Friday, September 7, 2018

ምስጢረ ቅብዓት በቅዱሳት መጽሐፍት

ስለ ምስጢረ ቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ የተነገረበትን ከቅዱሳት መጽሐፍት እስኪ እንመልከት


ቄርሎስ በሐይማኖት አበው ፣ዮሐንስ አፈወርቅ በድርሳኑ፣ ነብያት በትንቢታቸው፣ ኢጲፋንዮስ በስነ- ፍጥረት መጽሐፉ፣ሰማዕታት በገድላቸው፣ዝክሪናጳውሊ በብራና መጽሐፋቸው፣አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በመጽሐፈ ምስጢር፣ በመጽሐፍ ቅዱስ እና ሌሎችም ስለተቀባ የሚናገሩ መጽሐፍትን ዘርዝረን ባንጨርስም እነርሱ ያቆዩንን ሃይማኖት እንካድ ብንል አይሰድምና ነው፡፡

1. ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ጥቂቶቹን ስናይ
ኢሳ 61÷1 ማቴ 1÷16 (አንድምታ ትርጓሜ ) መዝ 2÷2 ሐዋ 10÷38 ዕብ 1÷8፤ መዝ 44÷7 1ኛ ዮሐ 2÷20 ሮሜ 1÷4 ዳን 9÷25 (24) ማር 8÷29 ዮሐ 5÷26 ሐዋ 4÷25-28 ሉቃ 9፥20 እንዲሁም ሌሎች የመፅሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ይገኛሉ::

2. መጽሐፈ ሚስጢር 20÷40-41 (አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ) "……… ለእግዚአብሔር የተለየ የተቀባ የሆነ የስሙ ትርጉም መሲሕ የሆነ ክርስቶስ እስከ ተወለደ ድረስ በገሊላ ነገሥታት ዘንድ መሲሕ ተብሎ መጠራት አልነበረም ፡፡ ክርስቶስም መሲሕም ናዝራዊም በማለት በአንድነት የተቀባ ተባለ መሲሕ ፡፡ መሲሕ የተቀባ ማለት ነው፡፡ ክርስቶስ የተባለ ኢየሱስ ተወለደ የተቀባ መባል በእርሱ ተፈፀመ፡፡"

3. መሲሕ መሰሐ-ቀባ ከሚለው:-
 የግዕዝ ግሥ የተገኘ/የወጣ/ ሲሆን መሲሕ ማለት የተቀባ፣ ቅቡዕ የተሾመ ወይም የነገሠ ማለት ነው፡፡ መሲሕም የተባለ ክርስቶስ ነው፡፡ ቅድመ ዓለም ንጉሥ ቢሆንም በሰውነቱ ተቀባ፣ ከበረ ፣ ተሾመ፣ ነገሠ ይባላል፡፡ (ከመምህር ስቡሕ አዳምጤ የስዋስወ
ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መ/ኮሌጅ የሐዲሳት ትርጓሜ መምህር)

4. ከመ መለኮት ኢይትቀባዕ ዘእንበለ ዳዕሙ ትስብእተ ሥጋሁ - በሰውነቱ እንጂ በአምላክነቱ ተቀባ ከበረ እንደማይባል አስረዳ (ድርሳን ዘ ዮሐንስ አፈወረቅ ድር 3)

5. አብ ቀባዒ፣ወልድ ተቀባዒ፣መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ አብ በልብ፣ወልድ በቃል፣መንፈስ ቅዱስ በእስትንፋስ ይመሰላሉ፡፡ ቅድመ ተዋሕዶ ወልድ (ቃል) በአብ ልብነት ያስባል በመንፈስ ቅዱስ እስትንፋስነት(ሕይወትነት) ሕያው ይሆናል፡፡ ቃል የተወሐደው ሥጋ ከአብ ልብን፣ ከመንፈስ ቅዱስ የባሕርይ ሕይወቱን ገንዘብ ቢያደርግ (በመንፈስ ቅዱስ ቢከብር) ተቀባ ተባለ፡፡ 
አብ ለወልድ በሥጋው መንፈሱን ሊሰጠው ፈቃዱ ቢሆን ቀባው ተባለ፤ ቃል በሥጋው መንፈስ ቅዱስን ከአብ ቢቀበል ተቀባ ተባለ፤ መንፈስ ቅዱስም ለቃል በሥጋ ርስት የባሕርይ ሕይወት ሊሆነው በመሰጠቱ ቅብዕ ተባለ (ዮሐንስ 5÷26፤መዝ 44÷7፣ ሐዋ 10÷38፣ድርሳነ ዘዮሐንስ አፈወርቅ፣ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት ወሰዋሰው ገፅ 780) ፡፡

