Saturday, September 22, 2018

እንጠያየቅ ክፍል ፪

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ
እንጠያየቅ ክፍል ፪
ይድረስ ለሰሚጆሮና ለአስተዋይ እዝነ ልቡና
========================


የዚህ ጽሑፍ ተከታታይ ወንድም እህቶቼ እንደምን ቆያችሁልኝ?ሕይወት?ጤና?ሥራ?መልካም እነሆም ለዛሬዉ ደግሞ የእንጠያየቅ ዘዉግ የሚያተኩረዉ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ዉስጥ ነገረ ቅብዐት ሲነሳ ብዙዎቻችሁ እንግዳ ፣ ዘላን ምድረ በዳ ትሆኑበታላችሁና መጻሕፍት ስለተቀብዐ ምን ይላሉ የሚለዉን ይሆናል ፡፡ እናንተ “ተዋሕዶዎች” ግን እኮ መጽሐፍ “እናንተስ ከቅዱስ ቅብዓት ተቀብታችኋልና ሁሉን ታዉቃላችሁ” 1ኛ ዮሐ 2 ፡ 20 ተብሎ ተነግሯል ፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ 

1ኛ ‹‹‹‹‹‹ ቅዱሱ ቅብዓት የተባለዉ ማን ነዉ?
2ኛ‹‹‹‹‹‹‹‹‹ከቅዱሱ ቅብዓት የተቀቡት እነማን ናቸዉ?
3ኛ ‹‹‹‹‹ ቅዱሱ ቅብዓት ስንት ነዉ?
እንዲሁም “እኛ ተዋሕዶዎች” የምትሉ ወገኖች እንዲያዉ ማን ከማን አንድ የሆነባችሁ ምሥጢረ ተዋሕዶ ሁናችሁ ነዉ እኛ ተዋሕዶዎች የምትሉት?እንዴ “እኛ ተዋሕዶዎች” ስትሉ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምሥክር አላችሁ?በእናንተ ቤት “ቅብዐቶች” የምንባል በትክክለኛዉ መጠሪያችን ግን “መሢሐዉያን ፣ ክርስቶሳዉያን ፣ ናዝራዉያን ፣ ኦርቶዶክሳዉያን ፣ ቅቡዓን” እንድንባል መጻሕፍት ይመሠክሩልናል ፤ መዝ 104 ፡ 9 ፣ መ. ምሥጢር 20፡ 40-41 እና 49 ፤ ድርሳ ቄርሎስ እና ሌሎችም ፡፡ ታዲያ የእናንተ “ተዋሕዶዎች” መባል ከየት መጣ?

በመቀጠልም ብዙዎቻችሁ “ቅብዓት ምንፍቅና ነዉ” ስትሉ ትደመጣላችሁ ፤ በዚህም ምክንያ ብዙ ምእመናንን ድጋሚ በማጥመቅ አረማዉያን ፣ ከሐድያን እያደረጋችሁ ትገኛላችሁ፡፡ እንዲያዉ ለመሆኑ በጥምቀት ምክንያት በማሕፀነ ዮርዳኖስ ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ሜሮን ቅብዓ ቅዱስ ተቀብታችሁ ፣ከሥሉስ ቅዱስየምትወለዱትን ዳግም ልደት ታምኑበታላችሁአታምኑበትም? ታዲያ ይህ ቅብዓት ከ7ቱ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን አንዱ ሜሮን አይደለምን? ሜሮን ማለት ዘይት -- ቅብዓት ማለት አይደለምን? ፤ ምንፍቅና ነዉ ካላችሁ ስለምን ቅብዓ ሜሮን ትቀባላችሁ? ፤ ቅብዓት ምፍቅና ነዉ ካላችሁ ቤተክርስቲያን ሲመረቅ ፣ ካህናትና ሊቃነ ጳጳሳት ሲሾሙ ፣ ደናግላን ሙሽሮች ቅብዓ ሜሮን መቀባታቸዉ ምንፍና ነዉን?
እናንተ ምንፍቅና ነዉ ያላችሁትን ቅብዓት ቅዱስ ኤጲፋንዮስ እንዲህ ይለዋል ፤ “ወቀደሰ ቅብዓ መዓዛሁ ዘታሐዩ ወታሌቡ ወበ፫ቱ ሠዓት ቀደሶሙ ለአጋዕዝት ወበ፬ቱ ሠዓት ቀደሶሙ ለኪሩቤል ወበ፭ቱ ሠዓት ቀደሶሙ ለሱራፌል፤ ወበ፮ቱ ሠዓት ቀደሶሙ ለኃይላት ምስለ ሊቆሙ ለመላእክት፡፡ከዚህ በኋላ አእምሮ እውቀት የሚሆናቸውን ቅብዓት አጣፍጦ አከናውኖ በሦስተኛው ሠዓተ መዓለተ አጋእዝትን ቀባቸው፤ በአራተኛው ሰዓተ መዓልት ኪሩቤልን ቀባቸው፤ በአምስተኛው ሠአተ መዓልት ሱራፌልን ቀባቸው በስድስተኛው ሰዓተ መዓልት ኃይላትን ቀባቸው፤ አለቃቸውም ሚካኤል ነው፡፡ ከዚህም በኋላ እግዚአብሄር ለመላእክት የብርሃን መጎናጸፊያ አጎነጸፋቸው፤ የብርሃን ዝናር አስታጠቃቸው፤ የብርሃን ዘንግ ማሕተሙ መስቀል የሆነ አስያዛቸው፡፡ የብርሃን አክሊል የብርሃን ዘውድ ደፋላቸው፡፡ እምቅድመ ቅብዓትሰ ነበሩ መላእክት ከመ ሕፃናት በዝንጋኤ ወሶበ ተቀብዑ መልዓ ላዕሌሆሙ አእምሮ ወኂሩት፣ ፍቅር ወትግስት፣ ትሕትና ወየውሃት፡፡ይህስ ቅብኣት ምንድ ነው ቢሉ መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡
 የቅብዓት ጣዕሙ ምስጢሩ ምንድ ነው ቢሉ መላዕክት ሳይቀቡ እእምሮ፣ እውቀት፣ እንደሌላቸው ሕፃናት ነበሩ፤ ከተቀቡ በኋላ ግን ፍቅር፣ ትሕትና፣ የውሃት፣ ትግስት፣ አደረባቸው፤ ምሥጋና እንደምንጭ እፈሰሱ እንደጎርፍ እጎረፉ ከአፋቸው የማይለይ ሆነ፡፡ (አክሲማሮስ ክፍል ዘእሑድ ክፍል 4)”
ታዲያ ይህ ቅብዓት ጣዕመ ምሥጢሩ መንፈስ ቅዱስ ከሆነ ፤ መንፈስ ቅዱስ ምንፍቅና ነዉን?

