Friday, September 21, 2018

ጥያቄ ቁ ፫:- ወልድ ቅብዕ፣ በተዋህዶ ከበረ ብላችሁ ለምታምኑ በሙሉ:-


1. “አብ ቀባዒ ወልድ ተቀባዒ መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ” ብለው ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን አስተምረው እናንተ ለምን የለም/አላስተማሩም አላችሁ?
፠ “እስመ ብሂለ ክርስቶስ ይመርህ ኀበ አብ ቀባዒ ወኀበ ወልድ ተቀባዒ ወኀበ መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ (ዮሐ/አፈ_ወርቅ_በድርሳኑ)”
፠ “አብ ቀባዒ ወወልድ ተቀባዒ ወመንፈስ ቅዱስ ቅብዕ” መጽሐፈ ዝክሪ የብራና ገጽ 78/የትርጓሜ ሊቅ/
፠ “እስመ ዝክረ ክርስቶስ ይመርኀ ኀበ ሰለስቱ አካላት ዝውእቱ አብ ቀባዒ ወልድ ተቀባዒ ወመንፈስ ቅዱስ ቅብዕ (ኪርያኮስ እና ቅ/ቄርሎስ በድርሳኑ)::”

2. ልደተ ክርስቶስን በዘመነ ዮሐንስ ለምን ታህሳስ 28 ቀን ታከብራላችሁ?
፠ ከ81 መጽሐፍ ቅዱስ ከሚካተተው የሐዋርያት የትዕዛዝ መጽሐፍ (ድድስቅሊያ) አዘዘነ ሲኖዶስ ዘጸሐፈ ቀለሜንጦስ ካለው ትዕዛዝ (ስምንት) ላይ በአንቀፅ 29 ልደት ሁልጊዜ 29 እንዲከበር ያዝዛል።
፠ ፍትሐ ነገስትበአንቀፅ 19 ሁልጊዜ በ29 እንድናከብር ያዝዛል። ይኸውም በድድስቅልያ አንቀፅ 29 በዓለ ልደትን በግብፃዊያን በ4ኛው ወር በ29ኛው ቀን አክብሩ በማለት የሚገኘው ነው።(የግብፃዊያን እና የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር ተመሳሳይ ነው)
፠ ሊቁ የኔታ ገ/ስላሴ አወቀ በፈለገ ጥበብ መፅሔት መግረሬፀር በሚል አምድ ስር ልደት በ28 እንዲከበር ያደረጉ መናፍቃን ሚናስና እንድራኦስ ናቸው ብለዋል። 
፠ መ/ር ልዑል ቃል እሸቱ የእምነት አደራ በሚለው መጽሐፋቸው በ28 ማክበር ያስጀመሩ መናፍቃን ሚናስና እንድራኦስ የተባሉ ሶሪያዊያን ናቸው ብለዋል።
፠ አቡነ ጎርጎርዮስ በ28 መከበር የተጀመረው በ1298 ዓ/ም ነው ብለው ያንኑ 29ኙን መያዙ ይሻላል ብለዋል (የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያንታሪክቁ.2):: 
፠ አቡሻኽር ወልደ አቤል ሄሬም በአንቀፅ 38 በእፎኬ ይደሉ ከመናብዕል ወንብላዕ በዕለተ ዘኢወለደት ቦቱ ድንግል (ድንግል ባልወለደችበት ዕለት ለምን እንበላለን ብሎ በ28 ቀን እንዳይበላ ደንግጓል።) ስለዚህ በ 29 መሆኑን ካልረሳችሁ በእፎኬ ይደሉ ከመናብዕል ወንብላዕ በዕለተ ዘኢወለደት ቦቱ ድንግል ይላልና ለምንባልወለደችበት ዕለት ትበላላችሁ? 
