ዕዝራ ሐዲስ(ሊቀ ሊቃውንት) Vs ዕዝራ ሱቱኤል
=========+========
ክፍል --አንድ
በክርስቶስ ክርስቲያን በወልድ ውሉደ እግዚአብሔር በመንፈስ ቅዱስ መንፈሳውያን የተሰኛችሁ ኦርቶዶክሳውያን አባቶቼ ካህናት ፤ ወንድሞቼ ዲያቆናት ፤ እህቶቼና ወንድሞቼ ሁላችሁም እንደምን ሰነበታችሁልኝ ፡፡ ከሰሞኑ በገባሁት ቃል መሰረት በ2008 ዓ.ም ድርሳነ ቄርሎስን ለሕትመት ያበቁትና በአሁኑ ሰዓት በስሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት በመንበረ መንግሥት መድኃኔ ዓለም የዐራቱ ጉባዔያት ትርጓሜ ምስክር መምህር ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ሐዲስ ቄርሎሱን ሲያሳትሙ ተቀብዓ የሚለውን ተሰብአ እያሉ እየለወጡ፣ በኢሳይያስና በዳዊት ስለ ተቀብዓ የተነገሩ ትንቢቶችን ቆርጠው እያስወጡ የጻፉት መሆኑን ለማሳወቅ እወዳለሁ ፡፡ በቅዱስ መጽሐፍ እንደተነገረን አባቶቻችን ቆጥረው ሰፍረው የሰጡንን እውነታ እየቆረጡ ማስቀመጥ ወይ ደግሞ ዘሩን ነቁን እየለወጡ ማሳተም ምን አይነት ዓላማ እንዳለው ለብህል አይነግሩምና ለእናንተ መናገር አይጠበቅብኝም ፡፡
ይህንን እየቆረጡ ያስቀሩትንና እየለወጡ ያስቀመጡትን እውነታ ከብራናው በዓይኔ በብረቱ ጠቅላ ቤተክህነት ቤተ መጻሕፍት ውስጥ ካለው የብራና ቄርሎስ ያኘሁትንና ከሌላ ቦታ ያስተያየሁትን ጽሁፍ በፎቶ አስደግፌ እለጥፍላችኋለሁ ፡፡ እንግዲህ “አንተሰ ጥበበ ስብክ ከመ አእምሮ ታውሥእከ (አንተስ አዋቂ ታሰኝህ ዘንድ ጥበብን አስተምር)” እንዳለ ምሳሌ 8 ቁ 1 ፤ እንደ ጥሩ ክርስቲያን ጥበበኛ መሆንን የምንሻ ከሆነ ካላወቁ አይጸድቁ እደተባለው ማወቅን ገንዘብ እናደርግ ዘንድ ያስፈልገናል ፡፡ ለማወቅም ጥበብን ገንዘብ እናድርግ ዘንድ የተገባ ነው ፡፡እንደመግቢያ እነ እንትና ከአሁን በፊት “ቅብዓት የሚል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የለም ብቻ ተዋሕዶ እንጅ” ፤ “ርትዕት ሃይማኖት ተዋሕዶ ናት፣ እኛ ተዋሕዶዎች ነን” ወዘተ የመሳሰሉትን ሲሉ ነበር ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ሲፈተሸ ደግሞ የመጀመሪያዎቹ በክርስቶስ አምነው የተጠመቁ ሰዎች ክርስቲያኖች እንደተባሉ ሃይማኖታቸውም ኦርቶዶክስ እንደሆነች ብዙ ሊቃውንት ጽፈዋል ፡፡ ለዚህም ግብረ ሐዋርያትንና ሃይማተ አበውን መመልከት ይቻላል ፡፡ አንድም ቦታ ላይ “ተዋሕዶ ሃይማኖታችን ብሎ የተናገረ አባት የለም ፡፡ የእነሱ መነሻ መሠረት ከየት