እንዲሁም “
ወልደ እግዚአብሔር ሕያዉ ወልደ ማርያም ሥግዉ በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ ከበረ” ብለን በማመናችን በእናንተ ዘንድ “ከሐድያን ፣ መናፍቃን ፣ አረማዉያን” የሚል ሌላም ሌላም ታርጋ ይለጠፍልናል ፡፡ የሚገርመዉ እነዚህ ታርጋዎችን የምትለጥፉልን ሰዎች አንድም የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል አትጠቅሱም ፣ እንድም የአበዉንትርጓሜ አታመጡም ፣ ዝም ብላችሁ ያዘዉ ጋብዘዉ አይነት የወንበዴ ንግግርን ታቀርባላችሁ እንጅ ፡፡ መጻሕፍትን ስንጠይቃቸዉ ግን “ ወመኑ ዉእቱ ሐሳዊ ዘእንበለ ዘይክሕድ ወይብል እስመ ኢየሱስ ኢኮነ መሢሐ---ኢየሱስ መሢሕ አይደለም ከሚል በስተቀር ፣ የሚል ነዉ እንጅ ሐሰተኛ ከሐዲ ማን አለ?” 1ኛ ዮሐ 2፡ 22 የሚሉ ናቸዉ ፡፡ 
በሌላም መልኩ ደግሞ “አብ ወልድን ቀባዉ አከበረዉ” ብለዉ መጻሕፍት የተናገሩትን ቃል ይዘን ብቅ ስንል ፤ “እንዴ ! እንዴት አብ ሊያከብረዉ ይችላል?ይህ እኮ አብ ወልድን ይበልጠዋል ማለት ነዉ?” እያላችሁ የፈጠራ ንግግርን ትናራላችሁ ፡፡ እናንተየ ይህ ጥያቄያችሁ ደግሞ “ አብ ወልድን ወለደዉ” ሲል መጽሐፍ “እንዴ እንዴት ሊወልደዉ ይችላል?ይህ ከሆነማ አብ ወልድን ይበልጠዋል ማለት እኮ ነዉ” የሚል የጨዋ ጥያቄን የምትጠይቁ ናችሁ ፡፡
አዎ “
ተቀብዐ እም አብ” አንጻሩ “ተወልደ እም አብ” እንደተባለለት ያለ ነዉ ፡ አብ ቀባዒ ማለት ቀድሞ ለአካለ ቃል ልቡና አእምሮ በመሆን እንደወለደዉ ፣ እነሆም በጊዜ ተዋሕዶ በቅብዐተ መንፈስ ቅዱስ ወልድን በትስብእቱ ልቡና አእምሮ በመሆን ወለደዉ” ማለት ነዉ መ.ምሥጢር 3፡46 ፤ መዝ 2፡7 ፣ ድርሳ ዮሐንስ አፈወርቅ ደር2፤ ድርሳነ ቄርሎስ ድር 24 እና ሌሎችንም መመልከት ይቻላል ፡፡ እናንተ ግን ወይ ስለራሳችሁ እምነት አታሳዉቁ ፣ ወይ ስለሰዉ እምነት አታሳዉቁ ዝም ብላችሁ እደ ዉኃ ላይ ኩበት ትንገዋለላላችሁ ፡፡
