Wednesday, November 28, 2018

"ስም ሰጥተው ግብር ነሱት"


ክፍል [ 2/2 ]

የድርጅቱ ተልእኮ:- “ማኅበሩ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ውጤት የሆኑትን የተለያዩ ትምህርተ ሃይማኖት ማስፋፊያ ዘዴዎችን በመጠቀም ግቢ ጉባኤያትና ምእመናን የወንጌልን ትምህርት፣ ሥርዓት፣ ትውፊት፣ እንዲያቆዩና እንዲጠበቁ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ መዋቅር እንዲጠናከር አቅሙ እንዲያድግ ማድረግና በየዘመኑ የሚከሰቱ ተለዋዋጭ ሃይማኖታዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች በመቃኘት የቤተ ክርስቲያኒቱን ሐዋርያዊ አገልግሎት ማጠናከር፡፡” ይላል::
 “ወሬ ብቻ” ምን ትርጉም አለው? የሚገርመው ደግሞ ሥርዓትና ትውፊት ጠባቂ፣ አስጠባቂ እናንተ ሆናችሁ እያለ የምትሽሩትም ደግሞ እናንተ መሆናችሁ ነው:: የበዓላትና የአጽዋማት ማውጫ ብሎ ያሰራው ሶፍትዌር በዓለ ልደትን በዘመነ ዮሐንስ ታኅሳስ 28 ቀን እንደሚከበር መናገሩ ነው:: እውነታው ግን ልደተ ክርስቶስን ታኅሳስ 28 ቀን ማክበር የጀመራችሁ ከ1298 ዓ/ም ጀምሮ እንደሆነ አቡነ ጎርጎርዮስ “በ28 መከበር የተጀመረው በ1298 ዓ/ም ነው ብለው ያንኑ 29ኙን መያዙ ይሻላል ብለዋል” (የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ):: ድርጅቱ ግን ይኼው ታኅሳስ 28 ቀን ልደተ ክርስቶስን ማክበር ክህደት፣ ምንፍቅና፣ ሥርዓትንና ትውፊትን መጣስ ሆኖ እያለ ደግሞ የጥንት ለማስመሰል የማይሰራው ስራ የለም::
ታዲያ ይህ ድርጅት እራሱው ስርዓት አልባ ሆኖ የትኛውን ሥርዓት ነው የሚያስተምረው፣ እራሱ ትውፊት እያበላሸ የትኛውን ትውፊት ነው ለትውልድ የሚያስረክበው? ድርጅቱስ በማያገባው እየገባ ሊቃውንትን ከሊቃውንት፣ ካህናትን ከካህናት ማጣላቱን፣ አባቶችን ማሳደዱን እንኳ ቢያቆም ለእሱ ሥርዓቱና ትውፊቱ እንዳስጠበቀ ይቆጠርለት ነበር:: አበው ቅዱሳን ይህን ክፉ ሥራ አልሰሩምና::
የቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ መዋቅሩ ችግር አለበት በማለት ለእሱ በሚመቸው መንገድ ነገሮችን በማደራጀት የቤተ ክርስቲያኒቱ ሁሉ ገቢ ወደ እርሱ እንዲሄድ በማድረግ “ከአጋም ጋር የተጠጋ ቁልቋል ሲያለቅስ ይኖራል” እንዲሉ ቤተ ክርስቲያንንም የወላድ መኻን በማድረግ ለእናትና ለአባቱ የማይታዘዝ ጋጠ ወጥ አባላትን ከያዘ ድርጅት ጋር ሳትወድ በግድ ጉርብትና በመግባቷ እያለቀሰች ትገኛለች::
ለመሆኑ ሃይማኖት እንደ ሸቀጥ በየዘመኑ ይለዋወጣል እንዴ? አይ አለመታደል! ሌላው ደግሞ “..... ፖለቲካዊ ችግሮች በመቃኘት” ይላል ምንም እንኳን ድርጅቱ ምንም አይነት ፖለቲካዊ አቋም እንደሌለው ዘወትር ቢናገርም “ከአንድ እራስ ሁለት ምላስ” እንዲሉ ውሸት መናገር ለእነሱ አዲስ ነገራቸው አይደለምና በራሳቸው አንደበት ተናገሩት:: ፖለቲካዊ አቋም ከሌላቸው ስለፖለቲካ ምን አገባቸውና ነው ፖለቲካዊ ችግር የሚቃኙት?