እንደሆነ አናውቅም ፡፡ ብቻ ግን መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት የሌለው ስያሜ ለእነሱ ብቻም ሳይሆን ለእኛ ሰጥተውናል ይህም “ቅብዓቶች” የሚል ነው ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን ስንመለከተው ግን በነቢያቱ “ኢትግሡሱ መሢሐንየ(የቀባኋቸውን አትንኩ) ተብሎልናል ፤ በሐዲስ ኪዳን ደግሞ “አንትሙሰ ጽውአን በስሙ ለክርስቶስ” እንዳለ ጳውሎስ ክርስቲያን (ቅቡዕ የተቀባ) ተብለን ተጠርተናል ፡፡ በዚህም አንጻር ቅቡዓን (የተቀቡ) ክርስቶሳውያን ክርስቲያኖች ብንባል እንጅ “ቅብዓቶች” አንባልም ፡፡እናም በሚናገሩት መሠረት የሌለው ልብ ወለድ ልንታለል አይገባንም ፡፡ እንደዚሁ በአሁኑ ዘመን ያሉቱ ሁለተኛ አጥማቂዎቻችን ደግሞ በ1990ዎቹ ወልደ-አብ በወረቀት ታትሞ ሲወጣ እዚያ ላይ “ወልድን ተቀባዒ ነው ስለአሉ ብቻ ተቀባዒ አይደለም ቀባዒም ነው እንጅ” የሚለውን ቃል ከወልደ አብ ላይ ከአነበቡ በኋላ እንደነ ሊቀ ሊቃውንት ስምዐኮነ መልአክ ያሉ ሰዎች በፊት “ቅብዓት ከሮም መጣ የአልፎንሱ ሜንዴዝ ትምህርት ነው” ሲሉ የነበሩ እነሱ እንደገና አዙረው “ለሊሁ ቀባዒ ወተቀባዒ ወለሊሁ ቅብዕ” ብለው በገሀድ ማስተማር ጀመሩ ፡፡ በደንብ አስተውሉ ቅብዓት ከሮም የመጣ ነው ሲሉ የነበሩ ሰዎች ራሳቸው አዙረው “ለሉሁ ቀባዒ ወተቀባዒ ወለሊሁ ቅብዕ” ብለው ሲያስተምሩ ስለ ቅብዓት ማውራታቸውን አልተውትም ፤ ግን ወልድ በሰውነቱ ተቀብቶ ክርስቶስ እንደተባለ እስከ አሁን ድረስ አላመኑም ፡፡ እነሱ እንዲህ ብለው ከማስተማራቸው በፊት እነ አባ ሠላማ ሦስኛ እና አባ ቄርሎስ ዐራተኛ ይህንን “ለሊሁ ቀባዒ ወተቀባዒ ወለሊሁ ቅብዕ” የሚለውን ትምህርት ዘርተው እንደሄዱ የታሪክ መዛግብትን አገላብጦ መመልከት ይቻላል ፡፡ የሆነ ሁኖ “ቅብዓት የሚባል ነገር” የለም ሲሉ የነበሩ ሰዎች “ለሊሁ ቀባዒ ወለሊሁ ተቀባዒ ወለሊሁ ቅብዕ” ብለው ሲናገሩ ቅብዓት ከሌለ ይህንን ከየት አመጡት? ቃል ከሥጋ ጋር መዋሐዱን ከአመኑትስ አንዱን አካል “ለሊሁ ቀባዒ ወተቀባዒ ወለሊሁ ቅብዕ” ብለው መናገራቸው ይህ ቅብዓቱ ምን አደረገለት? በቤታቸው “በቅብዓት የባሕርይ ልጅ መሆን አይቻልም” የሚሉ ሲሆኑ “ለሊሁ ቀባዒ ተቀባዒ ወለሊሁ ቅብዕ” ያሉት እነሱ በዚህ ቅብዓቱ ምን ሆነበት? የባሕርይ ልጅ ወይስ የባሕርይ አምላክ? ወይስ የጸጋ ልጅ የጸጋ አምላክ ሆነበት? ፡፡