6. ክርስቶስ የተቀብዖ (ሉቃ 9÷2፤ ዮሐ 1÷42) ስሙ ሲሆን አማኑኤል የተዋሕዶ ስሙ ነው (ማቴ ትርጓሜ 1÷16)፤ነገርግን አማኑኤል ተብሎ ክርስቶስ ያልተባለበት ክርስቶስ ተብሎ አማኑኤል ያልተባለበት አንዳችም ቅጽበት የለም ሁለቱም በአንድ ጊዜ ተፍጽመዋል እንጂ፡፡
መንክረ ገብረ ወልደ እግዚአብሔር ውስተ ከርሰ እሙ እስመ ፈጸመ ሥርዓተ ተዋሕዶ ወቅብዓተ ምዕረ ከመ ቅጽበተ ዓይን-የእግዚአብሔር ልጅ በእናቱ ማሕጸን ድንቅ ነገርን አደረገ የተዋሕዶን (የአንድነትን) እና የቅብዓትን ነገር እንደ ዓይን ቅጽበት አንድ ጊዜ ፈጽሟልና እነዳለ አውሳብዮስ ::

7. ወልድ ቅብዕ ማለት ደግሞ ሥግው ቃል በሥግውነቱ መንፈስ ቅዱስን አልተቀባም ማለታቸው ሰማዩም ሰማይ ምድሩም ምድር አይደለም እነደማለት ነው()፡፡እነዚህንም “ስሞሰ ለክርስቶስ ኢያእመሩ ወዘኢይደሉ ይሜህሩ፡፡እለሰ የአምኑ ርቱዐ ይሜህሩ ከመ በሥጋሁ ተቀብዐ እስመ ክርስቶስ ብሂል ቅቡዕ ብሂል፡፡እፎ ይሰመይ ክርስቶስ ዘኢተቀብዐ” ብሎ ቅዱስ ቄርሎስ ነቅፏቸዋል፤ሐዋርያውም ዘልፏቸዋል (1 ዮሐ 2÷20)::

“ስግው ቃል በስግውነቱ(ቃል የተወሐደው ስጋ) መንፈስ ቅዱስን አልተቀባም፣ ሀብታተ መንፈስ ቅዱስን አልተመላም፣ ጸጋ አልተቀበለም፣ በመንፈስ ቅዱስ ቅብዕነት ክህነትና መንግስት አልተሾመም፣ የሰውነት ክብር አልከበረም ማለት ሐሰትነቱ ሰማዩን ሰማይ ምድሩን ምድር አይደለም እንደማለት ነው ” አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት ወሰዋሰው ገፅ 550::

8. ምእመናን ሆይ አስተውሉ ተዋሕዶና በተዋሕዶ ከበረ የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡እኛም ብንሆን ተዋሕዶን የምናምን (ኦርቶዶክስ ተዋሕዶን የምንከተል) ሲሆን በተዋሕዶ ከበረን ግን አናምንም በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ ከበረ፣የባሕርይ አምላክ ሆነ ን እንጂ፡፡ይህም ከራሳችን የመነጨ አይደለም ነቢያት የተናገሩት፤ ሐዋርያት፣ ሊቃውንት የሰበኩት፤ በመጻሕፍትም ጽፈው ያስቀመጡት እንጂ፡፡

በአጠቃላይ ቅብዓት ማለት መንፈስ ቅዱስ ሲሆን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከባሕርይ አባቱ ከአብ በሥጋው የባሕርይ ልደት የተወለደበትና እኛን ምእመናንንም በጸጋ ከስላሴ እንድንወለድ ያደረገበት ምሥጢር ነው (1ኛ ዮሐ 2÷26፤ሃይ.አበው ዘቄርሎስ 80÷ 1-2)፤ የእርሱ ቅብዓት የባሕርዩና ውሳጣዊ ሲሆን የእኛ ግን የጸጋና ከአፍአ (ከውጭ) የሚገኝ ነው፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሐር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር አሜን !

No comments:

Post a Comment