Wednesday, June 3, 2020

ቅብዓት ማለት ምን ማለት ነው? ክፍል አንድ


በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ!!!
++++++=+++++++++
ቅብዓት ማለት ምን ማለት ነው? ክፍል አንድ
==========+==========
ውድ መሢሐውያን (በተለምዶ በአለአዋቂቀው አነጋገር ቅብዓቶች የሚሏችሁ) እናት አባቶቼ ፤ ወንድም እህቶቼ እንደምን አላችሁልኝ ! በዚህ ጽሁፍ ቅብዓት ማለት ምን ማለት እንደሆነ በሰፊው ከቅዱስ መጽሐፍ ማስረጃ እየጠቀስን እያጣቀስን እንነጋገራለን ፡፡ በኦርቶዶክሳዊት ቅድስት ቤተክርሥቲያን ውስጥ ቅብዓት እና ተዋሕዶ ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል በተለየ ከዊኑ ቃል በመባል የሚታወቀው ፣ በተለየ ግብሩ ተወላዲ የሆነ አምላክ ወልደ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው በመሆኑ የፈጸማቸው ዓበይት ምሥጢራት ናቸው ፡፡ እነዚህንም ደጋግ አባቶቻችን አስተምረውናል ፡፡ እንደምን አስተምረውናል ቢሉ ቅዱስ አውሳብዮስ በድርሳኑ መንክረ ገብረ ወልደ እግዚአብሔር ስተ ከርሠ እሙ (የእግዚአብሔር ልጅ በእናቱ ማኅጸን ድንቅ ሥራን ሠራ) ፤ እስመ ፈጸመ ሥርዓተ ተዋሕዶ ወቅብዓት ምዕረ ከመ ቅጽበተ ዓይን (የቅብዓትና የተዋሕዶን ምሥጢር (ሥርዓት) እንደ ዓይን ጥቅሻ አንድ ጊዜ ፈጽሞአልና)” በማለት ይገልጣል ፡፡ ሌሎቹ የሐዲስ ኪዳ መምሕራን ደግሞ በማቴዎስ ወንጌል አንድምታ ምዕራፍ 1 ቁ 16 ላይ ሲዋሐድም ሲቀባም አንድ ጊዜ ነው ከመ ቅጽበተ ዓይን እለሰ የአምኑ ርቱዓ ይሜህሩ ከመ ተቀብዓ ቃል በሥጋሁ ፤ ወእምአመ ኮነ ቃል ሥጋ አሜሃ አስተርአየ በመንፈስ ቅዱስ” ብለው አስተምረውናል ፡፡ ዮሐንስ አፈወርቅም “ወእመ አኮ ቀዲሙ ዘወረደ ወእምዝ ተሠይመ (ቀድሞ ሰው እንዳልሆነ ኋላ እንዳልተሾመ መጠን አንድ ጊዜ ሰው ለመሆን እንደመጣ አስረዳ ፡፡ አንድም ቀድሞ ሰው እንዳልሆነ ኋላ እንዳልተሾመ አስረዳ ፡፡ ሰው ሁኖ ኑሮ ኑሮ ተቀባ የሚሉ አሉና እንዲህ አለ ፡፡ አንድም በተዋሐደ ጊዜ ተቀባ አለ)” (ድርሳን 15 105) ብሏል ፡፡ እንግዲህ በደንብ አስተውል ቅብዓትና ተዋሕዶ አንድ ጊዜ የተፈጸሙ ምሥጢራት መሆናቸውን እንረዳለን ፡፡