በዚህ ሀሳባቸው ከቀጠሉ በኋላ ደግሞ በዚህ በያዝነው ዓመት በብእር ስማቸው “በአማን ነጸረ” የተባሉ ግለሰብ ደግሞ የተለያዩ የሀገር ውስጥ የውጭ ሀገር ሊቃውንትን ድርሳናት አጣቅሰው “አብ ቀባዒ ወልድ ተቀባዒ መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ” የተባለባቸውን አንቀጾች ጠቅሰው ካስቀመጡ በኋላ የባሕርይ ሕይወቱን መንፈስ ቅዱስ ዘኢይረብእ በምታሰኝ ንግግራቸው “ በዮርዳኖስ ከሆነው አካላዊ ርደተ መንፈስ ቅዱስና ጌታ በሥጋው ወራት ከፈጸመልን የማዳን ሥራ ጋራ እንጅ ከባሕርይ ትንታኔ ጋር አይገናኙም” የሚል ሀሳብን ተንፍሰውልናል ፡፡ ይሁን እነሱ እንደተመቻቸውና እንደፈለጉት ያድርጉት እኛ ግን አምላካችን መድኅን ዓለም ክርስቶስ በጊዜ ተዋሕዶ በአባቱ ቀባዒነት ስለሰውነቱ የደስታ ዘይትን ተቀብቶ ክርስቶስ ተብሎ እኛን በስሙ ክርስቲያን አሰኝቶናልና እንደ ባለአእምሮ ማሰብ እና ትክክለኛውን መምረጥ ግድ የሚለን ይሆናል ፡፡ ከዚህ ላይ “በአማን ነጸረ” እጅዎ ይባረክ ፤ምንም እንኳን ተቀብዓን ለራስዎ በሚመችዎ መንገድ ቢያስቀምጡትም ቅሉ ለማየት እድሉ ካልገጠመን የውጭ ሀገር ጸሐፍት ጋር እንድንተዋወቅ አድርገውልናል ፤ ቅዱስ ሲኖዶስ ያላመነውን ድርሳነ ቄርሎስን እርስዎ ስላመኑልን እናመሰግናለን ፡፡ በተጨማሪም ሊቁ ዕዝራ ሐዲስ እየቆራረጡ ያስቀመጧቸውንና የለወጧቸውን ግሶች ሳያሽሞነሙኑ እንዳለ እንደተለወጡ በማስቀመጥዎ ፈጣሪ ይስጥልኝ ብያለሁ ፡፡ በተጨማሪ እንደ አስተያየት በእጅዎ ላይ ያለውን የታተመውን ወልደ አብን እዚያ ቤተ-ክህነት ካለው አክሲማሮስ ከሚባለው መጽሐፍ ጋር ከጫፍ እስከ ጫፍ እንዲያስተያዩትና አስተያየትዎትን እንዲገልጹልኝ በአዛኝቷ ስም እማጸንዎታለሁ ፡፡
ወደቀደመ ነገሬ ልመለስና እነ እንትና ተቀብዓን ተሰብአ እያሉ እየለጠጡ እየለወጡ ተቀብዓን አመልጥ አመልጥ ሩጫ ላይ ናቸው ፡፡ አንዴ ተቀብቷል ይላሉ ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ አልተቀባም ብቻ በተዋሕዶ ከበረ እንጅ ይላሉ፣ ሌሎቹ ደግሞ ልክ እንደነ እዝራ ሐዲስ(ሊቀ ሊቃውንት) ያሉት ደግሞ አይ ተቀብዐ ተሰብአ ነው መባል ያለበት እያሉም የሚፈረጥጡ አሉ ፡፡ ይህ ሁሉ ሩጫ መደበቂያ ፍለጋ ነው ፡፡ ዳሩ ግን ሩጫቸው ከእሾህ ቢሸሹ ጋሬጣ ነው ፡፡ ምክንያቱም ከአሁን በፊት እንደተመለከትነው እነሱ “ተቀብዓን” ለውጠው “ተሰብአ” የሚሉት ከሆነ ቅዱስ ቄርሎስ “እስመ በዘተሰብአ ተቀብዐ ኪያሁ ይሰመይ መሢሐ” ይላል ፤ መሢሐ የሚለው ከፊት ነው ለእኛ እንዲገባን በኋላ የአመጣሁት ነው ፡፡ አሁን እንደነ እንትና ከሆነ በቁሙ ስንጽፍላቸው “እስመ በዘተሰብአ ተሰብአ ኪያሁ ይሰመይ መሢሐ” የሚል ይሆንላቸዋል ፡፡ በደንብ ተመልከቱልኝ ትርጉሙ “በዘ” የሚለው አገባብ ፍችው እንደ፣ ስለ እና ገንዘብ ተብሎ በሦስት ነገር ይፈታል ፡፡ እናም የእነሱን ንግግር ስንተረጉመው “ሰው በሆነ ገንዘብ /እንደመሆኑ/ ስለሆነ/ ሰው ሁኗልና መሢሕ ይባላል” የሚል የትፈሰስ ትርጉም የሌለው ሀሳብን ያመጣባቸዋል ፡፡ በተጨማሪም ለሰው ሰው ሆነ ተብሎ የሚነገር አንቀጽ የለውምና ትርጉማቸው የነሲብ ወይም ባዶ እንደሆነ በዚህ እንረዳለን ፡፡ ትክክለኛው ትርጓሜ ግን “እስመ በዘተሰብአ ተቀብዐ ኪያሁ ይሰመይ መሢሐ(ሰው ስለሆነ ገንዘብ / እንደመሆኑ/ በሰውነቱ ተቀብቷልና መሢሕ ይባላል” ነው ፡፡ በሌላ አንቀጽ ቅዱስ ቄርሎስ “ኢይጽህቅ ቅብዓተ በሕላዌ መለኮቱ(በባሕርየ መለኮቱ ቅብዓትን አይሻም)” ብሏል ፡፡ እንደነ እንትና ትርጓሜ “ቅብዓት” ማለት “ተዋሕዶ ማለት ነው” ቢባል ፡፡ ወፍራም ክሕደትን ያከናንባል ፡፡ ይኸውም “ኢይጽሕቅ ተዋሕዶ በሕላዌ መለኮቱ(በባሕርየ መለኮቱ ተዋሕዶን አይሻም” የሚል ይሆንባቸዋል ፡፡ በሦስተኛ ደረጃ አፈወርቅ ዮሐንስ ደግሞ “መለኮትሰ ኢይትቀባዕ (መለኮትስ አይቀባም/አልተቀባም)” ብሏል ፡፡ አሁንም እንደነሱ አነጋገር “ቅብዓት” ተለውጦ “ተዋሕዶ” ከተባለ “መለኮትሰ ኢይትዋሐድ(መለኮትስ አይዋሐድም/ አልተዋሐደም)” ያሰኝባቸዋልና ቅብዓትን ተዋሕዶ ብሎ ለውጦ ቢተረጉሙት አለአዋቂ ሳሚ ያሰኛልና አያስኬድም ፡፡ ጽኑዕ ክሕደትም ነው ፡፡
ይህንን መሠረት አድርገን የተቀብዓ ስደተኛው ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ሐዲስ ለውጠው ከተረጎሙት ከድርሳነ ቄርሎስ ላይ የሚገኘውን ክፍል የእሳቸውን ቃል እንደአለ አስቀምጬ ከሥር ደግሞ የብራናውን ፎቶ አስቀምጥላችኋለሁ የተስማማችሁን ውሰዱ ፡፡ አለመስማማት ይቻላል ፡፡ ይህ ግዴታ አይደለም ፤ ከእውነት ጋር ለመተባበር ዝግጁ የሆነ ብቻ ይጠቀምበት ከውሸትና መጽሐፍ ቅዱስን ከሚያድሱ ሰዎች ጋር አብሬ አድሳለሁ የሚልም ካለ መብቱ ነው አይከለከልም ፡፡
“..እስመ ሶበ ቃል ሥጋ ኮነ (ቃል ሥጋን በተዋሐደ ጊዜ)፤ አሜሃ ንብል ተሰምየ ክርስቶስ(ክርስቶስ እንደተባለ እንናገራለን) ፤ እስመ እንከ ከብረ ክብረ ሐሴት እመንፈስ ቅዱስ በኀበ እግዚአብሔር አብ(በመንፈስ ቅዱስ አዋሐጅነት ከአብ በተገኘ ክብር ከብሯልና)፡ ከአብ የተገኘ ክብርም አካለ ቃል ነው ፤ ወበእንተዝ ተሰምየ ክርስቶስ( በተዋሐደው አካል ከብሯልና ክርስቶስ ተባለ) ፡፡ ወእለሰ ርቱዐ የአምኑ (አንድ አካል አንድ ባሕርይ ብለው የሚያምኑ ሰዎች) ፤ይሜህሩ ከመ በሥጋሁ ተለዓለ(በሰውነቱ ከበረ ብለው ያስተምሩ)” በማለት ጽፈውታል ድርሳነ ቄርሎስ ድርሳን 44 ቁ 8-9) ፡፡