፠ ገድለ ፊልጶስም የሚናገረው በዓለ ልደት በአራቱም ዘመናት ታህሳስ 29 ቀን እንደሚከበር እንጅ በ28 እንዲከበር አይናገርም::
በአንዳንድ ቦታዎች ላይ እንደምትናገሩት ስንክሳርና ታምረ ማርያም በ28 እንደሚበላ ይናገራል ትላላችሁ በእርግጥ ከግራ አህመድ ወረራ ወዲህ ያለው ስንክሳር ይናገራል ነገር ግን ከዚያ በፊት የተጻፈው ስንክሳር በ 29 እንጅ በ28 አይልም :: ማረገገጥም ገፈልግህ የደብረ ብርሃን ስላሴ ስንክሳር፣ ጋይንት አንስታ ቁላ እስቴ ከሚባል ሀገር ከአንድ ቦታ ያለ ስንክሳር፣ በዘጌ መሐል ዘጌ ጊዮርጊስ ያለ ስንክሳር በ28 ቀን አክብሩ አላሉም:: ጳጉሜ 6 ስለሆነች፣ እለተ ምርያ አስመልክቶ ስለምታነሱት በሙሉ ሀሰት እንደሆነ ከየኔታ ገብረ ስላሴ አወቀ የመጽሐፍተ ብሉያትና ሐዲሳት፣ የቅኔና የአቋቋም ፣ የመጽሐፍተ ሊቃውንትና ፍትሐ ነገስት ሊቅ በፈለገ ጥበብ መጽሔታቸው አብራርተው ስለጻፉት ምንም መካድ አይቻልም:: መጽሐፉንም ከፈለግህ እልክልሃለሁ:: ከዚህ ውጭ በማስረጃ የተደገፈ ምላሽ ካለህ እቀበላለው ካልሆነ ግን ለምን ለ710 ዓመታት ያህል ህዝብን በጾም/በገሀድ/ እያስበላችሁ ኖራችሁ?
ደግሞስ በፆም ምክንያት ክርክር ቢነሳ አድልው ለፆም አይልምን ፍ/ነገስት?
• ይህ ሁሉ መጽሐፍት ማስረጃ እያለ ለምን በ28 ተበላ?
• ላሊበላዎች እና ደብረ ሊባኖሶችስ ለምን በ 29 በዓለ ልደትን አከበሩ?
አቡነ ጎርጎርዮስ ዘሸዋ ደግሞ ስለበዓላትናአፅዋማት ላይ ስለገሀድ ፆም በጻፉት አምድ ላይ ገሀድ ያለው ለጥምቀት እንጅ ለልደት ገሀድ የለውም ብለዋል ታዲያ ከዚህ የበለጠ ምን ክህደት አለ?
፠ ፍ/ነገስት አንቀፅ 15 ቁ 587 ልደት በፆም ቀኖች ረቡዕና ዓርብ ቢውል ይጸልዩ፤ ስጋውና ደሙን ይቀበሉ፣እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ ይጹሙ ብለው አይፍረዱ ::
፠ፍ/ነገስት አንቀፅ 15 ቁ 566 ዳግመኛም በእየሳምንቱ ሁሉ ዓርብናረቡዕን መፆም ነው፣በዓለ ሃምሳ፣የልደትና የጥምቀት በዓል የተባበሩባቸው ጊዜ ካልሆነ በቀር እንደ ተፃፈው እስከ 9 ሰዓት ድረስ ይጹሙባቸው:: ስለዚህ ታህሳስ 29 ቀን የልደት በዓልና ጥምቀት በዕለተ ዓርብና ረቡዕ ቢውሉ ይበላል:: የዋዜማው ግን ገሀድ አላቸው:: ፍ/ነገስትአንቀፅ 15 ቁ 567 “.......................................የልደትና የጥምቀት ዋዜማፆም(ገሀድ)”:: 