የቅብዓት ትርጉሙ ምንድን ነው? ቢሉ በቁሙ ቅብዓት ማለት ክብር ማለት ነው ፡፡ ስለዚህ ተቀብዓ ማለት ከበረ ወይም ተከበረ ማለት ነው ፡፡ ይህ ከበረ ወይም ተቀባ መባል ቃል ከሥጋ ጋር በተዋሐደ ጊዜ  በማኅፀነ ማርያም የተፈጸመ ምሥጢር ነው ፡፡ ለዚህ ነው ተዋሕዶና ቅብዓት ቃል ከሥጋ ጋር በአካል በባሕርይ በግብር አንድ ሲሆን አንድ ጊዜ የተፈጸሙ ምሥጢራት ናቸው ማለታችን ፡፡ ራሳቸውን “ቱዋሕዶዎች” ብለው የሚጠሩ ሰዎች ግን ተዋሕዶን እናምናለን እያሉ ቅብዓትን ደግሞ ክሕደት ነው ምንፍቅና ነው ሲሉ ይደመጣሉ ፡፡ ይህንን የሚሉት ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ ጠቅሰው አብራርተው ሳይሆን በ1982 ዓ.ም በመኪና አደጋ ሕይወታቸው ያለፈውና የቤተክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊ የሆኑት ጎርጎርዮስ ካልዕ(አቡነ) በመጽሐፋቸው ገጽ 53 ላይ “አልፎንሱ በሐማሴን አሞኛል ብሎ ተኝቶ በድብቅ የቅብዐትና የጸጋን ሃይማኖት ያስተማራቸው ሰዎች ኤዎስጣቴዎስ ዘሳንኳ ጊዮርጊስና (ጐጃም) ቆረንጭ መናፍቅ ተክለሃማኖት (ዘሸዋ) ናቸው ፡፡ የቅብዐትን ባህል ያስተማረው ለኤዎስጣቴዎስ ነው ፡፡ የጸጋን ባህል ለተክለሃይማኖት ነው ፡፡ ቅብዐትና ጸጋ በንባብ እንጂ በምሥጢር አንድ ናቸው ፡፡ የሮማ ካቶሊክ ሁለት ባሕርይ ዘውግ ናቸው…” ገጽ 62 ላይ ክብረ ነገሥታችን እንደሚለው አልፎንሱ አሞኛል ብሎ እዚህ (ምጥዋ) ተኝቶ ከጎንደር ተከትለውት መጥተው ለነበሩት ሁለት ኢትዮጵያውያን የቅብዓትንና የጸጋን ዕምነት አስተማራቸው ፡፡ በዚህ ጊዜ በኢትዮጵያ ሁለት እሾህ ተክየባታለሁ አለ ይባላል” የሚል ተረት ተረትን አስቀምጠውላቸው በመሄዳቸው ይህችን ተረት ተረት እንደ ቂጣ እየገመጡ እንደ ጠጅ እየጨለጡ እንደ ጡጦ እየመጠመጡ እንደ እምቧጮ እየቦጠቦጡ በመናገር ነው ፡፡ ዝም ብላችሁ ታዘቡኝማ በየትኛውም መንገዳቸው ስለ ቅብዓት ሀሳብ ብትጽፉ ፤ እነሱ “ቅብዓት የካቶሊክ ርዝራዥ….ምናምን ምናምን” ሲናገሩ እንጅ መጽሐፍ ቅዱስ ጠቅሰው አጣቅሰው አይናገሩትም ፡፡ ልቡናን ነፋ ደረትን ሰፋ አድርጎ የመናገር አቅም የላቸውምና በአሉ ይባላል ተረት ተረት የተሰፋች ልሳናቸውን ብቻ እየወረወሩ ይሮጣሉ መጽሐፉ ግን ዘወትር ሰሚ አጥቶ ይጮሃል እሪም እያለ ይገኛል ፡፡ ቅብዓት ማለት ክብር ሲሆን ቃል ከሥጋ ጋር ሲዋሐድ በድንግል ማርያ ማኅፀን ለወልድ በሰውነቱ መንፈስ ቅዱስ ክብር ሆነው አከበረው ማለት ነው፡፡ ከመጽሐፍ ቅዱስ ያይደለ እንደነሱ ተረት ተረትፈጠራ ነገር እንዳይመስልብን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃ እንደሚከተለው እንጠቅሳለን ፤ “…እስመ ዘይትወለድ እምኔሃ እመንፈስ ቅዱስ ውእቱ (ከእሱዋ የሚወለደው በግብረ መንፈስ ቅዱስ ነውና ፤ ማቴዎስ እመንፈስ ቅዱስ ያለውን ፣ሉቃስ መንፈሰ እግዚአብሔር ቅዱስ ይመጽእ ላዕሌኪ ያለውን ፣ ኢሳይያስ መንፈሰ እግዚአብሔር ዘላዕሌየ ዘበእቲአሁ ቀብዓኒ ያለውን ሊቁ ዛቲመ ትርጓሜሃ ለቅብዓት እስመ መንፈስ ቅዱስ አንጽሐ ሥጋሁ ለአዳም ብሎ ወስዶታል ፡፡ ንጽሕን ክብር የሚል ወዴት አለ ቢሉ ወሠዓርኮ እምጽሑ ይላል” ማቴ ምዕ 1 ቁ 20 አንድምታ ትርጓሜ በማለት የምሥጢሩን ፍሰጥ ያጣፍጠዋል ፡፡ አስተውል ከዚህ መልእክት ቅብዕ መሆን የመንፈስ ቅዱስ ግብር እንደሆነ እንረዳለን ፡፡ በወልደ አብ መጽሐፋችን ላይም የመንፈስ ቅዱስ ግብር ከሆኑት ውስጥ ቅብዕ መሆን አንዱ እንደሆነ ተጽፎ ይገኛል ፡፡ ብዙ ራሳቸውን “ተዋሕዶዎች” እያሉ የሚጠሩ ሰዎች ቅብዓት ማለት በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከሮም የመጣ የስሕተት ትምህርት እንደሆነ ሲናገሩ እናደምጣቸዋል ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ እንዲህ እንደምትመለከቱት ይነግረናል ፡፡ ይህንን የማቴዎስ ወንጌል አንድምታ ትርጓሜ ይዘን መጽሐፈ ዝክሪን ስንመለከተው ደግሞ “የቆላፍ ልጅ መናፍቅ ሆይ ስማ መንፈስ ቅዱስ ወደ አንች ይመጣል የልዑል ኃይልም ይጋርድሻል ባለ ጊዜ ገብርኤል ሦስቱ አካላት ሁሉ ሰው ለመሆን የመጡ አይምሰልህ ፤ እርሱስ ያለ አብ ቀባዒ ወልድ ተቀባዒ መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ ሁነው ወልድ ከሥጋ ጋር ሲዋሃድ ወደ ማርያም መጡ ፤ አብ ልጁን መንፈስ ቅዱስን ቀባው በማኅፀንም እንደ ዓይን ጥቅሻ አንድ ጊዜ ቅብዓት ንሥአት ኅድረት ሆነው” ብለው ከነገሩን ጋር ስምሙ ነው ፡፡ በደንብ አስተውለው በወንጌሉ ላይ “ዛቲመ ትርጓሜሃ ለቅብዓት እስመ መንፈስ ቅዱስ አንጽሐ ሥጋሁ ለአዳም ብሎ ወስዶታል” በማለት መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ ብሎ ግልጥልጥ አድርጎ ነግሮናል ፤ እኒያ ራሳቸውን “ተዋሕዶዎች” የሚሉ ሰዎች “ቅብዓትን አልፎንሱ አመጣው” እያሉ በአባ ጎርጎርዮስ ተረት ተረት ራሳቸው ቅልጥ ብለው “ቅብዓትን እናቀልጣለን” እያሉ ይናገራሉ ፡፡ ወዳጃችን አሁን የቀለጠው ማን እንደሆነ ከማን ተረዳህ?ከማቴዎስ ወይስ ከነእትና?መልሱን ለራስህ ፤ ተከተለኝማ ወንድሜ ፣ ተከተይኝማ እህቴ ወንጌላዊው “መንፈስ ቅዱስ ይጽእ ላእሌኪ” ያለው ያ ደረቅ ሐዲስ የሚባል ትንቢትን የተናገረ ደገኛው ነቢይ ኢሳይያስ በምዕ 61 ቁ 1 ላይ “መንፈሰ እግዚአብሔር ዘላዕሌየ ዘቀብዓኒ ዘበእቲአሁ አስተፍሥሖሙ ለነዳያን ፈነወኒ (የቀባኝ በህልውናዬ ያለ የእግዚአብሔር የባሕርይ ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስ ድኆችን ደስ አሰኛቸው ዘንድ ላከኝ” ብሎ ከተናረው ጋር አዛምዶ አወራርሶ ቀምሞ ነግሮናል ፡፡ እነሱ ግን አሁንም “አልፎንሱ አመጣው” እያሉ ሲጃጃሉ ይገኛሉ ፡፡ ቅዱስ መጽሐፍ ግን እንዲህ ይነግረናል ፡፡