የድርጅቱ አስፈላጊነት:- “የቤተ ክርስቲያቱ መዋቅር ያልሸፈነችውን ክፍተቶች በመሙላት ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማ የሚገቡትን የዘመኑን ትውልድ ከመንፈሳዊነትና ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን ትምህርት ጋር በማዋሐድና ከአበው በማቀራረብ ቤተ ክርስቲያን የምትጠብቅበትን ድርሻ እንድንወጣ ለማድረግ የማኅበረ ቅዱሳን አገልግሎት አስፈላጊ ነው፡፡”
የድርጅቱ ዓላማዎች:- “ማኅበሩ ከዚህ ቀጥሎ የተዘረዘሩትን ዐበይት ዓላማች አሉት፡፡
ሀ/ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማ ውስጥ የሚማሩ ወጣቶችን በማኅበሩ ሥር አደራጅቶ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን እምነት፣ ሥርዓት እና ትውፊት እንዲማሩ እና የአባቶች ተተኪ እንዲሆኑ ማድረግ፣
ለ/ የቤተ ክርስቲያን እምነትና ሥርዓት ሳይለውጥ ተጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ ለማድረግ ይቻል ዘንድ ለዘመኑ ትውልድ ትምህርተ ሃይማኖት እንዲዳረስ ማድረግ፣
ሐ/ ከሚመለከታቸው የቤተ ክርስቲያኒቱ አካላት ጋር በመነጋገርና በማስፈቀድ ትምህርተ ወንጌልን በተለያዩ ዘዴዎች በመጽሔት፣ በጋዜጣ፣ በበራሪ ጽሑፎች፣ በካሴት እና በመሳሰሉት እንዲስፋፋ ማድረግ፣
መ/ የተማረው የኅብረተሰብ ክፍል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን በገንዘብ፣ በዕውቀቱና በጉልበቱ እንዲያገለግል አስፈላጊውን ሁሉ ማመቻቸት፣
ሠ/ ስለ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጥናት የሚያደርጉ ሰዎችን በተለይ ወጣት ምሁራንን ማበረታታና በሚቻለው ሁሉ መርዳት፡፡” ይላል::
 ነገሩ ሁሉ በእውነት ያለ ሀሰት ቢሆን መልካም ነበር:: እውነት ነው ቤተ ክርስቲያንን ልጇ እንደ ደረሰላት እናት አይዞሽ ደረስኩልሽ ከዚህ በኋላስ ምንም የሚያስቸግርሽ ነገር አይኖርም እስካሁን የተሰቃየሽው ይበቃሻል ብሎ የልጅነትን ኃላፊነት ተቀብሎ መስራት ከአበው ሲወርድ ሲዋረድ የተቀበልነው ወግ ማዕረግ ነው:: ድርጅቱ ያፈራው ትውልድ ግን ሳያውቁ አወቅን በማለት፣ በማያገባቸው እየገቡ፣ ህግና ሥርዓትን ለይተው ሳያውቁ “ከእኛ በላይ ሊቅ ለአሳር ነው” በማለት ሁሉን ያወቅን ሁሉን የያዝን እየመሰላቸው “እህሌን የሚመገብ ሰኮናውን አነሳብኝ” እንዳለ መጽሐፍ ስተው የሚያስቱ፣ ገደል የሚከቱ፣ በሀሰት ካባ፣ በውሸት ደባ ተሸፍነው ቤተ ክርስቲያንን የሚበጠብጡ አባላትን እንጅ እውነቱን ከሀሰት፣ ምዕመናንን ከነፍስ ሞት ለመለየት የሚተጉ፣ በአበው ፈለግ የሚጓዙ ቢሆኑ ኖሮማ እሰየው ነበር::
ሀ/ እንኳንስ በአባቶች ተተኪ ትውልድ ሊሆን ይቅርና እራሱን እንኳ ቆም ብሎ ማየት የማይችል እንደ ጄሬ እሳት አንዴ ቦግ ብሎ የሚጠፋ ትውልድ ነውና የተፈጠረው ለህግና ለሥርዓት መጣስ ምክንያት ቢሆን እንጅ መፍትሔ ይሆን ዘንድስ ከቶ አይቻልም::
ለ/ ለሃይማኖቱ መጣረስ ምክንያት የሆናችሁ እናንተው ናችሁ:: በተዋህዶ ከበረ፣ ወልድ ቅብዕ የሚል ፍልስፍና ዘርታችሁ ክዳችሁ ታስክዳላችሁ:: ስለዚህ ሃይማኖቱን ለዋጭ ትውልድ እንጅ የአበውን ሃይማኖትና ትውፊት የሚያስቀጥል ትውልድ እንዳልፈጠራችሁ እወቁ::
ሐ/ ስብከተ ወንጌል መስፋፋቱ ባልከፋ ነበር:: ዳሩ ግን ትውልዱ ከመጽሔትና ከበራሪ ወረቀት ውጭ እንዳያነብና ወልድ ቅብዕ፣ በተዋህዶ ከበረ የሚለውናን ሌሎችንም ምንፍቅናዎቻችሁ እንዳያገኝ ሌሎች ጥንታዊያን ድርሳናትንና ገድላትን እንዳያነብ ልጓም አዘጋጃችሁለት:: እናንተ ደግሞ ምስኪኑን ምዕመን በዚህ መልክ ከያዛችሁ በኋላ መጽሐፍትን ከየገዳሙ በመሰብሰብ እንዲቆራረጡና ተጣመው እንዲተረጎሙ በማድረግ “አዛኝ ቅቤ አንጓች” መሰላችሁ:: ይህም ቢሆን ግን እውነትና ሀሰት መቼም ቢሆን አንድ አይሆኑምና ዘወትር እኛ ስናጋልጣችሁ እንኖራለንና ሰው የሌለ እንዳይመስላችሁ ለማለት እንወዳለን::
መ/ የተማረውን ማህበረሰብማ እናንተው በየግቢ ጉባኤው፣ በየወረዳ ጽ/ቤቱ፣ በሃገረ ስብከቱ፣ በየአጥቢያ ቤተ ክርስቲያኑ ድረስ በመሄድ የራሳችሁን ገቢ ለማሳደግ ስትማስኑ ትውላላችሁ እንጅ ቤተ ክርስቲያንንማ መቼ ዘወር ብላችሁ አያችኋትና::
ሠ/ ጥናት መደረጉ መልካም ቢሆንም እውነታው ግን የእናንተው ክህደት ተባባሪ ስለምታደርጉት ለቤተ ክርስቲያን ጠላት እንጅ ምንም ነገር የሚጠቅማት ሊሆን እንደማይችል ይታወቃል::

የድርጅቱ አቋም:- “በማንኛውም የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ምንም ዓይነት ጣልቃ ገብነት የለውም፡፡” ይላል::
  ነገር ግን ከላይ ደግሞ “..... በየዘመኑ የሚከሰቱ ተለዋዋጭ ሃይማኖታዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች በመቃኘት የቤተ ክርስቲያኒቱን ሐዋርያዊ አገልግሎት ማጠናከር፡፡” ይላልና ከፖለቲካው ዓለም ነጻ ከሆነ ለምን የፖለቲካ ችግር ያነሳል? “እቴ ስመኝ ለማያውቁሽ ታጠኝ” እንዲሉ እንዲያው የጻፋችሁት ነገር ገርሞኝ እንጅ ለፖለቲካውማ ከህወአት፣ ከአዴፓ፣ ከደህዴን፣ ...... እማ እናንተ አትበልጡምና ነው እንዴ? ልዩነቱ አጨዋወቱ ላይ ነው:: እነሱ በግልጽ በመውጣት በአለማዊ ሁኔታ በህገ መንግስቱ ስር ይጫወታሉ እናንተ ደግሞ በተቃራኒው በድብቅ፣ በስውር በመንፈሳዊው አለም ተሸሽጋችሁ፣ በቤተ ክህነቱ ስር ትጫወታላችሁ ያም ሆነ ይህ ግን ሓሳባችሁ፣ ዓላማችሁ ፖለቲካዊነት፣ ምድራዊ እንጅ መንፈሳዊ፣ ሰማያዊ እንዳልሆነ ከላይ ያላችሁት የድርጅቱ ጉዳይ አስፈጻሚዎች በግልጽ ታውቁታላችሁ ከታች ያላችሁት ምስኪን ምዕመናን ግን እስካሁን ድረስ ነገሩ ለእናንተ የተሰወረ ነውና ቶሎ ላትረዱት ትችላላችሁ ፍጻሜው ግን የከፋ ስለሚሆን አብረን እናየዋለን እያየነውም ነው::

