ፤ ትምህርቱም በሀገሩ ሁሉ ደረሰ በመላ ዘመኑም የሰንበታትና የበዓላት አከባበር የጸና ሁኖ ተሠራ ከሐዋርያትም ሕግና ሥርዓት ወደቀኝም ሆነ ወደግራ ሁሉም ፈቀቅ አላሉም ፡፡ ወደ ኢየሩሳሌምም  ሁለት ጊዜ ሔደ እግዚአብሔርም በእጆቹ የዕውራንን ዐይን በማብራት አንካሶችንና ጎባጦችን በማቅናት ፣ አጋንንትን በማስወጣት ቁጥር የሌላቸውን ተአምራት አደረገ ፡፡ ከዚህ በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም በእግዚአብሔር ፈቃድ ለመሔድ ባሰበ ጊዜ ለጆቹን ሰብስቦ  የመነኰሳትን ሥርዓት ይጠብቁ ዘንድ  ከመናፍቃንም ጋር እንዳይቀላቀሉ አማፀናቸዉ ፤ ልጁ አብሳዲንም በእነርሱ ላይ ሾመውና ወደኢየሩሳሌም ሰንበትን እያከበረና የክርስቶስን  ሃይማኖት እያስተማረ ሔደ ፡፡ ወደ ሊቀ ጳጳሳት አባ ብንያሚን ደርሶ ከእርሱ ቡራኬ ተቀበለ ፤ የሃይማኖትንም ነገር ተነጋገሩ ፡፡ 

ዳግመኛም ከከበሩ ቦታዎች መሳለም በረከትን ተቀበለ በዮርዳኖስም ተጠመቀ ፡፡ ከዚያም ወደ አርመንያ አገር ሔደ ፤ ወደ ኢያሪኮ ባሕርም ሲደርስ በመርከባቸው ያሳፍሩት ዘንድ መርከበኞችን  ለመናቸው በከለከሉትም ጊዜ ዓጽፉን በባሕሩ ላይ ዘረጋ በቅድስት ሥላሴ ስም በላዩ ባረከ ፤ራሱንም በመስቀል ምልክት  ምልክት አማተበ ፡፡  እንደ መርከብም ሁኖለት  በላዩ ተጫነ  ሁለት መላእክትም  ቀዛፊዎች  ጌታችንም እንደ ሊቀ ሐመር ሆኑለት ፡፡ ከባሕሩም ግርማ የተነሣ እንዳይፈሩ ልጆቹን አጸናቸው ፤ እንዲህም አላቸው “ልጆቼ በልባሁ ቂምንና ሽንገላን እንዳታኖሩ ተጠበቁ ፤ ለኔ ግን ከእናንተ አንዱ እንደሚጠፋ  ይመስለኛል ፤ ይህን ሲናገር ልቡ የቂም የበቀል ማከማቻ  ስለሆነ ወዲያውኑ አንዱ ከእነሱ መካከል ሠጠመ ፡፡ በእግዚአብሔርም ፈቃድ ባሕሩን ተሸግሮ ወደ አርመንያ ከተማ ደርሶ ከሊቀ ጳጳሳቱ ጋር ተገናኘ  ሰገደለትም ከእርሱ ቡራኬን ተቀበለ ሊቀጳጳሱም በአየው ጊዜ  ታላቅ ደስታን ደስ አለው በፍቅርም ተቀበለው ፡፡

አባታችን ኤዎስጣቴዎስም  ሁሉም በትምህርቱ አንድ እስኪሆኑ ድረስ የአርመንያን ሐዋርያት በሲኖዶሳቸው የሠሩትን ሥርዓት እያስተማራቸው ኖረ ፡፡
ከዚህም በኋላ ዕረፍቱ ሲደርስ ክብር ይግባውና ጌታችን ተገለጠለትና ስሙን ለሚጠራ ፣ መታሰቢያውን ለሚያደርግ ፣ ገድሉን ለሚጽፍ ለሚያጽፍ ቃል ኪዳንን ሰጠው ፡፡ በአረፈም ጊዜ ጳጳሳትና ካህናት በታላቅ ክብር ገንዘው በሰማዕቱ በቅዱስ መርምህናም  ቤተክርስቲያን ውስጥ ቀበሩት ከሥጋውም ብዙ ተአምራት ተገለጡ ፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር ኪያነኒ ይምሐረነ ፤
ጸሎቱ ወበረከቱ ተሀሉ ምስሌነ ፤
     ለዓለመ ዓለም አሜን

አርኬ፡- ሰላም ዕብል ለዘረከብከ ሞገሰ ምስለ ፈጣሪ ትትናገር ሡዔያተ ሠላሰ ፤
     ኤዎስጣቴዎስ ዘሦጥከ ዲበ በድነ ሕፃን ነፍሰ ፤
     ጊዜ ዐደውከ ማዕበላጠ ዘአልቦ አርማሰ ፤
በዘባነ ባሕር እንዘ ትሰፍሕ ልብሰ ፡፡

ከጻድቁ በረከት ለመሳተፍ የምትፈልጉ ዛሬ መስከረም 18/ 2010 ብሔረ ኦሪት ርዕስ  አድባራት ወገዳማት ዳግማዊት ኢየሩሳሌም ደብረወርቅ ማርያም ገዳም ንግስ ስላለ ሔዳችሁ መሳተፍ ትችላላችሁ ፡፡ ሐይማኖት መሢሐዊትንም እንዲሁ ስትሰበክ ሰምታችሁትመጣላችሁ ፡፡ የደብር ፍሬዎች እና መላዉ ኦርቶዶክሳዉያን እንኳን አደረሳችሁ ፡፡




No comments:

Post a Comment