3. አንድን የተጠመቀን ሰው ሁለተኛ ጥምቀት እያጠመቃችሁ ለምን ለገሀነም ትገብራላችሁ?
፠ ጥምቀት ከማይደገሙት ምሥጢራተ ቤተ-ክርስቲያን አንዷ ናት፡፡ ስለዚህ ወንድ ልጅ በተወለደ በ40 ቀኑ ሴት ልጅ በተወለደች በ80 ቀኗ የልጅነት ጥምቀትን ከተጠመቁ በኋላ ሁለተኛ ጥምቀት የለም፡፡ ለዚህም፡-
፠ ኤፌ 4÷5 አንድ ጌታ፣አንድ ሃይማኖት አንድ ጥምቀት በማለት ጥምቀት አንዲት መሆኗን ተናግሯል፡፡
፠ ዮሐ.አፈ ወርቅ ድርሳን 9 ጥምቀት አንዲትና ት ሁለተኛ የሚጠመቅ ሰው አረመኔ ነው ብሏል፡፡
፠ ሃ.አበው ዘሳዊ ምዕ 24 ክፍል 1 ቁ 22 ጥምቀትም እንዲህ አንዲት ናት፡፡አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ያለመለያየት በመለኮት አንድ የሆኑባት፡፡
፠ ፀሎተ ሃይማኖት (መሠረተሃይማኖት) ወነአምን በአሀቲ ጥምቀት (በአንዲት ጥምቀት እናምናለን)::
መጽሐፍት እንዲህ እያሉ ለምን ሁለተኛ ጥምቀት ማጥመቅ ጀመራችሁ? ፍ/ነገስት “በማያምን ካህን የተጠመቀ ሰው” ዳግመኛ ይጠመቅ ይላል በማለት የዋኃን ምዕመናንን ታታልላላችሁ ለመሆኑ የማያምን ማን ነው? እኛ ወይንስ እናንተ? እንደ ፕሮቴስታንት የያዛችሁትን መጽሐፍ የማትቀበሉ! ለመሆኑ እኛ ከየትኛው የቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ አስተምህሮ የወጣ ትምህርት ይዘን ነው እናጥምቃችሁ ማለታችሁ? መጠመቅስ ካለበት "ወፈለጥዎሙ ለወልድ እምአቡሁ ወእምቅዱስ መንፈሱ በብሂሎቶሙ ቃል አክበሮ ለስጋ" /ከዘርዓቡሩክ ገድል <የብራናው> ብላችሁ ወልድን ከባህርይ አባቱ ከአብ ከባህርይ ህይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ የለያችሁት ነበር መጠመቅ የሚገባችሁ::

ስለ ስልጣነ ክህነቱ ደግሞ:- “ኢየሱስም ወደ ፊልጶስ ቂሣርያ አገር በደረሰ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን። ሰዎች የሰውን ልጅ ማን እንደ ሆነ ይሉታል? ብሎ ጠየቀ።እነርሱም። አንዳንዱ መጥምቁ ዮሐንስ፥ ሌሎችም ኤልያስ፥ ሌሎችም ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ አሉት። እርሱም። እናንተስ እኔን ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ? አላቸው። ስምዖን ጴጥሮስም መልሶ። አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ አለ።
ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው። የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህምና ብፁዕ ነህ።
እኔም እልሃለሁ፥ አንተ ጴጥሮስ ነህ፥ በዚችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፥ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም።
የመንግሥተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ፤ በምድር የምታስረው ሁሉ በሰማያት የታሰረ ይሆናል፥ በምድርም የምትፈታው ሁሉ በሰማያት የተፈታ ይሆናል። ያን ጊዜም እርሱ ክርስቶስ እንደ ሆነ ለማንም እንዳይነግሩ ደቀ መዛሙርቱን አዘዛቸው።” ማቴ 16፥13-20
ስምዖን ጴጥሮስም መልሶ። አንተ ‘ክርስቶስ’ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ በማለቱ በጎቼን ጠብቅ ተባለ፣የመንግስተ ሰማያት መክፈቻ ቁልፍ እሰጥሃለሁ ተባለ ስለዚህ እኛም ክርስቶስ ማለት ደግሞ ቅቡዕ ፣ የተቀባ፣ መሲህ ስለሆነ እኛም ክህነትን የምንቀበለው ክርስቶስ ቅቡዕ፣ የተቀባ ብለው ከሚያምኑት ሐዋርያት እንጅ አልተቀባም፣ አልከበረም ከሚሉት ከካሮች አይደለም:: 

