በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ!
ይድረስ፦ ለሰሚ ጆሮና ለአስተዋይ እዝነ ልቡና ሁሉ!
============================
ራሳችሁን “ተዋሕዶዎች” እያላችሁ የምትጠሩና ፣ በተለምዶና በአለአዋቂዉ ማንነታችሁ “ቅብዐቶች” እያላችሁ የምትጠሩን ነገር ግን መሢሐዉያን ፣ ቅቡዓን ፣ ክርስሳዉያን ፣ ኦርቶዶክሳዉያን የምንባል እኛን በቤታችሁ “ተዋሕዶ” የሚለዉን የምሥጢረ ሥጋዌ ዘዉግ የማናምን የሚመስላችሁ ለምንድን ነዉ? ብዙዎቻችሁ የቅብዓቱን ምሥጢርና ጣዕመ ትርጓሜ ባታዉቁት “ቅብዐቶች” እያላችሁ ስትጠሩን ይህንን መጥሪያ ሰም ከየት አገኛችሁልን? ማለትም ከመጽሐፍ ወይስ ከመምሕር? መቼም ካላበዳችሁ በስተቀር ከመጽሐፍም ከመምሕርም አገኘነዉ አትሉንም ፡፡ ምክንያቱም መጽሐፍ “አንትሙሰ ቅብዐት ብክሙ እምነ መንፈስ ቅዱስ” ብሎ ተናገረ እጅን “አንትሙሰ ቅብዐት” ብሎ አልተናገረምና ፡፡ ታዲያ ከየት አመጣችሁት?
እንዲሁም መጻሕፍትና ሊቃዉንት ተባብረዉ “ንሕነሰ ኦርቶዶክሳዉያን ፣ ንሕነሰ መሢሐዉያን ፣ ንሕነሰ ክርስቶሳዉያን” ብለዉ ተናገሩ እንጅ “ንሕነሰ ቅብዐት” አዉ “ንሕነሰ ተዋሕዶ” አላሉም ፡፡ ብለዋል የሚል ካለ መረጃዉን ይዞ ከች ይበልና አብረን እንተራረምበት ፡፡ እኔ ለተከታታይ 7 ዓመታት እንዳጠናሁት ግን “ተዋሕዶዎች” እያላችሁ ራሳችሁን የምትጠሩ ወንድሞች እህቶች ፣ እናቶች አባቶች ፣ መምሕራንና ሊቃዉንት “አነ ዉእቱ ፈጣሆሙ ለእሉ ፍጡራን “ እንዳለዉ እደ ዲያብሎስ ሳታዉቁት ራሳችሁን “እኛ ክርስቶሶች ነን” እያላችሁ እደሆነ አለማወቃችሁን ነዉ ፡፡ በተለይ በተለይ ይህ የግቢ ጉባዔ አዳራሽ በሦስት ወርም ፣ በ3 ደቂቃም መምህር እያለ የሚሰይማችሁማ! መቼም ሊቀ ሊቃዉንት የሆን ሁሉ ነዉ የሚመስላችሁ ፡፡
አይ መኮፈሱንና ነጠላ ለብሶ ጳጳስ መምሰሉን ስትችሉበት! ከእኛ በላይ ለአሳር የሚያስብል ትዕቢትን እስከ አፍንጫችሁ ተከናንቧችሁ ፈራሽ ነገርን ሲያናግራችሁ ይኖራል ፡፡ በተለይ እንደእናንተ የማይኮፈሱ ፣ በእናንተ ልሳን የማይተነፍሱ ካህናትን ፣ ሊቃነ ጳጳሳትን ፣ ስታወራርዱና ስታዋርዱ ትችሉበታላችሁ ፤ ክን የክርስትናዋን ሕግና ሥርዓት ማን ወስኗት ይሆን?ይህ የ21ኛዉ ክፍለ ዘመን ወጣት ዝም ብሎ ወደነፈሰበትና ብዙ አጨብጫቢ ወዳለበት የሚነጉድበት ዘመን ነዉ ፡፡ አንዱ “ጋጠ ወጥ” ከመሬት ተነስቶ አንዱን ካህን ከመሬት አዉርዶ በስድብ ሲሞልጨዉ ሲመለከት ፣ ካህኑን እንኳን በመልኩ የማያወቀዉ የእኔ ቢጤ ይከተልና በለዉ እያለ ይወርድበታል ፤ እንዳንድ ጊዜ “እኔ ተዋሕዶዉ” እያለ ራሱን ከአምላክ አስገብቶ እየጠራ ጳጳሳትን ወይም ካህናትን ከሚተችና ከሚዘልፍ ሰዉ አይሁድ አልያም የማያምኑ የተሻሉ ናቸዉ ፡፡ ለምን ቢሉ “ዘሰ ኢይሄሊ ለቤቱ ወይገድፍ አዝማዲሁ ወፈድፋደሰ ለሰብአ ሃይማኖት ክሕደ ሃይማኖቶ ወየአኪ እምዘ ኢየአምን --ነገር ግን ለእርሱ ስለሆኑት ይልቁንም ስለቤተሰቦቹ የማያስብ ማንም ቢሆን ፤ ሃይማኖትን የካደ ከማያምንም ሰው ይልቅ የሚከፋ ነው” እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ በ ቀዳማይ ጢሞ ምዕ 5 ቁ 8 የካህናትንና የሊቃነ ጳጳሳትን ሰማያዊ ሥልጣን ሳያዉቅ ዘራፍ የሚል ሞኝ ትዉልድ የሚጠብቀዉ ቅጣት ከማያምኑት በላይ እንደሆነ ያስረዳናል ፡፡
ስለዚህ እባካችሁ በመጀመሪያ ራችሁን ሁኑ ፤ ከዚያም የምታምኑትን እወቁ ፣ ከዚያም ስለምታምኑት አሳዉቁ ፣ ከዚያም ስለሌሎቹ እምነት እወቁ ፤ ከዚያም ለትችት ቅረቡ ፤ እንጅ ዝም ብላችሁ “ሀሁን ሳትጨርሱ አንቀጽ ወደመጻፍ አትግቡ” ፡፡ ወደቀደመ ነገሬ ልመለስና ብዙዎቻችሁ በጭፍኑ እኛ(መሢሐዉያን፣ በተለምዶ “ቅብዐቶች” የምትሉን) ተዋሕዶን የማናምን ይመስላችኋል አይደል? ፤ ወንድሜ / እህቴ / እናቴ / አባቴ እባካችሁ ሰከን ባለ አእምሮ በሃይማኖት ለዛ ሁናችሁ እንነጋገር ዝም ብላችሁ ላይ ላዩን እየበረራችሁ ራሳችሁን አታስነቅፋችሁ ቤተክርስቲያንንም አታስነቅፏት ፡፡ ሊቃዉንተ ቤተክርስቲያን ቀደምትም ሆነ እኛ ወልደ እግዚአብሔር ሕያዉ ወልደ ማርያም ሥግዉ ስለ ስግዉነቱ (ስለሰዉነቱ ፣ ክብር የሚሻ ሥጋን ተዋሕዶ ክብር መሻትን ገንዘቡ በማድረጉ) በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ ከበረ ማለታችን እኮ ተዋሕዶውን በማመናችን ነው ፡፡ ተዋሕዶውን የማናምን ቢሆን ኖሮማ ከበረ ማለትም ባላስፈለገው ነበር ፡፡ ሕያው አምላክ ሞተ መባሉ መዋቲ ሥጋን ስለተዋሐደ ነው ፡፡ እንዲሁ ተቀብዐ ወይም ከበረ መባሉ ክብር የሚሻ ሥጋን ተዋሕዶ የሥጋን ገንዘብ ገንዘቡ በማድረጉ ነው ፡፡ “እኔ እግዚአብሔር ነኝ” እንዳለ እንደ ዲያብሎስ “ እኔ ተዋሕዶ ነኝ ፣ እኔ ተዋሕዶዉ ፣ ዘራፍ የተዋሕዶ ልጅ” እያልክ ራስህን ከአምላክ ተክተህ ሳታዉቅ የምትክደዉ ወዳጄ ሆይ! እስኪ ልጠይቅ ወንድማለም ተዋሕዶ ተዋሕዶ እያላችሁ ሁላችሁም ትናገራላችሁ
1ኛ‹‹‹‹‹‹ተዋሕዶ ማለት ምን ማለት ነው?
2ኛ‹‹‹‹‹‹ማን ከማን ጋር ተዋሐደ?
3ኛ‹‹‹‹‹‹‹‹‹በሥንት ነገር ተዋሐደ?
4ኛ‹‹‹‹‹‹‹ሲዋሐድ ተዐቅቦውና መገናዘቡ እንዴት ነው?
5ኛ‹‹‹‹‹‹ቃል ከሥጋ ጋር ሲዋሐድ የሥጋ ገንዘብ የሆኑት ከአብ ልጅነትን መሻት ፣ ከመንፈስ ቅዱስ ሕይወትነትን መሻት በተዋሕዶ ለቃል በትስብእቱ ይነገሩለታል ወይስ አይነገሩለትም?
6ኛ‹‹‹‹‹‹‹‹‹ካልተነገሩለት ቃል የሥጋን ገንዘብ ገንዘቡ አላደረገምን? ከተነገሩለት ቃል በሥጋዉ ከበረ ይባልለታል ወይስ ቃል ለሥጋዉ አክባና ክብር ሆነለት?
7ኛ‹‹‹‹‹‹እንዲሁም በሥጋዉ ከአብ ተወለደ ትላላችሁ ወይስ በቃል ልጅነት ልጄ አለዉ ትሉታላችሁ? ተወልዷል ካላችሁ አወላለዱ ምሥጢሩ እንዴት ነዉ? አልወለደዉም ካላችሁ ቃል የሥጋን ገንዘብ ገንዘቡ አላደረገም ማለታችሁ ነዋ? ንስጥስ ከሐዲም አብ የሚወልደዉን ድንግል አትወልደዉም ፣ ድንግል የምትወልደዉን አብ አይወልደዉም ብሏልና ከንስጥሮስ በምን ትሻላላችሁ?
ማሳሰቢያ፡- አደራ በእመብርሃንና በምትወዷት በወለደቻችሁ በእናታችሁ ልለምናችሁ እነዚህን ጥያቄዎቼን አስረዱኝ? ስድብና ነቀፋ ፣ ጥላቻና ዘለፋ የሚያስቀድም ሰዉ አእምሮዉን ያጣ ፣ የሚመልሰዉ የሌለዉ የሚያምነዉን የማያዉቅ ፣ ሲሄዱ አይቶ የሚጓዝ ፣ ሲጮሁ አብሮ የሚጮህ ብቻ ነዉ ና ሃይማኖታችሁን ለማስረዳት ከመንፈሰ ጽርፈት ይልቅ መንፈስ ቅዱስን ገንዘብ አድርጉ፡፡
ዛቲ ሃይማኖት መሢሐዊት
ዘትትአመን ባቲ ቤተክርስቲያን ቅድስት
ሥብሐት ለሥላሴ ምስለ ወላዲተ አምላክ ወ እጸመስቀሉ ቅዱስ
No comments:
Post a Comment