Thursday, November 21, 2019

ሃይማኖት መሢሐዊት ክፍል ሁለት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ!!
ሃይማኖት መሢሐዊት ክፍል ሁለት
በክርስቶስ ክርስቲያን በወልድ ዉሉደ እግዚአብሔር በመንፈስ ቅዱስ መንፈሳዉያን የተሰኛችሁ ማኅበረ መሢሐውያን እንደምን ሰነበታችሁ እንደምን አላችሁ እንደምንስ እስከ አሁኗ ሰዓት ድረስ ደረሳችሁ?አሜን እግዚአብሔር ይመሥገን ብለን ስሙን በኃጢአተኛ አንደበታችን እድንጠራው የወደደና የፈቀደ ልዑለ ባሕርይ ቅዱስ እግዚአብሔር በፈጠረው ፍጥረት አንደበት ሁሉ ስሙ ከአጽናፈ ዓለም እስከ ዓጽናፈ ዓለም ፣ ከአድማስ እስከ አድማስ ፣ ከበርባሮስ እስከ ጽርሐ  አርዓያም ድረስ የተመሰገነ ይሁን ፡፡ እሱን ጠርተን እሷን የማንተዋት የንጽኅናችን መሠረት የጽድቃችን አክሊል ፤ በካሮቹ ዘንድ ያለ ስማችን ስም የተሰጠንባት (ተቀባት ይላሉ እያሉ የሚናሩባት) አምላክን በድንግልና ጸንሳ በድንግልና የወለደች መልዕልተ ፍጡራን መትሕተ ፈጣሪ የሆነች ቅድስተ ቅዱሳን ንጽሕተ ንጹሐን ክብርት ድንግል ማርያም አምላክ በሰጣት ክብር መጠን የተመሠገነች ትሁንልን ፡፡ ጻድቃን ሰማዕታት ፣ ደናግል  መነኮሳት ፣ ነቢያት ሐዋርያት ፣ ቅዱሳን መላእክት እግዚአብሔር አምላክ በሰጣቸው ጸጋ መጠን የተመሰገኑ ይሁኑ ፡፡
የዛሬው መልእክት ሳይማሩ አስተማሪ ነን እያሉ የሚናገሩየግቢ ጉባዔመደዴዎች ለአእምሯቸው እና ለልቡናቸው ያልተረዱትን እኛ እደተሳሳትን አድርገው የሚናገሯቸውን ጉዳዮች በማንሳት ኦርቶዶክሳዊት መልስን መስጠት ይሆናል ፡፡ በጥሙና ተከታተሉኝ ፡፡

1ኛ፡- በወልደ አብ ሦስተኛ እትም ገጽ 108 ላይ እግዚአብሔር አምላክ ከመቅፅበት አምላክነቱን አጣ እንደገና ደግሞ የባህርይ አምላክ ሆነ” ይላሉ ቅብዓቶች” ››››››››.እያሉ የሰውን ልቡና ያሸፍታሉ ወደ ጥርጥርም ይወስዳሉ ፡፡ በእርግጥ እነሱ እናምነዋለን ብለው የሚናገሩትን ተዋሕዶን እንኳን አስተካክለው አገናዝበው የማይናገሩ ናቸውና ይህንን ቢሉ አይደንቀንም ፡፡ ጮርቃ መናፍቅ ድሮም ቢሆን ጫፍ እየያዘ መነሳት ልማዱ ነውና እኛ በእነዚህ ስንኳንስ የአምላክን ነገር ይቅርና የራሳቸውን የተፈጠሩባቸውን ዐራቱን ባሕርያት አስተካክለው መናገር የማይችሉ ምላስ ብቻ የሆኑ ሰዎች በሚናገሩት ዝርክርክ የሆነ ሀሳብ ማንነታችንን እንዳንክድ እንጠንቀቅ ፡፡ ለእነሱ አልገባቸውም ማለት አስተምህሮው ስሕተት ነው ማለት እዳይደለ ልንገነዘብ ይገባናል ፡፡
ወደ ጥያቄያቸው ስንገባ በወልደ አብ ሦስተኛ እትም ገጽ 108 ላይ ያለው የሚናገረው ሀሳብ አምላክነቱን አጣ የሚል ሳይሆን “ፅንሰቱ ምን ጊዜ ነው” በሚል አምድ ሥር የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን የተፀነሰበትን ጊዜ የሚናገር ነው ፡፡ ያልተጻፈ እያነበቡ ገደል ገብተው ሌላውን ገደል ከሚከቱ ከንቱ ሰዎች አምላክ በቸርነቱ ይጠብቀን ፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ አምላኩን አጣ የሚል ቆራጣ ትምህርት እደሌለን እያስገነዘብኩ በትክክለኛ ጥያቄያቸውና ሐዲስ አምላክ የሚለውን ድንቅ ምሥጢረ ሥጋዌ በምንመለከትበት በክፍል ሦስት እመለስበታለሁ፡፡
