Wednesday, September 26, 2018

“ፍልሰተ ሥጋሁ ለቅዱስ እስጢፋኖስ ወአባ ጴጥሮስ”

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ
“ፍልሰተ ሥጋሁ ለቅዱስ እስጢፋኖስ ወአባ ጴጥሮስ”
========================

አመ  አሥሩ ወሐሙሱ ለመስከረም በዛቲ ዕለት ኮነት ፍልሰተ ሥጋሁ ለቅዱስ እስጢፋኖስ ሊቀ ዲያቆናት ወቀዳሜ ሰማዕት--መስከረም አሥራ አምስት በዚህች ቀን  የዲያቆናት አለቃና የሰማዕታት መጀመሪያ ለሆነ ለቅዱስ እስጢፋኖስ ፍልሰተ ሥጋው ሆነ ፡፡ ይህም እንዲህ ነው ከአረፈበት ጊዜ ብዙ ዓመታት ካለፉ በኋላ ሦስት መቶ ዓመታ ያህል ከዚህም በሚበዛ ዘመን ጻድቁ ቈስጠንጢኖስ ሲነግሥ ፤ የቀናች ሃይማኖት ተገልጣ የሕያው የእግዚአብሔር አምልኮት በሁሉ ሲዘረጋ ያን ጊዜ የቅዱስ እስጢፋኖስ ሥጋ በአለበት አቅራቢያ የገማልያል ቦታ በምትባል በኢየሩሳሌም በአንዲት ቦታ ሰው ይኖር ነበር ፡፡የዚያ ሰው ስም ሎክያኖስ ይባል ነበር ፡፡
ተጋዳይ የሆነ እስጢፋኖስም ብዙ ጊዜ በሕልም ተገለጠለት ፡፡ እንዲህም ብሎ አስረዳው “አነ ውእቱ እስጢፋኖስ ወየጠየቆ  ከመ በውእቱ መካን ሀሎ ሥጋየ  ቅቡረ” ፤ ያም ሉክያኖስ የሚባል ሰው የኢየሩሳሌም ኤጲስ ቆጶስ ወደሆነው ሰው መጥቶ ነገረው ፡፡ኤጲስ ቆጶሱም እጅግ  ሰምቶ እጅግ ደስ አለው ፡፡ያን ጊዜም ሁለት ኤጲስ ቆጶሳትን ፣  ካናትንና የቤተክርስቲያን ሰዎችን ሁሉ ከእርሱ ጋር ይዞ  ተነሣ ፡፡ የቅዱስ እስጢፋኖስ ሥጋው በውስጡ ቀዳለበት ወደዚያ ሥፍራ  ደርሰው ሊቆፍሩት ጀመሩ፤ ታላቅ ንውጽውጽታም ሆኖ ፤ የቅዱስ እስጢፋኖስ ሥጋ  በውስጡ ያለበት ሣጥን ተገለጠ ከእርሱም  እጅግ በጐ የሆነ  የሽቱ መዓዛ ሸተተ ፡፡ “በሰማያት ለእግዚአብሔር ምስጋና ሆነ ፣ በምድርም ሰላም ለሰው ነፃነቱ ይሰው ዘንድ በጐ ፈቃድ” እያሉ ሲያመሰግኑ የመላእክትን ድምጽ ሰሙ ፡፡እንዲሁም መላልሰው ሦስት ጊዜ አመሰገኑ ኤጲስ ቆጶሳቱና ካህናቱ ቅዱስ እስጢፋኖስን በያዘ ሣጥን ፊት ለጌታ ሰገዱ ፡፡ ከዚህም በኋላ ወደጽርሐ ጽዮን እስኪያደርሱት ብዙ መብራቶችን አብርተው በመያዝ በማኅሌት ምስጋና እየዘመሩ ተሸከሙት ፡፡