አካላዊ ቃል ከድንግል የተከፈለን ሥጋ በብቻ አካሉ የባሕርይ ተዋሕዶ ሲዋሐደው አብንና መንፈስ ቅዱስን በጥንት ስማቸው ለማስጠራት፤ በጥንት ግብራቸው ለማጽናት የአብ ሕይወቱ በሆነ በመንፈስ ቅዱስ በድንግል ማኅፀን አካል ዘእምአካል ባሕርይ ዘእምባሕርይ ወለደው፤ ከድንግል የተከፈለን ሥጋ ቃል በብቻ አካሉ የባሕርይ ተዋሕዶ ሲዋሐደው አብ በራሱ በብቻ አካሉ የባሕርይ ልደት ወለደው፤ መንፈስ ቅዱስም በራሱ በብቻ አካሉ የባሕርይ ሕይወት ሆነው፡፡በዚህም ጥንተ ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስን በአካሉ ተቀብሎ የባሕርይ ክብር ከብሮበታል፡፡ ወልድ በሰውነቱ ሰው፣ ወልደ አዳም፣ ወልደ ዳዊት እንዲባል እንዲሁ በሥጋነቱ የባሕርይ አምላክ፣ የአብ የባሕርይ ልጅ ሁኖበታል ፡፡ 
ቀድሞ የባሕርይ ልጅ አልነበረምን?፤ ይህ ቃል የባሕርይ ልጅነቱ ተነሥቶት ነውን? የሚል ቢኖር ፤ የባሕርይ አምላክ የባሕርይ ልጅ መባልስ ቅድመ ዓለም ለተወለደ ቃል እውነት በእወነት የባሕርይ ልጅ አምላክ ነው፡፡ ነገር ግን ልጅነት የሌለውና አምላክነት የሌለዉን ከእመቤታችን የተከፈለ ሥጋ ወነፍስ ፤ ከቃል ጋር ቢዋሐድ ሥጋ በቃል ርስት የባሕርይ ልጅ፣ አምላክ ወልደ አምላክ ሲባል ቃል በሥጋ ርስት አምላክ ወልደ አምላክ፣ የባሕር ልጅ ይሉት ዘንድ እንዴት ይሆናል? ቃልን በሥጋ ርስት ሰው የሰው ልጅ ይሉታል እንጂ፡፡
የመጨረሻ ጥያቄ “ለተዋሕዶዎች”
1ኛ‹‹‹‹‹‹ሥጋ የቃልን ፤ ቃልም የሥጋን ገንዘብ ገንዘቡ ማድረጉን ታምናላችሁ ወይስአታምኑም?
2ኛ‹‹‹‹‹‹‹ ካመናችሁ ፍጡርነት እና ክብር መሻት የሥጋ ገንዘቦቹ ናቸዉ ወይስ አይደሉም?
3ኛ‹‹‹‹‹‹‹ ከሆኑ ቃል የሥጋን ገንዘብ ገንዘቡ ሲያደርግ በሥጋዉ ፍጡርና ክብርን የሚሻ አይደለምን?አይደለም ካላችሁ የሥጋ ገንዘቦች የሆኑ ፍጡርነትና ክብር መሻት ወዴት ሄዱ?ጠፉ እንዳትሉኝ ተዋሕዶ ተዐቅቦና መጠባበቅ አላት እንጅ አንዱ አንዱን ገንዘብ አጠፋ አትለንም ፡፡ ይባላል ካችሁኝ በሥጋዉ ፍጡር ሲባል ለምን አመማችሁ?ይባላል ካላችሁኝ “ተቀብዐ በሥጋሁ--በሥጋዉ ከበረ” የሚለዉን ብሂል “ ሥጋዉን አከበረ ለሥጋዉ ክብር ሆነ” ለምን አላችሁት?

ማሳሰቢያ፡- እባካችሁ ይህ ስድብና ነቀፋ ፣ ተንኮልና ዘለፋ የዲያብሎስ ስሆነ እሱን ለዲያብሎስ ስጡትና በሰከነ አእምሮና በሃይማኖተኛ ልቡናችሁ እንነጋገር?

ዛቲ ሃይማኖት መሢሐዊት ዘትትአመን ባቲ ቤተክርስቲያን ቅድስት
 በዲ/ን ብርሃኑ ሻምበል
ስብሐት ለአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ምስለ ወላዲተ አምላክ ወቅዱስ መስቀል

No comments:

Post a Comment