2ቅብዓቶች ወልድ ፍጡር ይላሉ”›››››››››.እያሉ በትክክል ያልተገለጠ ያልተተረጎመ ነጭ ውሸት ይዘው ሲዘሉ ይስተዋላሉ ፡፡ ለዚህም መነሻ የሚያደርጉት በወልደ አብ መጽሐፍ ላይ ከአምስቱ ግብራተ መንፈስ ቅዱስ አንዱ የሆነውመፍጠርበሚለው ረቂቅ ወልድ ከደመ ድንግልና ጋር ተዋሕዶ ተፈጠረ” የሚለውን ትምህርት ተመርኩዘው ነው ፡፡
በደንብ አስተውሉ ወገኖቼ! እኛ አባቶቻችን በዘመኑ በነበሩ ካሮች ተጽዕኖ ሥር ወድቀው እውነትን በአደባባይ ወጥተው እንዳይናገሯት አውደ ምሕረቱ የውርጋጥና የወንበዴ መዝናኛ ሆኖባቸውና እስከ ቅዱስ ሲኖዶስ ድረስ ብሎም እስከ “የሊቃውንት ጉባዔ” ድረስ ተጉዘው አንዳችም መፍትሄ ባለመሰጠቱ ሁሉንም ትተው ሹመትና ሥልጣንን ለነ ሆድ አደሩ አሽቀንጥረው ፤ እነሆ ኑሯቸውን ብእሴ ዓለም አርዌ ገዳም ከምታሰኝ ዓለማዊት ዝና ራሳቸውን አሽሽተው የተሰጠቻቸውን ዘመናቸውን በብሕትውና ለማሳለፍ ቆርጠዋልና ክርስትናቸውን ይዘው ከእውነት ጋር ላይለያዩ በየበረሃው ፣ በየ ፍርኩታው ገብተው ይገኛሉ ፡፡ ይሁን እንጅ የእኛ ጉትጎታ አላስቀምጥ ስላላቸው ለዘመናት በብራና ተጽፎ እውነተኛው የኦርቶዶክስ ክርስትና ሃይማኖት አስተምህሮ የተገለጠበት  ክቡር መጽሐፍ በወረቀት እንዲታተምልን ታስቦ በወረቀት ለሦስተኛ ጊዜ ታትሞልን እየተጠቀምንበት እንገኛለን ፡፡ ይሁን እንጅ ይህ ክቡር መጽሐፍ ሀሁን እንኳን አስተካክሎ በማይናገር መደዴ ትውልድ እየተዘነጠለ የሚነገርበት ይህ የስምተኛው ሽህ ዋዜማ! ገና ከዚህ የበለጠ ብዙ እንዲያሳየን ግልጽ ነው ፡፡
ወደ ሀሳቤ ልመለስና ወልደ አብ የተሰኘ ክቡር መጽሐፍ በጣና ደሴቶች ሳይቀር ትክክለኛ መጽሐፍ እንደሆነና እስ አሁንም ድረስ በየገዳማቱ እቃ ቤት እንደሚገኝ የሚታወቅ ሲሆን ፤ ከ1993 ዓ.ም ጀምሮ በወረቀት ታትሞ እየተጠቀምነው እንገኛለን ፤ ከዚህ ጋር ተያይዞ በየ አዳራሹ የሚዘሉ ጮርቃ ካሮች “ወልድ ፍጡር ይላል” እያሉ ይመጻደቁበታል ፤ ይባስ ብሎም ጫፉን ይዘው ሌላውንም እያስካዱበት ይገኛል ፡፡ በዚህ በወልደ አብ ላይ የሚገኘው “ወልድ ከደመ ድንግልና ጋር ተዋሕዶ ተፈጠረ” የሚለው አንቀጽ ፤ ትርጉሙ ተፈጠረ ሲል ነፍስ የሚሆነው ባሕርየ ነፍስ ፣ ሥጋ የሚሆነው ባሕርየ ሥጋ  ሆነ ፤ ዓይን ፣ ጆሮ ፣ እግር ፣ እጅ ቀረጸ ማለት ነው ፡፡ ይህም ምሥጢር እኛ ሰዎች የምንወለደው በዘርዓ ብእሲ (ከእናት ደም ከወንድ አባለ ዘር ተከፍሎ) ነውና ፤ በዚህ አንጻር ወልደ እግዚአብሔር ሕያው ወልደ ማርያም ሥግው እንበለ ዘርአ ብእሲ ከደመ ድንግልና (ከእመቤታችን ከተከፈለ ባሕርየ ሥጋና ባሕርየ ነፍስ ጋር) ጋር ተዋሕዶ የእለት ጽንስ መሆኑን የሚነግረን ነው ፡፡ በነገራችን ላይ ይህ ምሥጢር ለአእምሮ የከበደ ለሕሊናም የመጠቀ ነው ፤ ዳሩ ግን በወቅቱ የነበሩ አባቶቻችን ከካሮች ሊቃውንት አንድ እምጃ ወደፊት የመጠቁ ስለነበሩ ቁልጭ አድርገው ጽፈውልናል ፡፡ ታዲያ የዛሬ ውርጋጥ ትውልድ ስንኳን የፈጣሪን ነገር ራሱ የሚማረውን ሳይንስ እንኳን አስተካክሎ የማያውቅ ሳይሆን የተነገረበትን ምሥጢር ሳይረዳ “ቅብዓቶች ወልድ ፍጡር ይላሉ” እያለ ሲጃጃል ይስተዋላል ፡፡ ይህ ወልድ ፍጡር የሚለው ትምህርት እንዴት እንደሆና በምን እንደተባለ ፤ ካሮቹ እናምነዋለን ከሚሉት ከመጽሐፍ ቅዱስ እንደሚከተለው አወርበዋለሁ ፡፡