ከብራናው ላይ ያለው ቃል ደግሞ
“…እስመ ሶበ ቃል ሥጋ ኮነ ፤ አሜሃ ንብል ተሰምየ ክርስቶስ ፤እስመ እንከ ተቀብዐ ቅብዐ ሐሴት እመንፈስ ቅዱስ በኀበ እግዚአብሔር አብ ፤ ወበእንተዝ ተሰምየ ክርስቶስ ፡፡ ወእለሰ ርቱዐ የአምኑ፤ወይሜህሩ ከመ በሥጋሁ ተቀብዓ” የሚል ሲሆን
ትርጉሙ፡-…ቃል ሥጋን በተዋሐደ ጊዜ ክርስቶስ እንደተባለ እንናገራለን በእግዚአብሔር አብ የደስታ ዘይትን ተቀብቷልና ፤ በተዋሐደው አካል (በትስብእቱ) ከብሯልና ክርስቶስ ተባለ ፡፡ አንድ አካል ፣ አንድ ባሕርይ ብለው የሚያምኑ ሰዎች በሰውነቱ ተቀባ ከበረ ብለው ያስተምራሉ (ያስተምሩ))” የሚል ነው ፡፡
እንግዲህ የሁለቱን ልዩነት በደንብ አገናዝቡት ፡፡ ክርስቶስ የሚለው ስም ትርጉሙ የተቀባ የከበረ ማለት ሲሆን ይህ ስም ደግሞ ለመለኮት ወይም ለትስብእት ተነጥሎ የሚሰጥ እንዳይደለ ቅዱስ ቄርሎስ በደንብ አስተምሯል የሐዲስ ኪዳን መምሕራም በማቴ 1 ቁ 16 ላይ በአንድምታው አስረጅ አድርገው አቅርበውት ይገኛል ፡፡ ታዲያ ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ሐዲስ ከነቁ ላይ ያለውን “ተቀብዓ ቅብዓ ሐሴት” የሚለውን ቃል ለምን ለወጡት? ሐዋርያት እኛ የሰጠናችሁን ለውጡት ቀይሩት አሻሽሉት ብለዋል ወይስ እኛ ከአስተማርናችሁ ውጭ የሰማይ መላእክትም ቢሆን ቢያስተምራችሁ የተወገዘ ይሁን አሉ? የትኛው ይሆን እውነተኛው? ፡፡
አስከትለውም ሊቁ ዕዝራ ሐዲስ “ቅብዓ ሐሴት(የደስታ ቅብዓት)” የሚለውን ትተው “በመንፈስ ቅዱስ አዋሐጅነት” የሚል ሥርዋጽን ጨምረውበታል ፡፡ ልብ ብላችሁ አንብቡት ፤ ይህ ቅብዓ ሐሴት ወይም የደስታ ዘይት በነቢዩ ዳዊት መዝ 44 ቁ 7 ተነግሮ በቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ ዕብ 1 ቁ 9 ላይ ዘይኄይስ የሚል አስረጅ ተገልጦ ተነግሮለት በአፈወርቅ ዮሐንስ “እስመ ለእግዚእ ክርስቶስ አኮ በመሥፈርት ዘተውህቦ መንፈስ ፤ ይቤ ቅብዓ ትፍስሕት እምእለ ከማከ(ለክርስቶስ መንፈስ ቅዱስ በልክ በመጠን የተሰጠው አይደለምና ቅብዓ ትፍስሕት እምለከማከ አለ ዘይኄይስ ያለበት ነው)” ተብሎ የተተረጎመ ነው ድርሳን 3 ፡፡ እንግዲህ ብሩህ ዓይንና አስተዋይ እዝነ ልቡና ላለው ሰው ይህ የደስታ ቅብዓት ለክርስቶስ ከባለንጀሮቹ በተለየ በባሕርይ የተቀባው ሲሆን ይህንን የደስታ ዘይትም የተቀባው በሰውነቱ መሆኑን በዚያው በድርሳ 