የድርጅቱ አመሰራረት:- “ስለ ማኅበረ ቅዱሳን አመሠረራት ጥቂት ነጥቦችን እናስታውስ፡፡ በ1980ዎቹ የጋንቤላና የመተከል የሠፈራ ዘመቻ ጥቂቶቹን አገናኘ፡፡ ከዚህ ቀጥሎ ደግሞ ሌሎችን በጥበቡ እየጠራ በክረምት ጊዜ ዩኒቨርስቲዎቻቸው ሲዘጉ በዝዋይ ገዳም እንዲገናኙ አደረገ፡፡ በመጨረሻም አብዛኛዎቹን ወጣቶች በ1983 ዓ.ም በብላቴ ካምፕ አገናኛቸው፡፡ እነዚህ ሁሉ መልካም አጋጣሚዎች ሆኑላቸውና የተለያዩ ማኅበራትን እያቋቋሙ ወጣቱ ትውልድ ከቤተ ክርስቲያን ጋር የማስተዋወቁን ሥራ አፋፍመው ቀጠሉበት፡፡ በዚህ የተሰበሰበው ኃይል አሁንም ተደራጅቶ ጠንካራ አገልግሎት የሚሰጥበትን አንድ ማኅበር እየፈለገ መጣ፡፡ በዚህ ምክንያት የተለያዩ ማኅበራትን በመመሥረት የየአቅማቸውን አገልግሎቶች ሲፈጽሙ የቆዩት ወጣቶች በአንድ ማኅበር ቢሰባሰቡ የሚሰጡት አገልግሎት ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ተገነዘበ፡፡ በዚህ ጊዜ ነበር በመላእክት ስም፣ በእመቤታችን ስም፣ በቅዱሳን ስም የተሰበሰቡት ሁሉ ለመታሰቢያነት የሚጠሯቸውን ቅዱሳን የማያስቀርና ተልእኮአቸውን የማይለውጥ አንድ ማኅበር ለመመሥረት የወሰኑት፤ ወስነውም አልቀሩ መሠረቱት፤ ማኅበረ ቅዱሳንን፡፡
ውኃ ልትቀዳ ወርዳ ጌታችንን አግኝታ እንደተመለሰችው ሰማርያይቱ ሴት፤ ከሄዱበት ምድራዊ ዓላማ ተጨማሪ ሰማያዊ ዓላማን አንግበው መንፈሳዊ አገልግሎት የሚሰጥ ማኅበር ለመመሥረት ምክንያት የሆኑት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች እንደሙያ ዝግጅታቸውና ስጦታቸው ቤተ ክርስቲያናቸውን ለማገልገል አደራ ተቀበሉ፡፡ /ዮሐ. 4፤7/ ስለዚህም ማኅበሩ ሐዋርያዊ ተልእኮን ለማስፋፋትና ግቦቿን አሳክታ ከችግሮቿ ወጥታ ለሕዝቦቿ ማኅበራዊ ሕይወት ለውጥ የመሪነት ሚና የምትጫወት ቤተ ክርስቲያንን ለማየት የሚያስችል የአገልግሎት ስልት ነድፎ ብቅ አለ፡፡” ይላል::
  ቀድሞ እንደመሰረቱት እውነት ሰው አክባሪ፣ ሀገር አስጠሪ፤ ለቤተ ክርስቲያን ተቆርቋሪ፣ እግዚአብሔርን ፈሪ ትውልድ ለመፍጠርና የቤተ ክርስቲያንን ውጫዊና ውስጣዊ ችግር ለመቅረፍ ቢሆን ኖሮስ እኛም ክፉ ባልተናገርናችሁና አብረን አገልግለን መንግስቱን በወረስን ደስ ባለንም ነበር:: ነገር ግን የተመሰረተበት ዓላማና አሁን እያካሄደ ያለው አጀንዳ ፍጹም ተቃራኒ ከመሆኑ የተነሳ ድርጅቱን:- በእናት ቤተ ክርስቲያን ስም አትነግድ፣ በአበው ቅዱሳን ስም አትነግድ፣ የቤተ ክርስቲያንን እንቁ ልጆች እያሳደድክ ለዲያብሎስ አትስጥ፣ ተስፋ አታስቆርጥ፣ ታሪክ አትቅበር፣ ሕግ አትሻር፣ሳታውቅ አታስተምር፣ በማስመሰል አትኑር፣ ለእውነት እደር፣ በክህደት አትታሰር፣ ሥርዓት አታፋልስ፣ ሃይማኖት አታጣርስ፣ ደም አታፋስ ...... እንዲሁም ከሌሎች ክፉ ጥፉ ተግባርህ ተመለስ እያልን ዘወትር መናገራችንን እናቆም ዘንድ ከቶ አይቻለንምና ነው::