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ወልድ ፍጡር ብሎ ሲናገር አንቀጹን ለይቱ ንባቡን አቅንቶ ግብርና ባሕርይን አመላክቶ ቁልጭ አድርጎ ይናገራል እንጅ እንደ ካሮች በድፍኑ የሚናገረው አይደለም ፡፡ ይህንን ግርድፍ አነጋገር የሚናገሩ ካሮች አምላክ ሰው መሆኑን እናምናለን ይላሉ ፤ ነገር ግን ምን ዓይነት ሰው ሆነ ሲባሉ አብራርተው መናገር አይችሉም ፡፡ ጥንቱን መለኮት ፈጣሪ  ገባሪ ሲሆን ሥጋ ደግሞ ፍጡር ግቡር ነው ፡፡ ይህ ባሕርዩ ፈጣሪ ገባሪ የሆነ መለኮት (አካላዊ ቃል) ባሕርዩ ፍጡር ግቡር ከሆነ ሥጋ ጋር በአካል በባሕርይ በግብር ተዋሕዷል(አንድ ሆኗል) ፡፡ የዚህ አንድ የመሆን ምሥጢር ምሥጢረ ተዋሕዶ ይባላል ፡፡ በዚህ ጊዜ ቃል ከሥጋ ጋር ሲዋሐድ ቃልም ባሕርዩን(ፈጣሪነቱን እና ገባሪነቱን) አለቀቀም ሥጋም እንዲሁ ፍጡርነቱንና ተፈጣሪነቱን አለቀቀም፡፡ በዚህ ምክንያት ወልድ በሰውነቱ (ፍጡር ግቡር የሆነ ባሕርይ ባለው በሥጋው) ፍጡር ይባላል ፡፡ ይህን ደግሞ እኛ ያልነው ሳይሆን ቅዱሳን አባቶቻችን ጥርት አድርገው ያስተማሩት ትምህርት ነው ፡፡ ማስረጃችንም
v  ለሊሁ ፈጣሪ በእንተ ከመ ውእቱ አምላክ ወእግዚአብሔር ውእቱ ፤ወዓዲመ ንብሎ ፍጡረ እስመ ውእቱ ተወልደ እምብእሲት---እሱ አምላክ እግዚአብሔር ስለሆነ ፈጣሪ እንለዋለን ወዲህም ከድንግል በሥጋ ስለተወለደ ፍጡር እንለዋለንእንዳለ ቅዱስ ቄር በሃይ.አበው ስምዓት ምዕ 124 2 t 19 ::
v  ወካዕበ ይቤ ንብል በእንተ ዝንቱ ዋሕድ ቃል አሐዱ ኅቡረ ከመ ለሊሁ ፍጡረ ወመዋቲ በሥጋ ፤ወኢመዋቲ በመለኮት (ዳመኛም ስለዚህ ተቀዳሚ ተከታይ ስለሌለው በተዋሕዶ አንድ ስለኾነ ቃል እሱ በሥጋ ፍጡር መዋቲ ነው በመለኮት ግን ፍጡር መዋቲ አይደለም እንላለን) ፡፡ ወባሕቱ እስመ ሞትሰ መተፈጥሮ ለሥጋ ውእቱ (መፈጠርና ሞት ለሥጋ ነው) ወህላዌ መለኮትሰ ነኪር ውእቱ እምእሉ(መለኮት ግን ከመሞትና ከመፈጠር የራቀ ነው) ወባሕቱ በእንተ ዘተዋሐደ ምስለ ሥጋ ንብል በእንቲአሁ ፍጡር ውእቱ ወመዋቲ(ነገር ግን ሥጋን ስለተዋሐደ ፍጡር መዋቲ ነው እንላለን) ኢፍጡር እን ወኢመዋቲ በህላዌ መለኮት(በባሕርየ መለኮት ግን ያልተፈጠረ የማይሞት ነው ብለን እንናገራለን ፡፡ ወካዕበ ይቤ እመሰ ተወልደ ወተፈጥረ ንሬሲ እሎንተ ክልዔተ ለዘይደሉ ቦሙ ( ዳግመኛም ከተወለደ ሰው ከኾነ እነዚህን ሁለቱን ለሚገባቸው እናደርጋለን አለ) ተወልደ ቃል እም አብ እምቅድመ ኩሉ ዓለም በከመ ንቤ ንሕነ ወዘፈጠረ ሰብአ ኮነ በእንቲአነ በከመ ይቤ ወንጌላዊ ብጹዕ (እኛ እንደተናገርን ዓለም ሳይፈጠር ዓለም ሳይፈጠር አካላዊ ከአብ ተወለደ ሰውን የፈጠረ እሱ ስለ እኛ ሰው ኾነ አለ ስምዓት 124 29፡፡ ብለዋል አባቶቻችን በሃይማኖተ አበው ፡፡