እንግዲህ ይህ ቅብዓት የመጣው አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው መሆኑን ተከትሎ ነው ፡፡ ይህም ማለት ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት ቃል ከሥጋ ጋር ክብር የሚሻ ሥጋን በመዋሐዱ ስለሰውነቱ በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ ከበረ ተብሎ ይነገርለታል ፡፡ እንዲህ ብለን በማመናችን ከመጽሐፍ ቅዱስም ከሰዋስውም የራቁ አለአዋቂዎች “ቅብዓቶች” እያሉ ይጠሩናል ፡፡ ዋናው ስማችን ግን “ቅብዓቶች” ሳይሆን “ቅቡዓን ፣ መሢሐውያን” ነው ፡፡ ይህም እንዲሁ በተረት ተረት የተገኘ ሳይሆን መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ያለው ስያሜአችን እንጅ ነው ፡፡ ይኸውም በዚህ በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 1 ቁጥር 40 ጀምሮ ተጽፎ እንደሚገኘው ዮሐንስ ነዋ በግዑ ሲል ተመልተው ጌታን ከተከተሉት ከሁለቱ ደቀመዛሙርት መካከል አንዱ የሆነው እኁሁ ለስምዖን ጴጥሮስ ይለዋል እንድርያስ ለወንድሙ ለስምዖን ጴጥሮስ “ረከብናሁ ለመሢሕ ዘይብልዎ ክርስቶስ(ክርስቶስ የተባለ መሢህን አገኘነው ማስያስ በዕብራይስጥ ክርስቶስ በጽርእ መሢሕ በዓረብ ቅቡዕ በግእዝ” ብሎ ቁጥር 42 ላይ ዘግቦልናል ፡፡ አሁን ይህ ክርስቶስ የሚለው ስሙ በመቀባት የወጣለት ስሙ መሆኑን በዚህ እንረዳዋለን ፡፡ በደንብ አስተውሉ በግእዙ ቅቡዕ የሚለው ወደ አማርኛችን ስንተረጉመው የከበረ የተቀባ ማለት ነው ፡፡ ይህንንም በምን ተቀባ ብለን ብንጠይቅ ከላይ ያለውን መሠረት ማድረግ እንችላለን ቄርሎስም “በእንተ ቅብዓት ተሰምየ ክርስቶስ እስመ ክርስቶስ ብሂል ቅቡዕ በመንፈስ ቅዱስ ብሂል(ስለ ቅብዓት ክርስቶስ ተባለ ክርስቶስ ማለት በመንፈስ ቅዱስ የተቀባ ማለት ነው” ብሏል በድርሳኑ ፡፡ ድርሳኑን ማግኘት የማትችሉ ግብረ ሕማማት ዘዕለተ ዓርብ በዘጠኝ ሰዓት የሚነበበውን የቄርሎስን መልእክት ግእዙን ተመልከቱ ፡፡ ከዚያም እሱ በመንፈስ ቅዱስ ተቀብቶ ወይም ከብሮ ክርስቶስ እንደተባለ ሁሉ እኛ ም በዚህ ስም ክርስቲያን ቅቡዓን መሢሐውያን እንባልበታለን ፡፡ ይህንንም ከእኛ ከልቡናችን ያፈለቅነው ሳይሆን እነ ቅዱስ ቄርሎስ እንዲህ የነገሩንን ምሥክር ይዘን ነው ፤ ቄርሎስ ይቤ ነበብከ ርቱዐ ከመ በእንተ ቅብዓት ክርስቶስሃ ይሰመይ ዘውእቱ መሢሕ በከመ ሐዋርያ በእንተ ሐዊሮቱ ወመልአክኒ ይሰመይ በተልዕኮቱ ወዘከመዝ አስማተ በአማን በእንተ ሢመቱ ወግብሩ ይሰመይ ፡፡ አኮ ዘህላዌ አላ ዘገጽ ውእቱ ወበዝ ስም ተሰመዩ ነቢያት ቅቡዓነ ዘውእቱ መሢሓን (ቄርሎስ እንዲህ አለ ስለተቀባ ክርስቶስ እንደተባለ እውነት ነገር ተናገርክ) ፡፡  ይኸውም የተቀባ የከበረ ማለት ነውና ፡፡ ስለተሾመ ራስ ቢትወደድ ደጅአዝማች እንዲባል ስለሥራው በጅሮንድ አዛዥ እንዲባል ክርስቶስ የሚለው ስሙ በባሕርየ መለኮቱ ባሕርይ አካል ሲገኝ የተገኘ አይደለም ከበረ ስለተባለ ክርስቶስ እንደተባለ እውነት ነገር ተናገርክ ፡፡ በዚህ ስም ነቢያት የተቀቡ ተሰኙበት ተጠሩበት ይኸውም ትንቢት የሚናገሩ የከበሩ ማለት ነው ፡፡ በከመ ሀሎ  በመዝሙር ኢትግሥሡ መሲሐንየ ፤ ወካዕበ ይቤ ዕንባቆም ወጻዕከ ለአድኅኖ  ሕዝብከ ከመ ታድኅኖ ለመሢሕከ (በመዝሙር የቀባኋቸውን አትዳስሱ (አትንኩ) ተብሎ እንደተጻፈ ዳግመኛም ዕንባቆም ሕዝብህን ታድን ዘንድ ንጉሥህን ትልካለህ እንዳለ)” (ጰላድ ብራና ምቅ  32-3ሕትም 13 t 9-12) እንዳለ ፡፡ ኢትዮጵያዊው ቄርሎስ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ
ንሕነኒ ንሰመይ ክርስትያነ በከመ ተሰምየ ክርስቶስሃ ፡፡ ወንሰመይ መሢሓነ በከመ ተሰምየ መሢሐ ፡፡ ወንሰመይ ናዝራያነ በከመ ተሰምየ ናዝራዌ ፡፡ እስመ ለእሉ ሠለስቱ ጽዋዔ ፍካሬሆሙ አሐደ ይተረጐም ቅቡዕ ወቅቡዓን (እኛ ክርስቶስ እንደተባለ ክርስቲያን፣መሢሕም እንደተባለ መሢሐያን ፣ ናዝራዊም እንደተባለ ናዝራያን እንባላለን ፡፡ የእነዚህ የሦስቱ ስም አጠራር በአንድነት የተቀባ ፣ የተቀቡ ተብሎ ይተረጎማልና (.ምሥጢር ምዕ 20 49) ብለዋል ፡፡
“ቅዱስ እስጢፋኖስ ከሞተ በኋላ ምእመናን በአንድ ላይ ተሰብስበው በአንጾኪያ አንድ ዓመት ያህል ባስተማሩ ጊዜ ብዙ ሰዎች በክርስቶስ ስለአመኑና ቊጥራቸው እየበዛ ስለሄደ የደቀ መዛሙርቱ ኹሉ ስማቸው ክርስቲያን ተባለ ትርጓሜውም ቅቡዓን (የክርስቶስ ወገኖች) ማለት ነው ፡፡ በአንጾኪያ ክርስቲያን ተብለው ከመጠራታቸው በፊት ሐዋርያት ፣ ምእመናን ፣ ኅሩያን ፣አርድእት እየተባሉ ይጠሩ ነበር ፡፡ ከዚያ በኋላ በክርስቶስ ያመኑ ኹሉ ክርስቲያን ተብለው እንዲጠሩ ሥርዓት ሆነ ፡፡ የመሰብሰቢያቸውም ቤት ቤተ-ክርስቲያን ተባለ” (ሐዋ. ሥራ ምዕ 1126 ፤ ዜና ሐዋርያት ገጽ 56) ፡፡
 ስብሐት ለአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ
ይቀጥላል

5 comments:

  1. እግዚአብሔር አምላክ እድሜና ጤና ይስጥህ ወንድሜ ሰላሳና ስሳ መቶም ያማረ ፍሬ አፍርተህ ለፍሬ ያብቃህ የመንፈስ ቅዱስ ፀጋ

    ReplyDelete
  2. የእናታችን የቅድስት ድንግል ማርያም በረከት አይለይህ ባለህበት ይጠብቅህ ሀሳብህን ሁሉ ያሳካልህ

    ReplyDelete
  3. እግዚአብሔር አምላክ እድሜዉን ፀጋዉን ያብዛልን የዘላለም መስካሪ ያድርግልን በቤቱ ያፅናልን ያችን የማታልፈዋን እርስተ መንግስተ ሰማያትን ያውርስልን!!!

    ReplyDelete
  4. መድሀኒዓለም የአገልግሎት ዘመንንህን ያርዝምልን

    ReplyDelete
  5. እግዝአብሔር በረከት ረድኤት ያብዛልህ

    ReplyDelete