4. ክርስቶስ/ሥግውቃል / ተቀብቷል ወይስ አልተቀባም? ከተቀባስ ቀባዒው፣ተቀባዒውና ቅብዕ የሆነው ማን ነው?
 አልተቀባም እንዳይባል ዘርዝረን ባንጨርስም ቄርሎስ በሐይማኖት አበው ፣ዮሐንስ አፈወርቅ በድርሳኑ፣ ነብያት በትንቢታቸው፣ ኢጲፋንዮስ በስነ-ፍጥረት መጽሐፉ፣ሰማዕታት በገድላቸው፣ዝክሪናጳውሊ በብራና መጽሐፋቸው፣አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫበመጽሐፈ ምስጢር፣ በመጽሐፍ ቅዱስ እና ሌሎችም ስለተቀባ የሚናገሩ መጽሐፍትን አሉ:: ወልድ ቅብዕ የሚሉትን ወገኖች ሰማዩም ሰማይ ምድሩም ምድር አይደለም እነደማለት ነው፡፡ እነዚህንም “ስሞሰ ለክርስቶስ ኢያእመሩ ወዘኢይደሉ ይሜህሩ፡፡እለሰ የአምኑ ርቱዐ ይሜህሩ ከመበሥጋሁ ተቀብዐ እስመ ክርስቶስ ብሂል ቅቡዕ ብሂል፡፡እፎይሰመይ ክርስቶስ ዘኢተቀብዐ” ብሎ ቅዱስ ቄርሎስ ነቅፏቸዋል፤ ሐዋርያውም ዘልፏቸዋል (1 ዮሐ 2÷20)፡፡ ክርስቶስ የተቀብዖ (ሉቃ 9÷2፤ዮሐ 1÷42) ስሙ ሲሆን አማኑኤል የተዋሕዶ ስሙነው (ማቴትርጓሜ 1÷16)፤ነገር ግን አማኑኤል ተብሎ ክርስቶስ ያልተባለበት ክርስቶስ ተብሎ አማኑኤል ያልተባለበት አንዳችም ቅጽበት የለም ሁለቱም በአንድ ጊዜ ተፈጽመዋል እንጂ፡፡

5. ተቀብዓ የሚለው አንቀጽ ተዋህደ ተብሎ የተተረጎመው በየትኛው የቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ ነው? ከዚህ በታች የተጠቀሱት የቤተ ክርስቲያን መዝገበ ቃላት ተቀብዓን ተዋህደ ብለው አልተረጎሙም ታዲያ እናንተ ከየት አምጥታችሁ ተረጎማችሁት?
፠ ”ቀባ - መቀባት በመጽሐፍ ቅዱስ ስለ 3 ዓይነት ነገር ያገለግላል:: ክርስቶስ በመንፈስ ቅዱስ ተቀብቷል (በመንፈስ ቅዱስ ተሞላ የሐዋ 10፥38):: ምዕመናን በመንፈስ ቅዱስ ይቀባሉ 2ኛቆሮ 1፥21-22፤ 1ኛዮሐ 2፥22-27 ::<<መሲሕ>>በአረብ<<ክርስቶስ>>>በግሪክ ቋንቋዎች የተቀባ ማለትነው:: .........ቅብዓት/ቅባት/:- ከልዩ ልዩ እንጨቶች ተቀምሞና ተነጥሮ የሚወጣ ፈሳሽ አይነት ዘጸ 30፥22-32፣ የመንፈስ ቅዱስ ምሳሌነው 1ኛዮሐ 2፥20- 27” የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክመዝገበ ቃላት 1992 ዓ/ምእትም፣
፠ ”ቀባ/ቀብዐ/ ላከከ፣ለቀለቀ፣ደለሰቅቤን:: የህፃንን ሕዋሳት ሜሮን አስነካ፣በራስ ላይ ዘይትአፈሰሰ፣አከበረ፣ሾመ፣ስልጣን፣ሀብት፣መብት፣ችሎት አሳደረ አደለ ሰጠ፤ ካህን ነቢይ ንጉስ አደረገ:: አዲስ አማርኛ ሰዋሰው ከደስታ /ተ/ወ 1962ዓ/ምእትም ገጽ 1022”
፠ “ተቀብዐን ተዋሐደ እያሉአለቋንቋው፣አለንባቡ፣አለስልቱ፣አላገባቡ ይፈቱታል፤ቀብዐናተወሐደንተመልከት ” አለቃኪ/ወ/ክ/መዝ/ቃላትገፅ 550::
ስለዚህ ቅብዓት ትርጉሙ እንዲህ ከሆነ አሙካ እያሉ መሳደብ ተገቢ ነውን? ሎቱ ስብሐት!