እና እነህ ካሮች እነ ቅዱስ ቄርሎስ ያስተማሩትን ክሕደት አስመስለው ማቅረባቸው የጤነኝነት ነው ጎበዝ? እኔ የምፈርደው በካሮች ሳይሆን በእኛ ልጆች ነው በቃ ሃይማኖት ማለት አንድ ውርጋጥ በጮኸ ቁጥር ስሕተት ነው እያሉ መካድ ነውን? እስከመጨረሻው የጸና እሱ ይድናል ተባለ እንጅ በመጀመሪያ የካደ እሱ ይድናል ተብሏልን?፡፡ ካሮችምወልድ ፍጡር” የተባለበት አንቀጽ ሳይለዩ ዝም ብለው በጅምላ ሲናገሩ ልቡናቸው እንደምን ጨከነላቸው? እህ እኛ ከዚህ በላይ ምን ብለን እንናገር ጎበዝ!? ሰው ሆነ ብለው ያምናሉ ሰው በሆነበት አንቀጽ በባሕርየ ትስብእት ፍጡር ነው ሲባሉ ይጨነቃሉ ፡፡ ቆይ ግን ሰው መሆኑን ካመኑለት ፍጡር ያይደለ ሰው አለን? እኒህ ከንቱዎች ሰው ሆነ እያሉ ሲያምኑት የሰውን ባሕርይ (ፍጡርነትን) ወዴት ጣሉት?፡፡ እኛ ግን አባቶቻችን እደነገሩን ወልድ ፍጡር ብቻ ሳይሆን መዋቲ እንደሆነ እናምናለን ፡፡ አስተውል ፍጡር ነው ስንል ርጉም አርዮስ እንደተናገረ በባሕርየ መለኮቱ ፍጡር ነው ያልን አይደለንም ይልቁንም በሰውነቱ እንላለን እንጅ ፡፡ ለዚህም ማስረጃችን ከላይ በሃይማኖተ አበው እነ ቅዱስ ቄርሎስ የተናገሩት ቃል ነው ፡፡ ካሮች ካልፈለጉ ሃይማኖተ አበውን ይፋቁት ወይም ቆርጠው ይጣሉት እኛ ግን ማስረጃችን መጽሐፍ ቅዱስ ነውና መጽሐፍ ቅዱስ ያለውን ይዘን እንቀጥላለን ፡፡ ከላይ እንደ ገለጽኩት ወካዕበ ይቤ እመሰ ተወልደ ወተፈጥረ ንሬሲ እሎንተ ክልዔተ ለዘይደሉ ቦሙ ( ዳግመኛም ከተወለደ ሰው ከኾነ እነዚህን ሁለቱን ለሚገባቸው እናደርጋለን አለ)” ብለው አባቶቻችን መናገራቸው በባሕርየ መለኮቱ ሞት መፈጠር የለበትም በሰውነቱ ግን መዋ ፍጡር ነውና እዚህን ነገሮች ለመለኮትና ለትስብእት የሚገባቸውን ነገሮች ስንናገር እኖራለን እንጅ እንደ ካሮች አምላክነቱን አምነን ሰውነቱን አንክድም ፡፡ አምላክ ወሰብእ ሲባል ይኖራል እንጅ አምላክ ብቻ ወይንም ሰው ብቻ ሲባል አይኖርም ፡፡ አስተውል ፍጡር ነው ሲባል ከዐራቱ ባሕርያተ ሥጋ ከሦስቱ ግብራተ ነፍስ የተሠራ ሥጋን ተዋሕዶ በየማነ አብ በዘባነ ኪሩብ ተቀምጧል በዳግም ምጽዓትም በለበሰው በሦስት ክንድ ከስንዝር በሆነ ሥጋ ተገልጦ ይመጣል እያልን ነው እንጅ አይሁድ እንደሚሉት ዕሩቅ ብእሲ ወልደ ዮሴፍ ነው እያልን እንዳልሆነ ልንረዳ ይገባል ፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥወልድ ፍጡር በትስብእቱየሚለው ቃል በሰፊው ተነግሯል ፡፡ ካሮቹ ግን ኅሊናቻም ልቡናቸውም እንደ ፈርዖን የደነደነ በመሆኑ ዓይናቸውን ግንባር አድርገው ይታገሉናል ፡፡ አባ ጊዮርጊዝ ዘጋስጫ ወልድ ፍጡር የተባለበትን አንቀጽ እንዲህ አስተምረውታል ፡፡