3 ላይ አፈወርቅ “መጽሐፍ ቃልን በሥጋው ተቀባ ይለዋል” ብሎ ነግሮናል ፡፡ በደንብ አስተውሉ አሁንም ሊቁ እዝራ ሐዲስ ቅብዓቱን አጥብቀው ስለሚጾሙት በመንፈስ ቅዱስ ቅብዓትነት የሚለውን ትተተው በመንፈስ ቅዱስ አዋሐጅነት አሏት ፡፡ እሳቸው እንደዚህ ቢሉት ዮሐንስ አፈወርቅ “እስመ ለእግዚእ ክርስቶስ አልቦ በመስፈርት ዘተውህቦ መንፈስ” በማለት ይህ ቅብዓ ሐሴቱ አዋሐጅ የሆነ ሳይሆን በልክ በመጠን ያይደለ በመላ ክብር እንደሆነው እንደተሰጠው ይናገራልና የእሳቸው ተቀብዓን ጥለው ፍርጠጣ ከእሾህ ቢሸሱ ጋሬጣ ከምን ቢሸሹ ፈንጣጣ ሁኖባቸው ይገኛሉ ፡፡
አክለውም ሊቁ እዝራ ሐዲስ “ከአብ የተገኘ ክብር የተባለም አካለ ቃል ነው” ብለውት እርፍ ብለዋል ፡፡ በደንብ አስተውልልኝ ወዳጄ!! ክርስቶስ ማለት የተቀባ ማለት ሲሆን ይህ ለመለኮትም ለትስብእትም ለየብቻቸው ተነጣጥሎ የሚሰጥ አይደለም ፡፡ ታዲያ እንደሊቁ ዕዝራ ሐዲስ አነጋገር ክብር የተባለ አካለ ቃል ነው ከተባለ እነሆ የከበረው አካለ ሥጋ ነው ማለት ነው ፡፡ እነሆ አካለ ቃልን አክባሪ ካደረጉት ተቀባዒነት ለትስብእት ተነጥላ መሰጠቷን ልብ እንላለን ፡፡ ይህች ክርስቶስ ወይም መሢሕ መባል ለሥጋ ብቻ ሁናባቸው ቁጭ ትላለች ፡፡ በተጨማሪም ደግሞ ቃል ከሥጋ ጋር ተዋሕዷልና ተቀብዓ ፣ ሐመ ፣ ሞተ ……የሚባሉት ነገሮች ሁሉ የሚነገሩት ለሥግው ቃል በመሆናቸው ቃልን ከሥጋ ነጣጥለው ከፋፍለው ሁለትነትን(ምንታዌን) ታቅፈዋት ይገኛሉ ፡፡ አሁንም በደንብ አስተዉሉ ጥሬ ቃሉ “እስመ እንከ ከብረ ክብረ ሐሴት እመንፈስ ቅዱስ” የሚል ሲሆን ከዚህ ላይ “እምቃል” የሚል ሳይኖር በፈጠራ በልብ ወለድ ያለአግባቡ ያለ አገባቡ አምጥተው ቀላቅለው እውነትን እያጠፏት እንደሆነ ልንታዘብ ግድ ይለናል ፡፡
በቀጣዩ ክፍል የቅዱስ ዳዊትን “በእተዝ ቀብዓከ እግዚአብሔር አምላክከ ቅብዓ ትፍስሕት እምእለ ከማከ” የሚለውን ቆርጠው ያስቀሩበትንና የኢሳይያስን “በእንተ ዝንቱ ቀብዓኒ” የሚለውን አንቀጽ ቆርጠው ያስቀሩበትን ከብራው ጋር አያይዤ እጽፍላችኋለሁ ፡፡ እናንተም የሚመቻችሁን ትወስዳላችሁ የማይጠቅማችሁን ትተዋላችሁ ፡፡ እስከዚያው የሰላም አምላክ ድጋሚ ተጠመቁ ብለው ሰላማችንን የነሱንን ውሉደ ሱስንዮስ ምላስ ሳይሆን ልብ ይስጥልን ፡፡
ስብሐት ለአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ፤
ስብሐት ለማርያም ወላዲተ አምላክ እግዝእትነ ወመድኃኒት፤
ስብሐት ለመስቀለ ክርስቶስ እጸ መድኃኒት ኃይልነ ወጸወንነ፡፡
ይቆየን
No comments:
Post a Comment