 ከዚህም በኋላ እንዲህ ሆነ በኢየሩሳሌም ነዋሪ የሆነ  የቁስጥንጥንያ  ተወላጅ ስሙ እለእስክንድሮስ የሚባል ሰው ነበር ፡፡ ለቅዱስ እስጢፋኖስም ውብ የሆነች  ቤተክርስቲያንን ሠርቶለት  ሥጋውን አፍልሰው ወደእርሷ ወስደው አኖሩት ፡፡ በአምስት ዓመት በኋላም  እለእስክንድሮስ አረፈ ሚስቱም  በቅዱስ እስጢፋኖስ አስከሬን ጐን  ቀበረችው ፡፡ ከሌሎችም አምስት ዓመታት  በኋላ የእለ እስክንድሮስ ሚስት የባሏን  አስክሬን ወደ ቁስጥንጥንያ አገር  ይዛ ልትሔድ አሰበች ፡፡ በሏን ወደቀበረችበት ባሏ ወዳሰራት ቤተክርስቲያን  ሔደች ፡፡   የባሏ ሥጋ ሳጥን ግን የቅዱስ እስጢፋኖስን ሥጋ በያዘ ሣጥን አምሳል ነበር ፡፡ በእግዚአብሔርም ፈቃድ የቅዱስ እስጢፋኖስን  ሣጥን ወስዳ እስከ አስቃላን  ከተማ ተሸከመችው ከዚያም ወደ ቁስጥንጥንያ ልትጓዝ በመርከብ ተሳፈረች ፡፡በመርከብም ስትጓዝ ከሳጥኑ ጣዕም ያለው  ምስጋና የምትሰማ ሆነች ፤ እጅግም አድንቃ ያንን ሳጥን ልታየው ተነሳች ፡፡

በውሰጡ የቅዱስ እስጢፋኖስ  ሥጋ ያለበት እንደሆነም ተረዳች ፡፡ ይህም የሆነው ክብር ይግባውና  በእግዚአብሔር ፈቃድ እንደሆነ አወቀች ፡፡  ወደኢየሩሳሌም ትመለስ ዘንድ  አልተቻላትም ፡፡ ይህንንም ታላቅ ፀጋ ስለሰጣት እግዚአብሔርን አመሰገነች ፡፡ወደ ቁስጥንጥንያ አገርም በደረሰች ጊዜ ወደ ንጉሡ ሔዳ የቅዱስ እስጢፋኖስን  ዜና ፣ ከእርሱ የሆኑትን  ተአምራት ፣ወደቁስጥንጥንያ አገር ወደብም እንደደረሰ ነገረችው ፡፡ ሰምቶም እጅግ ደስ አለው ፡፡  ንጉሡም ከሊቀ ጳጳሳቱና  ከካህናቱ ፣ ከብዙ ሕዝቦች ጋር ወጣ ፡፡ ከወደብም አንስተው በክብር ወደ መንግሥት አዳራሽ እስከ አስገቡበት ድረስ በፍጹም እየዘመሩና እያመሰገኑ ተሸክመውት ተጓዙ ፡፡ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም  ከእርሱ ተአምራትን  ገለጠ በሠረገላ ሥጋውን ጭነው በሁለት በቅሎዎች በሚስቡት ጊዜ ቆስጠንጢኒዮስ ከሚሉት ቦታ ሲደርሱ የቅዱስ እስጢፋኖስን ሥጋ በዚያ እንዲያኖሩት ስለፈቀደ  የሚስቡት በቅሎዎች ቆሙ አልተንቀሳቀሱም ፡፡ በቅሎዎችንም ይመቷቸው ጀመሩ ፡፡ “የቅዱስ እስጢፋኖስን ሥጋ  በዚህ ሊያኖሩት ይገባል” የሚል ቃል ከአንዱ በቅሎ ሰሙ ፤ ይህንንም ያዩና የሰሙ ሁሉ አደነቁ ፡፡  እግዚአብሔርንም አመሰገኑ ፡፡

 የበለዓምን አህያ ያናገራት እኒህንም የቅዱስ እስጢፋኖስን ሥጋ የተሸከሙ በቅሎዎችን ያናገረ እግዚአብሔር እንደሆነ አወቁ ፡፡ ንጉሡም በዚያ መልካም የሆነች ቤተክርስቲያን  ሠርተው ይህንን የከበረና ንጹሕ የሆነ ዕንቈ ባሕርይ  በውስጧ እንዲያኖሩ አዘዘ ፡፡ ይኸውም ለተመሰገነና ለተባረከ ሐዋርያ ለዲያቆናት አለቃና የሰማዕታት መጀመሪያ ለሆነ ለእስጢፋኖስ ሥጋው ነው ፡፡ 
 ወስብሐት ለእግዚአብሔር 
 ኪያነኒ ይምሐረነ  በጸሎቱ ለቅዱስ እስጢፋኖስ  ወበረከቱተሀሉ ምስሌነ ለዓለመ ዓለም አሜን
አርኬ፡-ሰላም ለእስጢፋኖስ አፍልሶ ሥጋሁ ዘተሀበሉ፤
በዲበ አብቅልት ክልኤቱ እንዘ ያሌዕሉ፤
አመ ነድእዎሙ ሶበ ለርእዮ ዐቢይ ኃይሉ፤
ነበበ በቅል እንዘ ይብል አሐዱ እምእሉ ፤
መካነ ሥጋሁ ለቅዱስ ዘዝየ ይሄሉ ፡፡
ወበዛቲ ዕለት ካዕበ ኮነ  ተዝካረ ዕረፍቱ ለአብ ክቡር  ወጻድቅ አባ ጴጥሮስ  ዘአእምሐገረ ጠራው --በዚህችም ዕለት ጠራው ከሚባል ሐገር ለከበረ  ጻድቅ አባት አባ ጴጥሮስ  የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው ፡፡
 ይህም ቅዱስ ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ  ለእግዚአብሔር የተሰጠ የስእለት ልጅ ነው ፡፡  በአደገም ጊዜ ለታላቅ ተጋድሎ  ከልቡ በቆራጥነት ተነሣ ፤ በቀን በሌሊት በጾም በጸሎት  ተወስኖ ሁል ጊዜ  እግዚአብሔርን የሚያገለግል ሆነ ፡፡ ሰው የሚመገበውን  ምንም አይመገብም ፤ በዱር  ያገኘውን ጥቂት ሣርን ይመገባል እንጅ ፡፡  ደገኛው ምግቡ ግን  ክብር  ይግባውና የጌታችን  ኢየሱስ ክርስቶስን ስም ማመስገን ነው ፡፡  በዚህም  ምግባቸው  የእግዚአብሔር  ምስጋና  የሆነ መላእክትን መሰላቸው ፡፡

 አሎን በሚባል የወንዝ ውኃ ላይም ይመላለስ ዘንድ  ተገባው  እግሮቹም  አይርሱም ፤ ሥጋ እንደሌለው መንፈስ እስከሚሆን  በሕይወቱ ዘመን ሁሉ  ከችግር ብዛትና  ከሚለብሰው የብረት ልብስ ክብደት የተነሣ  ሥጋው እጅግ ደርቆ  የረቀቀ ሆኖ ነበርና  በእንዲህ ያለ ተጋድሎም  እግዚአብሔርን ከአገለገለው በኋላ ወደ አግዚአብሔር ሄደ ፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር ኪያነኒ  ይምሐረነ በጸሎቱ  ወበረከቱ ትብጽሐነ ለዓለመ ዓለም አሜን!
አርኬ፡-ሰላም እብል ለጰየጥሮስ ብሕትው  ኮከበ ጠራው፤
ወውስተ ዓለም ኅሩም እምበሊዐ ኅብስት ወጼው፤
እስከ አስተርአየ  በአምሳለ ምትሐት ሕስው ፤
ተሴስዮ ሣዕር አብደረ በበድው ፡፡

    

No comments:

Post a Comment