v  ሥጋው ፍጡር ባይሆን ኖሮ በጉልበት ባልታቀፈ በእጆችም ባልተዳሰሰ ነበር ፡፡ መለኮቱም ፈጣሪ ባይሆን ኖሮ ወንድ ከማታውቅ ሴት ልጅ ጡት የድንግልና ወተት ባልጠባለ ነበር አብርሃም ሳይወለድ እኔ ነበርሁ ባላለ ነበር ፡፡ ሥጋው ፍጡር ባይሆን ኖሮ በዮሐንስ እጅ ባልተዳሰሰ በዮርዳኖስም ባሕር ባልተጠመቀ መለኮቱም ፈጣሪ ባይሆን ኖሮ አብ ይህ የምወደው ልጄ ነው እርሱን ስሙት ብሎ ስለርሱ ባልመሰከረ ነበር ዳግመኛም መንፈስ ቅዱስ በሥጋዊ ርግብ አምሳል በራሱ ላይ ባላረፈ ፡፡ ሥጋው ፍጡር ባይሆን ለጥሙ ከሳምራዊቷ ሴት ውኃ ባልጠየቀ (ባልለመነ) በመለኮቱም ፈጣሪ ባይሆን ኖሮ የገሊላ ክፍል በምትሆን በቃና ውኃውን ወይን ባላደረገ ፡፡ ሥጋው ፍጡር ባይሆን ኖሮ ደም የሚፈሳት ሴት የልብሱን ጫፍ ኃጢአተኛዋም እግሮቹን ባልዳሰሱ ነበር ፡፡ መለኮቱም ፈጣሪ ባይሆን ኖሮ ልብሱን ስለዳሰሰችው ሴት ከእኔ ኃይል እንደወጣ አውቄአለሁ ባላለ ነበር ፡፡ መለኮት ኃይል አለው በመለኮትም ኃይል የደሟን ፈሳሽ አደረቀ እግሮቹን ስለዳሰሰች ኃጢአተኛይቱ ሴትም ኃጢአትሽ ተሠርዮልሻል አላት ከብቻው ከእግዚአብሔር በቀር ኃጢአትን ማስተሠረይ እንግዲህ ማን ይችላል? ፡፡ ሥጋው ፍጡር ባይሆን ኖሮ ልጄ ብሎ የኢያኢሮስን ሴት ልጅ ባልጠራት መለኮቱም ፈጣሪ ባይሆን ከሞተች በኋላ ሕያዊት ሆና ባላነሣት ነበር ፡፡ ሥጋው ፍጡር ባይሆን ኖሮ በምራቁ እንትፍ ብሎ መሬት ላይ ጭቃ ባላደረገ መለኮቱም ፈጣሪ ባይሆን ኖሮ ዕውር ሆኖ የተወለደውን ሰው ምራቁን በመቀባት ዓይኖቹን ባላበራ ፡፡ ሥጋው ፍጡር ባይሆን ኖሮ ሞገድ ሲነሳ በመርከብ በውስጠኛ ክፍል ባልተኛ በመለኮቱም ፈጣሪ ባይሆን ኖሮ መርከቧን ከነፋሳትና ከሞገድ መነዋወጽ ባላረጋጋት ነበር ፡፡ ሥጋው ፍጡር ባይሆን ኖሮ መንገድ በመሄድ ባልደከመ መለኮቱም ፈጣሪ ባይሆን እግረ ሰባሮችን (እካሶችን) ባላደናቸው እንደ ጎበዝ ሩጫም እንዲሮጡ ባላደረጋቸው ፡፡ ሥጋው ፍጡር ባይሆን ባልተራበ መለኮቱም ፈጣሪ ባይሆን ኖሮ አምስት ሽህ ሰዎች በአምስት እንጀራ በሁለት ዓሳዎች ዐራቱን ሽህ ሰዎች በሰባት እንጀራ በጥቂት ዓሳዎች ባላጠገባቸው ነበር ፡፡ ሥጋው ፍጡር ባይሆንስ በአልዓዛር ሞት ባላለቀሰ መለኮቱም ፈጣሪ ባይሆን በመጣራት ከመቃብር ውስጥ ባላወጣው ፡፡ ሥጋው ፍጡር ባይሆን በአህያይቱና በውርንጫዋ ላይ ባልተቀመጠ መለኮቱ ፈጣሪ ባይሆን በሕጻናትና በሚጠቡት አንደበት (አፍ) ባልተመሰገነ ፡፡ ሥጋው ፍጡር ባይሆን ኖሮ በሊቃነ ካህናት አገልጋዮች በጥፊ ባልተመታ ነበር ፡፡ መለኮቱም ፈጣሪ ባይሆን በጴጥሮስ ሰይፍ የተቆረጠውን ሰው ጆሮ ባልመለሰ ፡፡ ሥጋው ፍጡር ባይሆን በጲላጦስ አደባባይ ባልቆመ መለኮቱ ፈጣሪ ባይሆን ጲላጦስን መንግሥቴ በዚህ ዓለም ቢሆን ኖሮ አይሁድ ወደ አንተ አሳልፈው እንዳይሰጡኝ ባለሟሎቼ ፈጽመው በተዋጉልኝ ነበር ባላለው ነበር ፡፡ ሥጋው ፍጡር ባይሆን ኖሮ የጲላጦስ ወታደሮች ልብሱን ባልገፈፉት መለኮትም ፈጣሪ ባይሆን ኖሮ ጸሐይ ዕርቃኑን ለማየት ባላፈረ ዓለምንም ጨለማ ውስጥ ለመተው ብርሃኑን ባልሰወረ ፡፡ ሥጋው ፍጡር ባይሆን ኖሮ አምላኬ አምላኬ ለምን ተውከኝ ባላለ መለኮት ፈጣሪ ባይሆን ኖሮ አባት ሆይ ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ ባላለ ነበር ፡፡ ሥጋው ፍጡር ባይሆን ኖሮ ሞትን በሥጋ ባልቀመሰ መለኮቱም ፈጣሪ ባይሆን ኖሮ ምድርን ባላነዋወጣት የቤተ-መቅደስንም መጋረጃ ባልቀደዳት ነበር ፡፡ ሥጋው ፍጡር ባይሆን ኖሮ በጦር ባልተወጋ መለኮቱም ፈጣሪ ባይሆን የደሙ ጠብታ አለቱን ባልሰነጠቀ ከጎኑም የፈሰሰ የምሕረቱ ጠል ሙታንን ባላነሣ ፡፡ ሥጋው ፍጡር ባይሆን ቀድሞ እንደሞተ በመቃብር ውስጥ ባልተኛ መለኮቱም ፈጣሪ ባይሆን ኖሮ እርሱ እኔ ራሴ ነፍሴን በፈቃዴ እሰጣታለሁ በፈቃዴም ላኖራት ሥልጣን አለኝ ሁለተኛም ላነሳት ሥልጣን አለኝ ይህንን ትእዛዝ ከአባቴ ተቀበልሁ እንዳለ ባላስነሣት ነፍሱንም ወደ ሥጋ ባልመለሣት ፡፡ ሥጋው ፍጡር ባይሆን ኖሮ በተነሳባት እሑድ ምሽት ለመመገብ ከደቀመዛሙርቱ ጋር ባልተቀመጠ በመለኮቱም ፈጣሪ ባይሆን መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ ኃጢአታቸውን ይቅር ላላችኋቸው ይቀርላቸዋል ኃጢአታቸውን ይቅር ላላላችኋቸው አይቀርላቸውም ብሎ በደቀመዛሙርቱ ፊት ላይ እፍ ባላለባቸው ነበር ፡፡ ሥጋው ፍጡር ባይሆን ኖሮ መምህራን በተማሪዎች እንደሚያደርጉት ሥርዓት እጁን በሐዋርያት ላይ ባላኖረ (ባልጫነ) በመለኮቱም ፈጣሪ ባይሆን በእሳት ደመና ባልተጫነ ወደ ሰማይ ከፍ ከፍ ብሎ በአባቱ ቀኝ ባልተቀመጠ ” (.ምሥጢር አንቀጽ 3 t 37-45) በማለት ስለ ሥጋና ስለ መለኮት ህላዌ ተናግረዋል ፡፡
v  ወዓዲመ ይትበሀል ፍጡረ በእንተ ዘኮነ ሥጋ ወኀደረ ላዕሌነ (ዳግመኛም ባሕርያችንን ተዋሕዶ ሰው ስለሆነ ፍጡር ይባላል(ሃይ.አበው ዘጎርጎርዮስ ምዕ 35 t 6) ፡፡
v  ወዘሰ ንቤ ፍጡረ ውእቱ በእንተ ዘተሳተፈ ሥጋ ድካምነ በሥርዓት ዘገብሮ በእንቲአነ (ፍጡር ነው ያልነውም ስለእኛ ባደረገው ሥርዓት (ተዋሕዶ) ደካማ ባሕርያችንን ስለተዋሐደ ነው(ሃይ.አበው ዘኑሲስ ምዕ 35 t 3) ፡፡
v  ወካዕበ ይቤ በእንተ ተሠገዎቱ ለመድኅን ከመ ፍጡር ውእቱ (ዳግመኛም መድኅን ሰው ስለመሆኑ ሲናገር ፍጡር እንደሆነ ተናገረ)(ቃለ ስምዓት ምዕ 124 t 17) ፡፡
v  ዓዲ አመ ለብሰ አርአያ ሰብእ በእንተ መድኃኒት ኵልነ ይብል እሙነ ከመ ሰብእ እስመ እግዚአብሔር ፈጠረኒ (እንዲሁ ደግሞ እኛን ሁላችንን ለማዳን የሰውን ባሕርይ በተዋሐደ ጊዜ በእውነት ሰው እንደመሆኑ እግዚአብሔር ፈጠረኝ ይላል (ቃለ ስምዓት ምዕ 124 t 25) ፡፡
v  እስመ ሰብእሰ ፍጡር ውእቱ ወእንበይነ ዝንቱ ይብል እግዚአብሔር ፈጠረኒ በእንተ ውእቱ ዘኮነ ሰብአ (ሰው ፍጡር ነውና ስለዚህም እሱ ሰው ስለሆነ እግዚአብሔር ፈጠረኝ ይላል)(ቃለ ስምዓት ምዕ 124 t 26
v   ወከመዝ እንከ ሶበ ፈጠረ ሥጋሁ በእንቲአሁ ውእቱ ከመ ፍጡር እስመ ሥጋ ዘተፈጥረ ረሰየ ሎቱ ወህላዌ መለኮቱሰ ኢፍጡር ውእቱ (እንዲህ ሥጋን ፈጥሮ ስለተዋሐደ እሱ ፍጡር ይባላል የተፈጠረ ሥጋን እርሱ ገንዘብ አድርጓልና በባሕርየ መለኮቱ ግን ፍጡር አይደለም(ቃለ ስምዓት ምዕ 124 t 28