6. በእውኑ ቅብዓት ማለት አሙካ ነውን?

፠ መፅሐፈ አክሲማሮስ ዘሰሉስ(ክፍል-2) ዘኢተወልደ እማይ ወእመንፈስ ቅዱስ ኢይክል በዊአ ውስተ- መንግሥተ እግዚአብሔር እስመ ዘተወልደ እምሥጋ ሥጋ ውእቱ ወዘተወልደ እመንፈስ ቅዱስ ውእቱ፡፡
ይህም ቅብዓት መንፈስ ቅዱስ ነው፤ለሁሉ ፀጋ ክብር መንፈስ ቅዱስ እንደሆነ ሲያጠይቅ ጌታችን ከረቂቅ የተወለደ ረቂቅ ነው፤ከግዙፍ የተወለደ ግዙፍ ነው ሲል ከውሃ እናትነት፣ከመንፈስ ቅዱስ አባትነት ልጅነት ነስተው አህዛብ አረማውያን ረቂቅ መንግስተ ሰማያትን እዲወረሱ ተፃፈ፣ተነገረ ዮሐ3÷3-6
፠ 1ኛ ዮሐ 2፥20፡-እናንተስ ከቅዱሱ ያገኛችሁት ቅብዓት አላችሁ፤ሁሉንም ታወቃላችሁ ፡፡
፠ 1ኛ ዮሐ ምዕ2 ከ26-27፡-ስለሚያሰቷችሁ ሰዎች ይህን ፅፌላችኋለሁ፡፡ እናንተስ ከእርሱ የተቀበላችሁት ቅብዓት በእናንተ ይኖራል፤ማንም ሊያስተምራችሁ አያስፈልጋችሁም፤ ነገር ግን የእርሱን ቅብዓት 2ስለ ሁሉ እንደሚያስተምራችሁ እውነተኛም እንደሆነ ውሸታም እንዳልሆነ እናንተንም እንዳስተማራችሁ በእርሱ ኑሩ፡፡/ቅዱስ ቄርሎስ ዘኢየሩሳሌም/
እንግዲህ ቅዱሳት መጽሐፍት ቅባት ማለት መንፈስ ቅዱስ ማለት እንደሆነ አንድም ክብር መሆኑን በብዙ መጽሐፍት ላይ ተጽፎ እያለ መልስ ሲያጡ ፣ መውጫ መግቢያው ሲጨንቃቸው፣ የፈጠራ/የፍልስፍና ችሎታቸውን በመጠቀም “ቅባት የሚለውን አሙካ ብንለው ምን ይመስላችኋል በማለት” ለስምምነት ደርሰው ይህንን የተቀደሰ ስም ባለማወቅ ለሥድብነት ሲጠቀሙበት ይስተዋላል:: ወገኔ ምንም ብትበድን ምን ንሥሃ ብትገባ ይቅር ትባላለህ፣ምህረትም ታገኛለህ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስን የተሳደበ ምንም ንስሃ እንደሌለው ቅዱስ መጽሐፍ እንዲህ ይነግረናልና ቀኑ ሳይጨልምብህ፣ ጊዜው ሳይመሽብህ ከክፉ ግብራችሁ ብትመለሱ መልካም ነው:: ጌታ በወንጌሉ “ስለዚህ እላችኋለሁ፥ ኃጢአትና ስድብ ሁሉ ለሰዎች ይሰረይላቸዋል፥ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስን ለሰደበ አይሰረይለትም”ማቴ 12፥31 ይላልና ከፍርድ ይጠብቀን!!!

7. በማኅጸነ እግዝትነ ማርያም አካለ ቃል ከአካለ ሥጋ ጋር ሲዋሐዱ የአብ ግብርና የመንፈስቅዱስ 5ቱ ግብራት ምን ምን ነበሩ ?

8. “አስመ እንከ ተቀብዐ ቅብዐ ትስብእት ዘእመንፈስ ቅዱስ በኀበ አግዚአብሔር አብ -  በእግዚአብሔር አብ የደስታ ዘይት መንፈስ ቅዱስን እንዲህ ተቀብቷልና ”(ተረፈ-ቄርሎስ ምቅዋም 8 ገጽ 49 ብራናመጽሐፍ) ሲል ምን ማለቱ ነው?