ለማጠቃለያ 
ማህበረ ቅዱሳን[ማህበረ እኩያን] ከሚሰራቸው እኩይ ተግባራት:-
፩. የቤተ ክርስቲያን አባቶችን በእህቶች እንዲፈተኑ ማድረጉ[ለጽድቅ እንቅፋት መሆን]
፪. የቤተ ክርስቲያንን ሙዳዬ ምፅዋት ባዶ እያስቀረ የእሱን ካዘና ለመሙላት ደፋ ቀና ማለቱ[ገንዘብ ወዳድነቱ]
፫. የቤተ ክርስቲያን አስራት በኩራት ይሰብሰብም አይሰብሰብም ለእሱ ምንም አይጨንቀውም የእሱ ግን ካልተሰበሰበች ከአገልግሎት ሁሉ እስከ ማገድ ይደርሳል[መጽሔት ለማሰራት እንኳ ከ፩ኛ ዓመት ጀምሮ እያንዳንዷን ክፍያ ያስተፋኃል]
፬. ከላይ ከላይ መንፈሳዊ ሲሆን ውስጡ ግን ሰይጣናው ሥራ መስራቱ፣ ድንግልና ሥጋ ሳይኖራቸው ዲቁና ማሰጠቱ፣ አንዲት ጥምቀትን እንድትደገም ማድረጉ፣
፭. አንድ ሰው ከእርምና ወደ ክርስትና ሲመጣ ቢያንስ እስከ ሁለት ዓመትና ከዚያ በላይ ትምህርተ ክርስትናንና ስርዓተ ቤተ ክርስቲያንን መማር እንዳለበት መጽሐፍት ይናገራሉ እነሱ ግን በ2፣ በ3 ቀን ሥብከት ዝም ብሎ ምንም ያልተረዳውን ህዝብ ነጠላ እያለበሱ ለቁጥር መሞያ ያደርጋሉ፣ ዘላቂ ህይወቱ አያስጨንቃቸውምን?
በግቢ ጉባኤስ የሚደረገው ሥርዓት አልበኝነት፣ ህገ ቤተ ክርስቲያንን መደፋፈር ከየት የመጣ ነው?
፮. በማያገባው መግባቱ፣ ሥራህ ይህ ነው ተብሎ ተሰጥቶ እያለ ሁሉንም ካላየሁ ካልደረስኩ የሚል የጨዋ ስብስብ መሆኑ፣
፯. ለይስሙላ ጠረፍ ድረስ ቢሄድ እንኳ የማህሉን ቤተ ክርስቲያን እያተራመሰ መሆኑንና ለፕሮቴስታንት በር ከፋች መሆኑን ልትረዳ ይገባሃል፣
፰. እራስ ወዳድ መሆኑ፣ አንድ ሰው ማህበሩ ያለውን የማይቀበል ከሆነ ተሃድሦ፣ መናፍቅ ብሎ ከቤተ ክርስቲያን እንዲወጣ መንገድ ማመቻቸት
፱. ሁለ ነገሩ እንደ መንፈሳዊ ሳይሆን እንደ ዓለማዊ[ሰይጣናዊ መሆኑ]፣ ሰውን ሲያጠና በድብቅ፣ ደግሞ የሰውን ኃጢያት እየሰበሰበ እንደ ዲያብሎስ ይጽፋል ግሩም ነው [ሐራ ተዋህዶን ማየት ትችላላችሁ ብፁዓን አባቶችን እንዴት እንደሚያብጠለጥላቸው]
፲. ዘረኛ መሆኑ [ማህበረ ሸዋ] ለሌላው ምንም ደንታ ቢስ መሆኑና ምስራቅ ጎጃሞችን ለብቻ ማጥመዱ
፲፩. የግቢ ጉባኤውን ዳቦ ለቤተ ክርስቲያን ነው ብሎ እየሰበሰበ ለስራ አስፈጻሚዎች ቀለበት መግዣ ማረጉ[ደ/ማርቆስ ግቢ ጉባኤ]
፲፪. እውነት እሱ መንፈሳዊ ሥራ ቢሰራ ኖሮ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ምዕመናን ብዛት ከ50% በላይ የነበረው ወደ 43% አካባቢ ባልወረደም ነበር:: የድርጅቱ አባላትም ወደ ፖለቲካው ሳይሆን ወደ ገዳም መንነው በሄዱ ነበር::
ስብሐት ለሥሉስ ቅዱስ!
“ዛቲ ሃይማኖት መሲሐዊት ዘትትአመን ባቲ ቤተ ክርስቲያን ቅድስት፤ ብሂለሰ ከብረ በተዋህዶ ሃይማኖት ጳውሎስ ሳምሳጢ ውእቱ” መጽሐፈ ዝክሪ የብራና 

No comments:

Post a Comment