ወንድሞቼ እህቶቼ ሳይማሩ ተማሪ ነን እያሉ ሰውን የሚያሸብሩ ያውም ደግሞ በኦሪት ሳይቀር አምልኮተ እግዚአብሔርን ሲፈጽም የነበረ የጎጃምን ምእመን ሃይማኖት የለህም እያሉ የሚያስኮበልሉ መናጢዎች ወልድ በሰውነቱ ፍጡር ነው ካልተባለማ የሰውነቱ ባሕርይ ፍጡርነት ተለውጧል ሊሉት ነውን?በተዋሐደው ሥጋው ፍጡር ካልሆነማ የመለኮት ሥጋ አለውን?የትኛውን ሥጋ ነው የሚበሉን የማንን ደም ነው ጠጣን የሚሉት ወንድም እህቶቼ?የሚቆረሥ ሥጋና የሚፈስ ደም ከዐራቱ ባሕርያተ ሥጋ(ከእሳት፣ ከመሬት ከውኃ እና ከመሬት) የተገኘ አይደለምን?ነው ወይስ ደግሞ መለኮት በባሕርዩ ደምና ሥጋ አለው ሊሉን ይሆንን?እኛ እኮ ከአበው እንደተቀበልነው በወልደ አብ ላይ ተጽፎ የሚገኘውን ትምህርት የቀዳነውና የጻፍነው ከመጽሐፍ ቅዱስ ከሃይማኖተ አበው ነው እና ካሮቹ በሃይማኖተ አበው አያምኑምን?ካመኑ ግእዝ ከአማርኛ አድርጌ ይኸው ጠቅሸላቸዋለሁ በቤተክርስቲያናቸው ካለው የሃይማኖተ አበው ምዕራፍና ቁጥር አመሣክረው እስኪ ምን እንደሚል ይመልከቱት!፡፡

እናንት ከምሥራቅ ጎጃም ወደ ተለያዩ የትምህርት ተቋማት ሂዳችሁ ሃይማኖታችሁን ለውጡ ተብላችሁ የምትንገላቱ ሰዎች አይዟችሁ በርቱ የክርስትና ሕይወት እንዲህ እየተፈጠኑ የሚያልፉበት ፣ እየተሳደዱ ፣ እየተደበደቡ ፣ እየተገፉ የሚኖሩበት እንጅ እያሳደዱ እየገፉ የሚኖሩበት አይደለም ፡፡ ይህንን ደግሞ ከራሱ ከጌታችን ከመድኃኔ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ  መረዳት ይቻላል ፡፡ እነዚያ ክፉ ጥፉ አይሁዶች ከአምላክ በላይ እኛ እናውቃለን በማለት በግፍ አንገላቱት ፣ ደበደቡት፣ ተፉበት ፣ ተሳለቁበት በስተመጨረሻም ይሙት በቃ ፈረዱበት ፡፡ ነገር ግን እነሱ ቢፈርዱበት የመጣው ሰውን ለማዳን ነውና ሞትን ድል አድርጎ በክብር ተነሥቷል ፡፡ ዛሬም ካሮቹ እውነተኛዋን መንገድ እያስተው እነሱ በመሰላቸው መንገድ እየመሩ ፤ እነ ቅዱስ ቄርሎስ ፣ እነ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ፣ እነ ቅዱስ ሳዊሮስ …….የኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ደጋግ አባቶች የወሰኑትን እዉነት ሙጥጥ አድርገው ክደው እኛን ለማስካድ ሲያሳድዱን ይገኛሉና ሁላችሁም በያላችሁበት ጹኑ ፡፡ ከዚህ ላይ መናገር የምፈልገው ማንም ሰው የፈለገውን የማመን መብት አለው ፡፡ ይሁን እንጅ በካሮች የሽሙጥ ንግግር “ቅብዐቶች” የምንባል መሢሐውያንን “ ሃይማኖት የላችሁም” እያሉ ስለ እኛ እነሱ የሚያምኑልን እስከሚመስሉ ድረስ እንደ አይሁድ በተንኮላቸው ታሥረው በስድብና በምላስ ብቻ ሲያስኮበልሏችሁ ማየት እጅግ ከባድ ነውና ይህንን ጻፍኩላችሁ ፤ ከዚያም እናንተም ተከታይ ከሌላት እውነት ብዙ ተከታይ ያለው ውሸት ከበለጠባችሁ ምርጫችሁ የራሳችሁ እንደሆነ ለማሳሰብ እወዳለሁ ፡፡ ከዚህ ላይ ማስተዋል ያለባችሁ ነገር ግን ፤ ስትኮበልሉ አውቃችሁት ትክክለኛ መረጃ አግኝታችሁበት ቢሆን የተሻለ ነው ፡፡ በተለይ ደግሞ ከአሁን በፊት ሁለተኛ የተጠመቃችሁ ወንድሞችና እህቶች የእናንተ ድጋሚ ተጠምቆ መጥፋት አንሶ ሌሎቹን አታዋክቧቸው አታጥፏቸውም ፡፡ የማይሉትን ይላሉ እያላችሁ አታሳቋቸው ፡፡ ልብና አእምሮ ካላችሁ መጻሕፍትን ተመልከቱ እንደ ሉተር ልጆች ጫፍ ይዛችሁ አትንጎዱ ፡፡ እናም ወልድ ፍጡር የተባለበትን አንቀጽ ሳትለዩ በድፍኑቅብዐቶች ወልድ ፍጡር ይላሉእያላችሁ አትደናበሩ ፡፡ ወደ ጅምላ ፍርድ ከመሄዳችሁ በፊት ፍጡር ማለት ምን ማለት እንደሆነ ተረዱ ከዚያም ፍጡር የተባለበት መንገዱና ምሥጢሩ ምን እደሆነ በደንብ ተረዱ ፡፡ከዚያም በኋላ መጽሐፍ ቅዱስ ፍጡር ብሎ የተናገረበትን አንቀጽ አገናዝቡት ፡፡ ከዚያ ይህ የሰጠዋችሁ የሃይማኖተ አበው ክፍል ውሸት ከሆነ እውነትም ተሳስተናል ማለት ነው ፡፡ ከዚያ ውጭ “ቅብዐቶች እንዲህ ይላሉ” እያላችሁ ያልነውንና የምናምነውን ሳረዱ አንሸዋራችሁ ብትረዱት በዚያው በጠማማው መንገዳሁ ትነጉዳላችሁ እንጅ እኛ እደሆንን ያው እኛ ነን ፡፡
ከዚህ ላይ ልናስተውለው የሚገባን ጉዳይ ልክ ከአሁን በፊት እንደጠቀስናቸው ኃይለ ቃላት በሌሎችም ቅዱሳት መጻሕፍት ተጠቅሰው ብናገኝ ርጉም አርዮስ እንደተናገረው “ወልድ ፍጡር በመለኮቱ” ማለትን የሚያሳዩ አለመሆናቸውን ነው ፡፡ወሶበ ትሰምዕ ከመ ውእቱ ፍጡር ኢተሐሊ ግሙራ ከመ ዝንቱ ይትበሀል በእንተ ቃል ከመ እግዚአብሔር ፈጠሮ በከመ አርዮስ ርጉም ፤ አላ ይትበሀል በእንተ ሥጋ ከመ ውእቱ ፍጡር (እርሱ ፍጡር እንደተባለ ብትሰማ ርጉም አርዮስ ፍጡር ነው ብሎ እንደተናገረው ፤ ይህ አነጋገር እግዚአብሔር ቃልን እንደፈጠረው የተነገረ ነው ብለህ አታስብ ሥጋን ስለተዋሐደ ፍጡር ነው ይባላል እንጅ) ፤ እንዳለ ቅዱስ  ቴዎዶስዮስ (ሃይ.አበው ምዕ83 t 14) ፡፡
አርዮስም ለመወገዝ የደረሰበት ጥፋቱ እግዚአብሔር አብ ቃልን ፈጠረው(ወልድ ፍጡር በመለኮቱ) በማለቱ እንጅ ወልድ ፍጡር በትስብእቱ በማለቱ አይደለም ፡፡ ተፈጠረ ተብሎ መነገሩ እግዚአብሔር ቃል እምቅድመ ዓለም እንደ አብ እንደመንፈስ ቅዱስ ያልነበረ ሆኖ ሥጋ የተፈጠረ ጊዜ ተፈጠረ ወይም ተገኘ ማለት እንዳልሆነ እናስተውል ፡፡ ይልቁንም ቃል ከሥጋ ፣ ሥጋም ከቃል ጋር የተዋሐደውን ጽኑዕነት (የማይለያይ ፤ የማይለዋወጥ ፤ የማይፈርስ ፤ የቀንጃ ያይደለ የከዊን ፤ ተዓቅቦንና ተገናዛቢነትን የያዘ ፍጹም) ለመግለጥ የምንናገረው ነው እንጅ ፡፡ እንዴት ቢሉ ፤ ሥጋን በቃልነቱ ፈጣሪ እንዳልነው ኹሉ ቃልን በሥጋነቱ ፍጡር ካላልነው የሥጋንና የቃልን ተዋሕዶ የምናፈርስ እንሆናለንና ፡፡
ዛቲ ሃይማኖት መሢሐዊት ዘትትአመን ባቲ ቤተክርስቲያን ቅድስት
ስብሐት ለአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ
ስብሐት ለማርያም ድንግል ወላዲተ አምላክ እግዝእትነ
ስብሐት ለመስቀለ እግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ እጸ መድኃኒት ኃይልነ ወጸወንነ
ይቀጥላል

በክፍል ሦስት መልእክቴ ሐዲስ አምላክ ስለሚለውና መናፍቃን ካሮች “ቅብዓቶች ለጻድቃንና ለመስቀል ሥግደት አይገባም ይላሉ” ስለሚሉት ሉተራዊ ክሕደታቸው ሰፊ ማብራሪያ ይዤ እመጣለሁ ፤ እስከዚያው አምላክ በቸርነቱ ይጠብቀን ፡፡

No comments:

Post a Comment