9. ዘአንገሦ ለሥጋ አዳም በመንፈስ ቅዱስ ወረስዮ ቅዱስ ወማህየዌ - በመንፋስ ቅዱስ ህይወትነት የአዳምን ባህሪይ ያከበረው እርሱ ነው ሲል ምን ማለቱ ነው?

10. “በቀባኸው በቅዱሱ ብላቴናህ በኢየሱስ ላይ ሄሮድስና ጴንጤናዊው ጲላጦስ ከአሕዛብና ከእስራኤል ሕዝብ ጋር፥ እጅህና አሳብህ እንዲሆን አስቀድመው የወሰኑትን ሁሉ ሊፈጽሙ፥ በዚች ከተማ በእውነት ተሰበሰቡ።” የሐዋ 4፥27- 28 ይላልና “በቀባኸው በቅዱሱ ብላቴናህ በኢየሱስ ላይ” የሚለውን ምን ብላችሁ ትተረጉሙት?

11. ወልድ ቅብዕ /በተዋህዶ ከበረ/ ብላችሁ የምታምኑ ከየትኛው ነቢይ/ሐዋርያ/ሊቅ የተማራችሁት ትምህርት/ዶግማ ነው? ማስረጃ ጥቀስ? 

12. ስለካራ እምነት ከታሪክ መጽሐፍ ጠቅሰህ አስረዳኝ /በተለያዩ ዘመናት ያሏችሁን አስተምህሮዎችንም/? 

13. ኢትዮጵያዊው ቄርሎስ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ደግሞ ስለ ክርስቶስ ሲመሰክሩ “ለእግዚአብሔር የተለየ የተቀባ የሆነ የስሙ ትርጉም መሲሕ የሆነ ክርስቶስ እስከ ተወለደ ድረስ በገሊላ ነገስታት ዘንድ መሲሕ ተብሎ መጠራት አልነበረም። ክርስቶስም መሲሕም ናዝራዊ በማለት በአንድነት የተቀባ ተባለ መሲሕ ነው።መሲሕ የተቀባ ማለት ነው። ክርስቶስ የተባለ ኢየሱስ ተወለደ መሲሕ መባል በእርሱ ተፈፀመ።
እነሆ ናዝራዊ እየሱስ ቅባትን ተቀብቶ የመቀባትን መንግስት ተቀበለ አምላክ ሲሆን ሰለሰውነቱም የመለኮትን ቅብዓት ተቀብቶ ሰው ሆነ እግዚአብሔር ሰው ለመሆን ወረደ ሰውም እግዚአብሔር ለመሆን ከፍ ከፍ አለ ጳውሎስ እግዚአብሔር አለምን ተወዳጅ እንዳለ ዳግመኛም የሀጢያትን ስጋ ለበሰ ያችን ሀጢያት በስጋው ገዛት። 1ቆሮ 5፥19” መጽ/ምስጢር 20፥ 40-41 ታዲያ ቅዱሳን አባቶች ክርስቶስ እንደተቀባ፣እንደከበረ እየመሰከሩ እናንተስ ለመናገር፣ ለመመስከር ምን አሳፈራችሁ?

14. ቅብዓትን አልፎንሱ ሜንድዝ የተባለ ካቶሊካዊ አመጣው የምትሉት ለመሆኑ እኛና ካቶሊኮች አስተምህሯችን አንድ የሚሆነው ከየቱ ላይ ነው?

15. ቅብዓትን አልፎንሱ ካመጣው መጽሐፍ ቅዱስን፣ ድርሳነ ዮሐንስ አፈ ወርቅን/ድርሳነ ቄርሎስን፣ መጽሐፈ ምስጢርን እንዲሁም ቁጥር የሌላቸውን ስለ ምስጢረ ቅብዓት የሚናገሩ መጽሐፍትን የጻፋቸው አልፎንሱ/ካቶሊካዊው/ ነው የጻፋቸው ልትሉ ነውን? 

16. ተዋህዶ ብቻውን ማንኛው የቤተ ክርስቲያን አባት ነው ሃይማኖት ወይንም እምነት ነው ብሎ ያስተማረ? ማስረጃ?

ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር ይቆየን አሜን!

No comments:

Post a Comment